>
4:12 pm - Tuesday September 28, 2021

“…..የመሸበት ማደር!” [አስፋ ጫቦ Dallas Texas USA]

ESAT Yetsehafian Demitsoch Dr Merara Gudina  [Part1-Video]“እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር!” የሚል አባባል አለ። ወዳጄን ዶክተር መረራ ጉዲናን ሳስታውስ ያ አባባል ይመጣብኛል። ከዚያ የተሻለ ሊገልጸው የሚችል አባባል ሊኖር ይችላል።አልመጣልኝም!አሁን ታሰረ!በዚያ ምክንያት ነው ይህንን የምጽፈው

መረራ የሚያውቀውን እውነት፣ይጽፋል፣ ይናገራልም። ለማስቀየም ወይም ለማስደሰት ፤ወይም ፖለቲካዊ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ብሎ ሲናገር የሰማሁበት ጊዜ የለም። ያ በንግግሩ ፤በጽሑፍ ያነሳቸው ሌሎቹን አላስቀየመም፤አላበሳጨም አላጋለጠም ማለት አይደለም።ያ የመረራ ግቡ አይመስለኝም።ያ የተነገረው እውነት ፤የጻፈው እውነት ውጤትነው።ከዚህ የተነሳ ምሁርነቱ፤የፖለቲካ ተዋናኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መረራ ለኔ የሰፈር አስታራቂ ሽማግሌ!” መስሎ ይታየኛል። ባለ አንጣዎቹ የሽማግሌውን ምክር ሰምተው ላይታረቁ ይችላሉ።ይህ የሽማግሌው፤የመረራ ጥፋት አይመስለኝም። “እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ!”ብለው ፍንክች የማይሉ ተፋላሚዎቹ ጉዳይ ይመስለኛል። መረራ ጉዲና ከ1992 በፊት አላውቀውም። በስም ግን አውቀዋለሁ። እኔ ማእከላዊ ታስሬ የነበረ ጊዜ መረራ ከርቸሌ እስረኛ ነበር። በመኢሶንነት ነበር የታሰረው። ታዲያ በማእከላዊና በከርቼሌ መካከል ላይና ታች እስረኛ ስለሚመላለስ ከርቼሌ ወጣ ብለው ስለሚታዩት ግለስቦችና ቡድኖች በቂ መርጃ ነበረን።እኔ ነበረኝ!!

ማእከላዊ በተለያዩ  ምክንያቶች አንድ ወጥ የሆነ የሚያስቀና ትብብር ነበረን። ከርቼሌ ግን እንደዚያ ሳይሆን ውጭ ይባላ የነበረው የፖለቲካ ቡድን ያንኑ ስፍራው በሚፈቅደው መጠን ቀጥሎበት ነበር። በዚህ የተነሳ ፤መረራ  መኢሶን በመሆኑ እዚያ ጫና የፈጠረው ቡድን  “ገባር” ሊያደርገው ፈልጎ አልገብርም ብሎ አንገቱን ቀና አድርጎ  የተፈታ መሆኑን የሚያቁት ይነገሩኝ ነበር። ካልገበር የማግለልና የመገለል ሁኔታ (oetricized)ይፈጥርበታል። ከምግብ ከሌላውም የማግለል ሁኔታ ይፈጠራል። መረራ  ይህ ተፈጥሮበት ከአቋሙ ዝንፍ ሳይል ተፈታ ይሉኛል።

መረራን መጀመሪያ ያገኘሁት በ1993-94 ይመስለኛል። ዋሽንግቶን ዲ ሲ አሁን በሕይወት የሌለውን፤እንግዳ ተቀባይና  አስተናጋጁ ሙሉጌታ ኃይሉ ቤት ነበር። እኔ ከካሊፎርኒያ መረራ ከአዲስ አበባ መጥቶ እዚያ አርፈን ከረምንም መሰለኝ። አንድ በወቅቱ የነበር ኢድሐቅ የሚባል ድርጀት ባዘጋጀው ስብሰባ ለመገኘት ነበር የመጣው። ምርጫ በየጊዜው እየተደረገ ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ነበር የሚመረጠው ።በዚህኛው ዙር መረራ ጉዲና ተመረጠ።በየነ ጴጥሮስ አኮረፈው።መነጋገር አቆሙ!

