>
11:19 pm - Wednesday August 4, 2021

ግንቦት 20 ለማን፣ ምኑ ነው? [ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ]

ግንቦት 20 ለማን፣ ምኑ ነው?
.
Bedilu Waqjira DRዛሬ 25ኛውን የግንቦት ሃያ የድል ቀን አስመልክቼ፣ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ማለት የምፈልገው፣ ገበሬ ወይም ምስኪን የከተማ ነዋሪ ያልሆሉትን፣ የሀገር ሉአላዊነትና የወገን ጥቃት የማያማቸውን፣ የፍትህና የተጠየቂነት አለመኖር የማያስጨንቃቸውን፤ የሰብአዊ መብት መጣስ እንቅልፍ የማይነሳቸውን. . . . ወገኖቼን ነው፡፡ ለምን ቢሉ . . .
.
ግንቦት 20 ለገበሬው ምኑ ነው?
.
ደርግ ከሚመሰገንባቸው ተግባራቱ አንዱ፣ ገና በጠዋቱ መሬትን ከጥቂት ባላባቶች ነጥቆ ለባለቤቱ ለገበሬው ማከፋፈሉ ነው፡፡ ገበሬ ያለመሬትና በሬ ሰው ሊሆን አይችልም፤ እና የፊውዳሉን ስርአት የገረሰሰው ደርግ ጭሰኛውን ሰው አደረገው፡፡ የተሻለ ሊያመጣ ደርግን የታገለው ኢህአዴግ፣ ይኸው መሬቱን ለዘመናዊ ፊውዳሎች እያከፋፈለ ነው፡፡ በፊውዳሉ ዘመን የንጉስ ቤተሰብ ወይም ባለሟል ከሆንክ መሬቱን ጠቅልለህ ትወስደዋለህ፤ ዛሬ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ የኢህአዴግ አፍቃሪና ባለገንዘብ ከሆንክ ገበሬውን ጠርገህ መሬቱን ትረከበዋለህ፤ እንዲያውም የኢትዮጵያን ለምና ሰፊ መሬት ለመቀራመት ኢትዮጵያዊ መሆንም አይጠበቅብህም፡፡ እና ዋስትናዬ የሚለውን ጥብቆ ማሳውን ባሻው ጊዜ ለልማቱም ለጥፋቱም የሚወስድበትን፣ የእድሜ ልክ ዋስትናውን የመንፈቅ አስቤዛ በማገዛ የገንዘብ ካሳ የሚነጥቀውን ኢህአዴግን ያስቀመጠ ግንቦት 20 ለገበሬው ምኑ ነው?
.
ግንቦት 20 ለተራው ከተሜ ምኑ ነው?
.
ከተሜው በመኖሪያ ቤት፣ በትራንስፖርትና በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፡፡ ኢህአዴግ የከተሜውን ኑሮ ለማሻሻል፣ ለትራንስፖርት አውቶቡሶችን፣ ለመኖርያ ኮንዶሚኒየሞችን አቅርቧል፡፡ አውቶቡሶቹ በርግጥ የተወሰኑ የመንግስት ሰራተኞችን ያመላልሳሉ፤ በተጨማሪም ቀኑን ሙሉ በከተማው ውስጥ ያለስራ ተገትረው ስለሚውሉ ሰማያዊ ቀለማቸው እንደ መስቀል አደባባይ፣ ጥቁር አንበሳ ላሉት ክፍትና አዋራማ ቦታዎች ውበት አላብሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአውቶቡሶቹ አምራች ትልቅ ገቢ አስገኝቷል (ዋናው ጉዳይም ይህ ይመስለኛል)፡፡
የጋራ መኖሪያውም ቢሆን ከተራው ድሀ ከተሜ በላይ የጠቀመው ገንዘብ ያላቸውንና በስራው ላይ የተሳተፉ መስሪያ ቤቶችን አንዳንድ ሰራተኞች ነው፡፡ እዚህ ላይ በቅርቡ ከአዲስ አበባ መጥፋታቸው የተገለጸውን 88 የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ላይ በ40-60 እና 20-80 ቤት የሌላቸው ቆጣቢዎችን በማሰብ ከተሰሩት ቤቶች ውስጥ የደረሱት መቶ በመቶ ለከፈሉት በቅድሚያ እንደሚሰጥ የወጣ መመሪያ ስለመኖሩ የሚሰማው ጭምጭምታ የፕሮጀክቱ አላማ ችግር ውስጥ እንገባ ያመለክታል፡፡ በየከተማው የተለያ ቦታዎች ለልማት ሲባል የድሆች ቤት ይፈርሳል፤ በየከተማው ዳርቻ ለልማት ሲባል አሁንም የድሀ ቤት ይፈርሳል፡፡ ከሰሞኑ ህይወት እንደጠፋበት የሚነገረው፣ የቦሌ ክፍለ ከተማው፣ ‹‹ቤት አፈርሳለሁ – አታፈርስም›› የመንግስትና የዜጎች ጸብ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ መንግስት እነዚህን ቦታዎች በልማት ስም የሚቸበችበው ገንዘብ ላላቸው ነው- የራሱ የኢህአዴግ የመሬት አስተዳደርና ፖሊሲ ለፈጠራቸው ቱጃሮች፡፡ ይህ ይሁን ..