>
2:34 am - Wednesday February 1, 2023

መንግስት ”አፕሪል ዘ ፉሉን” ይቀንስልን [ኣንዱዓለም ቡከቶ ገዳ]

Thinking Man....by Mesfen Mamoጊዜዉ እንዴት ይሮጣል ግን እናንተዬ?! አሁን በቴሌቪዥን ቀጥታ ፕሮግራም ላይ ”የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስንተኛ አመት በአል እየተከበረ ነው” ሲባል እኮ ነዉ ጊዜውን አስቤ የደነገጥኩት…! ከመቼዉ?! ታላቁ መሪ የግድቡን ጽንሰ ሃሳብ አምጥተው በቤቢኒሻንጉል ጉባ አካባቢ እንዲገነባ አስጠንተዉ ሀሳባቸዉን ለመተግበር ሳይችሉ ሞት ከቀደማቸዉ ስንት አመት ሞላው ማለት ነው እናንተዬ….?!በትንሹ 50 አመት አለፋቸዉ እኮ…ተወዳጁ መሪያችን ሁል ግዜም እናስብሃለን….. አባይን ለመጀመሪያ ጊዜ የደፈርከው ቤቢኒሻንጉል እንዲገነባ ፕሮጀክት የነደፍከው ታላቁ መሪያችን አጼ ሃይለስላሴ ሁል ግዜም በልባችን ትኖራለህ……ሎል፡፡
በፊት በፊት የህዳሴ ግድብ በአል ሲደርስ የበአሉ አከባበር እራሱ የሆነ ደስ የሚል ሙድ ነበረዉ…..ኢቲቪም በአመት አንድ ጊዜ እውነት የሚያወራበት አጋጣሚ ይፈጠርለት ነበር….ያዉ ”ባለስልጣናት” እና ”አርቲስቶች” ኳስ ሲጫወቱ ጋዜጠኛዉ
”……ኳሷ በአቶ አባዱላ ገመዳ እጅ ትገኛለች….. አቶ አባዱላ እያታለሉ ነዉ…. አታለዉ ሲያበቁ…. ለአቶ ካሳ ተ/ብርሃን አቀበሉ…. አቶ ካሳም በበኩላቸዉ እያታለሉ ነዉ….. አታለዉ አታለዉ …….ሰፊ ቦታ ይዘዉ ለሚገኙት አቶ አለማየሁ ተገኑ በረዥም አቀበሉ….. ሰፊ ቦታ ይዘው የሚገኙት አቶ አለማየሁ ምንም ቦታ ያልያዘዉን ፋንቱ ማንዶዬን በቁሙ አታለዉ አለፉት…የሚገርም ነው…….ባላስልጣናቱ የሚገርም ቅብብል እያሳዩ ሲሆን በተቃራኒው አርቲስቱ ፈዟል…..የፍትህ ሚኒስቴሩ ሊመቱ ይመስላል….. ከሩቁ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ጥሩ ቦታ ለመያዝ እየተመቻቸ ይገኛል… በመሃል አርቲስት ቢኒያም ወርቁ አስጥላለዉ ሲል የፌዴራል ፖሊስ ሃላፊዉ አቶ ወርቅነህ ገበየዉ በሰሩበት ፋዉል በአናቱ ተከሉት…….ይገርማል….የብአዴን አባል የሆኑት የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃነ ሃይሌ የደከሙ ይመስላል…. መቀየራቸዉ አይቀርም… ኦያያ ይገርማል…..የመጀመሪያዉ ግብ ተቆጠረ…ግብ ያስቆጠረዉ የባለስልጣናቱ ቡድን ቢሆንም አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ አና ሸዋፈራዉ ደሳለኝ ከባለስልጣናቱ በላይ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ……አሁን ኳሱ ከመሀል ሜዳ ይጀምራል……..”
