>
7:07 pm - Thursday September 16, 2021

የቴዲ አፍሮ …ተሞክሮ! (ቁጥር አንድ) [ከኤርሚያስ ለገሰ]

Teddy-Afro1- Almariamየዛሬ ሁለት አመት በጸደዩ ወራት የኢሳት ስድስተኛ አመት ለማክበር በፍሎሪዳ ግዛት ታምፓ ከተማ ተጉዤ ነበር።-የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በዝግጅቱ ላይ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ጋር አብሮ የሰራ ድምጻዊ አብሮኝ ተጉዟል ። ይህ የሚወዳት አገሩን ተቀምቶ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ የከተመ አርቲስት ጋር በነበረን ወግ መሃል ስለ አርቲስት ቴዲ አፍሮ አንስተን የተጫወትንበት ነበር። ቴዲ አፍሮን በቅርበት የሚያውቀው ይህ የኪነጥበብ ሰው እንዳጫወተኝ ከሆነ የቴዲ አፍሮ የስኬት ምክንያቶች በዘፈቀደ የመጣ አይደለም። ይልቁንስ የቴዲ የስኬት ምክንያቶች የስራ ዲሲፕሊኑ፣ ትጋቱ፣ ለራሱና ለሙያው የሚሰጠው ዋጋ፣ በየጊዜው ብቃቱን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት፣ ትላንት የነበረውን አስተሳሰብ ዕድገት ለማምጣት ያለው ዝግጁነትና የጠለቀ የአሸናፊነት ስሜት ሰንቆ መጓዙ እንደሆነ ያምናል። በህይወቴ ጥንቅቄ የሚያውቅ እንደ ቴዲ አፍሮ አላጋጠመኝም ይላል።

እርግጥም ቴዲ አፍሮ እምቅ የሆነ ችሎታውን ለአለም ማሳየት የቻለው ሙያው ለሚጠይቀው ባህርያትና ክህሎት ጥልቅ ስሜት ያለው መሆኑን ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። አሁንም ከርቀት መታዘብ እንደሚቻለው ቴዲ አፍሮ ወቅታዊውን የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ መከታተል መቻሉና ተራክቦውን አንደበተ ርቱዕ በሆነ መንገድ መግልፅ መቻሉ የማህበረሰቡን ቀልብ ለመግዛት አስችሎታል። እንዲህ አይነት ግለስቦችላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ታዋቂው የአመራር ሳይንስ ፅሐፊ John Maxwell “በወርቃማ ቃላትና አንደበት ዕለምን መግዛት ይቻላል” በማለት ይገልጻል። ወርቃማ ቃላትን ሰዎችን ለማሳመን እንደቅድሚያ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን በማስገንዘብ።

በእኔ ዕምነት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የኪነጥበብ ሙያተኞች የሚጎላድላቸው ከላይ የተገልጸው የቴዲ አፍሮን ባህሪ መላበስ አለመቻላቸው ይመስለኛል። ለነገሩ የዚህ አጭር መጣጥፍ ትኩረት የኪነጥበብ ሰዎች ላይ በመሆኑ እንጂ ችግሩ በተለያዩ ሙያ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጨምር ነው። እንዲያውም የኋለኛው ሳይከፋ አይቀርም። አለማወቅ የራሱ በረከትና ጸጋ ያለው ይመስል አገዛዙ ያነገበውን አገር የማፍረሻ አሳብና መሳሪያ አለማወቃቸው የሚያስኮፍሳቸው ራሳቸውን “ምሁር” ጎራ የከተቱ በርካታ ሰዎች አጋጥመውኛል። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲህ አይነት ደካማ አቋም ያላቸው የምሁርነት ካባ ያጠለቁ ኋላቀሮች መኖራቸውን እጠብቃልሁ። ከስራ ዲሲፕሊንና ትጋት ይልቅ ልግምተኛና ተሳዳቢ፣ በየጊዜው የራስ ብቃትን ለማሳደግ ከሚደረግ ጥረት ይልቅ ወደ ዘለፋና አጉል አሽኮለሌ የሚያመራ፤ ከሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጥ የስነልቦና ዝግጅትና ለውጥ ከማሰብ ይልቅ በትላንትና የወደቀ አመለካከት ተቸንክሮ መቅረት የሚይታይባቸው ብዙ ናቸው። እጅግ በጣም በዙ።
