>

ኢትዮጵያዊያን የሚሹት “ግንብ “የሚያንጽላቸው መሪን ሳይሆን ድልድይ የሚዘርጋላቸውን ነው [ታምሩ ገዳ]

“በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ። እነዚህ በሃብታቸው እና በፍቅራቸው ወደር የሌለው ወንድማማቾች ከመፈቃቀራቸው የተነሳ የቤታቸው በራፍ እና መሰኮቶቹ እንኳን ሳይቀር ፊት ለፊት ነበር ።በዚህ እና መሰል ፍቅራቸው የተነሳ አላፊው አገዳሚው ሁሉ በሁለቱ ወንድማማቾች የቀናባቸው ነበር ። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን የጥላቻ መንፈስ በአንደኛው ወንድም ልብ ውስጥ ሰርጾ ኖሮ ወንድሙን በጭራሽ እንዳይመለከት ከሚያሰመኘው ደረጃ ላይ ይደርሳል።
Tamiru Geda's 08042016እነዚያ በአንድ ወቅት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች የነበሩት ወንድማማቾች ፍቅራቸው ተቀዛቅዞ ሆድ እና ጀርባ በሆኑበት ወቅት ላይ አንድ ሰው በጥላቻ መንፈስ ከወደቀው ወንድሙ ቤት ያንኳኳል ። ወንድምየውም እንግዳው ሰውን ‘ምን ፈለግህ?’ በማለት የጠየቀዋል። እንግዳውም የእጅ ጥበብ እንዳለው እና ለባለጸጋው ግለሰብ የፈለገውን ነገር ሊሰራለት እንደሚችል ይነግረዋል። በሩ የተንኳኳበት ባለጸጋም ያ በአንድ ወቅት ከእራሱ በላይ አብልጦ ይወደው የነበረው ወንድሙን ለዘላለሙ ላለማየት በመሻት በሁለቱ ወንድማማቾች ቤት መካከል ሰማይ ጠቀስ እና ግዙፍ ግንብ እንዲገነባለት ትእዛዝ በመስጠት እና የሚያሰፈልገውን መሳሪያዎችን ሁሉ በማቅረብ ወደ እሩቅ መንገድ ይሄዳል። እንግዳውም የተባለውን ሁሉ ለመፈጸም ቃል ገብቶ ስራውን የጀምራል ። ያ ተጓዥ ባለጸጋም ከመንገዱ መመለሱን የተረዳው ግንበኛም ሰራውን ማጠናቀቁን ለባለጸጋው በመግለጽ የስራውንም ውጤት በማስጎብኘት ርክብክብ እንዲያድርጉ ይጠይቃል።
ያ በወንድሙ ላይ በጥላቻ ሰሜት የሰከረው ባለጸጋ ወንድምም ከግንባታው ሰፍራ ሲደርስ የተመለከተው እርሱ የተመኘው እና ገንዘቡን ያወጣበት ሰማይ ጠቀስ “የጥላቻ ግንብን “ሳይሆን እጅግ የተዋበ እና ሁለቱ ወንድማማቾችን በቀላሉ የሚያገናኝ ድልድይን ነበር ። ያ እንግዳ (ድልድይ ቀያሽ) የባስ ብሎ ከድልድዩ ጫፍ ላይ አንድ እየሳቀ ፣እጁን እና ፊቱን በጥላቻ መንፈስ ወደ ወደቀው ባለጸጋ ወንድሙ ቤት የሚመለከት እና ፍቅር አዘል እጆቹንም የዘረጋ አንድ ሃውልት አቆመለት ። ታናሽ ወንድሙም ለጊዜው መጥፎ ምኞቱ ባለመሳካቱ ብስጭጭት ቢልም የቀድሞ ፍቅራቸውን