>
8:08 am - Tuesday August 9, 2022

ዩኤስኤአይዲ/USAID እና ረሀብ በኢትዮጵያ፡ ለመሆኑ ጋይሌ ኢ. ስሚዝ ምን እያለች ነው? [ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም]

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Gayle Smith pixየጸሐፊው ማስታወሻ፡  ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርበው ጽሁፍ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ለሆነችው ለጋይሌ ኢ. ስሚዝ እ.ኤ.አ መጋቢት 16/2016 በቀጥታ የጻፍኩላት ደብዳቤ ትክክለኛ ቅጅ እና ለዚህም ደብዳቤ ምላሽ በዩኤስኤአይዲ/USAID ረዳት አስተዳዳሪ በቲ.ሲ ኩፐር፣ ከሕግ እና የመንግስት ጉዳዮች ቢሮ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 7/2016 የተሰጠውን ምላሽ ያካተተ ነው፡፡

የላኩት ደብዳቤ ሚስስ ስሚዝ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሀብ በማስመልከት የሰጠችው መግለጫ እውነተኛ ስለመሆኑ እና የፖሊሲ ማብራሪያዎችን ይጠይቃል፡፡

የሚስተር ኩፐር ደብዳቤ በአስተዳዳሪዋ ላይ ስላቀረብኩት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጥ እና በተጨባጭ ያቀረብኳቸውን እውነታዎች እና የፖሊሲ ጉዳዮች ገሸሽ በማድረግ አልፎፏቸዋል፡፡

ቀደም ሲል ሚስስ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ እንድትሆን ቀርቦ የነበረው ሹመት እንዳይጸድቅ በጥብቅ ተቃውሜ እንደነበር በሰፊው የታወቀ ነገር ነው፡፡ ሆኖም የአሜሪካን ሴናት ሚስ  ስሚዝን ሽመት ስላፀደቀ እና እንደ አጥባቂ  የሕገ መንግስት ባለሞያ ሴናቱ የሰጠዉን ዉሳኔ ተቀብያለሁ  ተፈጻሚነቱንም አከብራለሁ፡፡

የእኔ የጥያቄ ደብዳቤ እንደ አሜሪካዊ ዜግነቴ እና እንደ ግብር ከፋይነቴ በግልጽ በሚያሳስበኝ ጉዳይ ቀጥታ የሚመራ እንጅ እንዲሁ ከሹመት ማጽደቁ ሂደት ጋር በተያያዘ መልኩ በባዶ ግላዊ መከፋት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡

የሚስስ ስሚዝን ሹመት በመቃወም ሳቀርባቸው ከነበሩት ትችቶቼ መካከል በመጀመርያውትጽሁፌ እንዲህ የሚል ቃል ገብቼ ነበር፣ “የስሚዝን ይፋ ድርጊት እና ውሳኔዎች የአሜሪካ ሕግ በሚፈቅደው እና ባለው በማንኛውም የሕግ አማራጭ ተጠያቂ አናረጋታለን…“

የእኔ የጥያቄ ደብዳቤ ዋናው ዓላማ “እርዳታን ለመጨቆኛ መሳሪያ“ እና ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ያለ የሙስና ታሪክ ካለው መንግስት ጋር በተያያዘ መልኩ የአሜሪካ ሕዝብ የግብር ዶላር አጠቃቀም ላይ ዩኤስኤአይዲ/USAIDን ተጠያቂ ለማድረግ ነው፡፡

ጥያቂያችን ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

===========  ==============  =============  ============

እ.ኤ.አ መጋቢት 16/2016
ሚስስ ጋይሌ ኢ. ስሚዝ
የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ
አስተዳዳሪ
1300 ፔንሲልቫኒያ አቬኑ፣ ኤንደብልዩ
ዋሽንግተን፣ ዲሲ 20523

