>

‹‹ድሃ-ወርቅ-አይግዛ› (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

daniel-kibret‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› ይላሉ የምንዳየ እናት አባዬ፡፡ ‹ምነው አባዬ ድኻ በመከራ የገዛውን ወርቅ እንዴት ይጥፋበት ይላሉ› ብለን ሞገትናቸው፡፡ ‹እይውልህ እኛ ሠፈር አራት ኪሎ አዲሴ የሚሏት አንዲት ጎረቤታችንነበረች፡፡ ቁርስ፣ ምሳና እራት የተዘበራረቁባት። ለነገሩ ላለው ነው እንጂ ለሌለው ሰው ምግብ ስሙ ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ምግብ – ቁርስ፣ ምሳ እራት የሚሆነው በሰዓቱ ስታገኘው ነው፡፡ በሰዓቱ ካላገኘኸው ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ከድንጋይ ትፈልቅቀው፣ ከሳጥን ትስረቀው ሳናውቅ አንድ ቀን በድንገት አራት ኪሎ ወርቅ ቤት ሄዳ ወርቅ ገዛች ተብሎ ተወራ፡፡ የቡና ሴቶች ‹ግማሽ ግራም ወርቅ ገዝታ በከረጢት ቋጥራ አስቀመጠችው› ብለው ያሽሟጥጧታል፡፡
የገዛች ለት ምሽት እኛ ቤት ቡና ተጠርታ መጣችልህ። ሴቱ ሁሉ ግጥም ብሏል፡፡ ተርብ ተርቦቹ ደግሞ የዛን ቀን አንድም ሳይቀሩ ተለቃቅመው መጥተውልሃል። ገና ወደቤት ስትገባ ከሁላችን ለይታ ‹ወይዘሮ የወርቅ ውኃ ደኅና አመሹ› አትልልህም፡፡ አሁን በእርሷ ቤት ወርቅ መግዛቷን ልትነግረን እኮ ነው፡፡ ተያየንና ‹ኡኡቴ› ብልን ዝም አልን፡፡ ገና ከጠፈር ወንበሩ ላይ ሳትደላደል ‹እኔኮ በዚህ ዘመን ድኻ እንዴት ይኖራል፤ እኛስ እሺ› ብላ አረፈችው፡፡ ‹እናንተ እነማን ናችሁ› አለቻት እቴኑ በዓይኗ ቂጥ እያየቻት፡፡ ከምንም ሳትቆጥራት ‹ኧረ እንዴው ተውኝማ፣ ወርቅ እንደዚህ ሰማይ ይንካ› አለች ቆሎውን እየዘገነች፡፡ ‹እኛ ወርቅ ዘመን እንጂ ወርቅ ምን ያደርግልናል› አሏት እማማ ትጓደድ። ላምሮት ተናደደችና ‹ምን ዳር ዳር ትያለሽ፣ ወርቅ ገዝተሻል› አለችና አፈረጠችው፡፡ ሴቱ ሁሉ አንድ ጊዜ ቤቱን በሁካታ ሞላው፡፡ መቼም እርሷ አፍርጠው ናት፡፡
ሳቃችንን ሳንጨርስ ‹ቆይ ቆይ እስኪ› አለች አዲሴ ጆሮዋን እንደ አንቴና ሰቅላ፡፡ መቼም ከአራት ኪሎ ሠፈር ጯሂና አስጯሂ አይጠፋም ብለን ጸጥ አልን፡፡ አራት ኪሎ ጠብና ዕርቅ የተለመደ ነው፡፡ ተደባዳቢና ገላጋይ በየተራ ነው፡፡ ዛሬ ትደባደባለህ፣ ነገ ደግሞ በተራህ ገላጋይ ትሆናለህ፡፡ ሁላችን ኮንዶሚኒየም ላይ እንደተሰቀለ ዲሽ ጆሮአችንን አከታትለን ብንሰቅልም የመንገደኛ ተረብ ብቻ ነው የምንሰማው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ሳንዱቁ ላይ በልብስ ተሸፍኖ የተቀመጠውን ራዲዮ እስከ አንጀቱ ድምጹን ለቀቀችው፡፡ አበደች እንዴ ብለን በግራ ዓይናችን ገላመጥናት፡፡
