>
7:38 pm - Thursday September 16, 2021

የኔ ትውልድ አዋጅ! [ዘወድአለም ታደሰ]

ኢትዮጵያን ባራቱም አቅጣጫ አራት ሲኦሎች ያዋስኗታል። ፈርኦን ደግሞ ያስተዳድራታል። ባርነትን በደሟ ብትታገልም በራሷ ልጆች ግን ደጋግማ ቅኝ ተገዝታለች። ከእስረኛው ይልቅ ታሳሪው የሚበዛባት ከምክኒያት ይልቅ አሉባልታ የሚነግስባት ጎስቋላ ሐገር ነች። የልጆቿ የነፍስ ዋጋ ከአንድ ዶላር ሲያንስ ለልጅ ልጅ የምታወርሰው ቂምና እዳ ደግሞ ከፍተኛ ነው።

ልጆቿ ሰው ሆነው ተወልደው ከፍ ሲሉ እፉኝት ይሆናሉ። ወላጆቻቸውንም ነድፈው ይገድላሉ። በየሃይማኖት ውስጥ የተሰገሰጉ ለመንጋው እረኛ እንዲሆኑ የተሾሙት አባቶች ደግሞ የሚያሰማሩትን መንጋ ስጋ እየበሉ ቆዳውን ለብሰው ያጌጣሉ። የትውልዱ አይኖች በተስፋ ባህር አሻግሮ ይመለከታል። የአሳ ነባሪ መኖ ፣ ለበረሃ ሽፍታ መጫወቻም ሆኗል።

አዋቂ ነን ባዮቿም ደም እያፋሰሱ የደም ውቅያኖስ ሰርተው በዋና ቤተመንግስት ለመግባት ይተጋሉ። ከመሞት ይልቅ መኖር ከብዷል። ከጎጆ ይልቅ መቃብር ስፍራ ረክሷል። የትውልዱ ጅማሬም ሆነ ፍፃሜ ከስቃይ እስከስቃይ ከሞት እስከሞት ነው። ባረጀ ትግል አዲስ ለውጥ አመጣለሁ የሚል የነፃነት ታጋይ እንጂ አዲስ ሃሳብ ይዞ የሚነሳ አብዮተኛ አይወለድም። ከተወለደም አይኖርም። ከኖረም ህልሙን አፍርሰው የሻገተ ህልማቸውን የህልሙ መቃብር ላይ ይተክላሉ።

ነገር ሁሉ ተስፋ ያስቆርጣል። ዙሪያችን እንደቄሳሮች የፍልሚያ አውድማ በእሳትና እሾህ ተከቧል። የኢትዮጵያ ሰማይ ጥቁር ነው። ሁሌ ክረምት፣ ሁሌ ጭጋግ ፣ የማይነጋ የሚመስል ለሊት ፣ የማያባራ ጩኸት ፣ ይማይገደብ እንባ ፣ የማያበቃ ስቃይ ፣ የማይነጥፍ ውሸት ፣ የማይቆም ክህደት ፣ የማይደርቅ ቂም ፣ መሃል ነው ምንኖረው። እቺ ነች የዛሬዋ ኢትዮጵያ!!

ቢሆንም! ቢ ሆ ን ም …

በስቃይ የማይደፈርስ ተስፋ ልባችን ውስጥ አለ። ደመናው ሲገፈፍ ጨለማው እንደመጋረጃ ለሁለት ተቀዶ የናፈቅናት ፀሃይ ዳግም ስታበራ ለማየት የሚጠባበቁ ተስፈኛ አይኖች አሉን። ከመውደቅ ባሻገር መነሳት ፣ ከህመም ባሻገር ፈውስ እንዳለ የሚያምኑ ተስፈኛ ልቦች አሉን። ምድሪቱ ዝም ስትል ሰማዩ መናገር እንደሚጀምር እናውቃለን። ድንቁርና የሞላትን ሐገር በእውቀት ብርሃን የሚወርሱ መሲሆች እንደሚወለዱ እናምናለን።

ፈረሰች ሲሉ የምትጠገን ፣ ወደቀች ሲሉ ትቢያዋን አራግፋ የምትነሳ የበረሃውን ዲንጋይ በተአምራዊ በትር መትታ ለአለም የሚተርፍ የፈውስ ጠበል የምታፈልቅ ሐገር እንዳለችን በእምነት የምንቆጥር ልጆቿ እልፍ ነን!

