>
9:19 pm - Sunday January 23, 2022

ደርግ ቢኖር ኖሮ . . . [እሳቱ ሰ]

ደርግ ቢኖር ኖሮ:- ቤት የሌለው ሰው አይኖርም ነበር፡፡ ቤት በአንድ አገር ዜግነት ስር የመኖር መሰረት ነው፡፡ አገሬ ሲባል የሚቆምበት መሬት ያስፈልገናል፡፡ ደርግ ‘ለአንድ ዜጋ አንድ ቤት’ የሚል ወርቃማ አሰራርን በመከተል ብዙ ሕዝብ ባለ ቤት አድርጓል፡፡ ለሁሉም ዜጋ በአገሩ መሬት ላይ ጎጆ የመቀለስ መብት ሰጥቷል፡፡ ቤት ልስራ ላለ ልዩ ድጋፍ አድርጓል፡፡ አቅም የለኝም ላለም የአንገቱ ማስገቢያ የጎኑ ማሳረፊያ እንዲኖረው በርካታ እርምጃዎች ወስዷል፡፡ ደርግ እስከ ዛሬ ኖሮ ቢሆን በኪራይ ቤት የሚያማርር ቤት አልቦ ዜጋ አይኖርም ነበር፡፡
………
ዛሬ መሬት የጥቂቶች ናት፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ዜጋ አገር እንጅ ቤት የለውም፡፡ አገር ያለ ቤት ምንም ነው፡፡ ትርጉም የለውም፡፡ አገሩ ላይ ቁራሽ መሬት የሌለው ‘አገር አለኝ’ ማለቱ ከንቱ ነው፡፡ አሁን አሁን እንኳን ለመኖሪያ ለመቀበሪያ ቁራሽ መሬት የማግኘት ጉዳይ ከባድ ሁኗል፡፡ በደናው ጊዜ ሞተው የተቀበሩትም መቃብራቸው ተቆፍሮ አስከሬናቸው ፈልሶ መሬቱ ለባለሀብት እየተሰጠ ነው፡፡
………
ደርግ ትርፍ ቤት ያለውን ቀምቶ ለሌለው ይሰጣል፡፡ ኢህአዲግ በደሳሳ ጎጆ የሚኖር አባወራ ቤት አፍርሶ ለባለሀብት ይሰጣል፡፡ ደርግ ቤት ልስራ ላለ መሬት ይሰጣል፡፡ ኢህአዴግ ከርስት ይነቅላል፤ ከመቃብር ቆፍሮ አውጥቶ ማረፊያ ያሳጣል፡፡ ደርግ ስልጣን በያዘ አጭር ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የነበረውን የመኖሪያ ቤት ችግር መፍታት ችሏል፡፡ ኢህአዴግ የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግርን ሳይፈታ ይሄው 25 ዓመታት አለፉ፡፡
………..
ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነውን ‘መጠለያ’ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሟላት ደርግ በብዙ እጥፍ ከኢህአዴግ የተሻለ ነበረ፡፡

