>

በመፍሰስ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያዊያን ደምን እና እምባን የሚያደርቀው ሃይል ማን ነው? [ታምሩ ገዳ]

በመፍሰስ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያዊያን ደምን እና እምባን የሚያደርቀው ሃይል ማን ነው -Tamiru Gedaከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አገራችን ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች አብዛኞቹን ለማየት፣ለመሰማት እና ለማማን ይከብዳል። “እውን በዚህ ዘመን ይህ አይነቱ ድርጊት ለምን እና እንዴትስ ይፈጸማል? ብሎ መጠየቅ ደግሞ ተገቢ እና ወቅታዊ መጠይቅ ጭምር ነው። ለዚህ መጣጥፌ መንደረደሪያ ሃሳብ የጫረብኝ ደግሞ የአልጃዚራው ጋዜጠኛ ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ለማለት የባለሰልጣናቱን ይሁንታን አግኝቶ(በ አገሪቱ ውስጥ ጋዜጠኞች እንደልባቸው ተንቀሳቅስው የመዘገባቸው መብት ውሱን መሆኑ ይታወቃል) በምእራብ የአገሪቱ ክፍል ኦሎንኮሚ አካባቢ ሰለ አለው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያጠናቀረው አንሰተኛ ነገር ግን ሰለ ወቅቱ በደል እና ጭቆና የሚያውቅ የማንኛውንም የሰብዊ ፍጡር ልብን የሚያደማው ዘገባው ነበር ።

ታሪኩ ባጭሩ ሲቃኝ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በ ወልቃት እና ጠገዲ እንዲሁም በኮንሶ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ በተለይ በ ኢሕ አዲግ አጠራር በኦሮሚያ ክልልዊ መንግስት ውስጥ የተለያዩ የማህበረስቡ ክፍሎች የቀሰቀሱት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከተሎ በ አገዛዙ ታጣቂዎች በጥይት አንገታቸው ላይ የተመቱት አንዲት እናት ሁለት ልጆች የእናታቸው ባለፈው የካቲት ወር መቁሰል እና አሟሟትን እንዴት እንደተቀበሉት ይዘግባል። የ 9 አመቱ ደረጀ ቱሪ ወላጅ እናቱ በታጣቂዎች በተመቱ ሰሞን ሰቃያቸውን እያየ መሪር የሃዘ እንባውን ከማፈሰሱ በተጨማሪ ወላጅ እናታችው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ባላፈው መጋቢት ወር የሚወዳኡቸው ሁለቱ ጨቅላ ልጆቻቸውን እና ይህቺን አለም በሞት ሲሰናበቱ ደረጀ ዳግም አንብቷል ።ቁርጡንም አውቋል ።አንደ ወንድ አያታቸው አቶ ቀና ገለጻ መሆኑ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ6 አመት ታናሸ እህቱ አቤ “እናቴ የት ሄደች?፣ከሄደችበትስ ቦታ መቼ ትመጣለች?”የሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ የወንድ አያታቸውን የአቶ ቀና እና የመላው ቤተሰባቸው ልብን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰብ አዊ ፍጥረት ሁሉ ልብን የሚነካ ፣እንቅልፍ የሚነሳ ቁሰል እና አፋጣኝ ምላሸ የሚሻ ጉዳይ ነው ።ይህ አይነቱ የንጹሃን ደም በከንቱ መፈሰስ ፣ ህይወት እንደዋዛ መቀጠፍ እና ከሚወዱት ቤተሰቦቻቸው በታጣቂዎች መነጠቅ የተከሰተው በታዳጊዎቹ በእነ ደረጀ ቱሪ እና በእህቱ በአቤ ቱሪ ቤት ብቻ ሳይሆን በመቶዎች አሊያም በሺዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች ውስጥ ሲስማ ታዲያ ሕዝቡ አፉን አውጥቶ ይሆን በልቡ እና በ አይምሮው አንድ ጥያቄ ማቅረቡ አይቀረም። እርሱም” በመፈሰስ ላይ ያለውን የወገኖቻቸን ደምን እና እምባን ማን ያብሰለናል/ያስቆምልናል?’ የሚለውን መሰረታዊ ፣ሞራላዊ እና ሰብ አዊ መጠይቅን ነው ። በሰሞነኛው በኦሮሚያ ፡ በአማራ፣ በደቡብ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በታየው ያለመረጋጋት አደጋ ሳቢያ በቁጥሩ ላይ ልዩነቶች ቢኖሩም በመቶዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን እንዳጡ፡ አካለ ሰንኩል እንደሆኑ፣ በሺዎች ለእስራት እና ለግዞት እንደተዳርጉ የአገዛዙ ሹማማንቶች ሆኑ በተቃዋሚ ዎች ጎራ የተሰለፉ ወገኖች ይናገራሉ ። የተለያዩ አገራዊ እና አለማቀፋዊ ተደራሽነት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃናትም ዘግበውታል ።

