>
3:58 pm - Tuesday September 28, 2021

የማለዳ ወግ ...መሪውን የበለጠ ህዝብ በተቃውሞ ጎዳና! [ነብዩ ሲራክ]

* ጀግናው ፈይሳ ሌሊሳን በሪዮ
* ጀግናው ኢብሳ እጅጉ በኪውቢክ
* የጀግና ሌሊሳ አርአያነት በኢብሳ እጅጉ ሲደገም
* የእኛን ሐገር ፖለቲከኞች ህዝቡ በልጧቸዋል

ኢብሳ እጅጉያን ሰሞን ጀግናው ልበ ሙሉ ሯጭ ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ 2016 ማራቶን ቆፍጠን ብሎ የሁለተኛነት ድልን ተጎናጸፈ ፣ ፈይሳ በሙያው ለህዝብ ያለውን ከበሬታ ሲያሳይ እጁን አጣምሮ ወደ ላይ ሲያነሳ ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ አድናቆቱን ሰጠው! የእኛ ፖለቲከኞች እና ካድሬዎቻቸው ግን አሸሞሩበት አላገጡበት ” እሱ ተራ ሯጭ ነው ፣ ምን ያውቃል !” እያሉ ያላገጡበትም ነበሩ ! ዳሩ ግን ጀግንነቱ ገዘፈ እንጅ አላንኳሰሱትም !

እነሆ የጀግናውን አትሌት አርአያ ሌላው ጀግና ተከተለ ፣ ሌላኛው ጀግና ሯጭ ኢብሳ እጅጉ ዛሬ ካናዳ ኪውቡክ ላይ በማራቶን ተወዳድሮ ሲያሸንፍ የጀግና ወንድሙን አርአያ ተከትሎ እጆቹን አጣምሮ ተቃውሞውን ገለጸ ! ኢብሳም እንደ ሌሊሳ በወገኑ የሚደርሰውን መረገጥ ሲቃዎም እጆቹን አጣምሮ ተቃውሞውን ተቀላቅሏል ! ይህች ጀግና የማታጣ ሐገረ ኢትዮጵያ የማታሳየን የለም ፣ እያስለቀሰኝ በፌስታል ጮቤም ታስረግጠናለች !

ሃገራችን ዛሬ እንደትናንት ለነጻነቱ የጠፋ ኩሩ ህዝብ እንጅ መሪ አስተዳዳሪ የላትም …የሌሊሳን ተቃውሞ ምክንያት መሰረት መርምረው ለአመታት መንገዱን ያላስተካከሉት ግን አሁንም ተቃውሞው ” የጥቂቶች ” እያሉ ከህዝብ ጋር መጋጨት ይዘዋል ። ተቃውሞው የአስተዳደር ችግር ነው እያሉ ይሸፋፍኑት ይዘዋል ፣ አመጻው ከአስተዳደር የወጣ በመድልኦ ከተጎዳ ህዝብ አብራክ የወጣ መሆኑን መቀበልና ለመፍትሔ ሁነኛ መድሐኒት ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ አስረክቦ ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን መሆኑን አውቀው ሐገር ገንቢ ፣ ትውልድ አዳም ታሪካዊ ስራን መስራት ግን አልቻሉበትም !

በተለያዬ ጊዜ የተነሳም ተቃውሞ ” የጥቂት ስብስብ ፣ የጸረ ሰላም ኃይሎች እጅ አለበት! ” ነው ይሉና ፣ ተሰብስበው ሲመክሩ ጥቂት ያሉት ወደ” ህዝብ ጥያቄ “ይቀይሩታል ፣ ጥቂቱ ወደ ህዝብ ይቀየርና ” የአመጻው መሰረት የአስተዳደር በደል አለበት ” ይሉሃል ! የእኛ ፖለቲከኞች እና ካድሬዎቻቸው ማላገጥ ይህን ያህል ነው…

እውነቱ ፣ በኦሮሞም ሸአማራም በመላ ሃገሪቱን የከፋው ችግረኛ ሞልቶ ተርፎ አምጿል … እነሱ ግን እድገት ትራንፎርሜሽኑን ከህዳሴው ግድብ ጋር ፣ መንገድ ፎቁን ለምጣኔ ሀብቱና ከሁለት ነጥብ በላይ እድገቱ ጋር እያሞካሹ ይደሰኩሩልሃል ” … እድገት ምጥቀቱ ፣ አውራ ጎዳና ህንጻው ኑሮውን ፈቀቅ ያላደረገው ብዙሃን ግን ዲስኩሩ አልገባህ ብሎታል! … ብዙሃኑን ረግጠው ስለ ጥቂት ባለጊዜዎች ብልጽግና ይተርካሉና ዲስኩሩ ፌዝ ፣ ቃል የተገባው የማይጨበጥ ሆኖበት ተቸግሮ 25 ዓመት መግፋቱን የበቃው ይመስላል ። … ለአመታት በተስፋ ” ነገ ይነጋል! ” ሲል ያልተመቸው ዜጋ ፣ በአድልኦ የተንገላታው ፣ የተገፋው ህዝብ ግን ዛሬም ጥቂት እየተባለ ብዙ ሆኖ በአመጽ መትመም ብቸኛ አማራጭ ሆኖ እነሆ ተጋድሎው ጋብ አላለም ፣ አላቋረጠም!

የእኛ ፖለቲከኞች እና ካድሬዎቻቸው የሁሉም አመጻ መንሥኤ ለ25 ዓመታት የታመቀ ግፍ የመተንፈስ ጅማሮ መሆኑ እየገባቸው ፣ አልገባቸውም ! የችግሩ ብዛት ተከምሮ ፣ በአመጻው በመንፈስ ያበሩትን የአማራና የኦሮሞ ኩሩ ህዝቦች ሊያጋጩ ተፍ ተፍ ሲሉ ሰው ቀድሞ ነቅቶ አትናችሁን ለአፈር ማል ይዟል …ሰላማዊ መንገድ ተከትሎ በኦሮምያ ሰልፍ የወጣው የኦሮምያ ነዋሪ በአንዳንዶቹ የህወሓት ደጋፊዎች ድጋፍ ሲያገኝ ፣ ቆርጦ ለመብቱ የተነሳው አማራ ለመሪዎቹ የጭቃ ሾህ ሆኗልና አመጻውን ህገ ወጥ አካሄድ ይሉት ይዘዋል!

የእኛ ፖለከኞችና ካድሬዎች በህዝብና በሐገር ላይ የማላገጥ ፖለቲካ እንዲህ ሆኗል ! ብቻ ቀጣፊ ፖለቲከኞችን ተራው ዜጋ በልጧቸዋል ! የእኛ ፖለቲከኞች እና ካድሬዎቻቸው ግን ቢያንስ መበለጣቸውን አምነው ተቀብለው የበለጣቸውን ህዝብ ድምጽ ሰምተው በእጃቸው ያለውን ሁነኛ መፍትሔውን አርቀውታል !

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

ነቢዩ ሲራክ

ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓም

Filed in: Amharic