በዩ.ኤስ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተረጋገጠ 

ውድ ሚስስ ስሚዝ፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 3/2016 ከጀምስ ኪርቢ ጋር አድርገሽው በነበረው ቃለመጠይቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ ስላለው ድርቅ “አዲስ እርምጃዎች“ ለመውሰድ ዓላማ አድርገን እንሰራለን ስላልሽው ሁኔታ ጉዳዩ ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመከታተል ነው ይህንን ደብዳቤ የጻፍኩልሽ፡፡ በደብዳቤየ የቅሬታ ስሞታ ከማቅረቤ በፊት እንዲሁም ጉዳዩ ግልጽ እንዲሆን ገና ከመጀመሪያው የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ሆነሽ እንዳትሾሚ እና ሹመትሽም እንዳይጸድቅ ጠንካራ ተቃውሞ ሳቀርብ የነበርኩ መሆኔን እንድተገነዘቢልኝ እወዳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 12/2015 የአንቺ ሹመት እንዳይጸድቅ ለዩኤስ ኮንግረስ በመጻፍ ተቃውሞየን አሰምቼ ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች በርካታ የውትወታ መልኮች እና መድረኮች እንዲሁም በእራሴ ድረ ገጽ ጭምር በመጠቀም ተቃውሞየን ስገልጽ ቆይቻለሁ፡፡

የአንቺ ዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪነት ሹመት እንዳይጽድቅ ስቃወም የቆየሁባቸው ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ፡፡ እነርሱም፣

1ኛ) በአፍሪካ የዴሞክራሲ፣ ነጻነት እና የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መስፋፋት እና መደገፍን አስመልክቶ ያለሽ ታሪክ ደካማ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

2ኛ) ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለአፍሪካ አምባገነኖች ስታደርጊ የቆየሽው የማያወላውል ድጋፍ የአፍሪካን ሕዝቦች ደህንነት ሲጎዳ የቆዬ መሆኑን አምናለሁ፡፡

3ኛ) አፍሪካውያን ለዘላለም ከአሜሪካ ጠንካራ ግብር ከፋይ ሕዝብ ኪስ ጋር ተቆራኝተው የሰብአዊ እርዳታ ተቀባዮች ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ በምታራምጅው የአሜሪካ የአፍሪካ የውጭ ፖሊሲ አቀራረብሽ ላይ ተቃውሞ አለኝ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህንን ጉዳይ ግልጽ እያደርግሁ ያለሁት ባለፈው ጊዜ ሳቀርብ የነበረውን ተቃውሞ ለመድገም አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይህ አስቸኳይ የጥያቄ ደብዳቤ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ በማሰብ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ድርቅ ለመቋቋም ዩኤስኤአይዲ/USAID እያደረገ ያለውን ጥረት በማስመልከት እ.ኤ.አ መጋቢት 3/2016 ለጆን ኪርቢ በሰጠሽው ቃለመጠይቅ እኔን ያስደነቁኝ፣ ግራ ያጋቡኝ እና እንቆቅልሽ የሆኑብኝ በርካታ ነገሮችን ተናግረሻል ፡፡

1ኛ) በቃለ መጠይቁ ላይ በሰጠሽው አስተያየት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድርቅ ኤልኒኖ እየተባለ የሚጠራው እና ከኢትዮጵያ በበለጠ ሁኔታ የትም ቦታ ጉዳት ያላደረሰውን በርካታውን የዓለም ክፍል እያጠቃ እንዳለ አድርገሽ የአየር ለውጥ (ኤል  ኒኖ ) ውጤት ነው የሚል ጠንካራ አቋም አራምደሻል፡፡

“ኢትዮጵያ ከየትኛውም የዓለም ክፍል በበለጠ ሁኔታ በፕላኔቷ ከሚገኙት ሀገሮች ሁሉ በብቸኝነት በድርቁ በእጅጉ የተጎዳች መሆኗ በልዩ ታምራዊ ኃይል እና ቁጣ ነው” የሚል እንደምታን የሚያመላክት በመሆኑ የሰጠሸው ትንታኔ በእጅጉ አስደንግጦኛል፡፡

ስለድርቁ ሁኔታ የሰጠሽው ትንታኔ ባለጥቁሩ ፈረስ የምጽዓት ቀን የደረሰ እና ኢትዮጵያን በመጎብኘት ከሌሎች ሀገሮች በተለየ ሁኔታ በልዩ ታምራዊ ኃይል ቅጣት የጣለባት በሚመስል መልኩ ያቀረብሽው ስለሆነ ነገሩን ሳስበው ሀሳብሽ እጅጉን አስደንግጦኛል፡፡

ኤልኒኖ በፕላኔቷ ውስጥ ካሉት ሀገሮች ሁሉ በበለጠ መልኩ ኢትዮጵያን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃበት ምክንያት ምንድን ነው?

