>
9:31 pm - Wednesday February 1, 2023

ወያኔ በራሱ ወጥመድ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

ኅዳር 2008

profeser mesfn photoራስን ሳያታልሉ ሌላውን ማታለል አይቻልም፤ ለራስ ካልዋሹ ለሌላ ሰው መዋሸት አይቻልም፤ ዞሮ ዞሮ ወደቤት እንደሚባለው ዞሮ ዞሮ ማታለልም ሆነ ውሸት ማደሪያ ሲያጡ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፤ ያኔ ፈጣሪና ፍጡር ይፋጠጣሉ፤ ፍጡር የማታለያ ልብሱን አውልቆ በዓለም ፊት ራቁቱን ይቆማል፤ በከመረው ውሸት መጠን ነቀፌታ ተሸክሞ ያቃስታል፡፡
የታወሩት ዓይኖቹ ይከፈቱና ሕይወት ነጠላ አለመሆኑን፣ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ውጣ-ውረድ መኖሩን፣ ጥላቻና ፍቅር፣ ጤንነትና ሕመም፣ ደስታና ሐዘን መፈራረቃቸውን፣ የግለሰብ ሕይወት በሞት ተሸንፎ መሻሩን፣ ገንዘብ የማይገዛው ነገር መኖሩን፣ ገንዘብ በከበደ መጠን ማቅለሉን አለማወቅ፣ ገንዘብ የማይመክተው ጦርና በገንዘብ ሊታጠቀው የማይችል መሣሪያ መኖሩን አለማወቅ፣ የደከመ እንደሚያይልና ያየለ እንደሚደክም፣ ዓለማችን በጣም የተያያዘና የተቆራኘ በመሆኑ አንዱን ሲያስነጥሰው ሌላውን እንደሚነዝረው የወያኔ ጎረምሶች አልተረዱም፡፡
ዛሬ ፈጣሪና ፍጡር ተፋጠጡ፤ ፍጡር የማታለያ ልብሱን አውልቆ በዓለም ፊት ራቁቱን ቆሟል፤ በከመረው ውሸት መጠን ውርደትን ተሸክሞ ያቃስታል፤ እያታለሉ ውሸትን መጠምጠም እያታለሉ ውሸትን እንደመተርተር ቀላል አይደለም፤ ውሸት ያከሳል፤ ውሸት ያዋርዳል፤ ውሸት መደገፊያ ያሳጣል፤ ውሸት ወዳጆችን ያሳፍራል፤ ጠላቶችን ያፈነድቃል፡፡
በውሸት ለሌሎች የተገነባው ወጥመድ ሲከፈት ማንም፣ ምንም የለበትም፤ ባዶ ግን አይደለም፤ ባለቤቱ አለበት! ባለቤቱ በገዛ ወጥመዱ ውስጥ! ታለለ የተባለው ሁሉ ዳር ቆሞ አታላዩ መታለሉን እያየ ይስቃል፤ አታላዩ የውሸት ምሰሶው መውደቁን ገና አልተረዳም፤ ውሸቱን አይቶ ወዳጁ እንደከዳው አታላዩ አልገባውም፡፡
ማታለልና መዋሸት በሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ዙሪያውን ገደል አደረገው፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአስታራቂነት ጥረት ከብዙ ዓመታት ጦርነት ወጥቶ በሰላም የነበረው ሱዳን አሁን ለሁለት ተገመሰ፤ ለሁለት መገመሱ አልበቃ ብሎ እንደገና ሊገማመስ እየተደባደበ ነው፤ የሶማልያ ትርምስ እየባሰበት ሄደ እንጂ አልተሻለውም፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደተኳረፉ ናቸው፤ ከዚያም በላይ በውክልና እየተቆራቆዙ ነው፤ የኢትዮጵያና የኬንያ ወታደሮች መጋጨታቸውና ጥቂቶች መሞታቸው አዲስ የሰላም ጠንቅ ነው፤ ጂቡቲ በፈረንሳይና በአሜሪካ ጦር የምትጠበቅ ስለሆነ አይበገሬ ትሆናለች፤ ሆኖም የአዲስ አበባ-ጂቡቲ ባቡር መቆም በጂቡቲ ሕዝብ ላይ የሚያስነሣው ግም ስሜት የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
የምዕራባውን ኃይሎች ፍላጎት ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ ከነሱ ምጽዋት የማትወጣ ፍጹም ደሀ፣ ያለምንም ስጋት አካባቢውን በሞላ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ሁኔታ የተመቻቸበት እንድትሆንላቸው ነበር፤ አሁን ግን ሰላም የሰፈነባት አገር እንደማትሆን ምልክቶችን እያዩ ነው፤ እንዲያውም በመሀከለኛው ምሥራቅ በግልጽም ይሁን በስውር እየበረታ የሚሄደው ጸረ-አሜሪካን ስሜት በአፍሪካ ቀንድ ላይ የተተከለ እንደሆነ ምዕራባውያን በመሀከለኛው ምሥራቅ ዘይት አምራች አገሮች ላይ ያላቸውን ጥቅም ሁሉ ክፉ ስጋት ላይ የሚጥልባቸው ሊሆን እንደሚችል የተገነዘቡ ይመስላል፤ በተጨማሪም ከኤርትራ ጋር በጠላትነት የተፋጠጠች ኢትዮጵያ ለምዕራባውያን የምትመች አለመሆንዋንም እየተገነዘቡ ነው፤ ስለዚህም ከኢትዮጵያ አገዛዝ ጋር በመሆን አሻክረውት የነበረውን ግንኙነት ለማለስለስ እየሞከሩ ነው፤ ይህ ሁሉም እየሆነ የኢትዮጵያ አገዛዝ ገና አልነቃም፤ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ቀስቃሽ ተልኮለታል፡፡
በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ለወግም እንኳን መጥፋቱን የአፍሪካ ኅብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተገነዘበው ይመስላል፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ለዓመታት የማይቋጭ ሆኖ የቆየውን የእስላሞች ጉዳይ ለማየት ውሳኔ ላይ ደርሷል፤ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት አለመኖሩን የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ ዋና ማረጋገጫ ነው፤ ዙሪያው ገደል መሆኑ የምዕራባውያን (አሜሪካና አውሮፓ) ኃይሎች ተማምነውበት የነበረውን የኢትዮጵያ አገዛዝ ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፤ ዙሪያው ገደል መሆኑ የኢትዮጵያ አገዛዝ የሰላም አራማጅ መስሎ እንዳይታይ አድርጎታል፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ አገዛዝ በአካባቢው ካሉት አገዛዞች ጋር የሻከረ ዓይነት ግንኙነት ስለሚያሳይ አሜሪካና አውሮፓ የሚወድዱት አይመስልም፤ ይህ ውጪውን ሲታይ ነው፡፡
ከውስጥ ሲመለከቱት ደግሞ ሌሎች የግጭት መድረኮችና ሌሎች ጉዳዮች ይታያሉ፤ ዋናውና መሠረታዊው ግጭት አገዛዙ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን ነጻነቶችና መብቶች ሰርዞ ምንም ዓይነት ልዩነት በቃልም ይሁን በጽሑፍ መግለጽ እንደሽብርተኛነት የሚያስቆጥርና የሚያስወነጅል መሆኑ ነው፤ ፕሮፌሰር ስርግው ሐብለ ሥላሴ ዓጼ ምኒልክ፣ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች በሚለው መጽሐፉ ኢትዮጵያውያን አእምሮ የሚባለውን ጋዜጣ መግዛት እንዲለምዱ በማለት አጼ ምኒልክ ጋዜጣውን ይዘው በአደባባይ እንደሚወጡ ይነግረናል፤ ዛሬ በአዳፍኔ አገዛዝ፣ መቶ ዓመታት ወደኋላ ሄደን ታዋቂ ጋዜጠኞች ሁሉ በእስር እየማቀቁ ጋዜጦች ሁሉ ጠፍተዋል፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተከልክለውና ታፍነው ባሉበት የወያኔ አገዛዝ፣ የፖሊቲካ ቡድኖች ተኮላሽተው አልጋ ላይ በዋሉበት ሁኔታ፣ ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎች፣ ዳኞችና የወህኒ ቤት አዛዦች እንደፈለጉ በሚሠሩበት አገር ግጭቶች ያለማቋረጥ እንደሚፈጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ የፖሊቲካ ውይይት፣ ክርክርና ንግግር በተከለከለበትና አንድ ድምጽ ብቻ ለማዳመጥ በተፈቀደበት ሥርዓት ብዙ እምቢ-ባዮች ይኖራሉ፤ አዳፍኔ ጎራዴውን እየሳለ በሄደ ቁጥር ሰላማዊ የፖሊቲካ ውይይትም በተስፋ-ቢስነት አላስፈላጊ አማራጭ ውስጥ ይገባል፤መለስ ዜናዊ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ›› ብሎ ተቀናቃኝ ቡድኖችን ከመረቀ ሃያ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ፤ አሁን ምርቃቱ የደረሰ ይመስላል፤ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታሰብ መለስ ዜናዊ ራሱን የረገመ ይመስላል፡፡
