አናኛቱ!
አንዱአለም በውቀቱ ገዳ
ቴዲ አፍሮ … ምን አገኛት ብዬ ስትዘገዪ እሰጋለሁ… ብሎ ያቀነቀነላት ልጅ የመንግስት ታጣቂዎችን ጥይት ስትሸሽ ገደል ገብታ የሞተችቱን፣ ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ እንድትል አስቴር አወቀ የገዛ ገዳይዋ ሃውልት ሰርቶላት ዛሬ ተመረቀ አሉ። በሃውልቱ ላይ የሞቱ መንስኤ ምን ተብሎ ቢጻፍ ጥሩ ነው…? ”ድንገተኛ ሞት” ጥይቱን የተኮሱት እኮ ባርቆባቸው ሳይሆን አስበውበት ነው። ለማንኛውም አንድ ወዳጄ እንዳለው በኢሬቻ ላይ ሲጮሁለት የነበረው እና የሞቱለት ጉዳይ ፍትህ ነው። ሟቾቹ ነፍሳቸውን ይማረውና፤ ሃውልት ከሚቆምላቸው ይልቅ ዛሬም ድረስ በወገኖቻቸው ላይ ያልቆመው እስር ቢቆምላቸው ነፍሳቸው ሰላም ታገኝ ነበር።
ራስ ገድሎ ራስ ሃውልት ማቆም ግን ማናለብኝነት ነው!
እሺ ወደ ልቦለዱ እንግባ
የልቦለዱ መግቢያ፡…….ቀኑ ጸሃያማ ነው፡፡(እንደማንኛውም የኢትዮጲያ ልብወለድ ቀኖች ማለት ነው)፡፡
ዛሬ የአኖሌ እና የጊፊቲ የፍቅር ጥንስስ የተጀመረበት የመጀመሪያ አመት አኒቨርሰሪያቸውን የሚያከብሩበት ቀን ነው፡፡ልክ የዛሬ አመት በወርሃ መስከረም ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በኢሬቻ በአል ነበር አኖሌ ጊፍቲን ያያት፡፡በበአሉ ላይ እንደተገኙት እንደአብዛኛው የኦሮሞ ጉብላሊቶች የሚያምር የባህል ልብስ ለብሳ ደምቃለች፡፡ ……”አከሚቲ በሬዲ !ወይኔ እንዴት አባቷ ታምራለች?!” አለ አኖሌ ..ገና እንዳያት…….
ረጅም ጥቁር ለስላሳ ጸጉሯ ከትከሻዋ ላይ ፍስስ ብሏል፡፡ግምባሯ ላይ በጨሌ የተሰራ የባህል ጌጥ አድርጋለች፡፡አንገቷ እና የእጅ አምባሯ ላይ ያደረገችው ጌጥ የሆነ እዚህ ጋር ስሙ የማይጠቀስ የፖለቲካ ፓርቲ አርማ ይመስላል፡፡ከአንዲት ጓደኛዋ ጋር እየተላፋች ትሳሳቃለች…..ስትስቅ ደግሞ የበለጠ ታምራለች….ልክ ስሟ የተጠራ ይመስል ድንገት ወደ አኖሌ ዞር አለች….አይናቸው ሲገጣጠም ድንግጥ ብላ አይኗን ስብር አደረገች…..አኖሌ በመዶሻ አናቱን የተመታ መሰለው….
አንባቢ ሆይ የአንተንም የእኔንም ጊዜ ላለመሻማት አኖሌ ፍቅር ሲይዘው የሆነውን እና የተሰማውን ነገር ሌላ ግዜ ካነበብካቸው የፍቅር ድርሰቶች ወስደህ ታሪኩን አሟላ..…..እኔን ብቻ አታድክመኝ…….
እሷስ!?
