>
12:14 pm - Monday November 29, 2021

የሚኒሊክ ኣፈር ፥ ምን ይልክ ኬኛ [ሄኖክ የሺጥላ]

Emye Minilik Henok Yeshitila 06042016አጤ ሚኒሊክን እወዳቸዋለሁ ። የምወዳቸው ደሞ ጀግና ሰለሆኑ ብቻም ኣይደል ፥ ነጭን ስላንበረከኩ ብቻም ኣይደል ፥ አጤ ሚኒሊክን የምወዳቸው የሳቸውን ፈለግ መከተል ስለምፈልግ ነው ። ይሰማል ?

እስከማስታውሰው ድረስ በ1996 ( «እንደ አማራ ኣቆጣጠር» ) ከወሩ ባንደኛው ቀን ፥ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ( «የአማራ ቤ/ክርስቲያን» ) ጠበል ልጠመቅ ሄጄ ፥ ጠበል ተጠምቄ ፥ ትንሽ ደሞ በጀሪካን ቀድቼ ፥ ወደ እንጦጦ ማሪያም በመዝለቅ የአጤ ሚኒሊክን መካነ መቃብር ጎብኝቼ ነበር ። ከመካነ መቃብሩ ኣጠገብ ቆሜ የጀግናውን ማረፊያ በኩራት እያየሁ በሃሳብ ቤተልሄምን ከበው ፥ የክርስቶስን መወለጃ ተብሎ የሚታሰበውን እርካብ ድንጋይ በከንፈራቸው የሚመጠምጡ ( ውዴ የኔ ነው እኔም የሱ ነኝ ፥ በከንፈሩ መሳሙንስ ይሳመኝ እንደሚሉ ማህለየ ሶሎሞናዊያን ) ፥ ኣፈሩን ፈጭተው የሚቀቡት ፥ እምነቱን ገላቸው ላይ ያለ ኣንዳች «ሰው ምን ይለኛል» ጭንቀት የሚነሰንሱት ድህነት ፈላጊ ፥ በፍቅር ሞት የሰከሩ ኣፍቃሪ ተከታዮች ፥ ምዕመኖች፥ በመንፈሴ ሽው ኣሉ ። የመሃመድን ካዕባ እየዞሩ የሚስሙትም በጭንቅላቴ መጡ። ዛሬ ደሞ እኔ በነጭ ፥ በጥቁር ፥ በባሪያ ፥ በኣስጋሪ፥ በሚሲዮናዊ ፥ በኣሳሽ ስለ ጀግንነቱ የተከተበለት ሰው መካነ መቃብር ፊት ለፊት ቆሜያለሁ ። በጥቂት እርምጃዎች ርቀት ላይ ፥ የሮም ወታደሮችን ያንበረከከ ፥ የጥቁር ህዝብ ታሪክን የቀየረ ፥ ነጮች እንዳይታበዩም ፥ ኣንዳይሽሩም ፥ ደሞ ኣንዳይሞቱም ኣድርጎ ያሸነፈው ያ! የጥቁር ፈርጥ ሚኒሊክ ካረፈበት መቃብር ፊት ለፊት ቆሜ’ያለሁ ። የምኒሊክ መካነ መቃር ኣጠገብ የበቀለው ሳር ፥ ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለውን ኣስታወሰኝ ። የምኒልክን ስም ለማጥፋት እለት እለት የሚረባረቡት ፥ መጥሃፍ የሚጥፉት ፥ ጉባኤ የሚቆሙትም በዛች ቅፅበት ትዝ ኣሉኝ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው» እንዳለው ፥ እኛም የነፃነትን ራስ ገደልነው ታሪክ ግን እኛን ሳይሆን እሱን ያስታውሳል ፥ እኛን ሳይሆን ምንሊክን ያነሳል ። ምክንያቱም በኛ ውስጥ ያለው ትዕቢት የምኒሊክን እውነት መገልበጥ የሚቻለው ኣይደለምና!

እርግጥ ሚኒሊክ በድንጋይ መቃብር ውስጥ በድኑ ቢታተምም ፥ ህልውናው ግን ተነስቷል ። ክርስቶስ መቃብር ፈንቅሎ እንዳይነሳ በትልቅ ድንጋይ ቀብሩን ያተሙት ኣይሁዶች (በወንጌል እንደተጻፈው) ለ መግደላዊት ማርያም ፥ የያዕቆብም እናት ማርያም ና ሶሎሜም ጭንቀትን ፈጥሮባቸው ነበር ። እኒህ ሴቶች ጌታችንን ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ በሄዱ ጊዜ ትልቁ ጭንቀታቸው የነበረው «ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?»የሚል ነበር። ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና። ግን አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ በአጤ ምኒሊክም የሆነው ያ ነው ። ስራውን ለመቅበር ትልቅ የኣኖሌ ድንጋይ ኣንከባለው ማንነቱ ላይ ቢጠርቡም፥ ስሙን ቢያጠፉም ፥ ቢሳደቡም፥ ቢዝቱም ፥ የምንሊክን ማንነት ለመቅበር የተከመረው ድንጋይ ተንከባሏል ። ኣለም የሚያውቀውን ጠሃይ የሞቀውን እውነት ማንሸራተት እንዴት ይቻላል ።

ኣዎ የሚኒልክ መካነ መቃብር ኣጠገብ ቆሜ’ያለሁ ፥ ኣፈሩን በእርጋታ በእጆቼ ጨበጥኩ ፥ በቀስታ ጠበል በተሸከምኩበት የውሃ ጀሪካም ውስጥ ኣፈሩን ዶልኩት ። ትንሽ ነቅነቅ ፥ ነቅነቅ ካደረኩ በኋላ ጠጣሁት ! የፍቅር ጠበል ፥ የነጣነት ጠበል ፥ የድል ጠበል ። ኣየህ ደሜ ያንን ኣፈር የተሸከመ ነው ። ሃዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ «አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም» የሚለው በኣፈሩ ውስጥ ያለውን ፍሬ ነው ። እሱን ነው የጠጣሁት!

“እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፬÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፭÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ” ምኒሊክ ከሞተ በኋላ በታሪክ መነሳቱ የትንሳኤው ምሳሌ ነው ፥ የኣጥንቱ ኣፈር በኔ ደም ውስጥ መዘዋወሩ የትንሳኤው ምሳሌ ነው ። የማይነሱት ታሪክ የሌላቸው ፥ ኣሻራ የሌላቸው ፥ በ አሉባልታ መንግስት መሆን የሚሹ ፥ በክስ ሀገር መንጠቅ የሚፈልጉ ፥ በትዕቢት ህይወት መሆን የሚፈልጉ ናቸው ፥ እነሱ ኑረው ስለማያውቁ ኣይሞቱም ። ስለዚህ ትንሳኤንም ኣያዩም!

ሚኒሊክ ኬኛ!
Filed in: Amharic