>
3:49 pm - Monday February 6, 2023

ጉዳዩ ትግሉን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ነው! [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

Exclamation_mark_Doneስርቆት ነውር ነው። ግድያ ደግሞ ጭራሹኑ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው። የሰው ነፍስ ለማትረፍ የተፈፀመ ስርቆት፣ ለኔ ‘ቅዱስ ስርቆት’ ነው።

እኔ ‘ሞራሊስት’ አይደለሁም። ይህ ማለት ግን ጉራ ሊመስልብኝ ቢችልም እንኳ በየትኛውም መለኪያ የሞራል ከፍታዬን ተጠራጥሬው አውቃለሁ ማለት አይደለም፤ በፍፁም። የትላንቱን ፈተና ያስተጓጎለውን ስርቆትም ያለምክንያት፣ ኢሕአዴግን ስለሚያበሳጨው ብቻ ብዬ አይደለም በይሁንታ የተቀበልኩት። Here is why.

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ለኔ ሕጋዊም ሞራላዊም ቅቡልነት ያለው መንግሥት አይደለም። ሥልጣን ላይ ያለው በማጭበርበር እና በኃይል ነው። በተለምዷዊው የምርጫ አካሄድ ይወርዳልም ብዬ አላስብም። ሕዝቡ ግን የሙሉ ሰዓት ኑሮን ለማሸነፍ ተፍጨርጫሪ በመሆኑ የሙሉ ሰዓት ፖለቲከኞች ምን እየተፈፀሙበት እንደሆነ በቅጡ አያውቅም። ሕዝቡ መንግሥቱን ‘በቃኸኝ፣ አትመጥነኝም’ ለማለት የሚያስችል ፋታ ኑሮው አልሰጠውም። ‘ይሄንን ሁሉ በደልማ አልቀበልም፤ በቃኝ’ የሚለው ግን የሚችለውን ትግል ጀምሯል።

እኔ የሰው ነፍስ የሚነጥቅ ትግል ተቃዋሚ ነኝ። በሠላማዊ ትግል ስትራቴጂ ደግሞ (ጂን ሻርፕ እንዳለው) ሦስት ዐብይ ዘዴዎች አሉ። ለማሳመን መጣር (to persuaded)፣ አለመተባበር (non-cooperation) እና ጣልቃ መግባት (intervention) ናቸው። ኦሮሚያ በተቃውሞ እና በመንግሥት ኃይሎች ምኅረት አልባ እርምጃ ቢያንስ ለአራት ወራት ስትታመስ ቆይታለች። ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ ሲከፈቱ ቆይተዋል። ተማሪዎች በዚህ መስተጓጎላቸው የሚያጠራጥር ነገር አይደለም።

በኦሮሚያ፣ ተማሪዎች እና ይመለከተናል ያሉ አካላት ፈተናው ጊዜው እንዲራዘም ጠይቀው እንደነበር እና አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ሰምተናል። ይህ ‘ለማሳመን የመጣር’ ትግል ነው። ነገር ግን እምቢታውን እንዴት መቃወም እንደሚችሉ ላያውቁ ይችላሉ። ‘አለመተባበር’፣ ምናልባትም ፈተናው ላይ አንቀመጥም ማለትን ይጠይቅ ይሆናል። ይህንን ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። አስተባባሪ መኖር አለበት። ይህንን ለማስተባበር የሚችል አገር ውስጥ ያለ አካል፣ ያውም ከዚያ ሁሉ የግፍ እርምጃ በኋላ እና ከወትሮው በላይ በጠበቀው ቁጥጥር መሐል የማይሞከር ነው። ስለዚህ አቅሙ ያላቸው እና አማራጩን የሚያውቁት፣ ውጪ ያሉት ሰዎች፣ ሦስተኛውን ዘዴ፣ ማለትም ጣልቃ መግባትን ተጠቀሙ እና የፈተናው ጊዜ እንዲተጓጎል አደረጉ። በኦሮሚያ አካባቢ ላሉ ተማሪዎች የተነፈገው ፍትሕ በአራማጆቹ ጣልቃ ገብነት እንደተፈፀመ ነው የምቆጥረው። Justice served.

ጉዳዩ ኢሞራላዊ ይሆን የነበረው አራማጆቹ ፈተናውን ሰርቀው፣ መልሱን በምሥጢር ተበደሉ ላሉት አካላት ቢሰጧቸው ነበር። እነርሱ ግን ያደረጉት አንጻራዊ ሠላም በነበረበት አካባቢ ያሉት ተማሪዎች ያደረጉትን ዝግጅት ያክል የመዘጋጃ ጊዜ እንዲሰጣቸው የፈተናው ቀን እንዲራዘም ነው። ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ቢኖር ኖሮ ቀድሞውንም ኦሮሚያ አካባቢ ላሉት ተማሪዎች ይህንን ጊዜ ፈቅዶ ቀሪዎቹ ተማሪዎች ብቻ እንዲፈተኑ ማድረግ ይችል ነበር።

የፈተናው መስተጓጎል፣ አንደአገርም እንደግለሰብም ብዙ ምስቅልቅሎችን እና ኪሳራዎችን እንደሚያስከትል አላጣሁትም። ነገር ግን ለምስቅልቅሎቹ ተጠያቂው የችግሮቹ ሁሉ መንስኤ የሆነው መንግሥት ተብዬው ስለሆነ ይቅርታ ቢጠይቅ ጥሩ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ነገር የማድረግ የሞራል ከፍታ ያለው ሰው በመንግሥቱ ስብስብ ውስጥ ስለሌለ ይህን አልጠብቅም።

ለሌላው ግን ፈተናውን በይፋ የመልቀቁ እና ጣልቃ የመግባቱን ጉዳይ መቀበል ወይም አለመቀበል፥ ሕገወጡን ስርዓት በሕግ እንዲገዛ ለማድረግ የሚደረገውን ትግል የመቀበል ወይም ያለመቀበል ጉዳይ ነው። To be or not to be there when you are needed.

Filed in: Amharic