>
12:58 am - Thursday July 7, 2022

የወዳጅ ናፍቆት [አጥናፍ ብርሃኔ - ዞን ፱]

Atinaf Brhaneጠባቡ ግቢ ውስጥ እመላለሳለሁ “ወክ” መሆኑ ነው። የቂሊንጦ ጸሀይ አናት ይተረትራል፤ ስለዚህ በግቢው ውስጥ ካለች ትንሽ ጥላ ስር ሁሉም ከራሱ ጋር እያወራ የሚመላለስ ሰው ማየት የተለመደ ነው፡፡ የሳምነቱ መጨረሻ እንደመሆኑ አዳዲስ እስረኞች ወደ ቂሊንጦ ምድር ስለሚቀላቀሉ “የማቀው ሰው ይመጣ ይሆን” እያልኩ ከራሴ ጋር አወራ ነበር፡፡ እንደ አለም በቃኝ ትልቅ ግንብና ሰማይ ብቻ በሚታይበት ግቢ ውስጥ ባለች ቀዳዳ በምትመስል ትንሽዬ በር አመራሁ። በኮሪደሩ በኩል ወደ ቀኝ ስዞር ከተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ክስ ተመስርቶባቸው የመጡ እስረኞች ተኮልኩለዋል። የሁሉም ፊት ገርጥቷል፤ ጸጉራቸው ተንጨባሯል። በአይኔ የሚታወቅ ፊት እየፈለኩ ሳላ አንድ ፖሊስ መቀስ ይዞ ያንዱን ወጣት ጸጉር መንጨት ይሁን መቁረጥ መለየት በማይቻልበት ሁኔታ ከወጣቱ ጭንቅላጥ ጋር ግብግብ ገጥሟል፡፡

ሁሌም አዳዲስ እስረኛ ሲገባ እስረኞቹ ላይ የማየው የመደናገጥ ፊት እኔ ቅሊንጠን ስረግጥ የገጠመኝን ያስታውሰኛል። በጠባብ ግቢ ውስጥ ጥቅጥቅ ያለ ህዝብ ክብ ሰርቶ ወክ ሲያደርጉ ስመለከት መካ መዲና ጭንቅላጤ ውስጥ መጣ፡፡ በተለይ የገባሁበት ቀን አርብ እንደሞሆኑና የእስልምና እምነት ተከታዮች ጁማን ለማክበር ነጭ ልብስ ለብሰው ስለነበር መካ መዲና ውስጥ ካባው እየተዞረ ነበር የሚመስለው።

የማቀው ሰው በማጣቴ ወደመጣሁበት ልመለስ ስል ዋናው የዞኑ መውጫ በር ተከፍቶ ብዛት ያላቸው አዳዲስ እስረኞች መግባት ጀመሩ። እርምጃዬን ገታ አርጌ ድጋሚ እስረኛን መቃኘት ጀመርኩ። ከበስተ መጨረሻ አጠር ያለ ሰው አየሁ፤ ሶስት ትላልቅ ቢጫ ፌስታሎችን ይዟል። የማውቀው ሰው አገኘሁ። አዎ ያ አጭር ሰው አብርሃ ደስታ ነበር። ማመን አቃጠኘ “እኔ ያለሁበት ዞን አመጡት?” ብዬ እራሴን ጠየኩ።

Abrha Desta (photo by Kuru Hagere FB)አብርሃ ደስታ መታሰሩን ያወኩት ማእከላዊ ከጨለማ ቤት እንድወጣ ተደርጌ በተለምዶ ሻራተን የሚባልና ከስሙ ጋር ምንም የማይገኛኝ ቤት ውስጥ ገብቼ በቤተሰብ መጠየቅ በጀመርኩበት ጊዜ ነበር። ከጨለማ ቤት እንድወጣ የተደረገበት ምክንያት የገባኝ እራርተውልኝ የጸሀይ ብርሀን ያግኝ ብለው ሳይሆን በዛ ቀን ከታሰሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እንዳንገናኝና መረጃ እንዳንለዋወጥ በማሰብ እንደሆነ ግልፅ ነበር። ከነአብርሃ መታሰር በኋላ ብዙም ሳንቆይ እኔና ጓደኞቼ ክስ ተመስርቶብን አለም ላይ ያሉ ከባባድ ወንጀሎች ተጭነውብን ወደ ቅሊንጦ ወረድን። ከአራት ወር ቆይታ በኋላ አብርሃ ደስታም ወደ እኛው ጎራ ተቀላቀለ።

