>
11:39 am - Monday November 29, 2021

ብርቱ ካህን ተመረቀች፤ ከዛስ... (ከ ኣቤ ቶክቻው)

ባለፈው ምርጫ መንግስት ብርቱካን ሚዴቅሳ ዳግም ወደ ፖለቲካው ተመልሳ ”አንድነት ፓርቲ የቅንጅት ህጋዊ እና ሞራላዊ ወራሽ” በማለት ከጓደኞቿ ጋር መስርታው ከዛም ሊቀመንበር ሆና መከሰቷ ቆሌውን ቀፎት ነበር። በዛም የተነሳ ከአንደበቷ ጠብ የሚል መክሰሻ ቃል ሲያፈላልግ ሲያፈላልግ በስዊዲን ለሚገኙ ደጋፊዎቿ ያደረገችው የምስጋና ንግግር ተገኝ። በንግግሩ ውስጥ በህግ አግባብ የጠየቅነው ይቅርታ የለም አለች። ይሄኔ ካድሬዎቹ ተሻምተው ያዟት። የምርጫውን ወቅትም እስር ቤት ውስጥ እንድታሳልፍ አደረጉ። ሟቹ ጥቅላይ ሚኒስትር ”እርሷን ከምፈታ ወይዘሮ አዜብን ብፈታ ይቀለኛል አሉ” ተብሎ እስኪነገር ድረስ ”ግግም” ብለው የመጣው ቢመጣ አንፈታትም። አሉ!
እውነት ግን እንዲህ ይሚያካርር ነገር ከዳኛዋ አፍ ውጥቶ ነበር ወይ የታሰሩት፤ የተባለ እነደሆነ መልሱ አይደልም ነው። በወቅቱ በብርቱካን ዙሪያ የተሰባሰበው ሃይል ቀላል አልነበረም። የብርቱካን ትግል ውስጥ መኖር ለተቃዋሚው ጎራ የሰጠው የመነቃቃት መንፈስም ዋዛ አልነበረም። ስለዚህ ገዢው ግንባር ጨነቀው ታድያ ሲጨንቀው ይሞታል እንዴ… (ይገድላል እንጂ…) ብርቱካንን አሰራት የተቃውሞውንም ትግል ባይገድለውም አቆሰለው፤
ብርቱካን የተናገረችው የሚያሳስር እንዳልሆነ ለመረዳት በጣም ቀላሉ መንገድ በወቅቱ የወጡትን ጋዜጦች ማገላበጥ ነው፤ እርሷ ”በሀግ አግባብ ይቅርታ አልጠየቅንም” በማለቷ የተሰጣትን ይቅርታ ክዳለች እንደታሰረች፤ መጀመሪያ ተደናግጠው የነበሩ ቀድሞ አብረዋት የታሰሩት የተቃዋሚ አመራሮች ትንሽ ቆየት ብለው በአደባባይ ”አዎ ይቅርታ አልጠየቅንም!” እያሉ ከእስር የተፈቱበትን ሂደት እያፍታቱ መጻፍ ጀመረው ነበር፤ እኛ የዋሆቹ በቃ አሰሯቸው እያልን ብንሳቀቅም አሳሪ ግን አልነበረም። ምክንያቱም የተፈለገችው እርሷ ነበረች። እርሷን በማሰር ብቻ ብዙ ነገር ማበላሸት ይቻላል። እናም ከዛ ቀጥሎ ያሉትን ማሰር በግንባሪቱ ዘንድ ዋጋ አልነበረውም እናም እንዳልሰማች ”ላሽ” አለች…!
ምርጫው ካለፈ በኋላ ብርቱካንን አስሮ ማቆየት ዋጋ አለነበረውም። እናም በቄስ በጓደኛ አስለምነው፤ በወታደር በፌደራል አሰፈራርተው የሆነ ነገር ብላ እንደትወጣ አደርጓት። ስትወጣ ምርጫው የለም። እንኳንስ ምርጫው እና ያሰቀመጠችው አንደነት ፓርቲም ያኖረችው ቦታ አልነበረም።
ያ ከሆነ አሁን አምስተኛ አመቱ ሊመጣ ነው… አዲስ ምርጫም መጣሁ መጣሁ እያለ ይገኛል። ሀዝቡ በአሁኑ ወቅት ”ኢንሻላህ በሁለት ሺህ ሰባት ምረጫ ኢህአዴግን እናሰናብታለን” በማለት ቀን እየቆጠረ ነው። ኢህአዴግ በእስላም ክርስቲያኑ ወጣት አዛውንቱ ”ቱ!” ተብሏል ለማለት አዋቂ መጠየቅ አያስፈልገውም…!
ኢህአዴግን የሚገዳደረው ተቃዋሚ ፓርቲ የተኛው እንደሆነ ለመናገር አዲስ አበባ እና በአራቱም መአዘን ሙሉ ኢትዮጵያን ውስጥ መገኘት ይጠይቃል። ውጪ ሀገር ሆኖ ግምትን ለማስቀመጥም ብዙ ተመስጦ ይጠይቃል። ነገር ግን እንደ ብርቱካን ሚዴቅሳ አይነት ፈርጦች የሚቀላቀሉት ፓርቲ በህዝቡ ዘንድ አንጸባራቂ ሆኖ እንደሚወጣ ለመገመት በጣም ቀላል ነው።
ብርቱ ካህን ወደ ወጪ ሀገር የወጣችው ለትምህርት እንደሆነ ቀድማ ነግራናለች። አሁን ትምህርቱ አልቋል። በቀጣይ ሀገር ቤት ሄዳ ሳይማር ያማረራትን መንግስት ለማስተማር ተነሳሽነት ብታሳይ በህዝብ ዘንድ የሚኖራት ተቀባይነት ቀላል እነዳልሆነ እኛም እናውቃለን እነርሱም ያውቃሉ እርሷም ተጠረጥራለች…
ስለዚህ ብርቱ ሆይ የበረታሽ ነሽ እና በርቺ አልልሽም!ባይሆን የፈረንሳይ ለጋሲዮን አድባር ትከተልሽ! ብዬ እመርቅሻልሁ!

Filed in: Amharic