>

መለስና -ካጋሜ ሃውዜንና ኪጋሊ [ሳምሶን ኣስፋው]

paul-kagame- Rwandameles_mexicoሰሞኑን በቪዲዪ ውቂያኖሱ ዩቱዩብ ሳንዣብብ “Rwanda’s Untold Story” በሚል ርዕስ የቢቢሲ ዶክሜንተሪ ቻናል በ2014 ከለቀቀው ለ58 ደቂቃ ከሚዘልቅ አስረጂ ቪዲዮ ጋር ተገጣጠምኩ። “Untold Story” የሚለው ርዕስ ጉጉቴን አጫረውና ተመለከትኩት።

ይህ አስቃቂ ጭፍጨፋ ከተፈጸመ 24 ዓመታት አልፈውታል። “Untold Story” የሚለው የቢቢሲ አስረጂ የቪዲዮ ቅንብር ደግሞ ከአመት በፊት ማለትም 2014 የተለቀቀ በመሆኑ ጭፍጨፋው ከተፈጸመ ከ23 ዓመት በኋላ ምን አዲስ ሚስጥር ይፋ ሆኖ ይሆን የሚል ጉጉት ማጫሩ አይቀርም።

ጭፍጨፋው የተፈጸመው ከጠቅላላ ህዝቡ 15-20% በሚሆኑት አናሳዎቹ ቱትሲዎች ላይ ሲሆን ፈጻሚዎቹ ደግሞ ከ75%-80% የሚሆኑት ሁቱዎች ናቸው።

በወቅቱ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የስልጣን ክፍፍል አድርጎ ፍጥጫውን በሰላም ለመቋጨት ስምምነት ተደርሶ ነበር። ይሁንና የሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ከቱትሲ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት እንደሚፈራረሙ ሲጠበቅ ኤፕሪል 6 1994 አየር ላይ እያሉ አውሮፕላናቸው ተመቶ ተገደሉ፡፤ ይህ መሆኑ ሁቱዎቹን በቀጥታ ወደ ጭፍጨፋው አሸጋገራቸው።

የጭፍጨፋው መጀመር ምክንያት የፕሬዘዳንቱ መገደል ከሆነ፤ ፕሬዘዳንቱ እንዲገደሉ ያደረገው ማነው? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። “Rwanda’s Untold Story” የተባለውም ይህ ነው። በሰላም ስምምነቱ ዋዜማ ፕሬዘዳንቱን ያስገደሉት በወቅቱ የቱትሲ ታጣቂዎች መሪ የነበሩት በአሁኑ ሰአት ደግሞ የሩዋንዳ 4ኛ ፕሬዘዳንት የሆኑት ፓዎል ካጋሜ ናቸው፡፡

አስረጂው ቪዲዮ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ተደብቀው የሚገኙትን የፕሬዝዳንት ፖውል ካጋሜ መንግስት ከፍተኛ የጦር ጄነራልና በአሜሪካ የሩዋንዳ አምባሳደር የነበሩ ከድተው እዛው አሜሪካ በስደት የሚገኙትን ዲፕሎማት ምስክርነት ያስደምጣል።

ሁለቱም ባለስልጣናት ካጋሜ ሊፈረም የነበረውን የሰላም ስምምነት ስለማይፈልጉ በዋዜማው ፕሬዘዳንቱን ማስገደላቸውን አስረግጠው ይመሰክራሉ። ካጋሜ ይህን ያደረጉት ፕሬዘዳንት የመሆን ጥማቸውን ለማርካት እንደሆነም ያስረዳሉ ምስክሮቹ።

ካጋሜ በሰላም ስምምነቱ የሚገኘውን የተሸራረፈ ስልጣን ባለመፈለጋቸው 1 ሚሊዮን ለሚጠጋው የራሳቸው ጎሳ እልቂት ምክንያት የሆነውን ግድያ ፈጸሙ፡፤ ካጋሜ ፕሬዘዳንቱን ሲያስገድሉ ቀጥሎ የሚሆነውንም ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፤