መሃይምነት ከኢትዮጵያ ይጠፋ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በቀላሉ ማንበብና መጻፍ የማይችል ዜጋ አይኖርም ነበር፡፡ ሕፃናትና ወጣቶች ጥራት በአለው ትምህርት ተኮትኩተው ያድጉ ነበር፡፡
………….
በደርግ ዘመን ከአፀደ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ሁሉም ዜጋ በነፃ ትምህርት የማግኘት መብት ነበረው፡፡ አቅሙ ላላቸውም የውጭ የትምህርት እድል በገፍ ይቀርብ ነበር፡፡ ትምህርት ለሁሉም ቀርቧል፡፡ ደብተርና ብዕር ለድሃ ልጆች በነፃ ተሰጥቷል፡፡ ከመሰረተ ትምህርት እስከ ኮሌጅ የሚሰጠው ትምህርት በወቅቱ ደረጃውን የጠበቀ ነበረ፡፡ በመለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን የሙያ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ እርሻ፣ wood work፣ metal work፣ electricity፣ ኑሮዘዴ ወዘተ የትምህርት ዘርፎች ለዚህ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
…………..
በኢህአዴግ ዘመን ትምህርት ‘ንግድ’ ነው፡፡ መንግስት ይነግዳል፣ ግለሰብ ይነግዳል፡፡ በነፃ የሚገኝ ትምህርት የለም፡፡ አራት ነጥብ ዘግተህ ዩንቨርስቲ ብትገባም ከፍለህ ትማራለህ – ሁለት ነጥብ ኖሮህ ብትወድቅም ከፍለህ ትማራለህ፡፡ ብር ካለህ ‘እውቀት’ አለህ፡፡ ዲግሪ አለህ፡፡ ዲግሪና ዲፕሎማ ከኮሌጅ የሚገዛ ሸቀጥ ነው፡፡ ለተሰጠህ ዲግሪ ደግሞ እንደገና ‘የብቃት’ መፈተኛ ብሎ ይመነትፍሃል፡፡ ነፃ የለም፡፡ መማርም መብት አይደለም፡፡ ብር የሌለው መማር አይችልምና፡፡ አንድ ታዳጊ 200 ብር የሚከፍልለት ወላጅ ከሌለው መሰናዶ ገብቶ መማር አይችልም፡፡ ወይም አንድ ወጣት ዲግሪ ተመርቆ ‘የብቃት’ ፈተና ለመፈተን 500 ብር ካላገኘ ዲግሪው መና ቀረ፡፡ የብቃት ፈታኞች ከዩኒቨርስቲ በላይ ናቸው፡፡ ዩንቨርስቲ አበቃሁት ያለውን አልበቃም ማለት ይችላሉና፡፡ ምክንያቱም ንግድ ነውና፡፡
……………
በዚህ ዘመን ትምህርት በስፋት ሰለመዳረሱ ዩንቨርቲዎች ሽህ ከሚሊዮን ሰለመድረሳቸው ይወራል፡፡ አሁንም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ማንበብና መጻፍ የማይችለው ከሚችለው በብዙው ይበልጣል፡፡ በትምህርት ሽፋን ግብ መትቻለሁ ማለት ሁሉንም ዜጋ የትምህርት ብርሃን አሳይቻለሁ ማለት ነው፡፡ በ25 ዓመታት የኢህአዴግ ጉዞ ግን ከግማሽ በላይ የአገሪቱ ዜጋ መሃይም እንደሆነ አለ፡፡ ደርግ በወራት ዘመቻ ብቻ ከ70% በላይ የአገሪቱን ሕዝብ ከመሃይምነት አላቋል፡፡
………………
ሰለትምህርት ጥራት ብዙ ተብሏል፡፡ ጥራቱን እንተወውና የኢህአዴግ የትምህርት እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተቃርኖ እንይ፡፡ ኢህአዴግ 85% ገበሬ ባለባት አገር – ግብርና መር ኢኮኖሚ እከተላለሁ እያለ መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ የግብርና ትምህርትን ከትምህርት ፖሊሲው መሰረዝ ነበር፡፡ ደርግ ሁሉም ዜጋ መሰረታዊ የግብርና እውቀትና ክህሎት እንዲኖረው – ዘመናዊ ግብርና እንዲስፋፋ እስከ 10 ክፍል ድረስ የእርሻ ትምህርት ለተማሪዎች ሰጥቷል፡፡ የተማረ አርሶ አደር እያፈራሁ ነው የሚለው ኢህአዴግ ግን አይደለም ለሁሉም ዜጋ የገበሬው ልጅ እንኳን የግብርና እውቀቱን እንዳያዘምን በሩን ዘግቶበታል፡፡
ኢህአዴግ ጥቃቅንና አነስተኛ ለሚለውም የሚረዳ ትምህርት በፖሊሲው የለም፡፡ በኮሌጅ ደረጃ የሚሰጠውም ተማሪዎችን ለተጨማሪ ወጭ እና የጊዜ ብክነት የዳረገ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ እስከ 10 ክፍል የሚሰጡ ትምህርቶች አሁን ጥቃቅን በሚባሉ የሥራ መስኮች ለመሰማራት ጠቃሚ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አንድ ተማሪ የእጅ ሥራ፣ wood work, metal work, electricity , ወይም ኑሮዘዴ ከተማረ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መሄድ ሳያስፈልገው ጥቃቅን በተባሉ የጊዜው የሥራ መስኮች መሰማራት ያስችለዋል፡፡ ይሄም ጊዜና ገንዘቡን ይቆጥብለታል፡፡
…………………
ኢትዮጵያን የእውቀት ብርሃን ለማሳየት ደርግ የሰራው ኢህአዴግ ከሰራው ይሻላል!፡፡

