>
9:17 am - Saturday February 4, 2023

ኢትዮጵያና ተቃዋሚዎች ባለፉት 26 ዓመታት (ዮናስ ሀጎስ)

the-most-important-question-markየኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ላይ ከተቀመጠበት ከባለፉት 26 ዓመታት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓይነት የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝቦችንና ተቃዋሚዎችን አስተናግዳለች። እነዚህ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችና ተቃዋሚዎቹ በየወቅቱ ይለዋወጡ እንጂ አንድ ግን በፍፁም የማይለወጥ ነገር ቢኖር የተቃውሞው ስትራቴጂ ነው። ይህንን መንግስት እድሜውን እያራዘሙለት ካሉ ነገሮች በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለውም ይሄው ከዓመት እስከ ዓመት የማይለወጥ የተቃውሞ ስትራቴጂ ነው።
•°•
የተቃዋሚ ሐይሎቻችን የተጠና የረዥም ጊዜ እቅድ ያለው እና ይህን መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሰናበት የሚችል የተቃውሞ ስትራቴጂ ይዘው ለመምጣት እስካሁን አስበውበት የሚያውቁ አይመስለኝም። ሁል ጊዜም ቢሆን የምናያቸው የተቃውሞ ትዕይንቶች መነሻቸው አንድ specific ጉዳይ ላይ ብቻ ይሆንና መጨረሻቸው ሳያምር ከስመው ይቀራሉ።
•°•
ምሳሌዎችን እንይ…

የ1997 ተቃውሞ «ድምፄን ተነጠቅኩ» በሚል የተነሳ የተጀመረ ተቃውሞ ነው። ይህ የተቃውሞ ትዕይንት በሐገሪቷ መዲና እንደመነሳቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከዛሬ ከተደረጉ የተቃውሞ ትዕይንቶች መንግስትን ለማስወገድ ተስፋ የነበረው ብቸኛ የተቃውሞ ትዕይንት ነው ቢባል ማጋነን አያስፈልገውም። ተቃውሞው ላይሳካ የቻለበት ምክንያት ሲታይ እንደ የመንግስት ያልተጠበቀ ኃይል የበዛበት ምላሽና ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች ክልሎች አለመዛመቱ ነው። (ሌሎች ክልሎች ድምፃቸውን አልተነጠቁ ይሆን?) ይህ ተቃውሞ ከእስከዛሬዎቹ በተሻለ ሁኔታ የተደራጀ ቢመስልም ቅሉ ዳር ሳይዘልቅ ሊከስም በቅቷል።

• ከዚያ ወዲህ በአማራ «ወልቃይት»ን በኦሮሞ «ማስተር ፕላን»ን ይዘው የተነሱ ተቃውሞዎችን አይተናል። ሁለቱም ተቃውሞዎች ከላይ እንደተገለፀው በጣም specific አጀንዳ ላይ በማተኮራቸው መሳተፍ የሚችለውን ሕዝብ ውሱን አድርጎታል። መንግስት ይበረታብኛል ብሎ ላሰበው የማስተር ፕላን ጥያቄ የተፈለገውን ምላሽ ሰጥቶ ተቃውሞውን ሲያዳፍነው በወልቃይት ዙሪያ የተነሳውን አመፅ በኃይል መቆጣጠር እችላለሁ ብሎ በማመንም ይሁን የተፈለገውን መልስ ብሰጥ ጥቅም አላገኝም ብሎ በማሰብ… ብቻ የወልቃይት ነገር ዛሬም እንደተንጠለጠለ ነው።