ብቻ ኮሜንታተሩን ስትሰሙት ጉዳዩ ኳስ ከመሆኑ ዉጭ ሌላዉ ሌላዉ በሙሉ ሰዎቹ በመደበኛነት የሚያከናዉኑት የእለት ተእለት ተግባራቸው በመሆኑ አቦ ኢቲቪ ይሄንን እውነት የማቅረብ ልማድ ቢቀጥልበት ማለታችሁ አይቀርም .(..ያኔም አሁንም የሚገርመኝ ግን ለምን በጫዋታው ላይ የእውነት ባለስልጣናት(ያዉ የህወሃት ማለቴ እንደሆነ ግልጽ ነዉ ) እንደማይሳተፉበት ነው)…..አቦ ይሄ ጨዋታ ድሮኮ አሪፍ ነበር ……አሁን አሁን ግን ባለስልጣናቱ እና እርቲስቶቹን አመቱን ሙሉ ተዛዝለዉ (ሽርጥ ባንገታቸዉ ካደረጉ ወዲያ እኪ በቃን!) በቲቪ ስለምናያቸዉ ነው መሰለኝ ኳስ ሲጫወቱ ጨዋታው እንደድሮዉ ሊያጓጓ እና ሊያስቅ ይቅርና እንደዉም የደደቢት የእግርኳስ ቡድን ለሁለት ተከፍሎ ማለት ኤ ቡድን ከተስፋዉ ቡድኑ ጋር ሲጫወቱ የምታዩ ስለሚመስላችሁ ቻናል ለመቀየር ሁላ ትገዳዳላችሁ ፡፡
ትላንት አንዱ ጠበቃ ጓደኛዬ ”አፕሪል ዘ ፉል” ሞከረብኝ፡፡ ጥዋት 3፡00 ሰአት ላይ ደዉሎ ”አንዲ ቶሎ ድረስልኝ…በጥዋት ከፍርድቤት ጉዳዬን ጨርሼ ስመለስ መኪና በፍጥነት ሳሽከረክር ከፌዴራል ፖሊስ መኪና ጋር ተጋጭቼ አደጋ ደረሰብኝ… አሁን ጥቁር አንበሳ ነኝ.. አልጋ ይዣለሁ ሀኪሞቹ እየተሯሯጡልኝ ነዉ ”አለኝ፡፡
በጣም ደነገጥኩ፡፡
ዉሸቱን እንደሆነ ለማወቅ ግን አፍታም አልፈጀብኝም፡፡ አንደኛ ”ከፍርድቤት በጥዋት ጉዳዬን ጨርሼ ስመለስ” ያለዉ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ማንም ፍርድቤት ጉዳይ ያለዉ ሰዉ በጥዋት ጉዳዩን ጨርሶ ተመልሶ አያውቅም፡፡ በነገራቸን ላይ የሀገራችን ፍ/ቤት በሁሉ ነገሩ ኋላቀር ቢሆንም በሰአት ላይ ግን ልክ እንደአዉሮፓውያን ነዉ….ለምሳሌ ልደታ ፍ/ቤት 2፡00 ተቀጠራችሁ ማለት ስማችሁ የሚጠራዉ 8፡00 ሰአት ነዉ ማለት ነዉ ….በፍርድቤትኛ 4፡00 ሰአት ማለት 10፡00 ሰአት እንደማለት ነዉ፡፡በዚህም የተነሳ የጠበቃ ዋናዉ ስራዉ ጥበቃ ነዉ፡፡
እና ጓደኛዬ በጥዋት ጉዳዬን ጨርሼ መጣሁ ሲል ውሸቱን ለማወቅ የመጀመሪያዉ ፍንጭ ሆነኝ…. ሲቀጥል ”ጥቁር አንበሳ አልጋ ይዤ” ያለዉም በዚያ ፍጥነት ዘመድ የሌለዉ ሰው በቀላሉ አልጋ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ እንደማያገኝ ስለሚታወቅ በዛ ላይም ሀኪሞቹም እንደማይሯሯጡ እየታወቀ ተሯሯጡልኝ ሲል ኤዲያ ምን አይነት የማይረባ ውሸት ነው ባካችሁ!? ….