>
4:53 pm - Sunday May 25, 0121

አቶ አባዲ ዘሞ በካርቱም ምን ይሰራሉ? (ኣቶ ኣስራት ኣብርሃ)


ባለፈው ሳምንት ከካርቱም ሱዳን በዚያ የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ያሉበት እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ ደርሶኝ ነበር፤ ባጋጣሚ በመንግስት ኃይሎች ተጠለፍኩና ሳልለጥፈው ቀረሁ። በሱዳን የሚኖሩ ዜጎቻችን በፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባና እስር እየደረሰባቸው ይገኛል። ወንዶቹ ይደበደባሉ፤ ሴቶቹ ደግሞ በፖሊሶቹ ይደፈራሉ፤ ባለፈው ሳምንት ብቻ ሶስት ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት ህይወታቸውን አልፈዋል። ኢትዮጵያውያኑ በዚያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቢያመለክቱም አምባሳደሩ አቶ አባዲ “ሁኔታውን የሚያጣሩ ሰዎች እልካለሁ” ብለው ከሸኟቸው በኋላ በቃላቸው መሰረት ሳይደርሱላቸው ቀርተዋል። ለዚህ ነው አቶ አባዲ ዘሞ በካርቱም ምን ይሰራሉ? ያልኩት። በመሆኑም እነዚያ በችግር ላይ ያሉት ወገኖቻችን አድራሻዪን አግኝተው “እየደረሰብን ያለውን መከራ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳውቅልን” ብለዋል። 


አቶ አባዲ ዘሞ የህወሀት ታጋይ ናቸው፤ ለዚያው ኢህአፓ የነበረች የራሳችውን እህት በህወሀት ነፍሰ ገዳዮች በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስደፍተው ወደ ጫካ የገቡ! ወደ ጫካ ከመግባታቸው በፊት የህወሀት ድብቅ አባል በነበሩበት ጊዜ ማታ ማታ በቤታቸው ከእህታቸው ጋር የጦፈ ፖለቲካዊ ክርክር ያደርጉ ነበር ይባላል። በዚህም የተነሳ የልጅቱ አደገኛነት በመገንዘብ ለህወሀት ሪፖርት አድርገው ነው እንድትገደል የተወሰነው የሚሉ አሉ። በትምህርት ዕረፍት ሰዓት ሽጉጥ ታጥቀው የመጡት ነፍሰ ገዳዮች በልጁቷ ደረት ላይ ሁለት ጥይቶች ከለቀቁባት በኋላ ያለምንም ችግር፣ ማንነታቸውም ሳይታወቅ ከተማውን ለቀው ሄዷል። አባዲ ዘሞም በዚህ ጊዜ ወደ ጫካ ገቡ ከዚያ በኋላ ደፍሮ ስለልጅቱ ያነሳ ሰው አልተገኘም።


አቶ አባዲ ዘሞ ታጋይ በነበሩት ወቅት ቀኝ እጃቸው በጥይት ተመተው በመፍለ የተመታው እጃቸው እንዲቆረጥ ተደርጎ ከሞት እንዲተርፉ ሆኗል። በዚህ እጃቸው መቆረጥ ምክንያት ይኩራሩበታል እየተባሉ ይታማሉ፤ ለምሳሌ አንድ ጊዜ የህወሀት አካል ጉዳተኞች በሰበሰቡበት ወቅት አንዱ ታጋይ “እንዲህ አካላችን ጎድሎ የትም ተጥለን ቀረን” ብሎ ሲናገር፤ እርሳቸውም የተቆረጠው ቀኝ እጃውን በማሳየት “አንተ ብቻ እኮ አይደለህም አካልህ የጎደልከው” ይሉታል፤ ታጋዩም የዋዛ ሰው አልነበረም “አባዲ ያንተ እጅ ቢትቆረጥም አሁን ብር ስትዝቅ ነው የምትውለው፤ እኛ ነን እንጂ ብርድና ዝናብ ቁንጫና ቱሀን እየተፈራረቀብን ያለው” ብሎ በድፍረት መልሶላቸዋል። የህወሀት አካል ጉዳተኞች እነርሱ የትም ተጥለው በስማቸው ግን ድርጅቱ በአዲስ አበባ እስታዲዮም አከባቢ “ይሓ” የሚባል ትልቅ ህንፃ ገንብቶ እያከራየ ሀብት እየሰበሰበት ነው። መቼም ህወሀት ትርፍ እስካስገኘለት ድረስ የማይነግድበት ነገር የለም።