በአሁኑ ዙር አሜሪካ የመጣ ጊዜ በስልክ አንድ ሁለት ሶስቴ አግኝቸው ነበር። በጫወታችን  መካከል የበየነ ጴጥሮስን ነገር አነሳሁበትና ሌላም የሰራውንና የሚሰራውን አነሳነው።” አስፋ እሱን እባክህ እርሳው! ጉዳት የለውም!” አለኝ። መረራ ነገር ፍቆ አልፎ መሔድ የሚችል መሆኑን አስተዋልኩ።

ከሚጻፋቸው ነገር አንዱ ትዝ የሚለኝ የኦነግ መሥራችና መሪ ስለነበረው ስለባሮ ቱምሳ በጦቢያ መጽሔት የጻፈው ነው። ባሮ የነጻ አውጭ ጦር ግንባር ለመክፈት ሐረርጌ ወርዶ እዚያ ነው የሞተው። “እገሌ…እነእገሌ አስገደሉት!” የሚል ወሬ በወቅቱ ስራዬ ተብሎ ጭምር ይናፈስ ነበር። መረራ ማስረጃና ስም ጠቅሶ “ባሮ የተገደለው አብሮትበዘመተ፣ ብዙ የሌለ ተስፋ ሰጥቶ ከወሰዳቸው፣ተስፋ ከቆረጡት ልጆች በአንዱ፤ ከአምቦ ነው መስለኝ በሔደ ወጣት ክላንሽኒኮብ ነው “ብሎ ጻፈ። የኦነግ ነን በሚሉ ብቻ ሳይሆን በሌላው ኦሮሞ ዘንድ ሁሉ “እውነተስ ቢሆን እንዴት ታጋልጣለህ!” በሚል ክስና ውቅስ የሚያመጣ ነው። የመረራ ስራ ግን እውነቱን ግሮ የመሸበት ማደር ነው።

የአሁኑ መሸበት ማደር ግን ማደሪያውን ወህኒ ቤት አደረገው። የወያኔ አድሮ ውሎም የለየለት እዉር መሆኑ ይደንቀኛል! አውቀዋለህ  ሆኖም ይደንቀኛል!ዶክተር መረራ ጉዲና እንዴት ይታሰራል? መታሰር የሚገባቸው እዚያ ውስጣቸው እንደ አሽን ፈልተው ማለቴ ነው። ድንገት የሚታሰር ሰው እጥረት ቢፈጠር እንኳን መረራ ጉዲና መታሰር የለበትም። ከኢትዮጵያ ወይም ከመረራ አንጻር ሳይሆን ከወያኔ አንጻር አይቸው ነው። መረራ ጉዲና አውሮጳ ይሁን አሜሪካ ፤አውሮጳ ፓርላማ ይሁን ካፌ ውስጥ የሚናገረው ከላይ ያልኩትን እውነት ነው።  እዚያው አዲስ አበባ ወያኔ ፊት ለፊት የሚናገርውን ነበር ለአውሮጳ ፓርላማ የተናገረው ።።እኔ እነደታዘብኩት መረራ ዲና ነገር መቀባባት ፤ሞቅ ሞቅ ማድረግ አያውቅበትም። እንደወረደ ነው። ታዲያ ከዚህ የተነሳ ፣መረራ ከሁሉም በላይ  ለወያኔ ጠቃሚ ሃብት ነበር።”ይኸው እንደልቡ የሚናገር ተቃዋሚ አለንኮ!” ለማለት ይጠቅማላ!

ወያኔ እባካችህ “እፍረት!” የሚባል ቃል ፈልጋችህ እፈሩ!

እና ዶክተር መረራ ጉዲናን ፍቱልን!

Filed in: Amharic