Derg Binor Noro By Esatu Seሰንደቅ ዓላማችን ክብር አታጣም ነበር፡፡. . . ውዷን አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንዳንይዝም በሕግ አንታገድም ነበር፡፡
…………………….
ደርግ በንጉሡ ጊዜ የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ በተደጋጋሚ ቀይሯል፡፡ በመጨረሻም የራሱን ሰንደቅ ዓላማ በሕግ አጽንቶ አውለብልቧል፡፡ የኢትዮጵያ እንደሆነም አውጇል፡፡
ሰንደቅ ዓላማው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሲሆን መሃከል ላይ ልዮ አርማ አለው፡፡ አርማው የስንዴ ዘለላ፣ የአክሱምን ሐውልት፣ ጋሻና ጦር፣ ቢጫ ኮከብ፣ የኢንዱስትሪ ምልክት፣ ጥቁር አንበሳን እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የሚል ጽሑፍ ጠቅልሎ የያዘ ነው፡፡ አርማው ማራኪ ቢሆንም ሕዝቡ አልወደደውም፡፡ አልቀበልም አለ፡፡ ደርግ የሕዝቡን መብትና ፍላጎት አከበረ፡፡ ሕዝቡ አርማ አልቦ ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውለበልብ ፈቀደ፡፡
…………………….
ኢህአዴግ ሃያ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ግንቦት 20 አዲስ አበባ ገባ፡፡ በሕዝቡ ሰንደቅ ዓላማ አላገጠ፡፡ የሸቀጥ መቋጠሪያም አደረገው፡፡ እንደ ደርግ የራሱን ሰንደቅ ዓላማም ሰራ፡፡ በተሰባበሩ መስመሮች የተሰራ ኮከብ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማው ላይ አሳረፈ፡፡ ሕዝቡ ጠላው፤ ተጠየፈው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ደርግ የሕዝቡን መብት እና ፍላጎት አላከበረም፡፡ ሕዝቡ ያሻውን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውለበልብ አልፈቀደም፡፡ ለዚህም ሕግ አወጣ፡፡ አርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ የያዘን እያደነ መቅጣት ጀመረ፡፡ ለአርማውም የባንዲራ ቀን አከበረለት፡፡ አሁን የኢህአዴግ የሰንደቅ ዓላማ አርማ የሰይጣን አምላኪዎች ምልክት ነው ተባለ፡፡ በጥላቻችን ላይ ጥላቻ ታከለ፡፡
…………………….
ሰንደቅ ዓላማ መቀየር ግድ ነው ቢባል እንኳ ደርግ የተጠቀመው አርማ ኢህአዴግ ከተጠቀመው በብዙ እጥፍ የተሻለ እና ኢትዮጵያዊነትን የገለጸ ነበር፡፡ሕዝቡ የፈቀደውን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውለበልብ – ለፈለገው አላማም እንዲያውል መብት በመስጠት ደርግ ከኢህአዴግ የተሻለ ዴሞክራት ነበር፡፡


