>
4:53 pm - Sunday May 25, 1727

"በርባንን ፍታልን!" (አንዷለም ቡከቶ)

የብአዴኑ ሰው በቲቪ ብቅ ብለው ከዚህ በኋላ ቆሮሶ እንጂ አምባዛ እንደማንበላ ቁርጣችንን ነግረውናል፡፡ለትላልቆቹ አሳዎች ያለሃሳብ እንዲዋኙ  የማረጋገጫ መግለጫ ሰጥተው” ምድረ የውሃ እናት ግን ወዮልሽ!” በማለት ዝተዋል፡፡አያይዘውም በሀገሪቱ ትልቁ ፓወር ያለው በዳይሬክተሮች እጅ እንጂ ሚኒስትሮችማ እዚህ ጋር ፈርሙ ሲሏቸው ዝም ብለው የሚለቀልቁ ተራ የፖለቲካ ተሿሚ እንከፎች እንደሆኑ በመግለጽ አበሻ “ሚኒስቴር ካልተያዘ ምኑን የጸረ ሙስና ዘመቻ ሆነ!?” እያለ ማላዘኑን እንዲተው አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጲያም መጀመሪያ ከንጉሳዊ ስርአት ወደ ወታደራዊ ስርአት ለጥቆም ከወታደራዊ ስርአት ወደ ዳይሬክተራዊ ስርአት እንደተሸጋገረች ህዝቡ እንዲያስተውል ጠይቀዋል፡፡በቅርቡ “የዳይሬክተሮች ምክርቤት” የሚያወጣው ደንብ እየናፈቀኝ ነው አቦ!

በነገራችን ላይ የህዝቡ ሃሳብ ግልጽ ነው…..ከልጅ እስከ አዋቂ ጣቱን እያወዛወዘ ያለው አንድ የቀድሞ ታጋይ ላይ ነው…ከጫፍ እስከጫፍ የዚህ ሰው ስም ከሌብነት ጋር ተያይዞ እየተጠራ ነው…..ስቀለው!…… ስቀለው….! ስቀለው…….የሚሉ ድምጾች እዚህም እዛም ይሰማሉ…..ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ግን ትላንት በመግለጫቸው …እንደጲላጦስ “…..እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ሃጢያት አላገኘሁበትም! ስለምንስ ስቀለው ትሉኛላችሁ!?” በማለት ህዝቡን ጠይቀዋል…..በእርግጥስ እንደጲላጦስ ከሆኑ ላይቀር ማለትስ የነበረባቸው “ይህስ በእኔ ስልጣን አይደለም ሂዱና ለሄሮድስ ስጡት!” ነበረ…….ሃጢያት ባያገኙበትም እንደጲላጦስ ህዝቡን አክበርው እጃቸውን ታጥበው “እንዳሻችሁ አድርጉት” ብለው አሳልፈው ለ”ተራው ህዝብ” እንደማይሰጡት እንኳን ግልጽ ነው!…….ይሁን እንጂ አንድ ከልጅነት እስከ እውቀት ለነጻነትና ለፍትህ ታግያለሁ የሚል ጓደኞቹን ቀብሮ እዚህ የደረሰ ሰው እንደዚህ በሌብነት ሲበጠለጠል ማየት አሳፋሪ ነው! ለግለሰቡም ሆነ በዙሪያው ላሉ ሰዎች የሞት ሞት ነው! ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ ግን በተለመደው ኢሃዲጋዊ ቴክኒክ በዚህ ሰው ሌብነት ላይ የተጠነቆሉ ሌባ ጣቶችን በሙሉ “የጸረ ህዝብ ሃይሎች ውንጀላዎች” በማለት አጥፈዋቸዋል፡፡የህዝቡንም ጥያቄ  “ኢህዲግን ለማዳከም በጸረ ሰላም ሃይሎች የተቀነባባረ በንጹህ ሰው ላይ የሚሰነዘር የአይሁዶች ጩኸት….  እየሱስን ስቀለው በርባንን ፍታልን አይነት ነገር” አድርገው አጣጥለውታል፡፡ይሁና! እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል!?…..ሻርክ ለማጥመድ “አባይ ወንዝ” ወርደን የነበረ ቢሆንም መረቡ የውሃ እናት ብቻ ነው የሚይዘው ከተባልን እነሱኑ ጠብሰን መብላት እንጂ በረሃብ አንሞት?….!…….እዚህ ጋር የሆነ ልጄ የነገረችኝ ተረት ትዝ አለኝ…የህጻን ተረት ቢሆንም አስተካክላችሁ ስሙላት…..

“ተለት ተለት ….አንዲት አንጾኪያ የምትባል ዜጎቿ በበግ እልባታ የሚተዳደሉ በሰሜን አሜሊካና በደቡብ አፍሊካ መካከል የምትገኝ ሀገል ነበረች…..ከዛ ህዝቡን የሆነ ካለ ሳር ምንም የማይመገብ ድብ ማታ ማታ በጎቻቸውን እየሰለቀ አስቸገላቸው ……ከእለታት አንድ ከን ሁሉንም በጎቻቸውን ሰልቆ በላባቸው…ከዛ ህዝቡ ድቡን ሊደበድቡት ዱላ ይዘው ወደ ቤቱ ሄዱ ….. ከዛ ……ድቡ በጎቹን በሙሉ በልቷቸው ጭልስ አልጓቸው….ኬክ ሊበላ ሄዷል ለካ…ቤቱ ሲደልሱ የሆነች አሞላ (አሞራ) እሱ ያስተለፈውን ቅንጥብጣቢ ስጋ ስትበላ አገኟት….አንቺ ሌባ አሉና ቅጥቅጥ አድርገው ገደሏት..ተለቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ”…….

ባልተያያዘ ዜና ….አቶ አባይ ጸሃዬ ድሮ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ይዘጋጅ በነበረው “ታገል” በተሰኘው ጋዜጣ የእንግሊዝኛ አምድ (ስትራግል) ላይ ዋና አዘጋጅ እንደነበሩ ያውቃሉ…..!?ወ/ሮ አዜብ መስፍን በትግሉ ወቅት የማባዣ ክፍል ሰራተኛ እንደነበሩስ ያውቃሉ?! ካላወቁ ደግሞ እንዳልነበሩስ ያውቃሉ?!….ዝሆን ዛፍ ተደግፎ እንደሚተኛ ያውቁ ኖሯል?!…

Filed in: Amharic