ብዕሬ ሌላ ቦታ ረግጦ እዚህ ገባሁ እንጂ ልፅፍ ያሰብኩት የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሙያተኞች ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ምን ትምህርት ሊቀስሙይገባል የሚለውን የግል ምልከታ ለማስቀመጥ ነበር። አስተያየቴ ስሜታዊነት አጥቅቶ ከሆነ ምናልባትም የወቅቱ የአገራችን ሁኔታ የፈጠረው ሊሆን ይችላል።ይህ ምልከታየ የሚቀርብበት ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህልውና አደጋ ያጋጠማት ሁኔታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ አደጋውን በሚያመላክቱ ቃላት የታጀበ ሊሆን ይችላል። አሁን የደረስንበት ደረጃ አካፋን አካፋ የምንልበት እንጂ አንዱ ሌላውን በቃላት ለመሸንገልና ለማቄል የሚሞክርበት አይደለም። ተወደደም ተጠላም “እኛ እና እነሱ” የሚል ነጭና ጥቁር መጋረጃ የተፈጠረበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በነጭና ጥቁር መሻሻል ደግሞ ግራጫ የሚባል እራፊ ጨርቅ የለም።
***
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን “ኢትዮጵያ” በሚለው አልበምም ሆነ በተከታታይ በሰጣቸው ቃለ-መጠይቆች የገለጠው ቀዳሚ ቁም ነገር “ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት አደጋና ፈተና ላይ ወድቋል!! በጎሳና ሐይማኖት መከፋፈል ተፈጥሯል!” የሚለውን ነው ይሄ የቴዲ አፍሮ አገላለጽ እጅግ የጠለቀና ከየትኛውም አጀንዳ በፊት ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ነው። የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሙያተኞች አደጋ ውስጥ ስለወደቀው ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት በየጊዜው መድረክ አየፈጠሩ መነጋገር አለባቸው:: በአንድ ውቅት ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አንደተናገሩት ኢትዮጵያዊነት አንዲቀጥል በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር መኖር አለባት ። የዛሪው ወሳኝ ትግል ደግሞ በቅድሚያ ኢትዮጵያን ማዳን ሊሆን ይገባል ። ኢትዮጵያን ለማዳን ደግሞ ማንኛውም ሰው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ፥ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድነቱን ለማምጣት ሲል የሚከተለውን ስትራቴጂና ታክቲክ ከሩቅ ሆኖ መመልከት አይቻልም። ከፍ ካለም ሞራላዊ ወንጀለኝነት ነው::በመሆኑም የህልውና ትግሉን ያለማቅማማት ተቀብሎ የዜግነት ግዴታን መወጣት ፍላጎት የሚያጣ የኪነ-ጥበብ ሰው የቀድሞ ዝናው የትየለሌም ይድረስ አፈር ከድሜ መጋጡ አይቀርም:: በአጠቃላይ መልኩ አሁን አየተደረገ ያለው ትንቅንቅ የሞት ሽረት ትግል መዳረሻ ህልሙ ኢትዮጵያን መታደግ መሆን እንደሚገባው መገንዘብ ያሻል።
ቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ የጣለ ጎሰኝነት ተፈጥሯል “ የሚለው አገላለጡም ወቅታዊ እውነታ ነው ። አርቲስቱ እንዳሰመረበት ዛሬ በሃገራችን የተነሰራፋውን የዘረኝነትና ጎሳዊ መንፈስ ድል አድርገን ብዙህነትን በሚቀበል አንድነት ውስጥ መኖር የምንችለው ችግሩን በቅጡ ስንገነዘብ ነው ። በሽታውን ያላወቀ መድሃኒቱን ማወቅ ይሳነዋል እንዲሉ የወቅቱ የኢትዮጵያ ችግር መፍቻ ኣብይ ቁልፍ ያለው እዚህ ላይ ነው ። በግልጽ እንደሚታየው ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ህውሃት መንግስታዊ ስልጣኑን በመጠቀም በፈጠረው “ የትግራይ አድሎአዊ ተጠቃሚነት “ ምክንያት ጎሰኛ አመለካከት እየተስፋፋ ሄዷል ። በተለይም ህውሃት በአማራና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ በቀል ለማድረስ ፖሊሲ ነድፎ መንቀሳቀሱ የመገፋት ስሜት ፈጥሯል ። ህውሃቶች ለትግራይ ክልል እንደ ገጸ በረከት ይዘውላቸው የመጡት “ ኤፈርት ትልማ እና ረስት “ የሚባሉ ኩባንያዎችና ማህበራት የፈጠሩት አድሎ እርስ በእርስ በጠላትነት መመልከትን ፈጥሯል ። አርቲስቱ እንደገለጠው ጉዞአችን አንድ ሐገር የመመስረት ከሆነ አንደዚ አይነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በባለቤትነት ስሜት ኣንስተን መነጋገር ይኖርብናል። አሁንም ቢሆን ልሰማው የማልወደውና ለመረዳቴ እንደ ቧልት የምቆጥረው “ትግራይ በህውሃት አልተጠቀመችም “ የሚለውን ነው ።
ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ትልቁ ጥያቄ ብሄራዊ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት መጥፋት ሆኗል ። ይህንን ጠንቅቆ አለማወቅ ተጨባጩንና ትክክለኛውን ሁኔታ አለመረዳት ያስከትላል ። ያየነውና እያየነው ያለነው ነባራዊ ሃቅ ጸረ እኩልነትና የራስን ዘር ለመጥቀም የሚካሄድ ሩጫ እንደ አንድ ሃገር መቀጠል የማያስችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ። በአንድ በኩል ህውሀት በሚከተለው በዘር ላይ የተመረኮዘ አድሎአዊ ፖሊሲ ምክንያት ከኢፍትሃዊነቱ ተጠቃሚ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ተፈጥረዋል ። በሌላ በኩል ከፖለቲካው ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች የተገለለው የሌላው ብሄረሰብ ተወላጅ ከበደሉ ብዛት አንጀቱ እየነፈረና ሌሎች አማራጮችን የሚያማትርበት ሁኔታ ተፈጥሯል ።
እናም ቴዲ አፍሮ በቃለ መጠይቁ “ኢትዮጵያዊነት የሚሻክራቸው ሰዎች ተፈጥረዋል” በማለት የጋረዳቸው ማህበረሰቦች ሊፈጠሩ የቻሉበት መሰረታዊ ምክንያት ይሄ ነው ። ህውሀት ካልተወገደ አልያም የዘረኝነት ፖሊሲውን እስካልቀየረ ድረስ በመገፋት የሚፈጠረው የጎሰኝነት ስሜት የሚስፋፋ እንጂ ሊጠፋ የሚችል አይደለም ። ይህም የበለጸገች ኢትዮጵያ ከመገንባት ይልቅ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና የተባበረ አቅም በመሸርሸር ወደ ዜሮ የሚወስድ ይሆናል ። ለዚህ ሁሉ አደገኛ ሁኔታ መፈጠር ተጠያቂው ሃገሪቱን በብቸኝነት እየመራ ያለው “ የትግራይ ነጻ አውጪ“ እንጂ ሌላው ሊሆን አይችልም ። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መገለል ምክንያት ኢትዮጵያውነታቸውን ጥያቄ የሚያነሱ ቢኖር ሊገርመን አይገባም ። ጥያቄውን የሚነሱት ሃይሎች አሜሪካ ይኑሩ አውስትራሊያ፥ አውሮፓ ይኑሩ አፍሪካ ፥ ኢስያ ይኑሩ አንታርክቲካ መነሻ ሃቅ አላቸው። ጎንደር ይኑሩ ሐረር፥ አዲስ አበባ ይኑሩ አላባ ፥ ኮፈሌ ይኑሩ ሰላሌ በመገለሉ ምክንያት ቅሬታ የቋጠረ ህዝብ ነው። የሲዳማ ህዝብ “ ኦላን ይዞ “ እንጂ በሎቄ አዋሳ የደረሰበት ጭፍጨፋ ለማኩረፍና ቂም ለማዘል በቂ ነበር ። የጋምቤላው ጭፍጨፋና የመሬት ንጥቂያ “ አገነ ገትያ! አነ ሚዬጎ! “ በሚሉ የፊቅር ቃላት ባይታጀብ ኖሮ የቂም ቋጠሮው ይፈነዳ ነበር ። “ አረጀች እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ፥ ሙሽራ ነሽ ጎንደር ይሰፋል ልብስሽ “ የሚለውን አገላለጥ ኢትዮጵያዊያን በሲቃ እየተያዙ የሚዘፍኑት ባለፉት ወራት ጥይት የተርከፈከፈባቸው ኢትዮጵያውያንን በማስብ ነው ። አዲስ አበባ ቀዳማዊ ሐይለስላሴ ያቆሙለትን ባለ 42 ሜትር ርዝማኔ እና 140 ሺህ ሜትር ስኩየር ስፋት አድባር “ ያምራል” እያለ ማድነቅ ያልቻለው “ በአዱገነት አድባር “ ውስጥ ያለው ዘረኝነት አይኑን ስለደፈነው ነው ። ( ይህን በተመለከተ “ ያምራል “፡ ቴዲ አፍሮና “ የመንዲ አድባር “ በሚል ርእስ ተከታይ መጣጥፍ ለማዘጋጀት እያሰብኩ ነው። )