2ኛ) በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል ስለመልካም አስተዳደር እጦት፣ በዕቅድ መመራት እና አስተባብሮ መስራት ባለመቻሉ ምክንያት ቢያንስ ቀረቤታ ያለው ወይም ደግሞ እውነተኛ ምክንያት ስለመሆኑ በሰጠሽው አስተያያት ላይ ፍጹም የጠቀስሽው ነገር የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአንቺ የድርቅ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ከፍተኛ በሆነ መልኩ ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ቢሆንም ቅሉ ድርቁ ላስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ደካማ ምላሽ እየሰጠ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ነገር ትንፍሽ አላልሽም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ተከስቶ ላለው ድርቅ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ እና አቅዶ መስራት ያለመቻል ለድርቁ መነሻነት፣ መስፋፋት እና/ወይም መንሰራፋት ያላቸው ሚና ትንሽ ነው ብለሽ ታምኛለሽን? በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ገዥ አካል ስለመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስለቢሮክራሲው ሽባነት/ብቃትየለሽነት እና ስለሙስና የእራስሽ ኤጀንሲ/ድርጅት ጥናት አድርጎ ስለድርቁ ወይም ደግሞ ድርቁ ስላስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ያቀረበው የጥናት ውጤት ይኖራልን?

3ኛ) በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰብአዊ እርዳታ እና ለድርቁ እርዳታ እገዛ የሚያደርግ ቡድን እየተባለ የሚጠራ የሰው ኃይል የተላከ መሆኑን ግልጽ አድርገሻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኤስ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ እርዳታ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ጠቁመሻል፡፡

በእርግጥ 500 ሚሊዮን ዶላር ያለምንም ጥርጥር ትልቅ ገንዘብ ነው፡፡ እንደ አሜሪካ ግብር ከፋይነቴ እንደዚህ ያለው ልግስና ምን ያህል እንደሚቆጠቁጥ አምናለሁ፡፡

የእኔ ጭንቀት ያለው 500 ሚሊዮን ዶላሩን ከመጠቀም አንጻር በሚፈጸመው ሙስና ላይ ነው፡፡ አንቺ እንደምትገነዘቢው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዥ አካል ለሰብአዊ እርዳታ ተብሎ የሚሄድን ገንዘብ እንደሚያባክን፣ እንደሚሰርቅ እና ለፖለቲካ ዓላማዎች (የምርጫ ድምጽ ለመግዛት) ማራመጃ እና ለሙስና ያውለዋል፡፡

እዚህ ላይ “ኢትዮጵያ፡ የሰብአዊ እርዳታ ለፖለቲካ ዒላማ መሳሪያ መጠቀሚያ“ በሚል ርዕስ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣውን ዘገባ እጠቅሳለሁ፡፡ ያ ዘገባ እንዲህ ይላል፣ “በኢትዮጵያ ያለው ጨቋኝ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ተብሎ የሚላክን የውጭ እርዳታ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ባለስልጣኖች ስልጣናቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም ለተጎዱት ዜጎች መድረስ ያለበትን እርዳታ ያለመስጠት ወይም ድግሞ ገንዘቡን የፖለቲካ ወገንተኝነት ላላቸው ካልሆነ በስተቀር ለሌሎች ማግኘት ላለባቸው ዜጎች አይሰጡም“ በማለት ይፋ አድርጓል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የዩኤስኤአይዲ/USAID ቢሮ ዋና ተቆጣጣሪ ኦዲተር እንዲህ የሚል ድምዳሜ ሰጥቷል (ገጽ 26 አባሪ 1ን ይመልከቱ)፡