‹ዛሬ በዋለው የዓለም ገበያ› ይላል ራዲዮኑ፡፡ እርሷ እዚያው እንደተለጠፈች ናት፡፡ እዚህ አራት ኪሎ ያለው የጉልት ገበያ የሚናፍቃት ሴትዮ የዓለም ገበያ ምን ሊያደርግላት ነው ብለን ሳቅን፡፡ ለወትሮው በዱቤ የሰጧት እንዳያንቋት ገበ ድርሽ አትልም ነበር ነበር፡፡ እንዲያውም እማማ ትጓደድ ‹አዲሴኮ ገበያ ብቻ ሳይሆን ገበያው የሚባል ሰውም ትፈራለች› እያሉ ይተርቧት ነበር፡፡
ራዲዮው ‹ዛሬ በዓለም ገበያ ወርቅ በካራት ይህን ያህል ተሽጧል› ሲል ‹እንዴው በደኅና ጊዜ ባልገዛ ይቆጨኝ ነበር፡፡ ለካስ ሰው ልጁን ወርቁ፣ ወርቂቱ፣ ወርቄ፣ ወርቅ አገኘሁ፣ ወርቅ አለማሁ፣ ጥሩ ወርቅ፣ አመለ ወርቅ እያለ የሚጠራው ወርቅ እየተወደደበት ነው› አለችና የግራ እጅ መዳፏን በቀኝ አራት ጣቶቿ ደበደበችው፡፡
ከዚያ በኋላ አዲሴን ማን ይቻላት፡፡ ከሱቅ በዱቤ ዕቃ ስትወስድ እንደ ድሮው መለመን፣ መለማመጥ ቀረ፡፡ ‹ማነህ ባለ ሱቅ፣ እስኪ አንድ አምስት ኪሎ ስኳር አምጣ› ትለዋለች፡፡ ‹እንዴ እማማ አዲሴ፣ በኋላ ባይከፍሉኝስ፤ ያለፈውን በመከራ አይደል እንዴ የከፈሉኝ› ሲሏት፤ ‹ያለፈው አለፈ፣ በቃ እናንተ ሰው ይቀየራል ብላችሁ አታስቡም፤ አምጣ ባክህ፣ ቢበዛ ወርቄን ሽጬ እከፍልሃለሁ› ትላቸዋለች፡፡ ኧረ እንዲያውም አንድ ቀን አንድ ቄስ በዚያ ሲያልፉ ጠራቻቸውና ‹ዛሬ ሲያቃዠኝ አድሯል ይርጩኝ› ትላቸዋለች፡፡ ‹የክርስትና ስምሽ ማነው› ይሏታል፤ ‹እኅተ ወርቅ› ትላቸዋለች፡፡ ቄሱ ደንግጠው፤ ‹እኅተ ማርያም› ማለትዎ ነው› ይሏታል፡፡ ቀኝ እጇን ወደ ጎን እያውለበለበች፤ ‹እርሱ የነዛ የነዛ ስም ነው› አለቻቸው፡፡ ‹ታድያ እኅተ ወርቅ፣ አይ፣ ያልተማረ ሰው ሰጥቶዎት እንዳይሆን› ይላሉ ያልገባቸው ቄስ፡፡ ‹ይኼው ነው አባቴ፣ካልተረዱት ይተውት› አለቻቸው፡፡
ድሮ አዲሴ ቀበሌ መሄድ አትወድም ነበር። ‹እነርሱ መዋጮ ብቻ ነው ሥራቸው› ትላለች። ወርቅ በገዛች ሰሞን ‹ምነው ስብሰባ በተጠራ፣ ልክ ልካቸውን ነበር የምነግራቸው› ማለት አበዛች። በልኳ ለብሳ የማታውቅ ሴትዮ ድንገት ተነሥታ ልክ ልክ ነጋሪ ሆነችልህ፡፡