***
አገራችን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት በግለሰብ ደረጃ ቆራጥ ውሳኔ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በኢትዮጵውያን ዘንድ እየተንጸባረቀ ያለው የለውጥ ፍላጎት ጥልቅ ስሜትና እምነት የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሳል። የኪነ-ጥበብ ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የፖለቲካ ትኩሳትና ቁጭት በሚመጥን መልኩ መንቀሳቀስ ካልቻሉ የህዝቡን መሰረታዊ ድጋፍ ሊያጡ ይችላሉ።ከአሁን በኋላ በግማሽ ጎን የአገዛዙን መድረክ እያደመቁ፣ በግማሽ ጎን “እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ነኝ” እያሉ፥ በሌላ በኩል ፖለቲካ አላውቅም የሚባለው አካሄድ ቢያንስ ከአጭር ጊዜ አኳያ የሚሰራ አይደለም።አይሰራም:: ይህ ማለት ግን ትናንትም ሆነ ዛሬ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለበሰ ቆሻሻ ልብስ ለማጠብ ጊዜው አልፏል ማለት አይደለም። ይልቁንስ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ህዝብ ህልምና ተስፋ በመሰነቅ፣ በኢትዮጵያውያን መሻሻል እንዲጠፋ የሚሞከረውን አንድነትና ፍቅር በመጠበቅ የራስ ሃውልት እንደገና ማቆም የሚቻልበት ሁኔታ የተመቻቸ ይመስላል። ግለሰብ ማንሳት ባይሆንብኝ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ለዚህ አገላለጥ ተስተካካይ ይመስለኛል። እርግጥ አንዳንዶች ራሳቸውን “የይቅርታ ደረጃ መዳቢ የስራ ሂዲት ባለቤት” በማድረግ ቀብተው መቶኛ ሲያወጡ መመልከቱ የሚያስተዛዝብ ቢሆንም የሚያዛልቅ አይደለም። በህዝብ ወገኖች ጫንቃ ላይ ብዙ የመከራ ሸክም እያለና ብስጭት ባለበት ሁኔታ መወቃቀሱ ደግ ላይሆን ይችላል። የግል ዕምነትን አስቀምጦ ለመሄድ ያህል ግን ኢትዮጵያዊነታችን ዋናና ዘላቂ ፈተና፥ ወደፊትም እንደሃገር መኖር አለምኖራችን የሚወሰነው ከተጋረጠብን የዘረኝነትና ቅስም ሰባሪ ድህነት ስንወጣ ብቻ ነው። እነዚን መቀርቀሪያ መቀርቀሪያ የሚያካክሉ አደጋዎች ተሸክመን በእጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ተገቢ አይመስለኝም። ታደለ ሮባ፣ ደረጀ ደገፋ፣ ነዋይ ደበበ፣ ሰለሞን ተካልኝ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ፣ ሰማኸኝ በለው ይቅርታ ጠየቁ አልጠየቁ ኢትዮጵያን ወደመበተን እየመራ ባለው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ የሚጨምሩት፣ ወይም የሚቀንሱት ነገር የለም። በግለሰብ ደረጃ ከታየ ግን ዋነኛ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው የኪነጥበብ ሰዎች ናቸው። ከገዳይና ዘረኛ ጋር ዕቁብ መጠጣት ደም ከመጠጣት የሚተናነስ አይደለም።
***
ቢፈቀድልኝ ቀደም ሲል ወዳነሣሁት እና የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ሊያውቁት ይገባል ወዳልኩት ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ልመልሳችሁ። አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን እንደገለጠው አገራችን ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቃለች። በኢትዮጵያ አየር ላይ ላለፉት ሩብ ክፍለ-ዘመናት ህወሐት የዘራው የዘር ፓለቲካ በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻ፣ አለመተማመንና የጠላትነት መንፈስ እንዲሰርፅ አድርጓል። በህወሐት አገዛዝ በታቀደ መልኩ እየተሰራ ያለው እኩይ ተግባር “ኢትዮጵያዊነት” እንዲደበዝዝና ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ምክንያት ሆኗል ።
