>
5:16 pm - Friday May 23, 2808

ስለ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዳይገባችሁ ጆሯችሁን ለዘጋችሁ! [የትነበርክ ታደለ]

ሀጫሉ ሁንዴሳ “ማለንጂራ” የሚለውን “ምኑን ኖርኩት” የሙዚቃ ክሊፕ የተመለከተ ሰው ማስተር ፕላን የሚለውን ጥያቄ ለመረዳት አያዳግተውም ብዬ አስባለሁ።

በዚህ ክሊፕ ላይ የሚታየው ገጸ ባህሪ (ሀጫሉ) “እዚሁ ከጎኔ ሆነሽ አጥር አጥረው ለያዩን፣ የጋራ መኖርያችንን አጥረው ፈረካከሱን፣ የምናውቀውን እንደማናውቀው አደረጉን፣ እያየሁሽ ራቅሽብኝ..” ይለናል።

ከአዲሳባ አስርና አስራ አምስት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ያሉ መንደሮችና ነዋሪዎች እንዲሁም ኑሮዋቸውን አስቧቸው እስኪ? አዲስ አበቢት የአፍሪካ መዲና፣ የጌጠኛ ቤቶችና የሰለጠኑ ሰዎች መኖርያ፣ የቅንጡ ነዋሪዎች ማደርያ እንዲሁም የሀገሪቱ ማእከላዊ መንግስት ማረፍያ ሆና ሳለ በከተማይቱ ቅርብ ርቀት ላይ የሚኖሩት ሰዎች ምንድነው የሚመስሉት?

ባል በጋ አርሶ ዘርቶ አጭዶ ወቅቶ ሽንብራ፣ ምስር፣ ሽንኩርትና ገብስ በጀርባው ተሸክሞ አዲሳባ ውስጥ ሲዞር ይውላል። የሚገዛው ካገኘ እሰየው ካላገኘም አንዱ ጠጅ ቤት ጎራ ብሎ በአደራ አስቀምጦ በብድር በተራበ ሆዱ ጠጁን ተጎንጭቶ በተጫማው ቦቲው፣ ላብ ላብ በሚሸተው ካፖርቱ እየተንገላወደ ወደ ማደርያው ይመለሳል። ታላቅ ከተማ ስር የከተመ ጭሮ አዳሪ ምስኪን ገበሬ!

ሚስቱ ደግሞ በጎን በኩል ቅቤ፣ ወተት፣ እሸት ሽንብራ፣ የባህር ዛፍ ቅጠል ሳይቀር ተሸክማ መርካቶ ወይም ሾላ ገበያ ድረስ ወርዳ ለአዲሳበቤ ስትሸጥ ውላ በለቀመችው ሳንቲም ጋዟን፣ ዘይቷን፣ ጨዋን ገዝታ ወደ ልጆቿ ትመለሰላች። ሻማ ጨርቅ ለባሽ ባለ ኮንጎ ጫማ የኔ ምስኪን!

ይህ የተጎዳ ህዝብ ነውኮ ጭራሽ በልማት ስም መኖርያህንም ማረሻህንም ነቅለህ ትነሳለህ እየተባለ ያለው! የዚህን እንግልቱ ህዝብ የህይወት ውጣ ውረድ ለማወቅ የግድ የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ መሆን አይጠበቅብንም። እስካሁን በሀገራችን ውስጥ በልማት ስም የተደረጉት ግብታዊ እርምጃዎች በቂ ማመሳከሪያ ሊሆኑን ይገባል።

የኦሮሞ ገበሬን ጉስቁልና ወይም ሊደርስበት ያለውን መገፋት ለመረዳት የግድ ኦሮሞ መሆን አይጠበቅብንም። ወይም ደግሞ የኦሮሞን ገበሬ ጥያቄ መደገፋችን ገና ለገና *እገነጠላለሁ* ለሚል አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እውቅና መስጠትም አይደለም። እንዲህ ማሰብ በራሱ ለኔ ዘረኝነት ነው። ይህ ጥያቄ በግለሰብ ደረጃ እንኳ ቢደርስብን “አይሆንም!” የምንለው መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

እና ሀጫሉ እንዲህ ይላል “ሴቀኒ ሴሴቀኒ ከን አዳን ኑባሰኒ!” ..”ገምሰው ገማምሰው ለያዩን!”….. ትናንት ከአጠገባቸው የነበረ ድንበር ተቆርሶ፣ እርሻውም ቀርቶ፣ የፋብሪካና የህንጻ ማረፍያ ሆኖ መሄጃ ሲጠፋቸው ልክ እንደ ሩቅ ሀገር…”ተለያየን!” ማለታቸው ለዝያ ነው።

ዛሬ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል የኔ ቤት” ማለት ካልቻልን እንደ ሀገር እንዴት አብረን ኖረናል ልንል እንችላለን?! ይህ የወቅቱ ጥያቄ ነው! ብንቆምም አብረን ብንወድቅም እንዲሁ እንጂ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ጉዞ የትም አያደርሰንም!!! እናም የገበሬውን ጩኸት ለማስተጋባት ገበሬም ኦሮሞም መሆን አይጠበቅብንም! ሀቅ እንጂ፣ እውነት ብቻ!

ኢትዮ ሪፈረንስ:- የኣርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ”ማለንጂራ¨ (ምኑን ኖርኩት)የሚለውን የሙዚቃ ክሊፕ ቀጥሎ ያለውን ሊንክ በመጫን ይመልከቱት።

Filed in: Amharic