ግን እንዴት ኢትዮጵያን የሚያክል ሰፊ ሀገር ዜጋ፣ ለአንዲት ጎጆ መቀለሻ 50 ካሬ ቦታ ለማግኘት ሚሊየነር መሆን ይጠበቅበታል? ኢትዮጵያ ራቁታቸውን የተወለዱ ዘጠና ሚሊየን ሰዎች መሬት ናት፤ ስለምን ቀድመው ኩታ የለበሱት፣ ጎጆ የቀለሱት፣ ሌላውን እርቃኑን ያስቀሩታል? እንዴት ኢህአዴግ ጎጆ እያፈረሰ፣ እርቃን እያጋለጠ ዜጋውን እርቃኑን ይጥለዋል? ከዚህች ሀገር ከሚገኝ ሀብትና በረከት ዘጠና ሚሊየናችንም ድርሻ አለን፤ ጥቂቶች በሚቆጥሩት ሚሊየን ውስጥ ድርሻ አለን፤ ይሁን ግድ የለም፣ ግን ከሀገሪቱ በተገኘ ሀብት መልሰው ሀገሪቱን እየሸቀጡ፣ ድሀው በዜግነቱ እንዴት 50 ካሬ ጎጆ መቀለሻ . . .የኔ…ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ያገኘሁት የሚለው ደጃፍ አይኖረውም? እና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳውን ኢህአዴግን ያስቀመጠበት ግንቦት 20 ለከተሜው ምኑ ነው?
.
ግንቦት 20 የሀገሩን ሉአላዊነትና ወገኑን ለሚወድ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?
.
ኢትዮጵያ የባህር በር ነበራት! ያውም በምድራችን ላይ በጣም ስትራቴጂክ በሚባል መተላለፊያ በቀይ ባህር፤ ይህንን ያጣነው በኢህአዴግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጀግንነታቸው የተፈሩና የተከበሩ ህዝቦች የሚኖሩባት፣ ባለታሪክ ሀገር ነበረች፤ ጎረቤቶችዋ ይቀኑባት ነበር፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ከተናቁት ሀገሮች፣ ኢትዮጵያዊነትም ከሚንቋሸሹት ዜግነቶች መካከል ናቸው፡፡ በግዛታቸው ውስጥ ያለውን ዥረትና ተራራ እንኳን በቅጡ የማያውቁ፣ ገና የነጻነት ትግል ዘመን ባሩድ ሽታ አንጎበር ያለቀቃቸው እነ ደቡብ ሱዳን እንኳን የሚንቅዋት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ደርግ ለኢትዮጵያ፣ ‹‹የራስዋን የማትሰጥ የሰው የማትነካ›› የሚል ዘፈን ያዘፍንላት ነበር፡፡ ኢህአዴግ የሰው ሊያምራት ይቅር፣ የራስዋን የምትበትን፣ ደጃፍዋ ማነህ ባይ የሌለው ጋለሞታ አድርጓታል፡፡ ፈጣሪ ህጉ ሲጣስ፣ መሻቱ ሲጎድል፣ አዳም ላይ ሞትን አላመጣም? ሰዶምና ገሞራ ላይ መአት አላወረደም? ኢህአዴግ ከፈጣሪ የላቀ ቸር ነው፤ የሀገሩ አላባ ቢነዳ፣ ህጻናቱ ለባርነት ቢነዱ ብትሩን አያነሳም፤ ስለወላጆቻቸው መገደል፣ ስለህጻናቱ ባርነት በምድረ በዳ ሰላምን ይሰብካል፤ ሀገሩንና ዜጎቹን ከፈጁት ወገን ሆኖ ይቅርታን ያስተዛዝንላቸውዋል፡፡ እና ዜጎችን የሚያርዱ፣ ህጻናትን የሚነዱ ባእዳንን እያቆላመጠ፣ በሀገሩ ላይ 50 ካሬ ያለፈቃዴ ቀለስክ ብሎ፣ በዜጎቹ ጎጆ ላይ ቡልዶዘር የሚነዳ፣ ካልኩት ወጣችሁ ብሎ፣ በወጣቶቹ ላይ ጥይት የሚያፈነዳ፣ የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ የሆነውን ኢህአዴግ ያስቀመጠ ግንቦት 20 ሀገሩን፣ ወገኑንና ሉአላዊነቱን ለሚወድ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?
