>

ከባዶ ጣሳ ወደ ተቀደደ ጣሳ – አዲስ አበባ ወደ ፊንፊኔ! (ታሪኩ አባዳማ)

የብሔር/ብሔረሰቦች መብት ይከበር ብሎ የተነሳው ኮምኒስታዊ የተማሪ እንቅስቃሴ በትግራይ በኩል ብሔረሰባዊ የትጥቅ ትግሉን በተሳካ ሁኔታ ካገባደደ በሁዋላ መንደሮችንና ከተሞችን ሳይቀር በዘር ግንድ ላይ በተሰመረ ድንበር ክልል (አጥር) ገድቦ አገሪቱን ወዳልታወቀ ጥፋት አቅጣጫ ይዟት መጓዙን ቀጥሏል። ለወያኔ ሹማምንት እና የጎጥ ካድሬዎች የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መረጋገጥ እና የህግ በላይነት ሳይሆን የትኛው ብሔረሰብ በየትኛው ‘ክልል’ የበላይ እና የበታች ይሆናል የሚለው ጉዳይ ሆኗል።Ethiopia, Addis Ababa

ዜጎች ዘራቸውን ሳይሆን ዜግነት በሚፈቅደው ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው አገራቸውን ብለው ከትውልድ ትውልድ በቆዩበት ፣ ወልደው ስመው ፣ ድረው ኩለው ፣ አሳድገው ለወግ አብቅተው ባረጁበት ስፍራ ሁሉ ማን አለቃ ማን ምንዝር ፣ ማን ከንቲባ ማን ግብር ከፋይ ፣ ማን መጤ ማን ባላገር ፣ ማን ልዩ ተጠቃሚ ማን ተርታ መንገደኛ… ምን ቀረ? ማን ወርቅ ማን መዳብ እንደሆነ ዘር ላይ የተመረኮዘ ድልድል ቀርቦ ሁሉም በጎጥ መስፈርት እንዲለካ እንዲመዘን ሆኗል። ከህወሀት የፖለቲካ ፕሮግራም ጋር የተዳቀለው የወያኔ ህገ መንግስት ይህ እንዲሆን ግድ ብሏል።

ይህን የምለው አዲስ አበባ የማን ናት ብለው ከፊሉ የዘር ሀረግ እየቆጠሩ ሌሎቹ ጥንታዊ አድባራት ስም እየጠሩ ከሚሟገቱት ካንዳቸውም ጋራ የማልስማማ መሆኔን ለማመልከት ነው። አዲስ አበባ የራሷ የበቃ ታሪክ ያላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የክፉም የደጉም ቀን መናኸሪያ ናት።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊነት ነው። ወያኔ ከምርጫ 97 አንስቶ በተቀነባበረ ስልት በከተማይቱ የሚያራምደው ፖሊሲ ያንን ኢትዮጵያዊነት ማኮላሸት ነው። ነዋሪዎች በልማት ስም ተፈናቅለዋል ፤ ለብዙ አሰርት አመታት በእድሩም በደጀ ሰላሙም ተቀራርበው የገነቡት መተሳሰር ተበጣጥሷል ፣ ወላጆች ሲፈናቀሉ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል ፤ አዛውንት እና አቅመ ደካሞች ጠዋሪ እና ሲታመሙ ጠያቂ እንዲያጡ ተበይኖባቸዋል። ዛሬ ደግሞ እስከናካቴው አዲስ አበባ የሚባል ከተማ የለም ተብለዋል።

አዲስ አበባ ፊንፊኔ ትሆናለች ምክንያቱም ቁምነገሩ ነዋሪዋ ማን ነበር አሁንስ ማን ነው የሚለው ሳይሆን አቀማመጧ የኦሮሞ ህዝብ ዙርያውን ከቦ መኖሩ ግምት ውስጥ መግባቱ ነው። ይህን መሰረት ያደረገ አዲስ አዋጅ ተረቆ በሚንስትሮች ፀድቆ ጨዋታው ወደ ወያኔ 99% ፓርላማ ሜዳ ተልኳል… ሰነድ የጨበጠ ወይንም በአፈ ታሪክ እንኳ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ ኖሮ ባያውቅም አዋጁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ‘መጤ’ የሚባሉ ዜጎችን ለይቶ አድሏዊ ስርዓት ለማስፈን መወጠኑን ያረጋግጣል።