ኢትዮጵያዊያንን እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰሩን ማህበራዊ እሴቶች እየጠፉ በመሄዳቸው በፈንታው ቂምና በቀለኝነት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ እየተስፋፋ ያለው የመጠፋፋት መንፈስ ከግለሰብ አልፎ “ኢትዮጵያዊነት” ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ላይ ነው። የህወሓት አገዛዝ እየተከተለ ያለው ቅጥ ያጣ የዘረኝነት ፓለቲካ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያጠለቀው ገመድ የታነቀች ኢትዮጵያን እንድንመለከት እያደረገ ነው። ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት “ደሃ አደግ” በሚለው ቲአትሩ እንደገለጠው የትላንቱ ጅል ጦርነት ዛሬ በዘር ጦርነት ተቀይሯል። ሠሞኑን በታደምኩበት አንድ የህዝብ ስብሠባ ላይ ተሠብሳቢውን ለማነቃነቅ ወደ መድረክ የወጣው ድምፃዊ ሻምበል በላይነህ በዘፈኑ መጀመሪያና ማሳረጊያ ላይ “ኢትዮጵያ በጎሳ ፓለቲካ አደጋ ውስጥ ገብታለች በዘር መደራጀት ቁምጥና ነው!” እያለ ሲያስጠነቅቅ ሠምቻለሁ። በውስጤም “እንደ ሻምበል በላይነህ የኢትዮጵያ ሁኔታ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ለማየት፣ ለመስማት፣ ለመናገር ስንቱ የኪነት ሰው አቅም አግኝቶ ይሆን?” የሚል ጥያቄ አንስቻለሁ።
መጨቅጨቅ አይሁንብኝና እስቲ እናንተ በቃለ መጠይቅ ውስጥ “የህዝብ ነን!” የምትሉ የኪነ-ጥበብ ሠዎች ራሳችሁን ፈትሹ። ከሙያ ባልደረቦቻችሁ ጋር ልብ ለልብ ሃሳብ ተለዋወጡ። አንዱ የጎደለውን አቅምና ወኔ ሌላው የሚሞላበትን መንገድ ፍጠሩ። ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት ተነጋገሩ። በህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ በተግባር ግን ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆኑ የህወሓት አገዛዝ ባለሞሎች ጋር በድብቅ የሚሠሩትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አድርጓል:: አንድ ልትገነዘቡት የሚገባው ነገር መስዋኣትነት የፓለቲከኞች ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ አርቲስቶችም በሞት፣ በእስራት፣ በመንገላታት እና በስደት የሚከፍሉት መስዋእትነት ሊኖር ይገባል። ኢትዮጵያ የታማኝ በየነ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የጅጋየው ሺባባው (ጂጂ) ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የብርሃኑ ተዘራ ብቻ አይደለችም።ኢትዮጵያ የቴዲ አፍሮ ብቻ አይደለችም።ኢትዮጵያ የሻምበል በላይ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የአብነት አጎናፍር ብቻ አይደለችም።
አሁን ያለንበትን የተመሰቃቀለ የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመረዳት፣ በአገሪቱ መጻኢ እጣፋንታ ላይ ያሰፈሰፈውን መአት ለመቋቋምና መፍትሔ ለመስጠት ዘወትር እነ ታማኝ በየነን የመስዋት በግ እያደረግን መቀጠል አንችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ለመቀስቀስ ዘወትር የነፍስ ዕዳ ከእነሱ የምንጠብቀው መቆም አለበት። ዛሬም መስቀል አደባባይ ቆሞ ” ባንዲራችን የአያቶቻቸን የደም ውጤት ነው!” የሚልልን የሺ-ኪነጥበብ ሰው እንፈልጋለን። ዛሬም ህዝቡ የማደኸየቱን፣ አገርን ታሪክ አልባ እያደረጉ ያሉትን፣ አሰቃይቶ መግዛትና ማጋጨት የኩራታቸው ምንጭ ያደረጉትን ዘረኞች “ፌዜራሊዝም” በማለት በመረጃና ማስረጃ ተደግፈው የሚያጋልጡትን ዕልፍ አእዕላፍ ጀግና አርቲስቶች እንፈልጋለን። የ “ወርቅ፣ ብርና ነሃስ ዘር” እንዳለ ለገለጡልን ዘረኞች “የትኛው ዕኩልነት?” ብሎ የሚሟገትና ይህ አካሄድ እንዲበቃ የሚጮሁ መጥምቁ ዮናንሶችን እንሻለን። የሻብዕያ ጫማ ጠርገውና መቀመጫ ልሰው ወደ ስልጣን የመጡትን “ማነው ተላላኪው?” በማለት የሃፍረት ካባቸውን እንዲያጠልቁ የሚያደርጉ አርቲስቶች እንዳለ እንደእንጉዳይ መፍላት ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ስንችል የህወሃት የፕሮፓጋንዳ ማሽን “አኬልዳማ!”