ወላጅ ወይም አሳዳጊ አጥተው ጎዳና ላይ የሚወድቁ ልጆች አይኖሩም ነበር፡፡
…………………….
ሰው ልጅ የሚወልደው ለማሳደግ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው የወለደውን ልጅ ይወዳል፡፡ አቅሙ በፈቀደለት መጠንም ተንከባክቦ ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል፡፡ የወለዱትን ማሳደግ ግን ለሁሉም አይሳካም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆች የወለዷቸውን ልጆች ጥለው ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ፡፡ አንዳንዴም ልጅ ለማሳደግ አቅም ያጥራል፡፡ በዚህ ሰዓት ሕፃናት ጎዳና ይወጣሉ፡፡ ባልጸና እግራቸው የሚላስ የሚቀመስ ፍለጋ ይንከራተታሉ፡፡
…………………….
By Esatu Se 27052007ደርግ ለእናት አገራቸው ሲታገሉ የተሰው ወላጆችን ልጆች በዋናነት ሌሎችንም ወላጅ እና ረዳት የሌላቸውን ሕፃናት በማሰባሰብ የሕፃናት አንባ መስርቶ በክብርና በፀጋ ያሳድግ ነበር፡፡ ልጆቹ አንዳች ነገር ሳይጎልባቸው እንዲያድጉ አድርጓል፡፡ በሥነ ምግባር የታነፁ አገር ወዳድ ዜጎች እንዲሆኑ ለፍቷል፡፡ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በእውቅ አርቲስቶች የጥበብ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ሥዕል፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ሙዚቃ አሉ በተባሉ ሙያተኞች እንዲሰለጥኑ አድርጓል፡፡ ለአብነት በዓለም ፀሐይ ወዳጆ ደራሲነት ሕፃናቱ ተሰምቶ በማይሰለች መልኩ የዘመሩትን መዝሙር እንይ፡፡
ፀሐዬ ደወቀች – ደመቀች
ብርሃኗን ለኛ ማለት – አወ አወቀች
ፀሐይ ብርሃን ፈንጥቃ
ከአድማስ ወደኛ መጥታ
ደመቀ ጠራ ሰማይ
በእናት አገር በማይ
(ይህ መዝሙር ልጆች በሕፃናት አንባው ከገቡ በኋላ ምን ያህል ሕይወታቸው እንደተለወጠና በተስፋ እንደተሞሉ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡)
…………………….
ወላጅ ላጡት ወላጅ የነበረው የደርግ ሥርዓት ወደቀ፡፡ የአንባው ልጆች ዳግመኛ ወላጃቸውን አጡ፡፡ ደመቀች ያሏት ፀሐይ ጠለቀች፡፡ ጥቁር አበባዎች ሆኑ፡፡ ኢህአዴግ አንባውን ተቆጣጠረ፡፡ በቅምጥል መንግስት ባሳደጋቸው ልጆችም ችጋሩን እና ሰቆቃውን አራገፈባቸው፡፡ የልጆቹ ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ በመጨረሻም በተናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በብዙዎች ላይ መከራው ፀና፡፡ ‘የጭን ቁስል’ በሚል መጽሐፍ የታተመው የአንድ እህታችን ታሪክ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
…………………….
በኢህአዴግ ዘመን ከጦርነት በከፋ ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቸውን ትተው በኤችአይቪ ኤድስ በሽታ ረግፈዋል፡፡ ሕፃናቱም ‘ጎዳና ነው ቤቴን’ እየዘመሩ መንገድ ላይ ፈሰዋል፡፡ አንዳንድ ደግ ግለሰቦች የቻሉትን ያህል ሕፃናት በመሰብሰብ ለማሳደግ ሞከሩ- አሳደጉም፡፡ መንግስት ግን ልጆቹን በአደገኛ ቦዘኔነት በመፈረጅ ለሰው ልጅ ምቹ ወዳልሆኑ በረሃዎች አጋዛቸው፡፡ ነብስ ያላወቁትንም መሸጥ ጀመረ፡፡ በጉዲፈቻ ስም ሕፃናት ለባዕዳን ሸጠ፡፡ ባህር አሻገራቸው፡፡ ከወላጆቻቸው ርስት ነቀላቸው፡፡
ደመቀ ጠራ ሰማይ
በእናት አገር በማይ . . . የተባለው ሰማይ ለ25 ዓመታት አሳዳጊ ላጡ ሕፃናት ጠቁሮ ቀረ፡፡

ሴቶች በተግባር ይደራጁ ነበር፤ ለስሙ የሚከበር መብት – ለታይታ የሚደረግ የእናትና እህቶቻችንን ሰልፍ አይኖርም ነበር፡፡
……………………
ደርግ ሴቶችን በማደራጀት ጠንካራ ማህበር እንዲመሰርቱ አድርጓል፡፡ ከማህበራዊ ጭቆናዎች ተላቀው በኢኮኖሚው እና ፖለቲካው ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሯል፡፡
የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር /አኢሴማ/ ከገጠር እስከ ከተማ በሴቶች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ የነበረው ማህበር ነበር፡፡
…………………….
ኢህአዴግ ሴቶችን ከማህበር በላይ በሚንስትር መስራያ ቤት ጀረጃ አጀራጅቻለሁ ይላል፡፡ አዎ መስሪያ ቤቱ አለ፡፡ ግማሹ ሰራተኛ ግን ወንድ ነው፡፡ “እኛ ሴቶች . . .” ብሎ በሚናገር ወንድ እየተመሩ ሴቶች ተደራጁ ማለት ተራ ወሬ ነው፡፡ ለነገሩ ሴቶች ሲጀመር ከሕፃናት እና ወጣቶች ጋር ነው መስሪያ ቤት ያቋቋሙት እንጅ ብቻቸውን እንዲቆሙ አልተደረጉም፡፡ ………
ኢህአዴግ በ25 ዓመት ታሪኩ እንደ ደርግ ጊዜው አኢሴማ በጠንካራ ማህበር ሴቶችን አላደራጀም፡፡ ሴቶች በአካባቢያቸው ለሁለንተናዊ ትግል ዝግጁና ብቁ እንዲሆኑ አልሰራም፡፡


