>
9:06 pm - Thursday February 2, 2023

ይድረስ ለመጥረቢያው እጀታዎች!!!!!!!!!!! [ኤፍሬም እሸቴ]

መጥረቢያ. Epherm Esheteከዕለታት በአንድ ቀን፣ ዘመዶቻቸው በመጥረቢያ የተጨፈጨፉባቸው ዛፎች ስብሰባ ተቀመጡ አሉ። አሉ የተባሉ የዛፍ ዘሮች በሙሉ ከነምሬታቸው እና ቁጣቸው ተሰበሰቡ። እነሆም ስብሰባው አንዲት አጀንዳ ብቻ ነበረችው። “እንደዚህ የሚጨፈጭፈንን መጥረቢያ ምን እናድርገው?” የምትል አንዲት ቀጭን አጀንዳ።
ዘመዶቻቸው በመጥሪያ ያለቁባቸው የዛፍ ዘሮች በሙሉ ተራቸው እየጠበቁ ሐሳባቸው አጎረፉ። ገሚሱ “መጥረቢያውን በትልቅ ጉድጓድ ቆፍረን እንቅበረው” አሉ። አንዳንዶቹ “አይደለም፤ ሁለተኛ የአገራችን መሬት ለመቀበሪያው እንኳን አንዳይሆን ከአስገምጋሚ ወራጅ ወንዝ ውስጥ እንጣለው። እየደፈቀ፣ ከአገር አውጥቶ ከበረሃ ይጣለው” አሉ። አንዳንዶቹም “እሳት አንድደን እናቅልጠው። የቀለጠውንም ከወራጅ ውሐ ውስጥ እንቀላቅለው” አሉ። ሌሎቹም የመሰላቸውን፣ ንዴታቸውን እና ቂማቸውን የሚያበርድላቸውን ውሳኔ ሁሉ ሰጡ።
በመጨረሻ ግን ቀኑን ሙሉ ምንም ያልተናገሩ አንድ አረጋዊ ዛፍ በሰለለች ድምጻቸው ዕድሜ ያስተማራቸውን ረቂቅ ሐሳባቸውን አቀረቡ። “ወገኖቼ፤ ያላችሁት ነገር ሁሉ ለዚህ ለመጥረቢያ ይገባዋል፣ እንዲያውም ሲያንስበት ነው። ነገር ግን አንድ ያልተገነዘባችሁት ነገር አለ። እንደምታዩት መጥረቢያው ብቻውን አይደለም ወገኖቻችንን የፈጀው። እንዲያውም ብቻውን ቢሆን ኖሮ ምንም ማድረግ አይቻለውም ነበር። ነገር ግን መጠረቢያው እኛን እንዲጨፈጭፈን መያዣ እጀታ የሆነው የኛው ወገን እንጨት ነው። እጀታው ባይኖር ኖሮ እንዲህ ባላለቅን ነበር” አሉ። ተሰብሳቢውም ንዴቱን በመጥረቢያው ላይ ሲያወርድ ለካንስ የዘነጋው እጀታው መሆኑን አስተዋለ። ነገሩ “እጄን በእጄ” መሆኑ ገባው። እናም ፍርዱ ሲሰጥ ከመጥረቢያው ይልቅ የእጀታው የጸና፣ የከፋ ሆነ።
*******
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት፣ ናዚዎች ለፍርድ በኑረነምበርግ ሲቀርቡ ከታዩትና በመጽሐፍ መልክ ከተዘገቡት ታሪኮች አንደኛው የአዶልፍ አይኽማን (Adolf Eichmann) የክስ ችሎት ነበር። በዚሁ የክስ ችሎት ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀው “Eichmann in Jerusalem: A Report on the Banality of Evil” የተሰኘው የአይሁዳዊቱ ወ/ሮ የHannah Arendt ፖለቲካዊ ሪፖርታዣዊ መጽሐፍ ካነሳቸው ነጥቦች አንዱ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ዘልቆ ከጠየቀ በኋላ ሰውየው በአይሁዶች ላይ ግፍ ቢውልም ምንም ዓይነት ጸጸት እንዴት ሊሰማው እንዳልቻለ፤ ይልቁንም የሰው ልጅ ግድያ ላይ መተባበርን እንደ ማንኛውም ሥራ ሙያዊ አገልግሎት እንደመፈጸም እንዴት ሊቆጥረው እንደቻለ ወይዘሮዋ የጠየቁት ነገር ትልቅ ሙያዊ መከራከሪያ ሆኗል። ሰውየው የናዚዎቹ እጀታ እንጂ መጥረቢያ አለመሆኑን ወይዘሮዋ ተከራክረዋል። እርሱ ነው ጥያቄ ያስነሳው።
*********
በዘመነ ደርግ፣ የደርግን ፍልስፍና እና ትርጉሙን በቅጡ የማይገነዘቡ ነገር ግን እጃቸው የገባውን እስረኛ በማሰቃየት ወደር የማይገኝላቸው ብዙ ገራፊዎች ነበሩ። በትርፍ ጊዜያቸው ሳይቀር “ትንሽ ገርፌ ልምጣ” ብለው ሥራ እንደሚገባ ሰው ወገኖቻቸውን ለማሰቃየት የሚተጉ። በዘመነ ኢሕአዴግም እንዲሁ ቀን ተሌሊት ተግተው ወገኖቻቸውን ለማሰቃየት እንቅልፍ የሚያጡ ብዙ ሰዎች እንዳሉ በቅርቡ የዞን ዘጠኝ ወጣቶች ስለራሳቸው ከጻፉት በስፋት ማንበባችን ይታወሳል።
በዘመነ ኢሕአዴግ በሶሻል ሚዲያ በየቀኑ እየተሰነደ (ሰነድ እየሆነ) በመቀመጥ ላይ ባለው የኢትዮጵያውያን ስቃይ ተካፋይ የሆኑት ሕወሐቶች ብቻ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። በየመንገዱ ሕዝቡን ከሚደበድበው ወታደር አብዛኛው ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም። ነገር ግን ድብደባውን በደስታ የሚፈጽመው የሕዝቡ ወገን የሆነው ወታደር ነው። ልክ እንደ ጀርመናዊው አይኽማን፣ እንደ ደርግ የቀበሌ ገራፊዎች ወዘተ።
***********
በኦሮሚያ እጅግ የሚዘገንን የጅምላ ጭፍጨፋ በመካኼድ ላይ መሆኑን ሪፖርቶች እየተዘገቡ ነው። በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም እንዲሁ። ሁሉንም ተመሳሳይ የሚያደርገው ግን የመጥረቢያው አንድ መሆን እና የእጀታዎቹ ከየአካባቢው የበቀሉ ዛፎች የመሆናቸው ጉዳይ ነው። መጥረቢያው እንዲጨፈጭፍ ከኦሮሚያ የበቀላችሁ፣ ከአማራ የበቀላችሁ እጀታዎች ችግሩ የእናንተም ነው። የመጥረቢያው እጀታዎች ሆይ፤ እኛ አይደለንም፣ መጥረቢያው ነው ማለት የማይቻልበት ጊዜ እየመጣ ነው። አሁንም አልረፈደባችሁም። አስቡበት።
++++++++++++++++++
“E pluribus unum = Out of many, one.”!!
ብዙዎች ስንሆን ግን አንድ ነን።

Filed in: Amharic