የመንግስት ሆስፒታልኮ ኢመርጀንሲ ተብላችሁ ሄዳችሁ እኮ ሀኪሞቹ ፊታቸዉ ላይ የሚታየው እርጋታ እኮ እኮ (መንጌ ስታይል) የመኪና አደጋ ሳይሆን በሁለት አመት የሚገድል ካንሰር ሊያክሟችሁ የሚንቀሳቀሱ ነው የሚመስለዉ…. ሁል ግዜ ልፍድድ ማለት ሲወዱ.. በደሃዉ ገንዘብ እንዳልተማሩ ሁላ…!.……!ባለፈው እናቴን ላሳክም ወስጄ የደረሰብኝን ”ሚ” ነኝ ነዉ የማውቀዉ …ከዛን ቀን ወዲህ የመንግስት ሆስፒታልን እርግፍ አድርጌ ተዉኩኝ… እድሜ ለገንዘቤ ከዛ ወዲህ እኔም ሆነ ቤተሰቤ ስንታመም ወደ ባህል ህክምና ላጥ ….ሎል፡፡
ብቻ የጓደኛዬ ”አፕሪል ዘፉል” በብዙ ሁኔታ ”ዘ ፑረስት አፕሪል ዘ ፉል” ነበር፡፡ በዛ ላይ የሱ መኪናኮ በፍጥነትም የምትሽከረከር አይደለችም…. አንዳንዴ በሱ መኪና እየዞርን ስንቀመቅም(ኮሜንት ላይ ”እየተጠጣ አይነዳም” የሚል ምክር እጠብቃለሁ……ባይ ዘዌይ ይህን ምክር ሁል ግዜ በራዲዮ የሚያስተላልፈው ሞተረኛው ሰውዬ እራሱ ስንት ቀን እየቀመቀመ ሲነዳ አይቼዋለሁ…ሎል)… እናላችሁ ይህቺ ድክሞ መኪና እንዴት ጨብሲያችንን እንደምታጠፋዉ አትጠይቁኝ! ሁልግዜ የመበላሸት እድሏ 99 በመቶ ነዉ …እኔ በበኩሌ ስገፋት እንጂ ስቀመጥባት ብዙ ትዝ አይለኝም ….እንድ ግዜ እንደዉም እየገፋናት(አስ ዩዡዋል) ወደ አንድ ማደያ ስንገባ ቀጂው ”የናፍጣ ነች የቤንዚን?” አለን… ኡኡቴ ለግማሽ ኪ.ሜ ያህል ሲገፋ የነበረው ጓኛዬ ምን ቢለው ጥሩ ነው…”አረ የላብ ነች!” ሎል…. አንገቱን አየሁት በማታ በላብ ተጥለቅልቋል….አሁን እንግዲህ እሷን ነው ”በፍጥነት ሳሽከረክር ተጋጨሁ” የሚለኝ ይሄ ወገኛ!……..በዛ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ መኪና ተጋጭቶም ጥቁር አንበሳ መወሰዱ እራሱ ..ሃሃሃሃ ብቻ ክፉ አታናግሩኝ …..ሽወዳው አልሳካ ሲለው በአካል ተገናኘንና ስለ ”አፕሪል ዘ ፉል” ተከራከርን….እሱ ይህ ባህል ቢስፋፋ ደስ ይለዋል …እንደውም መንግስት እራሱ ይህ በአል ሲደርስ የሆነ ነገር ብሎን ”አፕሪል ዘ ፉል” ቢለን እንኳን ደስ እንደሚለው ገልጾ እንደውም ምን አለኝ…
”ለምሳሌ ትላንት ጥዋት ተመስገን በየነ በዜና ብቅ ብሎ ”….. ኢሃዲግ በቀጣዩ ምርጫ ከተሸነፈ ስልጣን እንደሚለቅ ደ/ር ደብረጺዮን ገለጹ …” ካለ በኋላ ትንሽ ቆይቶ ፈገግ ብሎ ”አፕሪል ዘ ፉል” ቢል ሁላ ደስ ይለኛል፡፡” አለኝ፡፡ በጓደኛዬ የዋህነት ተገርሜ የሚከተለውን ነገርኩት….