…በድርጅቱ የስራ አመራር እና በዘገባ አቀራረብ ስርዓቱ ተልዕኮ ድክመት ምክንያት የተደረገውን ትክክለኛ የእርዳታ እገዛ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አልቻልንም፡፡ ከዚህም በላይ የዩኤስኤአይዲ/USAID/ኢትዮጵያ የስራ ዕቅድ እና ዘገባ እውነተኛ ስለመሆናቸው ኦዲተሩ መወሰን አልቻለም፣ ምክንያቱም የድርጅቱ ሰራተኞች ውጤቶቹ እንዴት እንደተገኙ መግለጽ አልቻሉም ወይም ደግሞ በዘገባው ለቀረቡት ውጤቶች ምን ዓይነት ድጋፍ እንዳረጉ ማስረዳት አልቻሉም፡፡

አገዛዙ ለሰብአዊ እርዳታ የተገኘውን 500 ሚሊዮን ዶላር ለፖለቲካ ማስፈጸሚያ እንዳያውለው ምን የተቀመጠ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች አሉ?

ከላይ የተጠቀሰውን ሰብአዊ እርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዳደር እና ከሙስና ለመከላከል ምን ዓይነት የተጠያቂነት ሂደቶች በስራ ላይ ውለዋል? በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ገዥ አካል ከተሰጠው 500 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ምን ያህሉን በእራሱ ስልጣን እንደሚጠቀምበት እና ምን ያህሉንስ በእራሱ ስልጣን ሊጠቀምበት እንደማይችል መጠኑ ይታወቃልን?

4ኛ) እንዲህ በሚለው መግለጫሽ ፍጹም በሆነ መልኩ ደንግጫለሁ፣ “ተረጅዎቹ መሬታቸውን የሚሸጡ ከሆነ ወይም ደግሞ ለጊዚያዊ ስራ ፍለጋ መሬታቸውን ትተው ወደ ሌላ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ይህ በጣም መጥፎው አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረሻል፡፡“

ይቅርታ! ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን ሁሉም መሬት የ መንግስት መ ሆኑንና ግለ ሰብ ለመሸጥ መለወጥ አንደማይቻል ታውቂያለሽን? የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት መሸጥ እንደማይችሉ በሕግ የተከለከሉ መሆናቸውን ትገነዘቢያለሽን? ኢትዮጵያን ከሌሎች መሬትን ሙሉ በሙሉ በግል ይዞታነት ከሚይዙ ሀገሮች ጋር አዳብለሽ በመያዝ ተምታቶብሽ ይሆን ?

5ኛ) እንደምታውቂው ሁሉ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል “የመሬት ቅርምት” ፖሊሲን በማስፋፋት ላይ በመሆኑ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ላለው አመጽ ዋና ምክንያት ሆኗል እየተባለ ይነገራል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሙያው የበቁ ትችት አቅራቢዎች ሲናገሩ እንደቆዩት ገዥው አካል የሀገሪቱን ለም መሬት በሊዝ/ኪራይ ለውጭ ኢንቨስተሮች በመቸብቸብ ላይ የቆየ ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ለተከሰተው ረሀብ እና የምግብ ዋስትና እጦት ከፊል ምክንያቶች ሆነው በመወቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች እጅግ ግዙፍ የሆነውን የሀገሪቱን ለም መሬት በሊዝ/ኪራይ ከመውሰዳቸው አንጻር በምግብ እህል እራስን ስለመቻል እና የምግብ እጥረትን ከመዋጋት አኳያ ምንድን እምነት አለሽ? ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት አልባ በመሆን እና በረሀብ አደጋ እና አስከፊነት መካከል ግንኙነት እንዳለ ትገነዘቢያለሽን?

