>
6:08 pm - Thursday September 16, 2021

ዋዜማ:-የፀረ ሙስና ዘመቻው ተቋርጧል! ሴተኛ አዳሪዎች ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየታፈሱ ነው...

Wazema Radio[ለዋዜማ ዋና አዘጋጅ የደረሱና እየተከታተልናቸው ያሉ ግርድፍ መረጃዎችን እናጋራችሁ]
-የፀረ ሙስና ዘመቻው ተቋርጧል!
-ግርማ ብሩ ይመለሳሉ? አይመለሱም?
-ሴተኛ አዳሪዎች ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየታፈሱ ነው

-የፀረ ሙስና ዘመቻው ተቋርጧል
የኢህአዴግ የፀረ-ሙስና ዘመቻ በድንገት ተቋርጧል። በተለይም ዘመቻው ለምን በሙስና የሚጠረጠሩ ትላልቅ ሹማምንትን እንዳላየ ያልፋል? የሚለው የህዝብ ጥያቄ በፓርቲው አካባቢ በስፋት መነሳቱ በደህንነት መስሪያ ቤቱና በጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ መካከል የዝግ ውይይት እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል። የደህንነት መስሪያ ቤቱ መረጃ ይዤባቸዋለሁ ያላቸውን የተወሰኑ ባለስልጣናት በስም ጠቅሶ ለአቶ ሀይለማርያም ሹክ ብሏቸዋል። ተጠርጣሪ ባለስልጣናቱን ይዞ ማሰር ለፓርቲውም ሆነ ለሀገሪቱ የሚያስከትለውን ትርምስ ለማስቀረት ጉዳዩ ከህግ ይልቅ በፖለቲካዊ መንገድ ቢፈታ ይሻላል የሚል ውሳኔ ተደርሶበታል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተጠርጣሪ ባለስልጣናቱ ጋር ተመካክረው የተወሰደ እርምጃን ለህዝብ ይፋ ቢያደርጉ የተሻለ መሆኑን ተመክረዋል። እስካሁን ጠሚሩ የተባለውን ምክክር ስለማድረጋቸው የታወቀ ነገር የለም። ለሙስና ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስፈለጉን ግን ለካቢኔያቸው ተናግረዋል። የሙስና ዘመቻው ባለሀብቶችን ክፉኛ ማስደንገጡና አንዳንዶች ከሀገር እንዲሸሹ ማድረጉ ያሳሰበው ኢህአዴግ ዘመቻውን ጋብ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ማመኑን የቅርብ ምንጮች ይጠቁማሉ።

ግርማ ብሩ ይመለሳሉ? አይመለሱም?

ESAT Special Documentary Ambassador Girma Biruበአሜሪካን ሀገር የኢትዮጵያ መንግስት ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት የአቶ ግርማ ብሩ ጉዳይ በኢህአዴግና በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አካባቢ መደነጋገርን እንደፈጠረም እየተሰማ ሲሆን ምክንያቱም በርሳቸው ምትክ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በአምባሳደርነት የተሾሙ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ አቶ ግርማ ሀገር ቤት አለመመለሳቸው ለተያዩ መላምቶች እንደጋበዘ ነው። አቶ ግርማ በመንግሥት በተጠሩበት ፍጥነት ሀገር ቤት አለመመለሳቸውና ምናልባትም ግለሰቡ ከአምባሳደርነት እንዲነሱ የተደረጉት እና ሀገር ቤት እንዲመጡ የተፈለገው በወንጀል ተጠርጥረው ሊከሰሱ ስለተፈለገ እንጂ ለየትኛው የተሻለ ሀላፊነት ሊሾሙ ታስበው ነው የሚለው ጉርጉምታና ሀሜት አስፈርቷቸው ሊሆን ስለሚችል በዚያው ሊቀሩ አስበዋል የሚል መላምት በሰፊው እየተደመጠ ነው ። ከአንዳንድ የመረጃ ምንጮች አቶ ግርማ እስከ አሁን ያልተመለሱት በህክምና ላይ በመሆናቸው ምክንያት መሆኑም እየተገለፀ ነው።

ሴተኛ አዳሪዎች ከኣአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየታፈሱ ነው

በአዲስ አበባ ሆቴሎች በራፍና በጎዳናዎች ላይ በስራ ላይ የነበሩ ሴተኛ አዳሪዎች በፖሊስ እየታፈሱ ነው። አፈሳው በቅርቡ ለሚደረገው ተከታታይ መንግስታዊ የአዲስ አመት አከባበር የፀጥታ ጥበቃ ሲባል እንደሆነ አንድ የፌደራሉ ፖሊስ የስራ ሀላፊ ለዋዜማ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባም በቅርቡ በአዲስ አበባ ስለሚካሄድ መንግስት ለከተማዋ ፀጥታ አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን እንደሚያውቁ ሀላፊው ነግረውናል።

Filed in: Amharic