>
5:36 am - Tuesday July 5, 2022

ህወሓት ካሣ ይክፈል!... የገንዘብ ወይ ንብረት ካሳ በህዝቦች ላይ ለደረሰው በደል አይመጥንም (ኣብርሃ ደስታ- ከመቀሌ)

Abrha Desta (photo by Kuru Hagere FB)“ለውጥ አመጣን” ይሉናል ራሳቸው ከደርጉ የጦርነት ዘመን እያወዳደሩ። ኢህአዴጎች ለውጥን የሚለኩት አሁን ማከናወን ከሚገባቸው ተግባር አንፃር ሳይሆን ካለፈው የደርግ ዘመን በማነፃፀር ነው። አሁን ለውጥ አለ ለማለት በደርግ ግዜ ምንም ለውጥ አልነበረም ብለው ይጀምራሉ። አሁንኮ ካለፈው ጋር አይወዳደርም።

እውነት ነው በደርግ ግዜ እዚ ግባ የሚባል ለውጥ አልነበረም። ምክንያቱም ደግሞ አለመረጋጋት ነበር። ጦርነት ነበር። በጦርነት ግዜ ልማት ማምጣት አስቸጋሪ ነው። ደርግ እንኳን የልማት እንቅስቃሴዎች ሊያከናውን ይቅር አብዛኛው የትግራይ ግዛት አልተቆጣጠረም ነበር። መንግስት አልመሰረተም ነበር። የልማት እንቅስቃሴዎች ሲጀምርም በወንበዴዎች ይዘረፍ ነበር። ለትምህርትቤት ግንባታ ገንዘብ ሲወጣ ወንበዴዎች መንገድ ላይ ጠብቀው ይዘርፉታል። በዓዲግራት ሆስፒታል ሊገነባ ታስቦ ለግንባታው የሚሆኑ ዕቃዎች በህወሓቶች መዘረፋቸው ሰምቻለሁ። እናም ህወሓቶች ሽፍተው ጫካ ገብተው አለመረጋጋት ፈጥረው ደርግን እንቅልፍ ነስተው በልማት ተግባራት እንዳይሰማራ አድርገው፣ “ሁሉም ወደ ጦር ግንባር …” እስኪፎክር ድረስ አስገድ ደው “በደርግ ግዜ የተሰራ ልማት የለም” አሉን።

አዎን! በደርግ ግዜ የተሰራ ልማት የለም። ምክንያቱም ደርግ በጦርነት እንጂ በልማት አልተሰማራም። የጦርነቱ መንስኤም አንዱ ህወሓት ነው። የደርግ የኃይል እርምጃና አጠቃላይ ፖለቲካዊ አካሄድ የሚደግፍ ያለ አይመስለኝም። ህወሓት ራሱ በፈጠረው ችግር ደርግን እየወቀሰ ራሱን ከጦርነት ዘመን ጋር እያወዳደረ እኛን ለማጃጃል ሲሞክር ግን ግርም ይለኛል።

አዎን! ጦርነቱ የተከፈተው በደርግ የፖለቲካ ችግር ነው። ደርግ ሰለማዊ ትግልን ዘጋ፤ ከዛ የኃይል መንገድ ብቸኛ አማራጭ ሆነ። ወጣቶች ጫካ ገቡ። ጦርነት ተከፈተ። ብዙ የሰውና የንብረት ዉድመት ደረሰ። አሁን የደርግ ጥፋት ያለፈ ታሪክ ሁኗል። አሁን የሚያገባን ስላለፈው መተረክ ሳይሆን ስላሁኑ መነጋገር ነው። ያሁኑ ችግር ደርግ ጨቋኝ መኖሩ አይደለም። ምክንያቱም የደርግን ጭቆና አልፏል። ያላለፈው የህወሓት ጭቆና ነው። የሚያሳስበኝ ነገር ቢኖር የደርግን መጥፎነት ሳይሆን የህወሓት ደርግን መምሰል ነው። ህወሓት የደርግን ፖለቲካዊ አካሄድ መኮረጁ ያሳስበኛል። ህወሓት ሰለማዊ ትግልን እየዘጋ ነው። የሰላም በር ሲዘጋ የኃይል በር እንደሚንኳኳ ታሪክ ይመሰክራል።

ይህን ህዝብ እስካሁን የከፈለው መስዋእትነት ይበቃዋል። ጭቆና ይበቃናል። አሁን የሚያስፈልገን ካሳ ነው። የንብረት ወይ የገንዘብ ካሳ አይደለም። ምክንያቱም የገንዘብ ወይ ንብረት ካሳ በህዝቦች ላይ ለደረሰው በደል አይመጥንም። ስለዚህ መከፈል ያለበት ካሳ የስልጣን ካሳ ነው። ስልጣን በካሳ መልክ ለህዝቡ መሰጠት አለበት። ህዝብ የስልጣን ባለቤት ይሁን። ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሲሆን ነፃነት ይኖራል፤ ገንዘብና ንብረት ይኖራል።

ስልጣን የህዝብ ሆነ ማለት ዴሞክራሲ ሰፈነ ማለት ነው። ዴሞክራሲ ሰፈነ ማለት ደግሞ ነፃነት ተረጋገጠ ማለት ነው። ስለዚህ ህወሓት ለፈፀመው በደል ህዝብን መካስ ካለበት በህዝብ ደም ያገኘውን ስልጣን ለህዝቡ ለባለቤቱ ያስረክብ። ስልጣን ለህዝብ ሳይሰጥ በኃይል ከስልጣን እስኪወገድ ድረስ ከቆየ ግን በህዝብ ትግል የተገኘ ስልጣን ለሌላ ታጣቂ ኃይል ይሰጠዋል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ክህደት ነው። ስልጣን ከህዝብ ነጥቆ ለሌላ ቡድን መስጠትን የመሰለ ጥፋት የለም።

ህወሓት ከደርግ ቢሻል መልካም ነው። ለፈፀመው በደል ካሳ ቢከፍል ጥሩ ነው።

                      ማስታወሻ:-  ኣብርሃም ደስታ የልደት ቀኑ በመሆኑ የራሱን ብዕር ደግመን ለማቅረብ ወደድን። ይህ ጀግና እንኩዋንም ተወለደ!Happy burthday Abriham Desta

Filed in: Amharic