6ኛ) “ቀደም ጀምረን እየተንቀሳስን ነው፣ በዚህም መሰረት ከለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ ከመንግስት እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር “ትክክለኛ ቅንጅት” በማድረጋችን ምክንያት በጣም ፈጣን፣ ፈጣን፣ ፈጣን በሆነ መልኩ ወደ ስራው እየገባን በመሆኑ የዚህን ድርቅ አስከፊ ገጽታ ለማስወገድ እንችላለን“ ብለሻል፡፡ ለመሆኑ በለጋሾች እና በሌሎች የሰብአዊ እርዳታ ሰጭ ማህበረሰቦች መካከል ያለው “ትክክለኛ ቅንጅት” በእርግጠኝነት ምንድን ነው? ቀደም ሲል በለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ወዘተ መካከል “ትክክለኛ ቅንጅት” ባለመኖሩ ምክንያት ነው እንዴ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተው እና በአስከፊ ሁኔታ የድርቅ ገጽታዎች ተንሰራፍተው የቆዩት?

7ኛ) የኢትዮጵያ መንግስት በቂ የሆነ ገንዘብ መድቧል በማለት ገልጸሻል፡፡ “እኔ እስከማስታውሰው ድረስ  በዚህ እኔን ዋቢ አድርገሽ ሳትጠቅሽ ስለቁጥሩ እነርሱን ጠይቂያቸው፡፡ 350፣ 400 ሚሊዮን ዶላር ይመስለኛል፡፡ [ቃለ መጠይቅ አድራጊው፡ እነርሱ ያሉት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡] በፍጹም፣ አይደለም፣ አይደለም፡፡ ደህና፣ ምናልባት፣ ምናልባት፡፡ የእነርሱ ቁጥር ያ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ያሳወቁትን እና ጠቃሚ የሆነውን እገነዘባለሁ፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ጠቃሚው ነገር መንግስት ለችግሩ ምላሽ እሰጠ መሆኑ ነው እናም ገንዘብ በመመደብ ከእርዳታው ስብስብ ጋር በማቀላቀል ለአስቸኳይ እርዳታው ጥሪ እያቀረበ የገንዘቡን መጠን ለመጨመር እየሞከረ ነው፡፡ ሆኖም ግን  በእርግጠኝነት ምን ያህል ገንዘብ እንደሆነ ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡

እንዲህ በማለትም ጨምረሻል፣ “እዚህ ላይ ጠቃሚው ነገር መንግስት ለችግሩ ምላሽ በመስጠት ላይ ነው፣ እናም ገንዘብ ከእርዳታ ስብስቡ ጋር እየቀላቀለ በጀቱን ከፍ ለማድረግ ለአስቸኳይ ጊዜው እርዳታ ጥር እያቀረበ ነው፡፡“

ተሳስቸ ከሆነ ለመታረም ዝግጁ ነኝ የኢትዮጵያ መንግስት አዋጣ ስለተባለው 1.2 ቢሊዮን እና ከጠቅላላ ስብስቡ ጋር ቀላቅሎ ስለመመደቡ ለሕዝብ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡ ያ 1.2 ቢሊዮን የተባለው ዶላር ነው ወይስ ደግሞ የኢትዮጵያ ብር ወይም ሌላ ገንዘብ ነው?

የኢትዮጵያ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን እ.ኤ.አ ታህሳስ 2015 እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ያጠቃውን ድርቅ ለመቋቋም 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡“

ዝም ብሎ 1.2 ቢሊዮን የሚል ቁጥር እያነበነቡ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ድጋፍ ሳይደረግ መዝለቅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳስታል፣ እና በመጨረሻ የዩኤስኤአይዲን/USAID ተማዕኒነት ከጥርጥሬ ላይ ይጥላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዩኤስኤአይዲ/USAID መግለጫ ቢያወጣ ኖሮ ጠቃሚ ነገር ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ ዋናው ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ስንት ዶላር ወይም ደግሞ ስንት ብር በመመደብ ከጠቅላላ የገንዘብ ስብስቡ ጋር ቀላቀለ የሚለው እና የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላትስ ምን ዓይነት የአስቸኳይ እርዳታ ጥሪ እያደረገ ነው የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ  ልታካፍይ ትችያለሽን?