ለችግሩም መፍትሔ በተመለከተ እንደዚሁ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ሰነባብተዋል።በመሰንዘርም ላይ ይገናሉ። እንደብዙዎች እምነት የችግሩ ምክንያትን በቅጡ ያልመረመሩት ወይም በምንቸገረን እሳቤ ተኝተው የሰነበቱት የአገዛዙ ጠ/ሚ/ር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እና ፓርቲያቸው “በአገር ቤት እና በውጪ የሚገኙ ተቃዋሚዎች እና የኤርትራ እጆች አሉበት “ በማለት ሲወነጅሉ ከርመው በሰተመጨረሻ ላይ “ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንደማይሞኝ ተረድተናል ፣ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ማንንም ተጠያቂ አናደርግም ፣ዋንኛ ተጠያቁዎቹ እኛው ነን ። ይቅርታም አደርጉልን ፣ ቤታችንንም እናጸዳለን” ሲሉ ተደምጠዋል። ምንም እንኳን በሰለጠነው አለም እና በዚህ ዘመን የቅርታ መጠየቅ እና ለተፈጸመ ስህተት ሃላፊነትን መውሰድ ግጭትን በማስወገድ (ኮንፍሊክት ሪዞሊሽን) ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሲሆኑ “ባዶ ይቅርታ ምን ሊፈይድልን ነው?፣ ይቅርታውም በ አሮጊ ጨርቅ ላይ አዲስ እራፊ ጨረቅ የመለበጥ ያህል ነው “ ያሉ እና ከይቅርታው ለጥቆ ወንጀል የፈጸሙ ሃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሞራል እና የአካል ጉዳት ሰለባዎች በተገቢው መንገድ እንዲ ካሱ፣ ያለ አግባብ ወደ እስር ቤት የተወረውሩ ወገኖች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቁ እና በመጠየቅ ላይ ያሉ ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

ከዚሁ ከጠ/ሚ/ሩ ሰሞነኛ “ይቅርታ አድርጉልን “ ተማጽኖ ጋር በተያያዘ የወቅቱ የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ፣የህዝቡን ስጋት እና ምሬትን የተገነዘቡ በአገር ቤት በሰላማዊ ትግል ከሚነቀሳቀሱት የፖለቲካ ሃይሎች መካከል የአንዱ ፓርቲ ሃላፊ ሰሞኑን “ችግሩን ለማስወገድ የሃዝቡን እልቂት እና ዋይታ ለመግታት ሲባል የሃይማኖት አባቶች በአገዛዙ ላይ ተጽኖ ያሳርፉልን “ በማለት በዚህ በቀውጢ ወቅት የመለኮታዊ ሃይል አሰፈላጊነትን በአማሪኛ ቋንቋ ለሚሰራጭ ለአንድ አለማቀፋዊ ተደራሽነት ባለው ራዲዮ አማካኝነት በግል የምልጃ መል እክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የግፍ በትር ለጊዜውም ቢሆን ያለነካቸው አንዳንድ የዋህ ወገኖች ” ከዚህ የባሰ አታምጣ” በማለት ተደላድለው መቀመጣቸው እንዳለ ሁሉ በሌላ ወገን ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ እየደረሰ ባለው የፍትህ እና የሰብ አዊ መብት ጥሰት ሳቢያ ዱር ቤቴ ብለው አገዛዙን በትጥቅ ትግል ለመፋለም እንቅሰቃሴ መጀመራቸውን የሚናገሩት ሃይሎችንም በተመለከተ “ምን እየሰራችሁ ነው ያላችሁት ?፣ ከዚህ የከፋ ምን እስኪመጣ ነው የምተጠብቁት?” በማለት የሚጠይቁ በጭንቀት እና በምሬት ወጀብ የሚናጡ ወገኖች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል።

አገሪቱ እና ሕዝቧ በዚህ እና በመሰል ችግሮች በተወጠሩበት በአሁኑ ወቅት ፣ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ ፓለቲከኞች” ብቸኛው መንገድ እና መፍትሔ የእኛ ጎዳና ብቻ ነው “ በሚሉን በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የፖለቲካ ምንነትን እና የፖለቲከኞች ማንነትን በጭራሽ የማያውቁ ከ400 ሺህ በላይ ጨቅላ ህጻናትን ጨምሮ በ ስድስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝባችን ላይ የ ረሃብ እና የሞት ደመና ባንጃበበት ፣ የለጋሽ አገራት እና ተቋማት የእርዳታ እጆች ከመቼውም ጊዜ በላይ ባጠሩበት በዚህ በአሳዛኙ እና አሳሳቢው ወቅት ላይ የመኖራችን ጉዳይ ሳይዘነጋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖቻችን እየፈሰሰ ላለው የንጹሃኖች ደምን እና እንባን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በፍጥነት የሚያደርቀው ሃይል/ወገን ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ በንጹህ አይምሮ ፣ በሰከነ ልቦና መጠየቅ ፣ለጋራ ችግር የጋራ ውይይት እና ምክክር ማድረግ ብዙዎች ወደ ሚያልሙት ወደ ዘላቂው እና ሰላማዊው ምእራፍ ያደርሳል። አገርንም ሆነ ሕዝቧን ከተደቀነባቸው ከመበታተን እና ከእልቂት አደጋ ያድናል ።

Filed in: Amharic