.
ግንቦት 20 ፍትህንና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?
.
ፍርድ ቤቶች፣ ፍትህ የሚገኝባቸው ቦታዎች መሆናቸው ቀርቶ፣ የዳኞች መኖሪያ ሆነዋል፤ ፍርድ ቤት ዳኛ እንጂ ፍትህ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በየትኛውም አገዛዝ፣ እንዲህ አይነት የተጠያቂነት አለመኖር ሰፍኖ አያውቅም፡፡ 88 ኮንዶሚንየም ጠፍብኝ ያለ ሚንስትር፣ ያለ ቅዠት ተኝቶ ማደሩ ሲገርመን፣ በማግስቱ በቪ8 መኪና ስራው ይገባል፤ በመንፈቁ እድገት ያገኛል፡፡ በ1.5 ሚሊየን ብር ጉድለት፣‹‹ጥንብ እርኩሱ›› እስኪወጣ የተገመገመና ከስራው የታገደ የከተማ ጽዳትና ውበት የስራ ሀላፊ፣ ታሰረ-አልታሰረ ብለን ስንሳቀቅለት፣ ባለ ብዙ በጀት የሆነው የከተማው የቤቶች ልማት ውስጥ ሀላፊ ሆኖ ይመደባል፡፡ እስቲ ባለፉት 25 አመታት በጥፋቱ (በሙስናው) ተጠያቂ ተደርጎ የተቀጣ (የተፈረደበት) እንቁጠር! በእርግጥ በአንድ እጅ ጣት የሚቆጠሩ አሉ፤ ለነዚህም ምክንያቱ የፖለቲካ አቋም እንደሆነ ነው የሚታማው፤ እውነት ግን ተጠያቂነት ቢኖር 90 በመቶ ባለስጣኖቻችን ዘብጣያ በወረዱ ነበር፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ባለስልጣን በመንግስት መኪናና ነዳጅ በመጠቀሙ፣ ዘብጥያ ማውረድ የፍትህ መጣመም ማሳያ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ለምን ቢሉ በዚህ አመት በዋና ኦዲተር ለምክርቤት የቀረቡትን ጉድለቶች ብቻ ማየት በቂ ነው፤ የ10 መኪኖች ሊብሬ እንጂ መኪኖቹ ያልተገኙበት መስሪያ ቤት ሀላፊ ምን ተደረገ? 70 ቢሊየን ብር ክስረት ያሳዩት መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎች ማን ጠየቃቸው? ለጉድለት የተዳረጉት፣ ያለመመሪያ የሰሩት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችስ? ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠያቂነት የለም፣ አጉድል..ሞስን…ስረቅ…ትገመገማለህ….በማግስቱ ትሾማለህ..ብቻ ከኢህአዴግ አትጣላ! ለምን ቢሉ ተጠያቂነት የለም፡፡ ግን ደግሞ በሚሊየን የሚገመት ግብር እነእከሌ አጭበረበሩ ሲባል ሰምተህ፣ ያለ ደረሰኝ ሽሮ ብትሸጥ ዘብጥያ ልትወርድ ትችላለህ፤ ለምን ቢሉ ፍትህም እኩልነትም የለም፡፡ ታዲያ ይህንን ኢፍትሀዊነትና በሀላፊነት አለመጠየቅ ያሰፈነውን ኢህአዴግን ያስቀመጠበት ግንቦት 20 ፍትህንና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?
.
ግንቦት 20 የሰብአዊ መብቱ መጣስ ለሚያንገበግበው ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው?
.
ሀሳባቸውን በአደባባይ በመግለጻቸው የተነሳ ዜጎች ለስደት ተደርገዋል፤ በእስር ቤት ታጉረዋል፤ በዚህ ድርጊት ለሚንገፈገፍ ዜጋስ ግንቦት 20 ምኑ ነው?

 

Filed in: Amharic