8ኛ) እንዲህ በሚለው መግለጫሽ ደንግጫለሁ፣ “በአሁኑ ጊዜ ውጤት አስገኝቷል የሚለውን አቃልሎ ማየት አልፈልግም፡፡ የእንስሳት ሀብት እልቂት ተከስቷል፡፡ በምግብ የመጎዳት ምልክቶች እና እያደጉ የመጡ በምግብ የመጎዳት ምልክቶች ተስተውለዋል፡፡ ደኃ ገበሬዎችን ከአደጋ ለመቋቋም የሚያስችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ ድሆች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ሆኖም ግን እዚህ ላይ ትልቁ ጠቃሚ ነገር የአስቸኳይ ጊዜ አደጋን ለመከላከል ብቻ ነው፡፡“

እንዲህ የሚል መግለጫም ሰጥተሻል፣ “ሁላችሁም እንደምታውቁት ሁሉ የተራቡ ልጆች የተጎዱ ምስሎች በጋዜጦች እና በቴሌቪዥን እስኪወጡ ድረስ መጠበቅ የሁልጊዜ ድርጊት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ጉዳት አለ፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ ሁኔታ ቀድሞ መሄድ ትክክለኛ ነገር ነው፡፡“

የአንቺ መግለጫ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ያደረገው ስላለቁት እንስሳት ብቻ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ብዙሀን መገናኛዎች “ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ከተከሰቱት ድርቆች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በከፋ መልኩ እየተመታች ነው“ የሚል ዘገባ በርዕሰ አንቀጽ አምዶቻቸው ላይ እያወጡ ነው፡፡ ከ32 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1984-85 ተከስቶ በነበረው ድርቅ በረሀብ ምክንያት በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ከ42 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1973-74 ተከስቶ በነበረው ድርቅ በረሀብ ምክንያት በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀዋል፡፡

ካለፉት አምስት አስርት ዓመታት ውስጥ እ.ኤ.አ በ2016 ኢትዮጵያ እጅግ በከፋ መልኩ በድርቅ ስትጠቃ አንቺ በጋዜጣዊ መግለጫሽ ለእንስሳቱ ብቻ ትኩረት በመስጠት ስለሰብአዊ ቀውሱ እና ህይወት ስለማለፉ እንኳ ምንም ነገር አለማለትሽ ፍጹም በሆነ መልኩ ግራ አጋብቶኛል፡፡

ለመሆኑ ዩኤስኤአይዲ/USAID በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ስለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ጥናት አድርጓልን? አዎ ጥናት አካሂዷል የምትይ ከሆነ በሰው ላይ የደረሱት ሰብአዊ ቀውሶች/ጉዳቶች በተጨባጭ ምን ምን ናቸው?

9ኛ) በሰጠሸው ቃለመጠይቅ ላይ እንዲህ ብለሻል፣ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰዎች ስቃይ ምላሽ እንዲሰጥ ብቻ አይደለም እየጠየቅን ያለነው፡፡ ሆኖም ግን እጅግ በጣም አስከፊ የሆነውን አደጋ ለመከላከል እጅግ በጣም አፋጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠት ያለበት መሆኑን ነው፡፡“

በዚህ ሁኔታ ግራ ስለተጋባሁ ይቅርታ አድርጊልኝ፡፡ ለመሆኑ በ50 ዓመታት ውስጥ በጣም አስከፊ ከሆነው ከዚህ የድርቅ አደጋ በላይ ምን አስከፊ ነገር አለ?

እ.ኤ.አ በ1973-74 ከተከሰተው ወይም ደግሞ በቀሳፊነቱ ከሚታወቀው እና እ.ኤ.አ በ1984-85 ከተከሰተው አስከፊ እና አውዳሚ የድርቅ አደጋ በላይ ምን አስከፊ አደጋ አለ?

እ.ኤ.አ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት የድርቅ አደጋዎች ሁሉ እ.ኤ.ኤ በ2016 የተከሰተው የድርቅ አደጋ እጅግ በጣም አስከፊ ነው ብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለመናገር የሞራል ብቃቱ እንዳለሽ ታምኛለሽን?