ከመነካከሰ ፖለቲካ ተርፈው ስለአንድነት እየዘመሩ በታላቅ ፍቅር የሚነሱ እንደምድር አሸዋ የበዙ ሰራዊቶች እንደሚነሱ፣ የጥላቻና የመከፋፈል ሃውልት እያፈረሱ ከአክሱም የገዘፈ የአንድነት ስብእና በትውልዱ ልብ ውስጥ የሚተክሉ ጠቢባን አንድ ባንዲራ ለብሰው ከየአቅጣጫው ሲጎርፉ ዛሬ ላይ ቆመን በተስፈኛ አይኖቻችን ነጋችንን አሻግረን ስለምናይ …. በሐገራችን ላይ ተስፋ አንቆርጥም!

በዚህ የመለያየት ዘመን አንድነትን የምናልመው እንደሚያሙን ባዶ ቅዠት የተዋሃደን ሃሳባውያን ስለሆንን ሳይሆን ተስፋ ከማድረግ ውጪ ምንም አይነት ምርጫ ስለሌለን ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ሐገራችን ነች። ማንነታችን ፣ ታሪካችን ፣ ሐብታችን ፣ ክብራችን ፣ ተስፋችን ነች! ሲከፋን የምንጠለልባት ምሽግ ፣ ሲገፉን የምንሸሸግባት የመማፀኛ ከተማችን ነች! የትኛውም ተስፋ ሐገራችን ላይ ተስፋ አያስቆርጠንም! የትኛውም ፍርሃት ይሄን እምነታችንን አያስጥለንም! ሐገር ተጥሎ ምንስ ይያዛል?

ስለዚህ አሁንም እንወዳታለን!! የፍቅራችን ውል የታተመው በብጥስጣሽ ወረቀቶች ላይ ሳይሆን በልባችን ላይ ነው! ለሐገራችን የገባነው ቃል ኪዳን የታሰረው ከነፍሳችን ጋር ነው! ኢትዮጵያዊነት ተፈጥሯችን ነው። ኢትዮጵያን መውደድ ምርጫችን አይደለም ግዴታችን እንጂ! ስንወለድ የቀዘፍነው አየር ፣ ስንፈጠር ያሸተትነው አፈር ከደማችን ጋር ስለተዋሃደ ፍቅራችንን ከውስጣችን አውጥቶ መጣል አይቻለንም!

The shadow of a supporter of Ethiopia's Unity for Democracy and Justice party (UDJ) is seen through an Ethiopian flag during a demonstration in the capital Addis Ababaበሐገር ፍቅር ልክፍት ስለታሰርን የትኛውም የጥላቻ ስብከት ከልክፍታችን አይፈውሰንም! ለዚህ ነው አሁንም አፋችንን ሞልተን ስለትንሳኤዋ የምንተነብየው! እንኳን ሐገር የስንዴ ቅንጣት እንኳ አፈር ውስጥ ገብታ ፣ ሞታ ፣ በስብሳ ፣ እንደገና እልፍ ሆና በትንሳኤ ሃይል ትነሳለች! ስለዚህ ስለሞቷ ሲያወሩ ትንሳኤዋን ፣ መክሸፏን ሲከትቡ ታላቅነቷን አየሩ ላይ እናውጃለን!

አዎ! ኢትዮጵያን እስከመጨረሻዋ እስትንፋሳችን ድረስ እንወዳታለን! እየወደድናት ኖረን እየወደድናት እናልፋለን። እየወደድናት ኖረን እየወደድናት ገና …. እንኖራለን!

Filed in: Amharic