የዛን ቀን በአሉን አብረው አከበሩ፡፡ ዱከም ድረስ ምንም ድካም ሳይሰማቸው ድሮ እንደሚተዋወቁ ፍቅረኞች እጅ ለእጅ ተያይዘው ወክ አደረጉ …ስለ ኦሮሞ ባህል፡ መብት ፡ትግል፡ ወዘተ ብቻ ስለ ብዙ ጉዳዮች ተወያዩ….ያው አንባቢ እንደጠረጠርከው …እሷም እራስምታት የሚያስይዝ ፍቅር ያዛት….እዚህ ጋር አንዳንድ ጨቅጫቃ አንባቢ” የልጅቷ ጓደኛስ የት ሄደች?!” ብሎ እንደሚጠይቅ ይገባኛል….ጭቅጭቅ ነው ንባብ ነው የያዝከው የኔ ወንድም?!…..ጓደኛዋ ቅድም በድርሰቱ ውስጥ የተጠቀሰችው “ጊፍቲ ከጓደኛዋ ጋር እየተላፋች ትሳሳቃለች” ለሚለው ዓ/ነገር ማሟያ እንጂ እኔ እያንዳንዱን ገጸባህሪ አንዴ ጠቅሼዋለሁ ብዬ ወደ ቤቱ የማስገባት ግዴታ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡
የልቦለዱ መሃል፡
ጊፍቲና አኖሌ አመቱን ሙሉ በፍቅር እብድ አሉ፡፡እንደውም በተገናኙ በዘጠነኛው ወር ጊፍቲ ጓዟን ጠቅልላ ለገጣፎ ከሚገኘው የአኖሌ የሚያምር ቪላ ገባች፡፡በየስራ ቦታቸው ተለያይተው ሲውሉ ቢያንስ አስር ግዜ ይደዋወላሉ….ከስራ እንደወጡ ያለምንም ወለም ዘለም ይገናኛሉ…ወክ ያደርጋሉ ……ፊልም ያያሉ……አኖሌ መጽሃፍ የሚያነብ ከሆነ ጊፍቲ ሆዱ ላይ ትተኛና የምትወዳቸውን ፊልሞች ቻናል እያቀያየረች ታያለች……ሁለት ሰአት ሲሆን እና እለቱ የእሱ እራት የማቅረብ ቀን ሲሆን አኖሌ መጽሃፉን ይዘጋና …ወደኪችን ይገባል….”ንግስት ሆይ ሺ አመት ይንገሱ” ይልና ልክ እንደ ቤተመንግስት አገልጋይ ወገቡን እያጠፈ ጠረጴዛው ላይ ሰሃኖቹን ይደረድራል…ጊፍቲ ትፍነከነካለች…… የሷ ተራ ከሆነም ተመሳሳይ መስተንግዶ ከልዩ አክብሮትና ፍቅር ጋር ይቀጥላል……አንዳንዴ ደግሞ በረንዳቸው ላይ ቁጭ ይሉና ከአርቲስት ጎረቤታቸው ቤት አልፎ አልፎ የሚሰማውን ማራኪ የፒያኖ ድምጽ ያጣጥማሉ…..ጎረቤታቸው 365 ቀናት ሙዚቃ መስራት የማይሰለቸው…..ቴድሮስ ካሳሁን የተባለ ተወዳጅ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡ከእነሱ በኋላ ነው ከእነሱ አጠገብ ያለውን ቤት ገዝቶ ለገጣፎ የገባው፡፡ትሁት ጻባዩ እና እራሱን አለማካበዱ ግርም ይላቸዋል…..ካለ ኦሮምኛ ዘፈን የማታዳምጠው ጊፍቲ “ይሄ ልጅ በዚሁ ከቀጠለ አንድ ቀን አሊቢራን ይተካል!” ትላለች…አኖሌ በዚህ አባባሏ ሁሌ ፈገግ ይላል፡፡
የልቦለዱ መገባደጃ
የ2009 ኢሬቻ በአል ለሁለቱ ፍቅረኞች የመጀመሪያ አኒቨርሰሪያቸውን የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ ከሌሎች ኢሬቻዎች በተለየ ጉጉት እየጠበቁት ቆይተው እነሆ ዛሬ ደረሰላቸው….
በሀገሪቱ ውስጥ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን በተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት መነሻ በበአሉ ላይ ችግር ይከሰታል በሚል መንግስት መትረየስ፡ታንክ ፡መድፍ እና ሄሊኮፕተርን ጨምሮ አንድ ከጅቡቲ ከፍ ከሩዋንዳ ዝቅ ያለችን አነስተኛ ሀገር ለመውረር የሚያስችል የተሟላ ጦር በስፍራው አስፍሯል……..
ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን ከበአሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ አኖሌ ጂም ውስጥ ስፖርት ሲሰራ አደገኛ የስር መዞር እግሩ ላይ ስላጋጠመው…እንኳንስ ሆራ አርሰዲ ለመሄድ ከቤት ወደ ደጅ ለመውጣት እንኳ የሰው ድጋፍ የሚሻ ሆኖ ቁጭ ማለቱ ነበር….….ጊፍቲ የፈለገ ቢሆን ከሆራ አርሰዲማ አልቀርም ብላ ከዛች የድሮ ጓደኛዋ ጋር በጥዋት ከአምናው እጥፍ አምሮባት ወደ ደብረዘይት አቀናች…….