10ኛ) ከዚህም በተጨማሪ ስትሰጭ በነበረው ቃለ መጠይቅሽ “የምግብ ለስራ ፕሮግራም/Safety Net Program እየተባለ የሚጠራው በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መሻሻልን አምጥቷል በማለት ስትኮፍሽ እና ስትክቢ ተደምጠሻል…ለእንስሳት፣ ለሰው እና ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ትንሽ ውኃ ለመሰብሰብ ትልቅ ግንብ ሲገነቡ ይታያሉ፣ ሆኖም ጎን በሰዎች ላይ እንዲህ ያለ አሰቃቂ አደጋ ሲደርስ…” ብለሻል፡፡

እንዲህ በሚለው መግለጫሽ በጣም ተበረታትቻለሁ፣ “እኛ እና አጋሮቻችን ከየት ተነስቶ ወዴት መሄድ እንዳለበት ሊያረጋግጥ የሚችል ጠንካራ የሆነ የክትትል ስርዓት በስራ ላይ እናውላለን፡፡“

እንደምታውቂው ሁሉ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባቀረቡት ዘገባ (ከገጽ 75-78) ዩኤስኤአይዲ/USAID እራሱ አንዱ አካል የሆነው የልማት ድጋፍ ቡድን/Development Assistant Group የምግብ ለስራ ፕሮግራሙ ለፖለቲካ ዒላማ ይውላል ተብሎ የወጣውን ዘገባ አይኑን ጨፍኖ ለማስተባበል ጥረት አድርጓል፡፡ ይኸ ፖለቲካን ዒላማ ያደረገ የገዥው አካል አካሄድ ባለፉት ስድስት ዓመታትም ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልተደረገበት እና አድሏዊው አሰራር ተንሰራፍቶ እንዳለ  የሚናገሩ በርካታ መረጃ ሰጭዎች አሉ፡፡

በምግብ ለስራ ፕሮግራሙ ላይ በርካታ መሻሻል እንዳለ በተናገርሽው ላይ መሻሻል ስትይ ምን ማለት ነው፣ እናም መሻሻልን የምተለኪባቸው መስፈርቶች በጠጨባጭ ምን ምን ናቸው? በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል በምግብ ለስራ በሚሰጠው እርዳታ ላይ የፖለቲካ ዒላማውን በማራመድ አድሏዊ አሰራር እንዳይሰራ ምን ዓይነት የመከላከያ መሳሪያዎች በስራ ላይ ውለዋል? ከየት ተነስቶ ወዴት ለመሄድ እንደሚቻል የሚያግዙት ጠንካራ የሆኑ የክትትል መሳሪያዎች በስራ ላይ የዋሉ መሆናቸውን የገለጽሽ ስለሆነ እነዚህ የክትትል መሳሪዎች ምን ምን ናቸው?

11ኛ) ከኢትዮጵያ አንጻር 10 ወይም ወደ 11 ከፍ በማለት ወይም ደግሞ ወደላይ በመውጣት እና ወደታች በመውረድ ቁጥሮችን በተደጋጋሚ በመመልከት በዚያው ለመቆየት ውሳኔ እናሳልፋለን፡፡ ስለሆነም ይኸ በተደጋጋሚ የሚሰራ ድግግሞሽ ነገር ነው ብለሻል፡፡

10 እና 11 የሚሉትን ቁጥሮች በድርቁ የተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጎጅዎች እንደማለት ወስጀዋለሁ፡፡ የአንቺ አስተያየቶች ለእኔ ግልጽ አይደሉም፡፡ ድርቁ ወደ ረሀብነት ሁኔታ ለመለወጥ የሚሊዮኖች ቁጥሮች ህዳግ ያስፈልገዋል የሚል ሀሳብ ለማቅረብ ፈልገሽ ነውን? በድርቁ ከተጠቁ ዜጎች ጋር በተያያዘ መልኩ በ10 ሚሊዮን ቁጥር ላይ ተጣብቆ የመቆየቱ አባዜ ጠቃሚነቱ ለምንድን ይሆን?