ወሬው ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ አለመረጋጋት የሚያመለክት ነው፤ ከጎንደር አስከቦረና ከኦጋዴን አስከጋምቤላ ወሬው ሁሉ የግጭት ነው፤ አንድም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይትና በስምምነት መደምደሚያ ሲያገኝ አይታይም፤ አይሰማም፤ ሁሉንም ነገር በጡንቻ በማስገደድ ለማስፈጸም የሚደረገው ሙከራ ያረጀና ያፈጀ መሆኑን ለማስታወቅ ተቀዋሚውም የጡንቻውን መንገድ እየተላመደው ነው፤ ጡንቻ ለጡንቻ መቆራቆዙ ደም እያፋሰሰ ጡንቻን ያነግሣል እንጂ ሕዝብን አይገነባም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የጡንቻ ግጭት መስፋፋት በሰሜን በኤርትራና በትግራይ፣በትግራይና በጎንደር፣ በትግራይና በወሎ፣ በምሥራቅ በሱማሌና በኦሮሞ፣ በሱማሌና በሐረሬ፣ በኦሮሞና በሐረሬ ፣ በደቡብና በምዕራብ በተለያዩ ጎሣዎች መሀከል የተጫረው እሳት ሲቀጣጠል ማብረዱ እንደማቀጣጠሉ ቀላል አይሆንም፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ እንደሚባለው ይሆናል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ የሚቀጣጠለው እሳት ድንበር ጥሶ የሚወጣና ጦሱ የማይበርድ ይሆናል፤ወያኔም ሆነ ለወያኔ ወንበር ያሰፈሰፉ ሁሉ፣ በጎሠኛነት ስሜት እየነደዱ የማመዛዘን ችሎታቸውን ያጡ ሁሉ የሰነዘሩት የጥላቻ ስለት በነሱው ላይም ሲያርፍ የተመኙትን ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸው ከመሸ በኋላ ይረዱታል፤ ለሌሎቹ አዲስ ይሆናል እንጂ ለወያኔ ከመሸ በኋላ መረዳት የባሕርይ ነው!
ከሶርያ በሶማልያና በኬንያ በኩል እያደፈጠ የሚገሰግሰው የሽብር ቡድን ወደኢትዮጵያ አይደርስም ማለቱ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እንደተለመደው ለከመሸ በኋላ ማሰብ ማስተላለፉ የመጨረሻው ስሕተት ሊሆን ይችላል፤ የመጨረሻው ስሕተት የተሠራውን አሰፋልት መንገድ አፍርሶ የባቡር ሀዲድ እንደመሥራት አይቀልም፤ የውጮቹን አካባቢ ኃይሎች እንደውስጡ አመራር በጡንቻ (የአሜሪካን ድጋፍ ቢኖርበትም) ለማስተናገድ ማሰብ ማሰብ አይደለም፤ ማሰብ የጎደለው መሆኑም በገሃድ እየታየ ነው፤ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገሮች በሚከተለው ሰንጠረጅ ተዘርዝረዋል፡፡
ወደአሥራ አንድ የሚጠጉ ጎረቤቶች እንኳን ለአላዋቂዎች አምባገነኖችና ለአዋቂ መሪዎችም ቢሆን በጣም ፈታኝ ነው፤ የኢትዮጵያ አገዛዝ አሜሪካንን ከመጠን በላይ በመተማመን የውጩን አመራር ልክ እንደውስጡ በጉልበትና በማታለል ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፤ ይህ ሁኔታ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል አድርጎታል፤ በዚህም ምክንያት እንዳይደርስ ከተባለበት ከጂቡቲ በቀር ከኢትዮጵያ ጋር በግጭት ያልተላከፈ አገር የለም፤ የኃያል አሽከር መሆን ኃያል የሆኑ የሚያስመስል ሕመም አለ፤ ጃንሆይ አማኑኤል ሆስፒታልን ሲጎበኙ አንዱን ያገኙትና ስሙን ይጠይቁትና ይነግራቸዋል፤ ቀጥሎም በተራው ያንተስ ስም ይላቸዋል፤ የኛማ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ነው ብለው ሲመልሱለት ከት ብሎ ይስቅና እኔንም ሲጀምረኝ እንዲህ ነበር ያደረገኝ ይላቸዋል! መማር የፈለገ አምባገነን እብድ ከተባለ ሰውም መማር ይችላል! አሜሪካኖች የኢትዮጵያን አገዛዝ የአካባቢው ሰላም ጠባቂነት በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ያደረጋቸው ይኸው ሳይሆን አይቀርም፤ አንዱና ዋናው የማሰብ ችግር ነው፡፡