ትንሽ ስለ ‘ፊንፊኔ’

እኔ እሰከማውቀው ድረስ የኦሮሞ ህዝብ አዲስ አበባን ፊንፊኔ በሚል መጠሪያ አያውቃትም። እንደ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ኢትዮጵያዊ መናገር የምችለው ፊንፊኔ የሚባል አጠራር የሰማሁት ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ወዲህ ነው። በማጠያየቅ እንደተገነዘብኩት ደግሞ ይህን ስያሜ ለከተማይቱ ያወጡት እነ ሌንጮ ለታ የኦነግን ፕሮግራም ሲቀርፁ በነበረበት ሰነድ ነው። እነኝህ ሰዎች ከወለጋ ቄለም እና ደምቢዶሎ መጥተው አዲስ አበባን ፊንፊኔ ናት ሲሉ ምን ታሪካዊ መሰረት ይዘው እንደሆነ የሚነግረኝ አላገኘሁም። ይሁንና ላንድ አፍታ ወጣ ብለው እኔ የተወለድኩበትን አካባቢ ህዝብ ቢያነጋግሩ ኖሮ ፣ እውን ለኦሮሞ ለህዝብ ታሪክ እና ባህል አክብሮት ቢሰጡ ኖሮ ምናልባት እንደ ወትሮው ‘ሸገር’ ይሏት ነበር። የሸዋ ኦሮሞ በራሱ ቋንቋ ሀሳብ ሲለዋወጥ አዲስ አበባን ሸገር ይላታል። የሚያወራው በአማርኛ ሲያነሳት ግን ያው አዲስ አበባ ይላታል።

አፌን በፈታሁበት እና የእረኝነት እድሜዬን ባገባደዱኩበት ጅባትና ሜጫ ፣ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የኖርኩበት ጨቦ ፣ በቾ እና አመያ ፣ አጠቃላይ የምእራብ ሸዋ ኦሮሞ ህዝብ በራሱ ቋንቋ አዲስ አበባን ‘ሸገር’ እያለ ሲጠራት መቆየቱን የሚያስተባብል የለም። ወግ ያለው ጥናት ቢደረግ የዚህ አጠራር መሰረት ምን እንደሆነ ማውቅ የሚቻል ይመስለኛል። ዛሬ ድረስ ብዙ ያራዳ ልጆች ጭምር አዲስ አበባን ሲያቆላምጧት ሸገር ማለታቸው አለምክንያት አይደለም። አጠራሩ ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኑ የተወረሰ መሆኑም አይጠፋውም። ይኼ እንግዲህ የህዝብን ባህላዊ እና ታሪካዊ መስተጋብር የሚያንፀባርቅ አሻራ ነው – የህዝብ መፈቃቀር። ይህም ሆኖ የአዲስ አበባን ታሪካዊ መሰረት የጨበጠ ስም መቀየር የሚያስፈልግበት አንዳችም ሰበብ የለም።

እጅግ ሁዋላ ቀር መገናኛ ተንሰራፍቶ በቆየባት አገራችን እያንዳንዱ መንደር ወይንም ቀዬ ፣ አካባቢ እና ሰፈር እዚያው ነዋሪ በሆነው ህዝብ ትርጉም ሊስጠው በሚችል መልኩ ስም ሲወጣ ቆይቷል። ይኼ እኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር በኖረባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚደረግ ነው። መንደሮች ወይንም አካባቢዎች ስም የሚወጣላቸው በጭፍን ወይንም የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ በፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አልነበረም። ለአካባቢው ነዋሪ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ስያሜ ይወጣል። አባ ጅፋር ወልቂጤ የሚል ስም ሲያወጡ ያካባቢውን ገበሬ ማማከር አላስፈለጋቸውም።

አዲስ አበባ የተቆረቆረችው ደግሞ በዘመኑ አገር እና ህዝብ የማሳደር ሀላፊነት ትከሻቸው ላይ በወደቀ የራሷ ዜጎች ነው። ያኔ አዲስ አበባ የሚለው ስያሜ ይበልጥ ትርጉም ይሰጥ የነበረው ለነዋሪው እና አከባቢው በቅርብ ርቀት ላለው ህዝብ ነበር ማለት ይቻላል።