• ዛሬ ደግሞ «ግብር» ተኮር የሆኑ ተቃውሞዎች እየተቀጣጠሉ እንደሆነ እየሰማን ነው። በየቦታው «አምቦ!» «ጊንጪ ወንዳታ!» የሚሉ መፈክሮችን እያየን ነው። ነገር ግን ምን ያህል ከበፊት ዓመፆቻችንና የተቃውሞ ስትራቴጂዎቻችን ትምህርት ወስደናል የሚለውን ማንም ዞር ብሎ ሊያጤን አይፈልግም።
•°•
በ1960ዎቹ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ዓመፅ ዋንኛ ጥያቄው አንድና አንድ ብቻ ነበረ። «ንጉሱ ከስልጣን ይውረዱ!» ደርግ በመሐል ገብቶ ተቃውሞውን ሐይጃክ ባያደርገው ኖሮ የተማሪዎቹ ጥያቄ ግቡን መምታቱ አይቀርም ነበረ። ተማሪዎቹ በተለያየ ማባበያ ሊሸወዱ አልቻሉም። (ጉልቻ ቢቀያየር…ን ያስታውሷል) የነበራቸው ዓላማ አንድና አንድ በመሆኑ እስከ ፍፃሜው ድረስ በፅናት በመታገላቸው ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል። የስድሳዎቹ ትውልድ የሚደነቅበት አንደኛው ምክንያት ይሄ ነው። ዛሬ በ«ምንትሴ ሪቮልዩሽን»፣ በ«ግብር ምህረት»፣ በ«ወጣቶች ስራ ፈጠራ» ተረት ተረት በቀላሉ መብቱን ለማስከበር ከወጣበት አደባባይ ወደ ቤቱ የሚመለሰው ትውልድን ስናይ የተቃዋሚ ኃይሎች የተቃውሞ ስትራቴጂያቸው ላይ ምን ያህል ደካማ እንደሆኑና ከዚህ በላይም እንደሚጠበቅባቸው ጥሩ አመላካች ነው።
•°•
ዛሬ ግብር ስለተጨመረበት አደባባይ የወጣው ነጋዴ ግብሩ ሲስተካከል ወደ ቤቱ ይሄዳል! ዛሬ በተቃውሞ አደባባዩን የሚሞላ ታክሲ ሹፌር ሂሳቡ ሲስተካከል ነገ ቀጥ ብሎ ወደ ስራው ይመለሳል። ስራ አጣሁ ብሎ ለአደባባይ የወጣ ወጣት አስር ቢልዮን ብር ሐገራዊ በጀት መድበንልሃል ሲባል እሱን ተስፋ አድርጎ በነጋታው ቀበሌ ተሰልፎ ሊያስገርመን ሁላ ይችላል።
•°•
ይህቺን ሐገር የሚያስፈልጋት ጥቃቅን የማስተካከያ እርምጃዎች ሳይሆን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው። ኢህአዴግ እንደሆነ ልክ ቴርሞ ሜትር እንደያዘ ሰው አንዴ እዛ ጋር ለኮስ ያደርግና በጣም ጋል ሲል ውኃ ቸልሶ ደግሞ ሌላውን ለመለኮስ ይሄዳል እንጂ ስር ነቀል ተሐድሶ እንደማያደርግ ራሳቸውም የሚደብቁት ነገር አይደለም። ትንሽ ኮሽ ብሎ እሱን የማረጋጋት ስራ ለመስራት ሲራወጥ «አይ ወያኔ አብቅቶለታል!» «ከዚህን ዓመት አያልፍም!» «ወያኔዎች ተርበድብደዋል!» በሚል ቀቢፀ ተስፋ ራሱን የሚያጃጅል ተቃዋሚ ለኔ ልክ እንደዛች ቀበሮ ነው። «የበሬ ቆለጥ ይወድቅልኛል ብላ ከኋላው ስትከተለው ዋለች» የተባለላት ቀበሮ።
•°•
