>

ሐይሌም እንደ ሌላ….[ህይወት እምሻው]

Samuel Zewun carton of Haile GebreSilaseሐይሌ ገብረስላሴን እጅግ አከብረዋለሁ፡፡

ለእርሱ ያለኝን አክብሮት በተደጋጋሚ ሚዛን ላይ እንዳስቀምጥ እያደረገ ባይፈታተነኝ ሐይሌን አከብረዋለሁ፡፡

ዛሬ ደግሞ በሶስት ደቂቃ ከምናምን ውስጥ ራሱን ሶስት ጊዜ በተጣረሰበት የቢቢሲ ቃለመጠይቁ ‹‹ዲሞክራሲ ለአፍሪካዊያን ቅንጦት ነው›› ማለቱን ሰማሁና እንደገና ፈተነኝ፡፡

ሐይሌ ‹‹መልካም አስተዳዳሪን ካገኘን ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው›› ይላል፡፡

እኔ የምልህ ሐይሌ፤ ለመሆኑ ዲሞክራሲን የቅንጦት እቃ የሚያደረግ መልካም አስተዳዳሪ እንዴት ያለ ነው… ?መልካምነቱስ ምኑ ላይ ነው?

ነው ወይስ አንተም ያንን ‹‹ከዲሞክራሲ ዳቦ ይቅደም›› አዝግ ክርክር ልትጀምረን ነው ?

‹‹ለኮስማናው ህዝባችን ዲሞክራሲ እንደ ቦርቃቃ ልብስ ስለሚሰፋው ‹‹ሩህሩህ አምባገነን›› (ቤኒቮለንት ዲክታተር) ይበቃዋል›› ይሉት ዘፈን ልትዘፍንብን ነው?

<<አፍሪካውያን ደግሞ ዳቦ ከበሉ መች አነሳቸው?>> እያልክ ልትዘባነንብን ነው?

አንተም እንደሌላ ፤

‹‹እናንተ አፍሪካውያን፤

ሩህሩሁ አምባገነናችሁ ቢነክሳችሁ ሊስማችሁ ፈልጎ ነው
ቢጥላችሁ ሊያዝላችሁ ሲሞክር ነው›› ልትለን ነው?

ሐይሌ፤ አንድ ጥያቄ ብቻ አለኝ፡፡

ድፍን የሀገርህ ህዝብ ከአንተ አይነቱ ጀግናው የተስፋ ክትባት በሚለምንበት በዚህ ጊዜ ‹‹ዲሞክራሲ ይበዛብሃል›› ብለህ ኩም ካደረግከው፣

ቀኝ ገዢዎቻችን ባሳመኑን ዘዬ ‹‹ለአፍሪካዊ ትንሽም ብዙ ነው›› ልትለን ከፈለግክ፣

አንድ ምስኪን አፍሪካዊ ሯጭ ሳለህ..

ስለምን አንደኝነትን አጥብቀህ ፈለግክ?
ስለምን ውራ መውጣት ስትችል አውራ መሆንን ናፈቅክ?
ስለምን የተሳትፎ ምስክር ወረቀትን ትተህ ለወርቅ ሜዳልያ ላብህን አንጠባጠብክ?

ስለምን ምርጡን ብቻ ፈለግክ?

ነው ወይስ ሌላው የአፍሪካ ህዝብ አመድ ሲያፍስ ወርቅ ወርቁ የሚገባው ለአንተና ለአንተ መንገድ ለጠረጉት ብቻ ነው?

አፋሽ አጎንባሹ የተሰጠውን ሲቀምስ ምርጥ ምርጡ የሚገባው ለተመረጡት ጥቂቶች ብቻ ነው?

Filed in: Amharic