”ይኸዉልህ ወዳጄ ….መንግስት ከአራት መቶ በላይ መብታቸዉን የጠየቁ ኦሮሞዎችን ገድሎ ዋና ጥያቄያቸዉን ሳይመልስ አይዟችሁ ለጠፋዉ ንብረት ካሳ እከፍላለሁ ሲል እኮ በአፉ አልተናገረዉም እንጂ ”አፕሪል ዘ ፉል” ማለቱ እኮ ነዉ…..
ከ20 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጲያዉያን ተርበዉ ምግብ ማቅረብ አቅቶት አለምን እየተማጸነ ያለ ድርጀት በሀዋሳ የመላዉ ኢትዮጲያ ጫወታዎች ”ከቤጂንግ ኦሎምፒክ አነስ ከለንደን ኦሎምፒክ በለጥ ያለ የመክፈቻ ስንስርአት”(አንድ ካድሬ ጓደኛዬ እንዳስቀመጠው) በሚሊየኖች ብር ከስክሶ ሲያዘጋጅ በአፉ በግልጽ አልተናገረም እንጂ ”አፕሪል ዘ ፉል” ማለቱ እኮ ነዉ ወዳጄ…
ህዝቡ ስርአቱ በሙስና ተጨማለቀ በፍትህ እጦት ተሰቃየን ”አምላክ ሆይ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ” ብሎ አምላኩን ሲያማርር የሰማዉ መንግስት ሙሰኞቹን ባለስልጣናት ከክፍለከተማ ክፍለ ከተማ ቦታ ብቻ እያቀያየረ ”ዋጋቸዉን አግኝተዋል” እያለ ሙድ ሲይዝብን (ልክ ቤቢሹ ከእናቱ ጋር ሲጣላ እኔ ”ፑ በል” እለዉና የዉሸት የእናቱን እጅ ጧ ሳደርግለት ለቅሶዉን አቁሞ እንደሚስቀውዉ ማለት ነዉ) መንግስት አልተናገረውም እንጂ ”አፕሪል ዘ ፉል” ማለቱ እኮ ነዉ …………
ምርጫስ እራሱ በየአምስት አመት ስለሚደረግ ነው እንጂ ”ዘ ቢገስት አፕሪል ዘ ፉል” አይደል እንዴ….ፓርቲ አቋቁመህ ምርጫ ስትወዳደር መአት በደል ይደርስብሀል…ምርጫ ቦርድ ሄደህ ለደ/ር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር በደልህን ስትነገርው …”ቆይ ይጣራል” ይልሃል ትንሽ ቆይቶ ”እንዳጣራሁት ምንም ችግር የለም አርፈህ ቀጥል” ይልሃል…ከዛም ”ሞቶ በሞቶ ኢሃዲግ አሽንፏል” ሲልህ ”አረ ደ/ር አዲሱ ቅሬታዬን አይተህልኛል ግን ?” ስትለው ”አዎ በቃ ንካው!” ይልሃል….ይደብረሃል…ሆድ ሲብስህ ሰላማዊ ሰልፍ ትጠይቃለህ… መንግሰት እምቢ ይልሃል….. በራስህ ግዜ ፕሮቴስት ታደርጋለህ…..ፖሊስ አስከፊ እርምጃ ይወስድበሃል…. አረ ኡኡኡ ፓሊስ ጎድቶኛል ትላለህ…. ”ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን ያጣራው” ትባላለህ….. ቅሬታህን ይዘህ ስትሄድ… አሁንም ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር ማልያ ቀይሮ ምርጫዉን ባስፈጸመ ማግስት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆኖ ይጠብቅሃል….ይሄን ሰውዬ የት ነው የማውቀው እያልክ ቅሬታህን ታቀርባለህ…. ውጤቱን ግን በፊትም ለምደኸዋል…. አሁንም ታውቀዋለህ …….ድንገት ሰውዬውን ከዚህ ቀደም የት እንዳየኸው ትዝ ይልሃል…. ኦ ማይ ጋድ …ታዲያ ከዚህ በላይ ”አፕሪል ዘ ፉል” አለ እንዴ!? ጀለሴ በጥዋት ክፉ አታናግረኝ….
እናንተ ግን
ይመቻችሁ

 

Filed in: Amharic