ከዚያም ከዚህም ወያኔ የሚለኳኩሳቸውን አነስተኛ እሳቶች እየተከተሉ ማራገብ ወያኔን መቼም አይጥለውም። በኔ በኩል «አምቦ ቁጣው በርትቷል! ሕዝቡ ተነስቷል…!» ምናምን ዓይነት ፖስቶችን ከማየት የበለጠ በተቃዋሚው ተስፋ የሚያስቆርጠኝ ነገር የለም። አምቦ የተነሳው ግብር በዝቶበት ከሆነ ግብሩ ሲስተካከል ተመልሶ ወደ ቤቱ ይገባና it will be business as usual። የዛኔ ኋላ ኋላ እየተከተለ ሲያራግብ የነበረው ተቃዋሚ በሐፍረት አንገቱን አቀርቅሮ ይቀራል። ልክ ኦሮሞ ፕሮቴስት ብለን አንድ ሰሞን ስክሪናችን እስኪግል ፖስተን ጩኸን እጃችንን አጣምረን ፎቶ ተነስተን አብሮነታችንን ለመግለፅ መከራችንን በልተን ካበቃን በኋላ ኦሮሞ ፕሮቴስት ወደ ኦሮሞ ሪቮልዩሽን ተቀይሮ እጃችን በሐፍረት ከሰቀልንበት እንዳወረድነው ማለት ነው። (ለነገሩ የዛኔዎቹ ኦሮሞ ሪቮልዩሽን ዋና አቀንቃኞች ሳይቀሩ ዛሬ ከወሬና የመሰረተ ድንጋይ ክምር ውጭ ወፍ እንደሌለ ቀስ በቀስ እየተገለጠላቸው ቢሆንም ቅሉ)
•°•
ለማጠቃለል ያህል የተቃዋሚው ሐይል ስርዓቱን መቀየር ግቡ ያደረገ ጥሩ ስትራቴጂ መንደፍ ይጠበቅበታል እላለሁ። አርቲስት ቦይኮት ማድረግ፣ በየውጭ ሐገራት የሚሄዱን ባለስልጣናት እግር በእግር እየተከታተሉ ልክ ልካቸውን መንገር፣ በተለያዩ ሐገራት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጉባዔዎችን ማዘጋጀትና መምከር፣ ሐገር ቤት የሚነሱ ትኩሳቶችን ሙቀት እንደ ኢህአዴግ እየለኩ እንዲተሳሰሩና ወደ ሐገራዊ ትዕይንት እንዲያድጉ ማድረግ… እነዚህ ሁሉ ወደ ግቡ የሚወስዱን አጫጭር ክዋኔዎች መሆን ሲገባቸው አሁን የምናየው ለተቃዋሚው ሐይል እነዚህ ክዋኔዎች በራሳቸው እንደ ግብ ተይዘው ፕላን ተደርገው እየተሰራባቸው መሆኑን ነው። ዋናውን ግብ ትተን በአጫጭር ክዋኔዎች ላይ ከልክ በላይ የሆነ ጊዜ በማጥፋት ለግባችንም ካለመብቃታችን ሌላ በየቀኑ የኢህአዴግን መሰረት እያጠናከርነው እንደምንሄድ ማወቅ አለብን።
•°•
ማስታወሻ፦ ኢህአዴግ ስልጣኑን ቢተው ሐገሪቷ የመበታተን ስጋት ይኖርባታል ወይ? በኔ ግምት ይህ ነገር 50 በ 50 ነው። እዚህ ዓይነት ግምት ላይ ለመድረሴ የተቃዋሚው በየፊናው ለመፈንጨት መሞከር ወሳኝነት አለው ብዬ አምናለሁ። በዚህ አንድ ሰበብ ብቻ ኢህአዴግን እየጠሉ ግን ሐገሪቷ እንዳትበታተን በመስጋት ለኢህአዴግ የይምሰል ድጋፍ እየሰጡ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አምናለሁ። (ካላመናችሁ የበፍቃዱ ዘ ሐይሉን ገፅ ጎብኙና ከአስሩ ጥያቄዎች በተለይ በዚህ ጥያቄ ላይ አብዛኞቹ የሰጡትን ምላሽ እዩ) ተቃዋሚው አንድ መሆንና አንድ ዓይነት ግብ መያዝ እስካልቻለ ድረስ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን መተማመኛ ድምፅ ማግኘትና ኢህአዴግን መተካት አይቻለውም።
Filed in: Amharic