እኔ ደግሞ አቶ አባዲ ዘሞ የማስታውሳቸው አጋጣሚ አለኝ፤ በ1998 ከ97ቱ ምርጫ ማግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ መንግስትና የግል ኮሌጆች የመምህራን በሰማዕታት ሀወልት አደራሻ በሰበሰቡት ጊዜ እኔ በህይወቴ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ንግግር ያደረኩበትና በስርዓቱ ላይ ያለኝን ተቃውሞ ለመጀምርያ ጊዜ በአደባባይ የገለፅኩባት ዕለት ነበረች። እንደዚያ ዓይነት ተቃውሞ በትግራይ ክልል በህወሀት ላይ ሲሰነዘር ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም፤ አዳራሹ በጭሆትና በተቃውሞ ተናጋ፤ አቶ አባዲ የዚያን ቀን ያሳዩት ትዕግስት ግን እኔንም ሳያስገርመኝ አልቀረም፤ ተሰብሳቢዎቹ ዝም እንዲሉ ካደረጉ በኋላ ንግግሬን እንድቀጥል አደረጉ፤ እኔ ስቀጠር የአድዋ መማህራን ኮሌጅ ዲን የነበረውና በኋላ የትግራይ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ የሆነው አቶ አብርሃ ኪሮስ እኔ በማስተዳድረው ኮሌጅ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ሰው ሊገኝ ቻለ ብሎ አዳራሹን ለቆ ወጣ። እኔ ንግግሬን ቀጠልኩ፤ “እቺ እናንት የተሳፈራቹባት መኪና አርጅታለች፤ ወይ ባግባቡ መታደስ ወይም ደግሞ መቀየር አለባት” የሚል ይዘት ነበርው። 


ከዚያ ቀኑ ሙሉ እኔ ባነሳሁት ሀሳብ ላይ ሆነ ሰብሰባው፤ እርግማንና ተቃውሞ ሳስተናግድ ዋልኩ፤ በምሳ ሰዓት ላይ እንደተረዳሁት ከምር ያዘኑልኝ ሰዎችም ነበሩ፤ የሆነ ነገር ያደርጉታል ብለው፤ የህወሀት ሰዎችም በነጋታው ለብቻዬ ሊናግሩኝ ሞከሩ የት እንደ ደተወለድኩ፤ በምን ምክንያት ህወሀትን እንደምቃወም ሁሉ ጠየቁኝ፤ ነገሩ ጠንከር ያለመሆኑን ስረዳ ረጋ ብዬ “እናንተ የታገላችሁት እኮ እንደእኔ ያለሰው ሀሳበቡን በነፃነት እንዲገልፅ መሰለኝ፤ ደግሞ የአሰራር ችግር ሲኖር ችግር አለ ማለቱ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይደለም” ወደሚል የተለሳለሰ አቀራረብ ወረድኩ፤ በእውነቱ አዲስ ተቀጣሪ ስለነበርኩ፤ በሌላ በእኩል ደግሞ ውስጥ ውስጡን አረና ለመመስረት የምንቀሳቀስበት ወቅት ስለነበር መፍራቴ አልቀረም።


ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስና አቶ አባዲ ዘሞ እጃቸው ከተቆረጠ በኋላ ወደ ማረት ተመድበው ድርጅቱን በኢኮኖሚና በውጭ ግንኙነት የተሻለ ስራ እንዲሰራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ታጋዮች ጋር ስማቸው ይጠቀሳል። እንደዚሁም ከእነስየ መውጣት በኋላ አቦይ ስብሀትን ተክተው የህወሀት ግዙፉ ድርጅት ኢፈርትን ከመሩና የአቶ መለስ ቀኝ እጅ ናቸው ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ናቸው። በኋላ ግን አቶ መለስ ኢፈርትን ለወ/ሮ አዜብ መስፍን ለመስጠት በመፈለጋቸው ምክንያት አቶ አባዲ ዘሞ በሰሜን ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተብለው ወደ ካርቱም ተሸኙ። አሁን በካርቱም በአምባሳደርነት ስም የተንደላቀቀ ህይወት ይኖራሉ ተብሎ ይወራላቸዋል። አሁን አቶ አባዲ ዘሞ ይህን ዕድል ተጠቅመው እዚያ በሱዳን እየተሰቃዩ የሚገኙት ዜጎቻችን ቢደርሱላቸው ምን ነበረበት!

Filed in: Amharic