የተራቆቱ ተራራዎች በደን ይሸፈኑ ነበር፡፡
……………………..
ደርግ በጋራና ተራረዎች ሁሉ ደን ይተክል ነበር፡፡ አረንጓዴ ኢትየጵያን ለማየት ይጥር ነበር፡፡ በአጭር ዓመታትም የአገሪቱን ተራራዎች በተለያዩ የደን ዓይነቶች በመሸፈን ማራኪ አድርጓቸዋል፡፡
…………………….
ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ከወሰዳቸው አሳፋሪ እርምጃዎች አንዱ በደርግ ዘመን የተተከለውን ደን መጨፍጨፉ ነበር፡፡ ለአብነትም በአንድና ሁለት ዓመት ውስጥ በጎንደር እና ጎጃም ደን ለብሰው የነበሩ ተራራዎችን አራቁቷቸዋል፡፡ ይሄን የደን ጭፍጨፋ የታዘበ የጎንደር ሰውም “ወያኔ ደኑን አረንጓዴ ሆኖ ሲያየው የደርግ ወታደር እየመሰለው ጨረሰው” ብሎ አሽሟጠጠ፡፡ ኢህአዴግ ግን ደኑን ያወደመው እንደ ደርግ ወታደር ዮኒፎርም አረንጓዴ ሆኖ ሰለታየው ሳይሆን ለአካባቢው ምንም ዓይነት ተቆርቋሪነት እንደሌለው ለማሳየት ነው፡፡
…………………….
አሁን ከጭፍጨፋ የተረፈ ደን ከተገኘ “መለስ ፖርክ” ይባላል፡፡ ይህ ማለት ግን ደን ማውደሙ ቁሟል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከደብረ ብርሃን ወደ አንኮበር በሚወስደው መንገድ በቁንዲ ተራራ ላይ የሚገኘው የባህር ዛፍ ደን እየተቆረጠ ነው፡፡ ደኑ የ16ኪሜ ርዝመት ያለው ነው፡፡
.…………………..
በደርግ ዘመን የሚተከለው ሁሉ ያድግ ነበር፡፡ አሁን ግን እንኳን ባለስልጣን ጳጳሱ የተከሉትም አይፀድቅ፡፡


ብዙ ወጣት ያልቅ ነበር፡፡
…………………….
ደርግ የተቃወመውን ሁሉ የሚያስር – የሚገርፍ – የሚረሽን መንግስት ነበር፡፡ ደርግ ብዙ ዓይነት ተቃዋሚዎች ነበሩት፡፡ በዋናነት ኢህአፓ፣ ጀብሃ፣ ሻዕቢያ፣ ወያኔ፣ ኦነግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተቃዋሚዎቹ ጠንካራዎች ነበሩ፡፡ የሚታገሉትም መሳሪያ አንግተው ነው፡፡ ደርግን በከተማና በገጠር መፈናፈኛ አሳጥተውት ነበር፡፡ አምባገነኑ መንግስትም ማሰርና መግደልን መፍትሔ አድርጎ ወሰደ፡፡ እስከ ውድቀቱ ቀንም የተቃወመውን ሁሉ ፈጀ፡፡
…………………….
ጨፍጫፊው ደርግ ወደቀ፡፡ ጨፍጫፊው ኢህአዴግ ተነሳ፡፡
…………………….
በኢህአዴግ እና በደርግ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ደርግ ያሰረና የገደለ “ከተቃወማችሁኝ አልምራችሁም” ብሎ አውጆ መሳሪያ ይዘው የሚፋለሙትን ተቃዋሚዎች ነበር፡፡ የአቅም ልዩነት ይኑር እንጅ ጨዋታው ጥይት ለጥይት ነበር፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የሚያስርና የሚገለው “የመቃወም መብት አላችሁ” ብሎ አውጆ በብዕር ብቻ የሚቃወሙትን ነው፡፡ የዚህ ዘመን ጨዋታ እንደ ደርግ ጥይት ለጥይት ሳይሆን ብዕር ለጥይት ነው፡፡
……………………
ኢህአዴግ እንደ ኢህአፖ ዓይነት ተቃዋሚ ቢገጥመው የሚተርፍ የአዳም ዘር አይኖርም፡፡ በ25 ዓመት እድሜው ኢህአዴግ የገጠመው ጠንካራ ተቃዋሚ ቅንጅት ነው፡፡ ቅንጅት እንደ ኢህአፓ የራሱ ጋዜጣ እና ጥይት አልነበረውም፡፡ ለረጅም ዓመታትም መታገል አልቻለም፡፡ ኢህአዴግን ብዕር አንግቶ በሕዝብ ድምጽ ረትቶ በገጠመበት ስድስት ወራት ግን የበርካታ ዜጎችን ሕይወት አስቀጥፏል፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ ደርግ በ5 ዓመት ከአሰረው በላይ በ5 ወር አስሯል፤ ገሏል፡፡