፣ “ጀሃዳዊ ሃረካት”፣ አዲስ አበባ እንደባግዳድ” የሚሉ ትያትሮችን ውጤት አልባ እናደርጋቸዋለን። ተደጋግሞ እንደተገለጸው ይሄን ለማድረግ ግን መስዋዕትነት ይጠይቃል። በህዝብ ላይ የሚፈጸምን ግፍ እንደ ራስ ላይ የተፈጸመ አድርጎ በመውሰድ “አናኛቱ” ማለት ያስፈልጋል።
ከዚህ በፊት በተለያዩ መጣጥፎች ደጋግሜ ብዬዋለሁ። አሁንም እደግመዋለሁ። የኢትዮጵያ አርቲስቶች ለአገራቸው እና ለወገናቸው የነበራቸውን (ያላቸውን) ተቆርቋሪነት አሳንሶ የማሳየት ፍላጎት የለኝም። አምባገነን እና ፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝን ለመታገል በስውርና ግላጭ የከፈሉት መስዋእትነት ለደቂቃም ሊዘነጋ አይገባም። እንደውም የሰሞኑን የፖለቲካ ጡዘት በአርቲስቶች ዙሪያ መሆኑን ስመለከት ዛሬም ሆነ ነገ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ወሳኝ የፖለቲካ ሃይል መሆነቸውን ተረድቻለሁ። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ይሄን መጣጥፍ እየከተብኩ እዚህ መስመር ላይ ስደርስ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር የስራ ወንበሬ ላይ ቁጭ ብዬ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ሲጨዋወት እያደመጥኩት ነበር። እኔም መፃፌን አቁሜ የውይይቱ ተካፋይ ሆንኩኝ። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አሻራውን አስቀድሞ ያኖረው ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በቅርብ ቀን በሚያወጣው የግጥም መድብል ውስጥ ያስቀመጠው ማዕከላዊ መልዕክት “ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቃለች፤ አባቶቻችን ኢትዮጵያ ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ ለማቆይት የከፈሉት መስዋዕትነት ዘወትር ሊታወስ ይገባል” የሚል እንደሆነ አጫወተን። እንግዲህ ለደቂቃም ሊዘነጋ አይገባም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። እርግጥም በክፉ ዘመን “ሴጣን ሲዘምር” ፣ “ተኖረና ተሞተ” የሚል ግጥም ወደ አደባባይ ያዋል የኪነ-ጥበብ ሠው መዘንጋት የህሊና ተጠያቂ ያደርጋል። “ የኋላው ከሌለ የፊቱ የለም “ የተባለው በዚህ ምክንያት ነው ።
ከዚህ እውነት ጎን ደግሞ አንድ መዘንጋት የሌለበት ቁምነገር አለ። አገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ማለፍ የማንችላቸውን የህልውና ጥያቄ ከፊታችን አምጥቶ የደነቀረ ብች አይደለም። ኢትዮጵያ የገባችበት ብሔራዊ ውርደት፣ የህዝብ እልቂት እና የተስፋ መጨለም በቁጭትና አጣዳፊነት መፍታት ካልተቻለ የዘር ፍጅት ከፊታችን የተገተረ መራር እውነት እንደሆነ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ይህንን መራር እውነት በቁጭትና እውቀት ተኮር በሆነ መንገድ ለመጋፈጥ መድፈር ያስፈሊጋል። አሁንም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የተነጠፈው መራር እውነታ የሕዝብ ጠላቶች የሆኑት የህወሓት አመራሮችና ጋሻጃግሬዋቻቸው የግፍ ስርቸውን እንዲያቆሙ አልተከላከልንም። በዘር ማበላለጥ ላይ የተሞረከዘ ፓለቲካቸውን አላስጣልናቸውም። ድምፃዊ ኤደን ገ/ስላሴ (የድምፃዊ አብርሃም ገ/ምድህን ባለቤት) የፓሊስ ማርሽ ባንድ አጅቧት የሙዚቃ ሲዲዋን ስታስመርቅ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በጣም