>
1:02 am - Thursday July 7, 2022

የዳላስ መልዕክት ለእንትና ሰዎች [በፈቃዱ ሞረዳ]

ድብልቅልቅ ያለች አሜሪካ፣ድብልቅልቅ ያለች ዳላስ…ድብልቅልቅ ያለ ስሜት፡፡

በአሜሪካ የጥቁር ሰዉ ሟችነት፣የነጭ ፖሊስ ገዳይነት ዜና አስገራሚ አለመሆኑ እዉነት ነዉ፡፡ ነጭ ፖሊስ ጥቁሩን ይገድላል፡፡ጉዳዩ ፍርድ ቤት ይቀርባል፤ወይም በሸንጎ (ጁሪ) ይታያል፡፡ በመጨረሻም ‹‹የፖሊሱ ገዳይነት አግባብ ነዉ፤ የጥቁሩም ሟችነት ልክ ነዉ›› በሚል ዓይነት መንፈስ ፍትህ ሲበየን ይስተዋላል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአሜሪካ ግዛት ይህ እዉነት በእያንዳንዱ ቤት ዉስጥ አለ፡፡
Befeqadu Moreda about USA-Dalas 08072016ይህ እየገደሉ ‹‹የሕግ›› ይሁንታ ማግኘት፣ የይበልታና የይበርታ ያህል ተቆጥሮ ለነጭ ፖሊሶች የልብ ልብ የሰጠ ይመስል ግድያዉ ዐይን ባወጣ ሁኔታ ሲቀጥል እንጂ ሲቆም አይታይም፡፡
ከእነዚያ ሁሉ ግድያዎች ግን፣ በዚህ ሳምንት በሁለት ቀኖች ልዩነት በሉዚያናና በሚኒሶታ በሁለት ጥቁሮች ላይ የተፈፀመዉ ግድያ እጅግ ዘግናኝ፣ እጅግም አስቆጪ ነበር፡፡
በሉዚያና አንድ መንገድ ላይ ሲዲ እየሸጠ በሚያገኛት ሳንቲም ልጆቹን የሚመግብ ጥቁር ሰዉ በሁለት ነጭ ወጠምሻ ፖሊሶች ሁለት እጁ ተጠምዝዞ መሬት ላይ በጀርባዉ ይዘረራል፡፡ ፖሊሶቹ እዚያዉ በላዩ ላይ እንደተጋደሙ ደረቱን በጥይት መአት ቦተራረፈዉ፣ልቡን አፈራርሰዉ ገደሉት፡፡ከሟች ልጆች መራራ ለቅሶ በስተቀር ያ ሰዉ ስለተገደለበት በቂ ምክንያት አልሰማንም፡፡
በሚኒሶታ ከአራት ዓመት ሕፃን ልጁና ከሚስቱ ጋር መኪና እየነዳ የሚሄደዉን ጥቁር አሜሪካዊ አንድ ነጭ ፖሊስ አስቆመዉ፡፡ በሕግ አግባብ መኪናዉ ዉስጥ እንደተቀመጠ ፖሊሱ የሚጠይቀዉን ጥያቄ ሲመልስ ነበር፡፡ ከመልሶቹ መሐል አንዱ ሽጉጥ እንደያዘ፣ መሣሪያዉም ሕጋዊ ፍቃድ እንዳለዉ መናገር ነበር፡፡ የመሣሪያዉን ፈቃድ ለፖሊሱ ለማሳየት እጁን ወደኪሱ ሲከት ፖሊሱ ጥይት ይቆጥርበት ጀመር፡፡ በአምስት ጥይት ደብድቦት በሚስቱና በሕፃን ልጁ ፊት ገደለዉ፡፡
እነዚህ የጭካኔ ተግባሮች ካስለቀሱዋቸዉ ሰዎች መሐከል እኔም አንዱ ነኝ፡፡ ለቅሶዬ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ልቦናዬ ያዉቀዋል፡፡
ከለቅሶዉም ሌላ በዉስጤ ሲመላለስ የዋለዉ ነገር፣ ‹‹To stop killing , start killing ›› የሚል ዓይነት ስሜት ከየትና እንዴት እንደመነጨ አዉቃለሁ፡፡በእርግጥ ነፍሴ እንዲህ ያሰበችበት ምክንያት አላት፡፡ ድምዳሜዋ የምክንያቱ መፍትሔ ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ ባትሆንም፡፡
Befeqadu Moreda about USA-Dalas 08072016.jpg 1አንድ በሰሞኑ የአሜሪካ ፖሊሶች ድርጊት በቁጣ ያበደ ጥቁር፣ እምባ እያፈሰሰ ለCNN ሲናገር ፣ ‹‹ it is too much!›› ይል ነበር ደጋግሞ፡፡ ‹‹ በዛ፣ በጣም በዛ..›› ማለቱ ነዉ፡፡ ያ አባባል በእዝነኅሊናዬ ደጋግሞ አስተጋባ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ መረን የወጣ ነገር ከሚፈጥረዉ የወል ቁጣ ባሻገር፣ የአንዳንድ ግለሰቦችን ነፍስ ከቁጥጥር ዉጪ ቢያደርግ አይገርምም፡፡ በዳላስ የተፈጠረዉና ፖሊሶችን ብቻ ለይቶ ያስጠቃዉ ስሜትም ከዚሁ በእልህና በቁጭት ከጦዘች ነፍስ የመነጨ ይመስላል፡፡
ዳላስ ላይ የሞቱት ፖሊሶች ሉዚያናና ሚኒሶታ ግዲያ የፈፀሙቱ አይደሉም፡፡ ምናልባትም በግድያዉ የተናደዱ ፣የተቆጩ ሰዎችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ነገር ግን፣ የኒዉዮርክ ፖሊስ ሲገድል፣ ነፃ ሲወጣ፤ የችካጎዉ ንፁህ ሰዉ ገድሎ የሕግ ከለላ ሲሰጠዉ…በፍሎሪዳ፣በቴክሳስ፣በካንሳስ፤ በኦሀዮ፣ በሜሪላንድ፣ በሲያትል… ነጭ ፖሊስና ታጣቂ ጥቁር ወጣቶችንና አዋቂዎችን እየገደለ ከተጠያቂነት ነፃ ሲሆን ጉዳዩን የአጠቃላይ የፍትህ ሥርዓቱ ይሁንታ ያገኘ ያስመስልና ‹‹ፖሊስ›› የተባለዉን ሁሉ ከዳር እስከዳር በተበቃዮች ጥርስ ዉስጥ ያስገባል፡፡ የመለዮዉና የደንብ ልብሱ(ዩኒፎርም) ጥላቻ በመላዉ ሀገሪቱ ይስፋፋል፡፡ምስኪን የዳላስ ፖሊሶችም የዚህ ጥላቻ ሰለባ የሆኑ ይመስለኛል፡፡
ግድያ በማንኛዉም መለኪያ ወይም ለማንኛዉም ሰበብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሕግን ተገን፣መለዮዉን ከለላ በማድረግ በማን አለብኝነት የተወሰነን የማኅበረሰብ ክፍል ለይቶ ማጥቃት፣ማጥፋት ሲበረታ ግን ራስንም መከላከል የወገኖችንም ደም የመበቀል ፍላጎት ገንፍሎ ይወጣል፡፡ ወደአደገኛ ዉሳኔም ያደርሳል፡፡
ልጅን በአባትና እናት ፊት የሚገድሉ፣ አባትና እናትን በልጆቻቸዉ ፊት በጥይት የሚነድሉ…ጨካኞች ፣ የሟች ዘመዶችና ወገኖች የሚሰማቸዉን ሕመምና ሀዘን የሚያጣጥሙት ቀምሰዉ ሲያዩት ብቻ ነዉ፡፡ ሁልጊዜ እነርሱ ብቻ ገዳዮች ከሆኑ ግድያ ሥራ እንጂ ወንጀልም፣ ኃጥያትም፣ነዉርም ሊመስላቸዉ አይችልም፡፡
ግን፣ ሁሌ እየገደሉ መኖር እንደሌለ ጊዜ ያስተምራቸዋል፡፡ ጊዜዉ ሲደርስ፣‹‹ It is too much…enough is enough!›› ማለት ሳይወድ በግድ ይመጣል፡፡