ሁቱዎች ጭፍጨፋውን ሲፈጽሙ በካጋሜ የሚመሩት ታጣቂዎች በከፍተኛ ፍጥነት የሃገሪቱን አብዛኛውን ክፍል እየተቆጣጠሩ ገሰገሱ። በኋላም ጁላይ ውስጥ ኪጋሊን በመቆጣጠር ለ100 ቀናት የዘለቀውንና 1 ሚሊዮን ህይወት የጠፋበትን ግድያ በማስቆም የነጻ አውጭነት ሞገስና ማዕረግ ተጎናጸፉ፡፤ በሚሊዮኖች ደም ነገር ግን በአቋራጭና በአጭር ጊዜ ውስጥ ስልጣን ተቆናጠጡ። የአስረጂ ፊልሙ ጭብጥም ይሀው ነው። ፕሬዘዳንት ካጋሜ ነጻ አውጭ ሳይሆኑ ለሚሊዮኖች ሞት ምክንያት የሆነውን ጭፍጨፋ ፊሽካ ነፍተው ያስጀመሩ ወንጀለኛ መሆናቸውን በህይወት በሚገኙ ምስክሮች አስረግጦ ያሳያል።

ለመጻፍ ያነሳሳኝ ግን ፕሬዘዳንት ካጋሜ በስልጣን ጥም ታውረው የፈጸሙትና ለራሳቸው ጎሳ እልቂት ምክንያት የሆነው ተግባራቸው አይደለም። እንድጽፍ ያነሳሳኝ የካጋሜ ተግባር የኛው ጉዶች (ህውሃቶች) በሃውዜን ህዝብ ላይ ካስፈጸሙት የእጅ አዙር ጭፍጨፋ ጋር ያለው ተመሳሳይነት ነው።

ካጋሜ 1 ሚሊዮን ቱትሲዎችን አስጨፍጭፈው በ100 ቀናት ውስጥ ገስግሰው ኪጋሊ እንደገቡ ስንመለከትና ህውሃት ከሃውዜን ጭፍጨፋ በኋላ በምን ያህል ፍጥነት ወደ ድል ይገሰግስ እንደነበር ስናስታውስ ተመሳሳይነቱ ጎልቶ ይታየናል።

የህውሃትና የካጋሜ ታጣቂዎች አሳፋሪ ገድል እንደሚመሳሰል ሁሉ መሪዎቻቸውም ብዙ ተመሳሳይ ባህሪና ገድለ-ግፎች አሏቸው።

መለስ አብሮ አደጎቹን ሳይቀር እያጠፋ እንደተጓዘ ሁሉ ካጋሜም በጦርነት ወቅት ከሱ ቀጥሎ ከነበረው ጄኔራል ጀምሮ በርካታ አጋሮቹን እያጠፋ ዘልቋል።

የሚገርመው ደግሞ ሁለቱም መሪዎች በምዕራባዊያን ሞገስን ያገኙ መሆናቸው ነው። በግዜው የእንግሊዝ ጠ/ሚር የነበረው ቶኒ ብሌር የአፍሪካ ተስፋ! ወጣት መሪዎች ሲል ካሞካሻቸው መካከል መለስና ካጋሜ ግንባር ቀደሞቹ እንደነበሩ ልብ ይሏል።

በአዲሱ ለገሰ አቀንቃኝነት በካጋሜ ቅኝት የተዘፈነውን “ኢተርሃምዌ” የተሰኘው የምርጫ 97 የህውሃት የፕሮፓጋንዳ ነጠላ ዜማም ዝምድናቸውን ያጠናክረዋል።

ሌላው የምንገነዘበው ቁምነገር፤ ምዕራባዊያን ሁሌም ከብዙሃን ጎሳ ይልቅ አናሳ ጎሳ ስልጣን ቢቆናጠጥ እንደሚመርጡ ነው። በብዙሃን ላይ የተቀመጠ የአናሳ ጎሳ መሪ ለህልውናው ሲል ጥሩ አሸከር ይሆናል። መለስና ካጋሜን የመሰለ ታታሪ አሽከር የሚያፈራው የአናሳ ጎሳ ማህጸን ብቻ እንደሆነም ጠንቅቀው ያውቃሉ።

Filed in: Amharic