>

ዐይናችን ተከፍቷል ህሊናችን ነቅቷል [ከአንተነህ መርዕድ]

ታህሳስ 2008 ዓ ም
የመጀመርያው የኬንያ ፕሬዝደንትና የነፃነት ታጋይ ጆሞ ኬንያታ ብዙ ጊዜ የሚጠቀስላቸው፣ ስለ ቅኝ ገዥዎች የተናገሩት እውነት ይህን ይመስል ነበር። “ሚሲዮኖች ወደ አፍሪካ ሲመጡ እነሱ መጽሃፍ ቅዱስ፤ እኛ ደግሞ መሬት ነበረን። ዐይናችንን ጨፍነን እንዴት እንደምንጸልይ አስተማሩን። ዐይናችንን ስንገልጠው ግን እነሱ መሬታችንን እኛ መጽሃፍ ቅዱሱን ታቅፈናል” አሉ። “When the Missionaries arrived, the Africans had the land and the Missionaries had the Bible. They taught how to pray with our eyes closed. When we opened them, they had the land and we had the Bible”.
ኬንያም ሆነ ሌላውን የአፍሪካ አገር በሚሲዮንነት ቆይቶም ለቅኝ ግዛት ወርረው የያዙት፣ ለአገሩ ባዳ ለሰው እንግዳ የሆኑ ነጮች ነበሩ።በመሆኑም አገሬው ባለው አቅሙ እየተባበረ ታግሏቸው ነፃ ወጥቷል። ሌሎች አፍሪካውያን ያዩትን የውጭ አገዛዝ እኛ ልጆቻቸው እንዳናየው ከመላ ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ አባቶቻችን ዘርና ቋንቋ ሳይለያቸው ተደራርበው ድንበሯ ላይ በመውደቅ ነፃነታትንን ከማስጠበቃቸውም በላይ ለመላው ቅኝ ተገዥ ኩራትና የነፃነት ቀንዲል ሆነው አልፈዋል። እኛ ግን አሁን አባቶቻችንን ከገጠመው የተለዬ የአገርና የህዝብ ጠላት ገጥሞናል። ከሃያአምስት ዓመት በፊት የመጡት ወራሪ ወንድሞቻችን ወያኔዎች አገሪቷን ሲቆጣጠሩ አንገታቸው ላይ ኩሺታ(መቀበርያቸው ጨርቅ) ምላሳቸው ላይ የዘረኝነት ከፋፋይ መርዝ ይዘው መጡ። “ሁላችንም በጎጥ እንደራጅ፣ በማንነታችንና በቋንቋችን ላይ እናተኩር” ብለው ሰበኩን።
OROMO PROTEST FACEBOOK BY Natinael Mokonnen BIYA KEGNA IRETI GUDENA ESA DEMINA -YADEGINBETIN MERET YET TILEN ENHIEDበተቀነበበልን የጎጥ አጥር ተጨፍነን ገባንላቸው፣ ያለፈ አስቀያሚ ታሪካችንንና አፅም እየቆፈርን የምንበቃቀልበትን ስልት እያዘጋጁ ሲሰጡን ሳንመረምር ተቀበልን። ካለፈ ታሪካችን ስህተት በባሰ ስህተት ውስጥ ገብተን መሳርያ ሆንን። አሁን ባንነን ዐይናችንን ስንገልጥና ልቦናችንን ስናቀና እነ አቦይ ስብሃት፣ እነ አቦይ ፀሃይ፣ እነ ሳሞራ የኑስን የመሳሰሉ ወያኔዎች መሬታችን፣ቀሪውን ሃብታችን፣አጠቃላዩን ህልውናችን በእጃቸው ውስጥ ሆኖ ሲሳሳቁና ሲዘባበቱብን አገኘናቸው። ከእኛ እጅ የቀረው ክፍፍልን፣ ለብሄረሰብ መብታችን በየዓመቱ ተሰባስቦ መጨፈርና በርሃብ ማለቅ ሆነ።
አባቶቻችን አይደለም መጽሃፍ ቅዱስ፣ መድፍና መትረየስ ይዘው የመጡ የውጭ ጠላቶችን እጃቸውን እየሰበሩ መልሰዋቸዋል። የኤይድስ ቫይረስ ከሌላ የሰውነት ህዋሳት ጋር ተመሳስሎ በማጥቃቱ መከላከል እንደሚያስቸግረው ሁሉ የእኛ ደም፣ ቀለምና ቋንቋ የተካኑ የባንዳ ልጆች ለይቶ ማጥቃት ስላልተቻለን አሁን አለንበት አዘቅት ውስጥ ተገኝተናል። የህወሃቶች ብቸኛው ሃይላቸው ህዝበን የመከፋፈል ክህሎታቸው፣ የብዙሃኑ ህዝብ ድክመትም በአንድነት ቆሞ የጋራ ጠላቶቹን መታገል አለመቻሉ ነው። ከብዙ ልፋትና መከራ በኋላ ዐይኑን መግለጥ የጀመረው ኢትዮጵያዊ የተከሰተለት እውነት ቢኖር ይኸው ነው።
አንገታቸው ላይ ኩሺት ብቻ ጠቅልለው የመጡ ወያኔዎች በአንድ ጀንበር ሚሊዬነር፣ የብዙ ፎቆች ባለቤቶች፣ ሰፋፊ የከተማና የእርሻ መሬት ከበርቴዎች፣ በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካና በቻይና የብዙ ካምፓኒዎች ባለቤትና ባለድርሻ ሲሆኑ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የከተማ መሬቱን ተነጥቆ ዘበኛቸው፤ እርሻው ተነጥቆ የቀን ሠራተኛቸው፤ መብራቱ ጠፍቶበት ሻማ ይዞ እነሱን እራት የሚያበላቸው፤ መድረሻ ካጣም በስደት የእየአገሩን እስር ቤት የሚሞላና ኩላሊት ገባሪ ሆኗል።
ዛሬ የወላጆቻችን መሬት ሊነጠቅ አይገባውም ብለው የተነሱ የኦሮምያ፣ የጋምቤላ፣ የጎንደር ልጆችን የሚጨፈጭፉት ህወሃቶች አገዛዛቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ ህዝቡ በገባርነት እንዲኖር የትምህርት ስርዓቱን ሲገድሉት፤ የእነሱ ልጆች በስዩም መስፍን ተቆጣጣሪነት በቻይናና በምዕራቡ ዓለም ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች ተምረው አሁን ያሉትንና ወደፊትም የሚፈጠሩትን ይህወሃት ካምፓኒዎች እንዲመሩ፤ እያረጁ ከፖለቲካው የሚገለሉትን አባቶቻቸውን የሚተኩ መሳፍንት እንዲሆኑ እየተዘጋጁ ነው። አገር ውስጥም ልጆቻቸው አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ወላይትኛ እንዲማሩ ተመቻችቶላቸው በመላ አገሪቱ እንዲሰማሩ ሲደረግ፤ ሌላው ህዝብ ከራሱ ቋንቋ ውጭ ሌላውን በጥላቻ እንዲያይና ወንዝ እንዳይሻገር ሆኖ በመንደሩ ታውሮና ደህይቶ እንዲኖር ፈርደውበታል።

የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው። እኩይ ዓላማቸው የገባው ኢትዮጵያዊ ከዳር ዳር ተንቀሳቅሷል። ዐይኑን ገልጧል። በቆየም ቁጥር አጥርቶ ያያል። በተለይም ሁለቱን ታላላቅ ህዝብ አማራንና ኦሮሞን ለመለያየት ብዙ የደከሙበት ቢሆንም የቋጠሩት መተት መፈታት ጀምሯል። የተረጨው መርዝና የተፈጠረው ክፍተት ብዙ በመሆኑ ከሁሉም ወገን የሰከነ እንቅስቃሴን ይጠይቃል። እንደህወሃቶች የእንግሊዞች መርዝ ያንገበገባቸው ጆሞ ኬንያታ ለወገኖቻቸው የሰጡት ምክር የቆየ ቢሆንም ለእኛ ዛሬ ላለነው ሁኔታ ስለሚጠቅም ላካፍላችሁ። “የነበረው የዘር ጥላቻ ማብቃት አለበት። የቆየው የጎሳ ጥቃት መቆም አለበት። ባሳለፍነው መራራ ታሪካችን ውስጥ ስንቆዝም አንኑር። ያለፉትን የከፉ ታሪኮቻችንን ከማስብ የወደፊቷን አዲሲቷን ኬንያ ማለም እመርጣለሁ። ይህንን ዓይነት ብሄራዊ ስሜትና ማንነት ከፈጠርን የኢኮኖሚ ችግራችንን ለመፍታት ረጅሙን ጉዞ መሄድ እንችላለን” ብለዋል። (Where there has been racial hatred, it must be ended. Where there has been tribal animosity, it will be finished. Let us not dwell upon the bitterness of the past. I would rather look to the future, to the new Kenya, not the bad old days. If we can create this sense of national direction and identity, we shall have gone a long way to solving out economic problems).