የአገር ሀብትና ንብረት በተደራጁ ወንበዴዎች አይዘረፍም ነበር፡፡
…………………….
ደርግ ለሕዝብ ሀብትና ንብረት ተቆርቋሪ መንግስት ነው፡፡ ባለስልጣናቱም በሙሰኝነት የሚታሙ አይደሉም፡፡
.……………………
ኢህአዴግ ከተራ አባል እስከ ሚኒስትሩ ድረስ የዘራፊዎች ስብስብ ነው፡፡ በቁስ አካል ሰቀቀን የተጠቁ ድውያን ድርጅት ነው፡፡ የአገር ሀብት – የሕዝብ ንብረት የሚል ነገር አያውቁም፡፡ በዘር ተደራጅተው መዝረፍ ነው ሥራቸው፡፡ አዘራረፋቸው ለከት የለውም፡፡ ከአንድ ሳንቲም ጀምረው ማጋበስ ነው፡፡ ከድሀው ጎሮሮ ነጥቀው ይውጣሉ፤ ፋብሪካ እና መንጠድ በቀላሉ ይሰለቅጣሉ፡፡ በቁስ ስስት ተለክፈዋልና አይጠግቡም፡፡


ከአዋሽ ብቻ የፍራፍሬ አምሮታችን በተወጣን ከጎጃም ወተት በጠጣን ነበር፡፡
…………………….
በደርግ ዘመን አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ በማስፋፋት እና በማዘመን የታሸጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶችን ለሕዝቡና ወታደሩ ማድረስ ተችሎ ነበር፡፡ ደርግ ሲወድቅ ኢንዱስትሪዎች አብረው ወደቁ፡፡ የሕዝቡን አመጋገብ ለማዘመን የቀረቡት የመርቲና ዝግኒ የቆርቆሮ ምግቦችም የደረሱበት ጠፋ፡፡
በእንሰሳት ተዋጽኦ በኩሉም ደርግ ጎጃም የትኖራ ላይ ሲሰራ ነበር፡፡ ገበሬዎችን በሕብረት ሥራ ማህበር በማደራጀት የእንስሳት ተዋጽኦ በስፋት እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ ሲገባ ኢትዩጵያን ወተት ያጠጣሉ የተባሉት የየትኖራ ገበሬዎች ዋሻቸው ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ፡፡
…………………..
ወደ ኋላ ጉዞውም ቀጠለ፡፡


በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ለም ወደሆኑ አካባቢዎች ይሰፍሩ ነበር፡፡
.……………………
ደርግ የሰፈራ ፕሮግራም በማካሄዱ ብዙ ጊዜ ይተቻል፡፡ ሕዝቦችን በኃይል በማጋዙ ይወቀሳል፡፡ ፕሮግራሙ ግን ክፋት አልነበረበትም፡፡ ምንአልባትም ከተራቆቱና ለማምረት ምቹ ካልሆኑ አካባቢዎች ሕዝቡን አንስቶ ለም ቦታዎች ላይ ማስፈርን ቀጥለንበት ቢሆን ኖሮ በሚሊዮን የሚቆጠር የተራበ ሕዝብ አይኖረንም ነበር፡፡ አሁን ሕዝብ የለባቸውም ተብለው ለሱዳን የተሰጡ ለም መንደሮችም በኢትዮጵያውያን እጅ በቆዩ ነበር፡፡
…………………….

Filed in: Amharic