ሐረር ወይንም ደምቢዶሎ የሚኖር ኦሮሞ በዚያን ዘመን ስለ አዲስ አበባ ታሪካዊ ስፍራ የሚያውቀው ወይንም እንዲያውቅ የሚጋብዘው ምክንያት አልነበረም። መቀሌ እና ሽሬ የሚኖር ትግሬ ፣ ጎጃም እና ጎንደር ነዋሪ የሆነ አማራ ምናልባትም እድሜውን ሙሉ ያችን አዲስ አበባን ላይጎበኛት ይችላል። ዘመን ሲለወጥ እና የመገናኛ አገልግሎቱ ፣ የልማት አውታሩ እየሰፋ ሲሄድ ዩንቨርሲቲ ለመማር አለበለዚያም ዘመድ ለመጠየቅ ወይንም ስራ ፍለጋ… ምናልባት ይጎበኛት ይሆናል። ለሱ አዲስ አበባ ማለፊያ ማግደሚያ ደማቅ ያገሬ ርዕሰ ከተማ እንጂ ሌላ አልነበረችም። ሲመጣ ተቀብላ ታስተናግደዋለች ፣ ሲሄድ የማይረሳ ትዝታ አስታቅፋ ትሸኘዋለች።

በመሰረቱ ዛሬ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት የጎጥ ጦር አበጋዞች አዲስ አበባን የሚያውቋት ቁምጣ እና ሸበጥ ታጥቀው በወረሯት ጊዜ ነበር። ስለ ነዋሪዋ መስተጋብር ፣ ስለ ህዝቡ አኗኗር ፣ ስነልቡና እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር ፀንቶ ስለቆየው ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ግንዛቤ ዚሮ ነበር ማለት ይቻላል። በምርጫ 97 ወቅት የደረሰባቸውን ሽንፈት አስተውሎ መሪያቸው “አዲስ አበባ ውስጥ የዘር ፖለቲካ አይሰራም” ወደሚል ድምዳሜ መድረሱንና ካድሬዎቹ አደረጃጀት ስልት በመቀየር የወጣት ፣ የሴት ሊግ እያሉ እንዲያሰባስቡ ቀጭን መመሪያ መስጠቱ ያስታውሷል። ወቅቱ አዲስ አበባ ለጎጥ ፖሊቲካ አልመችም ብላ ድምፁዋን ከፍ አድርጋ ያስተጋባችብት አጋጣሚ ነበር።

በመሆኑም አዲስ አበባ ስለ ስሟ ማንነት ቆርቁሮት ፣ እንደ ችግር ተቆጥሮ ጥያቄ ያቀረበ ወገን እንዳለ ተሰምቶም አያውቅም። ዛሬ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ፋይዳ ያለው ጠቀሜታ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ብትሆንም አገሪቱ የምትመራው ደግሞ በዘር ማንነት ላይ በተደራጁ የጦር አበጋዞች ስለሆነ ዘረኛ ልዩ ጥቅም ፣ ልዩ መብት የሚባል ፈሊጥ ተቀስቅሶ ከተማይቱ ላይ ተዘምቷል። ገበያ ፣ ገንዘብ እና ስልጣን ያሰከራቸው የጎጥ ጦር አበጋዞች ለስልጣናቸው ዕድሜ ማርዘሚያ ሌላ የዘር መስፈርት እያዘጋጁላት ነው።

መሰረታዊ ሰብአዊ መብቱን በታጠቀ ወራሪ ጦር የጨፈለቁትን ህዝብ ዛሬ ልዩ መብት ልናጎናፅፍህ ነው የሚል አዋጅ ያስነግራሉ።

አዲስ አበባ ዘር አላት?

አባ ጅፋር ከጂማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ እርፍት አዳር የሚያደርጉባትን መንደር ‘ወልቂጤ’ ብለው ሰይመዋል። ትርጉሙ ‘እኩል በኩል’ ማለት ሲሆን ይኸውም ያች መንደር በጅማ እና አዲስ አበባ መካከል እኩል ርቀት ላይ መሆኗን ለማመልከት እንደነበር

Filed in: Amharic