ዞር ብሎ ሲቃኘው ከወንድሙ ጋር ከሚያቃቅራቸው የሚያፋቅራቸው ነጥቦች መብዛቱን በመረዳት ወንድሙን ይቅርታ እንዲያድርግለት ሳይውል ሳይድር ወደ ወንድሙ ቤት ነጎደ። የጥላቻ ግንብ እንዲሰራ የታዘዘውም ግንበኛ ማነነቱን ሳይገልጽ ከስፍራው ተሰውረ።” ይህ ስር ነቀል እና ምሳሌያዊ ትምህርት ሰሞኑን ብዛት ላላቸው ምእመናኖቻቸው ያሰተላለፉት በአሜሪካው በሎሳንጀለስ ከተማ ውስጥ ከሚገኙት አያሌ የኢትዮጵያዊያን የእምነት ትቋማት መካካል አንዱ በሆነው በድንግል ማሪያም የኢ/ኦ /ተ/ቤ/ክ ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ አንደበተ ርእቱ ፣ በመንሳዊ ብቃታቸው ትጉህ እና ቀና የሆኑ አባት የአብይ ጾምን እኩሌታ( ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ሰለ መጨረሻው ዘመን/ምጻት ምልከቶች /በደብረዘየት ተራራ ላይ ተጥይቆ የሰጠው ሰብከትን (ማቴ 24) )በማሰመልከት ነበር።
Tamiru Geda's 08042016-1እኔም የስብከተ ወንጌሉ ማሳርጊያ የሆነው ይህ ምሳሌያዊ እና እጅግ ማራኪ ትምህርቱ እንዳበቃ ውስጤ ብዙ ነገሮችን እንዳወጣ እና አንዳውርድ አጫርብኝ። ለጊዜውም ቢሆን ከምንኖርበት የምእራቡ አለም አንስቶ በብዙ ሺህ ማይሎች እርቀት ላይ የምትገኘው አሰከ እናት ኢትዮጵያ ያለውን ዘመን አመጣሹ የፖለቲካ አዙሪትን በምናቤ እንድቃኘው ተገደድኩኝ። አሜሪካዊው ቱጃር የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪው ዶናል ትራምፕ “ከመረጣችሁኝ አሜሪካንን ከጎረቤት ሚክሲኮ የሚጋርድ/የሚያግድ ሰማይ ጠቀስ ግንብ አስገነባልሁ፣ እናንተም እፎይ ትላላችሁ፣ሙስሊሞችም ቢሆኑ ወደ አሜሪካ ምድር ዝር እንዳይሉ/ አንዳይገቡ አደርግላችኋለሁ “። በማለት ለደጋፊዎቻቸው ምን አይነት ያረጀ እና ያፈጀ “የጥላቻ ግንብን “ እንዴት እንደሚገነቡ መገለጻቸው አይዘነጋም። በዚህ ዘረ እና ሃይማኖትን ማእከል ካደርገው የዘረኝነት ቀሰቀሳቸው ሳቢያ በአሜሪካ የተወለዱ ፣ ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው የኢትዮጵያዊነት ደም ያላቸው በርካታ ኢትዮ- አሜሪካን ህጻናት ሳይቀሩ ወላጆቻቸው “የጥላቻ ግንብ “ አናጺው ትራምፕን እንዳይመርጡ ባቸው በጽኑ ሲማጸኑ ለመሰማት ችያለሁ። ሁኔታውም የ”ዘረኝነት ግንብ”የቱን ያህል በትውልድ ተረካቢዎቹ በህጻናቱ ዘንድ ሳይቀር ምን ያህል የተወገዘ እና የተጠላ መሆኑን በአጭሩ ያመላክታል።