ግልጥ ነው። አገዛዙ በሚቆጣጠረው የፕሮፖጋንዳ ማሽን አንድ የትግራይ ተወላጅ አንዲት ነጠላ ሲዲ በ50ሺህ ብር እንደገዛ ሲነገር አሁንም እንዲታወቅላቸው የፈለጉት ነገር እጅግ በጣም ግልጥ ነው። በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ አልፎ በአለም ደረጃ አነጋጋሪ የሆነንና ሪከርድ የሠበረን ድምፃዊ እቤቱ ድረስ መጥቶ ቀረፃ ካካሔዱ በኋላ ማገድ የዘር ፓለቲካው የት ጫፍ እንደደረሠ የሚያመላክት ነው። የፓለቲካ ስልጣኑን ከየትኛው ዘር የፈለቁ ሠዎች እንደተቆጣጠሩትና አድራጊና ፈጣሪው እነማን እንደሆነ የተጋለጠበት ነው።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በመንግስት የፕሮፓጋንዳ ማሽንም ሆነ ብሮድካስቲንግ ፍቃድ ሠጥቶአቸው የሚሰሩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በሙሉ (ኢቢሲ፣ ፋና፣ ኢቢኤስ፣ ዛሚ፣ ሸገር…) የህወሓት ባለስልጣናት ሳይፈቅዱላቸው ቴዲ አፍሮንም ሆነ እንደ አጫሉ ሁንዴሳና ጃንቦ ጆቴን የመሳሰሉ ድምፃውያን ማቅረብ እንደማይችሉ የፀና እምነት አለኝ። የእነዚህ ድምፃውያን መቅረብም ሆነ መቅረት ፓለቲካዊ ነው። እዛው ሳለ የህወሓት መከፋፈልን የሚያሳይ ነው። በተባራሪ እንደሠማሁት ከሆነ የወቅቱን አደጋ መሻገር የሚቻለው “ኢትዮጵያዊ ጭምብል” ካጠለቅን ነው የሚለው የህወሓት ብድን ቴዲ አፍሮን በሚዲያው ላይ በማቅረብ ተቀባይነቱን ከፍ ለማድረግ አስቦ ነበር። ይሄኛው ሀሳብ በገዱ አንዳርጋቸው በሚመራው የብአዴን ክፋይ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበረም ተነግሯል። ባለፉት ወራት የአማራ ራዲዬና ቴሌቪዥን አጼ ቴድሮስን፣ አጼ ሚንሊክን፣ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ ለማሳየት የሄደበት ርቀት የድጋፍ ምልክት ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። በሌላ በኩል ቴዲ አፍሮ መቅረብ የለበትም የሚለው የህወሓት ብድን የወቅቱን አደጋ መሻገሪያው መንገድ የዘር ፓለቲካ አጡዞ ማስቀጠል እንደሆን አምኖ የሚንቀሳቀሰው ነው። ይሄኛው ሀሣብ ኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦህዴድ ክፋይ የሚቀበለው ሲሆን “እኛም አጫሉንን ጃምቦ ጆቴን እንድናቀርብ ይፈቀድልን” የሚል አቤቱታ ያቀረቡ እንደሆን ይነገራል። እንግዲህ በሁለቱ ተቃራኒ አመለካከቶች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም። ቴዲ አፍሮም የለም። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ነው።
አረረም መረረም፣ ተቀበልነውም አልተቀበልነውም ህወሓት በድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን ላይ የፈፀመው አይን ያወጣ ወንጀል ህዝብን ከመናቅ የሚመነጭ ነው። አደባባይ ወጥተን መቃወምም ፤ ደፈር ብሎ ጩኽት ማሰማትም፤ በየልባችን ያለውንም አውጥተን ለመግለጥም ስለምንፈራ እንጂ ሁላችንም በውስጣችን አልቅሰናል። ተናደናል። አንዳንዶቻችን ልጓም የሌለው የስልጣን በቅሎ ላይ ቁጢጥ ያሉትን እየተሳደብን የጾም ሽለላና ቀረርቶ አሠምተናል። ጥቂቶቻችን ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ጆሮ ያልፈጠረባቸውንና አፍንጫቸውን ፎንነው የሚገዙንን ህወሓቶች አደብ እንዲያስገዛልን ፈጣሪያችንን ለምነናል። ሠማይ የወደቀባቸው የመሰላቸውና አንጀታቸው የተኮማተረባቸው ደግሞ በፌስቡካቸው ቀጥታ ስርጭት እየተንዘፈዘፍ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ቅሬታ ቂምን፣ ቂም ደግሞ ህዝባዊ አምፅን ሊወልድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ማልቀስ ብቻ ! መናደድ ብቻ ! ቀራርቶ ብቻ ! መንዘፍዘፍ ብቻ !