የአንች ሹመት እንዳይጸድቅ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሳቀርብ ስለነበር ላቀረብኳቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ትሰጫለሽ የሚል ቅዠት የለኝም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የእኔ ጥያቄዎች ከመልካም እሳቤ ጋር በተያያዘ መልኩ ያልቀረቡ ናቸው የሚል ስሜት የሚሰማሽ ቢሆንም የሚደንቀኝ ነገር አይሆንም፡፡

በቅርቡ በሰጠሽው ቃለመጠይቅ ምላሾች ላይ ጥያቄዎች ያሉኝ እኔ ብቻ ያልሆንኩ መሆኑን እንድታውቂው እፈልጋለሁ፡፡

እኔ ይህንን ደብዳቤ የጻፍኩልሽ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው እንደሚያስብ እና ግብር ከፋይ ዜጋ ላቀረብኳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንድትሰጭኝ በማሰብ መሆኑን አረጋግጥልሻለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ይህንን ደብዳቤ የጻፍኩልሽ የዩኤስ አሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት (በገጽ 242) ላይ የኤፍኦአይኦ/FOIA “ዋና ተግባር የዴሞክራሲ ስርዓት አሰራር እንዲሳለጥ፣ ሙስናን ለመቆጣጠር እና ገዥዎች ለተገዥዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል ውሳኔ ሰጭ ዜጋን ለመፍጠር ነው” በሚለው መሰረት እኔም ለዚህ መርሆ ተገዥ በመሆን የእራሴን ቅን መንፈስ በመጠቀም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት ላይ የአለኝን ንቁ የዜግነት ተሳትፎ እውን ለማድረግ ነው ይህንን ጥያቄ ያቀረብኩልሽ፡፡

በፖለቲካ ተጫዋችነት አላምንም፡፡ የነጠረውን እውነታ አጉልቶ በማውጣት ገዥዎች ለተገዥዎች ተጠያቂ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡

ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁበት ዩኤስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምትሰጠው ሰብአዊ እርዳታ ለተገቢው አገልግሎት እንዲውል እና በዩኤስ አሜሪካ ሕጎች መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆን ለማረጋገጥ ስለሆነ እንደምትቀበይው እተማመንብሻለሁ፡፡

ያም ሆነ ይህ እነዚህን እዚህ ያነሳኋቸውን ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላሉ አንባቢዎቼ እንደማነሳቸው ተስፋ አድረጋለሁ፡፡

ጥያቄዎቹ ተገቢዎች ናቸው ብለሽ ምላሽ የምትሰጭ ከሆነ የአንቺንም ምላሽ ምንም ዓይነት እንዳለ በማውጣት ለአንባቢዎቼ አቀርባለሁ፡፡

የአንቺን ምላሽ እ.ኤ.አ አስከ ሚያዝያ 8/2016 ድረስ እጠብቃለሁ፡፡

አክባሪሽ፣

አለማየሁ (አል) ገብረ ማርያም፣ ፒኤችዲ. ጀ.ዲ፣

ፕሮፌሰር እና የሕግ ጠበቃ

ግልባጭ፡
ለዩኤስኤአይዲ/USAID
ትኩረት፡ ለዋናው ኦዲተር ጽ/ቤት

1300 ፔንሲልቫኒያ አቬኑ፣ ኤንደብልዩ

ዋሺንግተን፣ ዲሲ 20523

በዩኤስኤአይዲ/USAID ረዳት አስተዳዳሪ በቲ. ቻርለስ ኩፐር የተሰጠውን ምላሽ እውነተኛውን እና ትክክለኛውን የፒዲኤፍ ግልባጭ ለማንበብ እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

[1] ማስታወሻ፡ በዋናው ደብዳቤ የቀረቡ ማስረጃዎች በግርጌ ማስታወሻ ወደ ሀይፐርሊንክ ተቀይረው ቀርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ሚያዝያ 3 ቀን 2008 .

Filed in: Amharic