ይህ “የጥላቻ ግንብ “ ከነጮቹ አልፎ በተለያዩ የአለም ዳርቻዎች ተበታትነው የሰደት ኑሮን በሚገፉ ቀላል በማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥም መሰርቱን ጥሎ “የግንቡ” ከፍታም በእየ ጊዜው ወደጎን እና ወደ ላይ እያደገ መምጣቱ ይታያል። ነገሩ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት …ወዘተ “እንዲሉ ካልሆነ በቀር ለወትሮ የ ዘር ፣የሃይማኖት እና የቋንቋ ልዩነቶች ያልገደባቸው በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያዊያኖች ዛሬ ባለማወቅም ይሁን ለአለት ጉርሳቸው ሲሉ የአምልኮት ስፍርራዎቻቸውን እና የተለያዩ እለታዊ የማህበራዊ ግልጋሎት መሰጫ ዎቻቸውን ሳይቀር “በልዩነት ግንብ” አጥረው በሃላ ቀር እና በተራ አሰተሳሰብ ወስጥ ሲዳክሩ ለመታየታቸው አሊ አይባልም ። እነርሱም ቢሆኑ ሰለ እኩይ ድርጊታቸው አይክዱም ።

በአገር ቤትም ቢሆን ድሮ ለጋብቻ ሆነ ለተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸው ሲሉ የሚያቀራርቧቸው ድልድዮችን ሲገነቡ የኖሩት ኢትዮጵያዊያኖች ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ በዘረኞች እና በ ከንቱ ፖለቲከኞች ሳቢያ በቋንቋ ፣ በዘር ፣ በሃይማኖት ፣በጎጥ እና መሰል “ግንቦች “ ውስጥ ተከልለው ሲራኮቱ ለመስተዋላቸው ብዙም ምስክር እና ማስረጃ የሚያሻው ጉዳይ አይመሰልም ።ምክንያቱም ሁሉንም ነገር እያየነው እና ሕዝቡም ሳይወድ በግድ እየኖረበት በመሆኑ ነው። ይህ አስቀያሚው “የጥላቻ ግንብ” አገሪቱን እና ሕዝቧን ዛሬ ምን አይነት ኪሳራ ውስጥ አንደከተታቸው “የጥላቻ ግንብ መሃንዲሶቹ” ብዙም ባይረዱትም ፣የችግሩ ሰለባዎ ች የሆኑት ሕዝቦቿ ግን የመከራው ጊዜ አንዲያጥር፣ በከንቱው የጥላቻ ግንብ ፋንታ ወደ ቀደመው በመፈቃቀር እና በሰላም ላይ የተመሰርተው ኑሯቸውን የሚመልስላቸው ድልድይ የሚዘረጋላቸው እና የሚቀይስላቸው መሃንዲስ /መሪ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ ይሻሉ።

የሁለተኛው የአለም ጦርነትን ያሸነፉት ጣምራ ጦረኞቹ ጀርመንን ምስራቅ እና ምእራብ በማለት ከመከፋፈላቸው በተጨማሪ አንድ የነበሩትን ሕዝቦችን ለግማሽ ክፍለ ዘመን በተቀበሩ ፈንጂዋች አማካኝነት የጋረዳቸው 28 ማይልስ/45 ኪሎ ሜትር “የጥላቻ ግንብ” ወይም የበርሊን ግንብ አኤ አ በ 1989 ሲደረመስ እርምጃው ከጀርመኖች አልፎ መላው የአለም ሕዝብን በሙሉ አስፈንድቋል። ጀርመንም ትደቅኖባት ከነበረው ከ “ጥላቻ ግንብ ” እና ከመፈረካከስ አደጋ ተላቃ ዛሬ በአውሮፓ ቁጥር አንድ ከሚባሉት እና በመላው አለም ደግሞ ከአገር ውስጥ ትርፋማነት አኳያ አምስተኛዋ ቁንጮ አገር ለመሆን በቅታለች። እኛ ኢትዮጵያዊያንስ ብንሆን ተባብረን የዘረኝነትን እና የጥላቻን ግንብን ተባብረን ከደረመስነው ሌሎቹ አገራት ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያግደን የትኛው ምድራዊ ሃይል ይሆን?። በጭራሽ የለም። ሊኖርም አይችልም።

Filed in: Amharic