በሌላ በኩል “አበስሁ ገበርሁ” በሚያስብል መልሱ የአገዛዙ ባለቤቶች፣ የእልፍኝ አስከልካዮችና በጥላቻ ላይ የተሞረኮዙ የዘውግ ፓለቲከኞች በህወሓቶች እርምጃ ጬቤ ሲረግጡ ለመታዘብ ተችሏል። ሀሣብን በሀሣብ ማሸነፍ ያቃታቸው እነዚህ ድውያኖች የበቀል ጅራፋቸውን ባልተቆጠበና ባልተገራ አንደበታቸው ሲያረግፉት ማየት ያሸማቅቃል። በግልፅ ለመናገር እነዚህ አሳዳጊ የበደላቸው የአገዛዙ ግልገል ማጋጣዎች የሚናገሩትንና የሚፅፉተን መመልከት ሠው መሆናቸውን ያጠራጥራል። የስነ-ህይወት ጠበብቶች ሰው እንደ ሰውና እንደ ሰው ባህርይ መኖር ካልቻለ እንደ እንሰሳ ይቆጠራል። እነዚህ ልባቸው ከድንጋይ የጠጠረ እንስሳዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አይናችሁ ላፈር ብሏቸው እንኳን ከኣኩይ ድርጊታቸው መቆጠብ አልቻሉም። እርግጥ ይህን ፀሐይ የሞቀው ሚስጥራቸውን ሕዝቡ ይበልጥ እየትረዳው በመምጣቱ በፍርሃት ተወጥረዋል። የሚሰነዝሩት ብትረ የፈሪ ዱላ ሆኗል። የፈሪ ዱላ ደግሞ ቦታ አይመርጥም። ይሄ ብቻ አይደለም ። “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንደሚባለው በፈሪነታቸው ላይ ድንጉጥንት ስለታከለበት ሁሉንም ሠው በጠላትነት የመፈረጅ ህመም ተጠናውቶአቸውል። በዚህ ምክንያት ያገኙትን ሁሉ ለመጥረግ ይፈልጋሉ።
አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን ላይ ህወሓቶች የወሰዱት እርምጃ ስሩ የሚመዘዘው ከዚህ መሰረታዊ ባህሪያቸው ነው። ህወሓቶች ፈሪዎች ናቸው። ህወሓቶች ድንጉጦች ናቸው። ለህወሓቶች ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላታቸው ነው። ሌላው ቀርቶ እነሱ የፈለቁበት የትግራይ ህዝብ ለቀናቶች ፊቱን ቢያዞርባቸው አፈሙዛቸውን በማዞር ጥይታቸውን ያርከፈክፉበታል። ባለፉት ወራት በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታና የአመራር ለውጥ ፍላጎት ያላስተናገዱበት መንገድ ከላይ የቀረበውን አባባል ትክክለኛንት የሚያረጋግጥ ነው። ተጋዳሊት ፈትለወርቅ ገ/እግዜብሔር (ሞንጆሪኖ) እና የክልሉ ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱ እንዴት የለውጥ ጥያቄ ይነሳል በሚል በቁጣና በምሬት እርምጃ መውሰዳቸውን በግላጭ ሰምተናል። የትግራይ ህዝብን አቅጣጫ ልማስቀየር የስፖርት ውድድርን ተገን አድርገው አማራና ትግሬውን እርስ በራስ ለማጨፋጨፍ የጎነጎኑት ሴራ መጋለጡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከአካላቸው ላይ መጥፋት ያልቻለውን ሰምበር ለመሸፈን ያደረጉት እኩይ ተግባር ነው ።
ነገ ከነገ ወዲያ የትግራይ ህዝብ ካንቀላፋበት ሲነቃና ወደ ውስጡ መመልከት ሲጀምር በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተነሳውን የለውጥ ንፋስ መከላከል ሳይሆን የለውጥ አካል ይሆናል። የትግራይ ህዝብ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን እየተገለለ ያለው የስጋና ደም ልጆቹ በፈጠሩት አፓርታይድ መሠል ፓሊሲ መሆኑን መገንዘብ ሲጀምር መራራውን ትግል ልጆቹ ላይ ማንጣጠሩ አይቀርም። በትግራይ ተወላጆች አዛዝነት የሚመራው ሠራዊት በሕዝቡ ላይ መተኮሱን አቁሞ ጠመንጃውን ወደእነሱ ማዞር የሚጀምርበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። እርግጥ ከአጭር ጊዜ አኳይ አብዛኛው የስርአት ለውጥ ፈላጊ የሆነው ኢትዮጵያዊ ከላይ በቀረበው ሃሣብ እንደማይስማማ ይረዳኛል። ይሁን እንጂ በለውጥ አመራር ሳይንስ ውስጥ እንደተገለፀው የለውጥ ንፋስ አቅጣጫ ካልተጠበቀ ቦታ ሊነሳ ይችላል። ምንአልባትም ከአባይ ወልዱ መኖሪያ ቤት፣ ምንአልባት ከሳሞራ የኑስ እቁባቶች ቤት ፥ ምንአልባትም ከአዜብ መስፍን ቤተሠቦች ቤት። ማን ያውቃል?

Filed in: Amharic