>

ግብር በአምባገነን አገዛዝ (ታደሰ ብሩ ከርሴሞ)

fb_img_1501480100748ስለ አምባገነን አገዛዝና ግብር ሲነሳ መጥቀስ የምወደው የእውቁ ኢኮኖክስ ማንኩር ኦልሰን Dictatorship, Democracy, and Development ነው። ከዚህ ጽሁፍ በዛ አድርጌ ልጥቀስ።
ዘላን ወንበዴዎች /roving bandits/ ነጥቀው ይሮጣሉ፤ መቼ እንደሚመለሱ አይታወቅም። እነዚህ ወንበዴዎች ነጥቀው በሮጡ ቁጥር የማኅበረሰቡ ሀብት የማፍራት ፍላጎት ስለሚዳከም በሚቀጥለው ዙር የሚዘርፉት ነገር እያነሰባቸው ይመጣል። ቀን ባለፈ መጠን ነጥቆ መሮጥ ራሳቸውን እንደሚጎዳቸው ይገነዘቡና ከተዘዋዋሪ ወንበዴነት ወደ ቋሚ ወንበዴነት /stationary bandit/ ይቀየራሉ። ለንጥቂያቸውም ሥርዓትና ልክ ያበጁለታል፤ ስሙን “ግብር” ይሉታል። ማኅበረሰቡንም፣ ራሳቸውንም ከሌሎች ተዘዋዋሪ ወንበዴዎች ይከላከላሉ። ይህ ሥርዓት ከሥርዓተ አልበኝነት የተሻለ፣ የቅሚያውም መጠንም አስቀድሞ የሚታወቅ ከመሆኑ ጋር ማኅበረሰቡ ለሚከፍለው ተመጣጣኝ ባይሆንም የሚያገኘው ጥቅም (ሰላምና ሌሎችም ማኅበራዊ ምርቶች) ስላሉ ምርት ይጨምራል፣ ዕድገትም ይኖራል።

ይሁን እንጂ አምባገነን ሰፋሪዎች በተደላደሉ መጠን ፍጆታቸው እየናረ መሄዱ ፈጽሞ የማይቀር ነው። ለጦር ሠራዊቱ፣ ለቤተመንግሥቱ፣ ለማሰልጠኛው፣ ለመታሰቢያ ሀውልቶች ግንባታ፣ ለአዳራሾች ግንባታ፣ ለአምባገነኖች፣ ለተከታዮቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የክብር ልብሶችና ጌጣጌጦች፣ “ለመጠባበቂያ“፣ ….. የሚያስፈልገው ወጪ በጨመረ ቁጥር ሕዝቡ በግብር አሊያም በሌላ መንገድ እንዲከፍል ስለሚገደድ ሥርዓት በመስፈኑ ምክንያት አንሰራርቶ የነበረው የሥራ ፍላጎት እንደገና ያሽቆለቁላል። የሰፋሪ ወንበዴዎችን የሀብት ማጋበስ፣ ምቾትና እዩልኝ ፍላጎቶችን ማርካት አይቻልም።

በማንኩር ኦልሰን ላይ የምጨምረው የለኝም፤ ሁሉንም ብሎታል። ሙሉውን ማንበብ ለምትፈልጉ የመጣጥፉን ጠቋሚ አያይዣለሁ።

ወንበዴዎች ሕዝብን ለማስገበር ሁለት ነገሮች ያስፈልጓቸዋል። አንዱ ጉልበት ነው። ሞኝ ሽፍታ ዘርፎ ይሮጣል፤ ብልጣብልጥ ሽፍታ ደግሞ ቁጭ ብሎ መዝረፍ ያምረዋል። ብልጣ ብልጥ ሽፍታ ራሱን በመንግሥትነት ሰይሞ ለዘረፋው “የመንግሥት ግብር “ የሚል ስያሜ ሰጥቶ ተዘራፊን አሰልፎ ደረሰኝ እየሰጠ ይዘርፋል።

ቁጭ ብሎ ደረሰኝ እየሰጡ ለመዝረፍ ግን ከጉልበት በተጨማሪ ለዘረፋ ሰበብ የሚሆኑ ማኅበራዊ ምርቶች (public goods) ማምረት ያስፈልጋል። ካድሬዎች ሕዝቡን “ግብር የምትከፍለው ለመንገድ፣ ለጤና አገልግሎት፣ ለትምህርት …” ብለው መቀስቀስ አለባቸው። ግብር ግዴታ መሆኑ ቢታወቅም ምክንያታዊ እንደሆነ ማብራራት መቻል አለባቸው። በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ከተሰበሰበው ግብር ምን ያህሉ ወደ ማኅበራዊ ምርት፤ ምን ያህሉ ደግሞ ወደ ባለሥልጣናቱ ኪስ እንደሄደ የሚጠይቅ የለም። መንገዱም ሆነ ሕንፃው ቢሰራ ለማን፣ ለምን ብሎ የሚሞግት የለም። ሕዝቡ አምፆ እስካላስቀረው ድረስ ደረሰኝ እየተቀበለ ይዘረፋል።

በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ይህ ነው። የህወሓት ሠፋሪ ወንበዴዎች በግብር ስም እያስራቆቱን ነው። ህወሓት የዘረጋው የግብር ሥርዓት ወንበዴው ቁጭ ብሎ ለፍቶ አዳሪውን የሚመጥበት፤ ድሀው ሀብታሙን የሚደጉምበት ነው። እንዲህ እንዳሁኑ አንዳንዴ የሙስና ዜና ሲኖር ነው በግብር የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደተከማቸ በወሬ ወሬ የምንሰማው።

ሌላም ላነሳው የምሻ ጉዳይ አለ: “ግንዛቤ ማስጨበጥ” የሚሉት።

አገራችን ውስጥ የወር ደመወዝ ተከፋይ ምንም ከግብር ማምለጫ ቀዳዳ የሌለው በመሆኑ ከሁሉ በላይ ተበዳይ እንደሆነ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መጠነኛ እውቀት ያለው ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው። የግብር ዕዳን ለማስተካከል ሲባል “ነጋዴ ላይ ግብር መጫን የወር ደመወዝተኛው ኑሮ ያሻሽላል” የሚል “ግንዛቤ ማስጨበጥ” “እኔ ብጎዳም ያንተ ከኔ ይበልጥ መሰቃየት ያስደስተኛል” ዓይነት ሰይጣናዊ አመክኖ ነው። በነጋዴ ላይ የሚጫን ግብር ውሎ አድሮ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ሸቀጦች ዋጋ መተላለፉ አይቀርም። ይህንን ሽግግር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አያስቀረውም። እናም የወር ደመወዝ ተከፋዩ የሚጠቀመው በለፍቶ አዳሪው ላይ የግብር ዕዳ በመጫኑ አይደለም። የወር ደመወዝተኛው የሚጠቀመው በለፍቶ አዳሪው ብቻ ሳይሆን በሱም ላይ የተጫነው የግብር ዕዳ ሲቀንስ ነው።

ላጠቃለው።

ወገኞቼ፤ ለህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ግብር አልከፍልም ማለት ተገቢ ነው። ለአንባገነን ሥርዓት አልገብርም ማለት ከሥነ ምግባር አንፃር ተቀባይነት ያለው የጽድቅ ሥራ ነው። ለህወሓት አንገብርም ማለት የሚኖርባቸው ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

Filed in: Amharic