“ስልክሽን ደግሞ እንዳታጠፊ ፍቅር! “አላት ከቤት ስትወጣ…ግምባሯን ሳም አደረጋትና “ኦፍ ኤጊ “አላት በድጋሚ………
ከቀኑ 9 ሰአት ሆኗል……
አኖሌ በአንድ እጁ ምርኩዝ ተደግፎ ጊቢ ውስጥ ይንጎራደዳል….ከቢሾፍቱ አካባቢ የሚሰማው ዜና መልካም አይደለም……የጊፍቲ ስልክ ይጠራል የሚያነሳው የለም………ሆዱ ተሸበረ…….
ጎረቤቱ ቴዲ አፍሮ ቱታ ለብሶ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ሁል ግዜ የዘፈን ግጥም የሚጽፍበትን ቡኒ ክርታስ ይዞ ቡዝዝ ብሎ ደጅ ደጁን ይመለከታል……የእሱንና የአኖሌን ቪላ የሚለየው አጭር የሚያምር የእንጨት አጥር ነው፡፡
“አኖሌ ማልታቴ!?”….አለ ቴዲ ….አኖሌ ቴዲን ኦሮምኛ እያለማመደው ሲሆን ለዚህ ውለታው ቴዲ አኖሌን አልፎ አልፎ ፒያኖ ያስተምረዋል፡፡
“ጊፍቲ ቢሾፍቱ ጥዋት ሄዳ እስከአሁን አልተመለሰችም ….. ስለአካባቢው የሰማኸው ነገር አለንዴ ?ስልኳ አይሰራም! ምክንያቱን ለማወቅ በጣም ተጨንቂያለሁ….ደግሞ ስተዘገይ ሁሌ እሰጋለሁ….”አለ አኖሌ …..
“አይዞህ ምን አትሆንም ወይ መታም ይሆናል! ” አለ ቴዲ ፡፡በቢሾፍቱ ግርግር ተነስቶ ቀላል የማይባሉ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ጭምጭምታው የደረሰው ቢሆንም ጭንቀቱን አኖሌ እንዲያውቅበት አልፈለገም…..
“አረ ቴዲዬ ልቤን ግራ ገባው……ላያት ከቤት እደጅ ስንቴ ገባሁ ስንቴ ወጣሁ…”አለ…..አኖሌ በጭንቀት…
“ወይ አንዱን ልጅ ልኬ ባረፍኩኝ ከስጋት …..ቀርታስ ቢሆን ሄዶ ከመንገድ ማን አያት……”አለ አኖሌ በድጋሚ…..አሁን የተናገረው ለቴዲ ይሁን ለራሱ ግልጽ አይደለም……
“ያንን ልጅ ላከው……”አለ ቴዲ ከአጥር ውጭ ወደ ቆመው ጩጬ እየጠቆመ….
“…..ኢጆሌ እስቲ መንገዱን እይና ተመለስ” አለ አኖሌ ጮክ ብሎ…… ከድጅ የቆመው ልጅ “ማንን?” ብሎ መጠየቅ አላስፈለገውም…….እየበረረ ሄደ…..
ሰአታት አለፉ ……ቴዲ አኖሌን ማጽናናት ከሚችለው በላይ ሲሆንበት እቤቱ ገባና መተከዣው ፒያኖ ላይ ቁጭ አለ….ውስጡ ተረብሿል…..ስልኩን አነሳና የፌስቡክ አካውንቱን ከፈተ…..የሚያያቸው ገጾች በሙሉ በቢሾፍቱ የተፈጀውን ህዝብ ፎቶ ይዘዋል….ብላቴናው ልቡ በሀዘን ስብር እንዳለ…አለፍ አለፍ እያለ….የሚዘገንኑትን ፎቶዎች ማየት ቀጠለ….ድንገት አንድ ፎቶ ላይ አይኑ አረፈ…..ሰውነቱ ሽምቅቅ አለ…በአንድ የገደል ጫፍ ላይ በዛ ያለ የወጣቶች እሬሳ ይታያል….በጉልህ ከሚታዩትና እንደዋዛ በአቧራው ላይ ክልትው ካሉት ወጣቶች ውስጥ የአንደኛዋን ውብ ወጣት ፊት …….ቴዲ በደንብ ይለየዋል……ጣቶቹ በደመነብስ የፒያኖውን ቁልፎች እየነካኩ ከእያንዳንዱ ምት ጋር የእምባ ዘለላዎች አኩል መንጠባጠብ ቀጠሉ…….
መታስ ቢሆን ማን አያት
ቀርታስ ቢሆን ማን አያት
ጠፍታስ ቢሆን አናኛቱ…………….
.
.
የዚህ ጽሁፍ መታሰቢያነቱ በእለቱ እንደዋዛ ለተጨፈጨፉት የኦሮሞ ወጣቶች ይሁንልኝ፡፡
ምንም ቢሆን ምንም
ይመቻችሁ፡
አንዱአለም በውቀቱ ገዳ