እስር ቤት ባለሁበት ጊዜ ከአብርሃ ደስታ ጋር ጥሩ ቆየታ ነበረኝ። ለረጅም ጊዜ መቅዱሴ ነበር(አብረን እንበላ ነበር)፣ የባጥ የቆጡን እናወራለን፣ ገዢዎቻችንንም አምተናል፣ ጠለቅ ያለ የፖለቲካ እውቀጡንም ሳይሰስት አካፍሎኛል። ከአብርሃ ጋር ሁሉ ነገር ፍልስፍና ነው። ሳንስማማ ስንቀር “ጀመረህ ደግሞ …..” ብዬ ካጠገቡ እጠፋለሁ።
አብርሃ ከሁሉም ጋር ይግባባል። በተለይ ችሎቱን ‘አሻንጉሊት’ ብሎ ተናገረ የሚለው ወሬ አብረሃ ከፍርድ ቤት ሳይመለስ ወሬው ቅሊንጦ ደርሶ ነበር። ሲገባ ሁሉም በትንግርት አየው። በጣም ታጋሽ ነበር። የማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደሮች እየጠሩ “የኛ ሆነህ እንዴት ከአሸባሪ ጋር ትገናኛለህ?” በማለት ሊያስጨንቁት ቢሞክሩም እሱ ግን በትህትና ያስረዳቸው ነበር። አንዳንዴ እሱ የሚነግራቸውን ነገር ለማመን ሲዳዳቸው ደንግጠው መጥራት አቆሙ፡፡ ሀይለኛ ሰባኪ መሆኑ የገባኝ ያኔ ነው። የሀይማኖት ሳይሆን የፖለቲካ።

ከፖለቲካው፣ ከፍልስፍናው፣ ከወሬው….. ባሻገር አብርሃ ሌላ ነገር ጎበዝ ነበር። ሀይለኛ ሶልጀር ቦክስ ተጨዋች ነው። ይህ ጨዋታ ያየሁት እስር ቤት ውስጥ ነው። ክብ ትናንሽ የእንጨት ቁራጮችን እየወረወሩ ከፊት ወዳለችው ቀዳዳ አልሞ መጣል የጨዋታው አካል ነው። በዚህ ጨዋታ በፍቃዱ ሀይሉና አብርሃ የሚችላቸው አልነበረም። “አሸባሪ ከተባልን አይቀር መተኮስ እንለማመድ” ይል ነበር፤ ጨዋታውን ተኩስ ብሎ የጠራዋል አብርሃ። አንድም ቀን አሸንፌው ስለማለውቅ “በሰላማዊ መንገድ ነው የምታገለው ተኩስ አልችልም” እያልኩ እቀልድበት ነበር።
ችሎት በመድፈር አመት ከአራት ወር ሲፈረድበት ወደ ፍርድ ክልል ማለትም ወደ ቃሊቲ ሊወሰድ እንደሚችል ጠርጥረን ነበር። የፈራነው አልቀረም ፤ ድንገት “ቃሊቲ ተጓዥ ስለሆንክ እቃህን ይዘህ ውጣ” ተባለ። በቂሊንጦ የሚገኘው እስረኛ አብርሃን ለመሰናበት ከበበው። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ዳግም የምወደውን አብርሃ የማየው አልመሰለኝም። እቃውን ይዤ እስከ መውጫው በር ድረስ ሸኘሁት። ዳግም እንደማላገኘው ልቦናዩ ስለነገረኝ አጥብቄ አቅፌ ስሰናበተው አይኔ እንባ አቅርሮ ነበር።

እስር ቤት ውስጥ ከባዱ ነገር የቀረቡትን ሰው መለየት ነው። ብዙ ወዳቼን ከማእከላዊ እስከ ቅሊንጦ ሸኝቻለሁ። እኔም አብርሃም ካለብን ከባድ ክስ አንጻር ዳግም የማገኘው ባይመስለኝ አይገርምም። ዛሬ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰማው ወሬ ግን አብርሃን እስር ቤት ሳይሆን ከእስር ቤት ውጪ ላገኘው እንደምችል የሚያበስር ነበር። ማመን ቢከብደኝም!! እርግጥ ነው ምንም ወሬ ቢወራ ፈፅሞ የማይገመት መንግስት ባለበት አገር እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የፍርድቤቱ ትእዛዝ የሚፈጸም ከሆነ አይኔ እምባ አቅርሮ ሳይሆን በፈገግታ አብርሃ ደስታን እቀበለው ይሆናል!!!!

Filed in: Amharic