ባለፈው ታሪካችን አባቶቻችን ሉአላዊነታችንን ለማስጠበቅ የከፈሉትን ጉልህ አኩሪ መስዋዕትነት ያህል ብዙ አስከፊና አሳፋሪ ታሪክ አለን። ያንን አስከፊ ታሪካችንን የሚክዱትም ሆኑ ዘወትር የሚቆፍሩት ሁሉ በትናንት የሚኖሩ ኋላቀሮችና ዛሬን የማያዩ ጨለምተኞች ናቸው። ከሁሉም በላይ ሳያውቁት የህወሃት መሳርያዎች ናቸው። የኢትዮጵያ አፈር ትናንት በደርቡሾች፣ በግብፆች፣ በጣልያኖች ጥይት ተደራርበው ከወደቁ ኦሮሞዎች፣ አማሮች፣ ትግሬዎች፣ ወላይታዎች፣ ሶማሌዎች፣ ሲዳማዎች፣… ደምና አጥንት ውህደት የተቀመመ ነው። ዛሬም የወያኔ አጋዚ ጥይትና ዱላ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ፣ በአምቦ፣ በወለጋ፣ በጎንደር የሚወድቁ ወጣቶች እየታደሰ ያለ አፈር ነው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር አፈር! ሰሞኑን ገዛሃኝ ኦሊጋ፣ጉቱ አበራ ዴሬሳ፣ ካራሳ ጫላ፣ ደበላ ታፋ ቢሮ፣ ደጀኔ ሰርቤሳ፣ ሚፍታህ ጁነዲ ቡሽራ፣ ሙራድ አብዲ ኢብራሂም፣ በቀለ ሰይፉ፣ በቀለ ሰቦቃ ሁንዴ፣ ኢብሳ መብራቱ በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች በግፍ ተገድለዋል፤ በጎንደር ደግሞ ሽመልስ አቡሃይና ከሰላሳ በላይ እስረኞች ተገድለው በእሳት እንዲነዱ ሆኖ የግፍ መስዋዕቱ ደም ጨሶ ሰባቱን ሰማያት አዳርሷል። ወያኔዎች ይህንን ሁሉ ሥራቸውን የሚከፍሉበት ሰዓት ተቃርቦ እያቃጨለ ነው። አምባገነኖች እስከመጨረሻዋ ሰዓት አይባንኑም። ሩቅ ሳንሄድ የደርግ ባለስልጣናት አዲስ አበባ በወያኔ መድፍ ስር ሆና የቤታቸውን ቀለም ያስቀቡ ነበር። ወያኔዎች ገንዘብ አሽሽተናል፣ እናመልጣለን ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል። ኢትዮጵያዊ የሌለበት ዓለም የለም። እንደናዚ ወንጀለኞች ተለቅመው ፍርድ ያገኛሉ። እንደባተቱም ይኖራሉ።
ዛሬ ባከማቹት ጦር መሳርያና በሰራዊቱ ይመፃደቁ ይሆናል። ከአመራሮች በቀር ጦሩ የህዝብ ልጅ ነው። የተመኩበትን መሳርያ ያዞርባቸዋል። ደርግም መላ አፍሪካን የሚያስርድ ሰራዊትና መሳርያ ነበረው። በታላቁ የኬንያ መሪ ጥቅስ የጀመርሁትን በተከታዩ መሪ ጥቅስ ልዝጋ። ይቃወሙኛል ያላቸውን የህዝቡን ልጆች ጨፍጭፎ በምስራቁም ድል ተኩራርቶ የሶሻሊስቶችን መሳርያ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ደርግ። እብሪቱ ከፍ አለ። የሚደፍረኝ የለኝም፤ ዘላለማዊ ነኝ ብሎ ፏለለ። ይህንንም ዓለም በተለይም አፍሪካውያን መሪዎች እንዲያዩለት በአስረኛው የአብዮት በዓል በብዙ ሚሊዮን ዶላር ደገሰ (እንደ አሁኑ በተመሳሳይ ወቅት ብዙ ሚሊዮኖች በርሃብ እየረገፉ እንዳይነገር ታፍኗል) አብዮት አደባባይ ላይ የሰራዊት፣ የሚሳይል፣ የታንክ፣ የአየር ሃይል ትርኢት አሳዬ። ከእንግዶቹ መካከል የዚያን ጊዜ የኬንያ መሪ አራፕ ሞይ ነበሩ። ያዩት መሳርያና ሰራዊት ብዛት አስደነገጣቸው። ጎረቤት ናቸውና። አገራቸው ሲመለሱ በአንድ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ “የምን ኢምፔርያሊዝም፣ የምን ቅኝ ገዥ ያስፈራችኋል። የሚፈራስ ጎረቤታችን ሆኗል” ካሉ በኋላ በርሃብ እየተጥናፈረች ላለችው አገር መሳርያ ሳይሆን ሰላምና ምግብ መሆኑን አፅንዖ ሰጥተው ንግግራቸውን ሲዘጉ “ኩላ ቻኩላ፣ ሲታ ማዚዋ፣ ላላ ሰላማ” ብለዋል። (የስዋሂሊ ትርጉሙ “ስጋችሁን ብሉ፣ ወተታችሁን ጠጡና በሰላም ተኙ” ነው) ወያኔዎች ሆይ የሚበላው እህል የራበው፣ ፍትህ የጠማውና ግፋችሁ የጎመዘዘው ህዝብ ከድግምታችሁ ነቅቶ ሊበላችሁ እያዛጋ ነው። ካልነቃችሁ መልካም እንቅልፍ! ላላ ሰላማ!!

Amerid2000@gmail.com

Filed in: Amharic