የስብሰባው አጀንዳ ‹ሴቶች በልማት ይሳተፉ› የሚል ነው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ‹ለሴቶች ዕድገት ወሳኙ ወርቅ ነው። እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል እንድንሆን ወርቅ ያስፈልገናል› ስትል አንዷ ‹ታዲያ እንደ መሠረት ደፋር አትሮጭም፣ ማን ከለከለሽ› ብላ አሳቀችባት። ‹የሴቶችን ችግር ለመፍታት ስብሰባ ሳይሆን ሴቶች ወርቅ የሚገዙበት መንገድ መመቻቸት አለበት› ብላ ስትቀመጥ ሰብሳቢዋ ምናልባት መልስ ቢሰጡ ብላ ነው መሰለኝ ለወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ ዕድል ሰጠቻቸው፡፡ ሊያነጥፉላት ነው፡፡
‹ድኻ ወርቅ አይግዛ፣ ከገዛም ይጥፋበት ትል ነበር አያቴ፡፡ ወ/ሮ አዲሴ ትናንት ግማሽ ግራም ወርቅ ስለገዛሽ፣ ወሬሽ ሁሉ ምነው ወርቅ ብቻ ሆነሳ› ሲሉ ሁሉም የኮረኮሩት ያህል በሳቅ ፈነዳ፡፡ ‹ባለፈው እዚህ ሠፈራችን ያለ ጎረምሳ መጽሐፍ አሳተመ ተብሎ ደስ አለን። ምንም ቢሆን ያሳደግነው ልጅ ነው ብለን። እሱ ግን ፊደል የፈጠረ እንጂ መጽሐፍ ያሳተመ አልመሰለውም፡፡ ቡና ልንጠጣ ቤታቸው ስንሄድ፣ የዛሬው የቡና ቁርስ የኔ ግጥም ነው ብሎ ግጥም ሊያነብልን ጀመረ፡፡ ምነው ሸዋ! ሐዲስ ዓለማየሁም እንዲህ አላደረጉ፡፡ ደግሞኮ
አራት ኪሎ ኪሎ
አራት ኪሎ ኪሎ
የድንጋይ አሎሎ› የሚል ግጥምኮ ነው፡፡› ሰብሳቢዋማ ከጠረጴዛው መነሣት እስኪቸግራት ተደፍታ ነው የሳቀችው፡፡ ያው ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ከሳቅክላቸው ማንጠፍ ነው፡፡ ‹ይባስ ብሎ ቀበሌ አዳራሽ ልጆቹን ሰብስቦ ‹ታዋቂው ደራሲ› የሚል ፖስተር ለጥፎ ልምድ አካፍላለሁ ይላቸዋል፡፡ ‹እርሟን ጠምቃ፣ ሰጠች ጠልቃ› አሉ፡፡
አንበሳ ተኝቶ ፍየል ዘለለችው
ንቆ ቢያሳልፋት ሞኝ አደረገችው› አለ የሀገሬ ሰው። በብጥሌ ወረቀት አላሳተምንም እንጂ ስንት ግጥም ነበረንኮ፡፡
መቶ ታምሳ ዜማ የሚሰማብሽ
ድኻ ባለጠጋ የማይጠፋብሽ
ፀሐይ እንደ እንግሊዝ የማይጠልቅብሽ
የሁሉ እኩል ሀገር አራት ኪሎ ነሽ› ብሎ እንደመግጠም፣ ‹አራት ኪሎ ኪሎ፣ የድንጋይ አሎሎ› ብሎ አሎሎ የሚያህል ግጥም የጻፈን ልጅ ልምድ አካፍላቸው ማለት በአሎሎ ደብድባቸው እንደ ማለት ነው፡፡› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው። ድኻ ወርቅ አያግኝ ማለት ይኼ ነው፡፡ አሁን እኛን የቸገረን እንዲህ እንደ አዲሴ የሚባርቅባቸው ድኾች ናቸው፡፡ ሥልጣን አይቶ ለማያውቀው ሥልጣን ትሰጡትና ይባርቅበታል። የቢሮውን መኪና በሠፈራችን እያፈጠነ ካላሳየን ሞቶ ይገኛል። በታክሲ ሲሰቃይ ለከረመ ሰው ቪ ኤይት መኪና መስጠት፣ በውኃ ጥም ለከረመ ሰው ቅቤ አቅልጦ እንደማጠጣት ነው። ሁለቱም ጤና አይሆናቸውም። አበሉ፣ ስብሰባው፣ ግብዣው፣ ፊርማው፣ ብርቅ ይሆንበታል፡፡ ቀበሌውና ክፍለ ከተማው የግል ንብረቱ ይመስለዋል፡፡ እኛም አሽከሮቹ እንመስለዋለን፡፡ የተሾመ ሰሞን ብርቅ ስለሚሆንበት ያገኘውን ገንዘብና መሬት ይጠበጥበዋል፡፡ ያልራሰ መሬት ማለት’ኮ ነው፡፡ ምን ውኃ ይመጥነዋል፡፡ ‹አይቶ አያውቅ ዳቦ ፍሪዳው ነው› ይባላል። አንድ ስብሰባ ላይ አንዲት እንግሊዝኛ የሰማ ዕለት እኛን ሰብስቦ እርሷን ካልተናገረ ይሞታል፡፡ ውጭ ሀገር ሄዶ አንዲት ነገር ካየ፣ ብርቅ ስለምትሆንበት ‹ቻይና ሳለሁ፣ ኮርያ ሳለሁ› እያለ መከራ ያሳየናል፡፡ ድኻ ወርቅ አይግዛ የተባለው’ኮ ለዚህ ነው፡፡
አላያችሁም እንዴ… በድንገት ሀብታም የሆነን ሰው፡፡ ሳይነግራችሁ ታውቁታላችሁኮ፡፡ የውሻ ማሠሪያ የሚያህል የአንገት ወርቅ፣ ክብደት መለኪያ የሚሆን የእጅ ሰዓት፣ የሚታይ ከናቴራ፣ ከከናቴራው ላይ አዲስ ሸሚዝ፣ በሸሚዙ ላይ አዲስ ሹራብ፣ በሹራቡ ላይ አዲስ ኮት፣ በኮቱ ላይ አዲስ የውጭ ካፖርት፣ በካፖርቱ ላይ ስካርፕ ደርቦ ታዩታላችሁ። ይህን ስታዩ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ› በሉና ሽሹ፡፡ መኪና ከገዛማ አይጣልባችሁ፡፡ በግራ እጁ መሪ ይዞ፣ ወንበሩን ወደ ኋላ ስቦ፣ ልጥጥ እያለ፣ የአስፓልት ውኃ እየረጨባችሁ ያልፋል፡፡
እና አዲሴ ተይን እባክሽ፣ አንቺ ዛሬ ወርቅ ስትገዥ የችግራችን ሁሉ መፍቻ ወርቅ መሰለሽ። የክፉ ሐኪም ምክር አትምከሪን፡፡ ክፉ ሐኪም ሥጋው የገጠጠ በሽተኛ በቀበሌ ደብዳቤ በነጻ እየታከመ እያየ፣ ከምግብ በፊትና ከምግብ በኋላ ሦስት ጊዜ የሚዋጥ መድኃኒት ያዛል፡፡ ይህ ማለትኮ ሰውዬውን አትድንም ተስፋ ቁረጥ ማለቱ ነው። መድኃኒቱንስ በነጻ አገኘ፡፡ ምግቡን ማን ይሰጠዋል? አሁን ያስቸገሩን እንዳንቺ ያሉት ናቸው፡፡ ሲበሉ የበላን፣ ቤት ሲሠሩ የሠራን፣ አበል ሲከፈላቸው የተከፈለን፣ ሲሾሙ የተሾምን፣ የእነርሱ ችግር ሲፈታ የእኛ የተፈታ የሚመስላቸው የአእምሮ ድኾች፡፡ ድኃ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ወርቁ ጠፍቶባቸው ከሥልጣን ሲወርዱ፣ ከሀብት ሲናዱ ምን እንደሚመስሉ አይተናቸዋላ፡፡
ሞቅ አድርገን አጨበጨብንላቸው፡፡ ራሷ ሰብሳቢያችን አጨበጨበች፡፡ እኔም ከእርሷ ወስጄ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› እላለሁ፡፡
አሉኝ የምንዳየ እናት አባዬ፡

Filed in: Amharic