ይህ የአሜሪካ ብቻ እዉነታ አይደለም፡፡ የትም ግፍ ሞልቶ በፈሰሰባቸዉ ቦታዎችና ሁኔታዎች ሁሉ ይፈጠራል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ታጣቂ ኃይል ዘርና ወገን እየለየ ንፁሐንን የኢላማ መለማመጃ የሚያደርግበት፣ ምስኪኖችን እየገደለ ከሹመት ወደሹመት መረማመጃ የሚያገኝበት ጊዜ ‹‹በቃ!›› የሚባልበት ሰዓት ሩቅ አለመሆኑን ባለጥይቶቹ እነሳሞራ የኑስና ጌታቸዉ አሰፋ ልብ ማለት ካልቻሉ ዳላስ ለእነርሱም ግልፅ መልዕክት አላት፡፡
ሰሞኑን በፊንፊኔ በቤት አፍራሽ አጃቢ ፖሊሶችና የቀበሌ ሹሞች ላይ የደረሰዉ አደጋ የማንቂያም የማስጠንቀቂያም ደወል መሆኑን ልብ የማይል ካለ እርሱ በእርግጥም ልብ የለዉም፡፡ የመረረ ዕለት ጥይት ሳይሆን ዱላ ምን መስራት እንደሚችል የጠቆመ መልዕክት ነዉ፡፡
ምናልባትም የአሜሪካ ሸንጎ (ጁሪ) ከእንግዲህ የነጭ ፖሊሶችን ገዳይነት ቡራኬ ላለመስጠት ቆሞ ለማሰብ እንደሚገደደዉ ሁሉ፣ እነአዲሱ ገብረእግዚአብሔርም ኣግዓዚ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የፈፀመዉ ጨፍጨፋ፣ ‹‹ ትክክለኛ ነዉ፣ ያልተመጣጠነ አይደለም…›› ብለዉ በሀቅ ላይ የሚኮሱበት፣በፍትህ ላይ የሚያላግጡበት ጊዜ ማብቂያዉ ሩቅ አለመሆኑን አባዜያቸዉ ሹክ የሚላቸዉ አሁን ነዉ ብለን እንገምታለን፡፡
በሰለጠነ አግባብና በጨዋነት ‹‹ ተዉ››ሲባሉ መስማት ከተሳናቸዉ፣ግድያን ለማስቆም ፣ግድያን መጀመር የግድ እንደሚል ማመን አለባቸዉ፡፡ቢያንስ ቢያንስ ራስንና ቤተሰብን ለመካላከል፡፡
ይህ በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ እዉን እንዲሆን የማንፈልገዉን ያህል፣ ፍትህ በሌለበት ቦታ ሁሉ ሠላምን መጠበቅ ቢያንስ ሞኝነት፣ ሲበዛም እብሪት መሆኑን እናምናለን፡፡
‹‹ለሰዉ ብሎ ሲያማ…›› የዳላስ መልዕክት፡፡

Filed in: Amharic