ኢትዮጵያና ጎረቤቶችዋ
2008 ዓ.ም.
ተ፣ቁ. አገሮች የኢትዮጵያ ጦር ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት የውስጥ ሰላም

1 ኢትዮጵያ የለም
2 ሱዳን1 አለ አለ የለም
3 ሱዳን2 አለ የለም
4 ሱዳን3? ?
5 ኬንያ ? አለ አለ
6 ሰማልያ አለ የለም
7 • ስባሪ1 የለም
8 • ስባሪ2 የለም
9 • ስባሪ3 የለም
10 ጂቡቲ አለ
11 ኤርትራ አለ አለ

ምናልባት ከባሕር ማዶ ያለው ጎረቤታችን፣ የመን በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ የተለየ መዘዝ ይዞላቸው ይመጣ ይሆናል፡፡
አሁን ደግሞ ከሁሉም የባሰው መጋለጥ መጣ፤ ማንም በማይደርስበት ፍጥነት እያደገ ነው የተባለው ኢኮኖሚ አከርካሪቱን ተመታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በችጋር ጥቃት ስር ወደቀ፤ የወያኔ የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የአገሩን ሕዝብ ያቀጨጨው የወያኔ ጡንቻ ውሀ ሆኑ፤ ኢኮኖሚ በጡንቻ አያድግም፤ ችጋር በጡንቻ አይገፋም፤ ሕጸናትንና አሮጊትና ሽማግሌዎችን የገጠር ነዋሪዎች እያመነመነ በመጣል የሚጀምረው ችጋር አይደበቅም፤ ከወራት በኋላ ማምለጥ ያልቻሉትን ሁሉ ችጋር እየበላ በያለበት ሲጥላቸው በዓለም ጋዜጦች ይወጣል፤ ያኔ መዋሸትና ማታለል ዋጋ ያጣሉ! ያኔ ጡንቻ ዋጋ ያጣል! ያኔ ስለእድገት ማቅራራት ዋጋ ያጣል!
ዓላማው ሁሉ ታወቀ፤ ዘዴው ሁሉ ታወቀ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓላማውም ዘዴውም ሰለቸው፤ ምዕራባውያን ኃይሎች ውሸትን መጠገን ሰለቻቸው፤ የአፍሪካ ሕዝቦች የጎሠኛነት በሽታ እንዳይተላለፍባቸው ፈሩ፡፡

Filed in: Amharic