>

ያልታደለ ሕዝብ “የቀብር ቀን” ሲጠብቅ “የፍቅር ቀን” ይመጣበታል! (ስዩም ተሾመ)

ነገ፥ ነሃሴ 26/2009 ዓ.ም “የፍቅር ቀን” ነው። ቀኑ “በፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ እናት ኢትዮጲያ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ ከተጠቀሱት ዝርዝር ተግባራት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡- “ሁለት ታዋቂ ሞዴሎች በባህላዊ ልብስ ተውበው በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየዞሩ የአበባ ስጦታ ያበረክታሉ። በሆስፒታል ለሚገኙ ሕሙማን፣ ለሕግ ታራሚዎች፣ ለሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶች “የፍቅር ስጦታ ፖስት ካርድና አበባ ያበረክታሉ…” እነዚህ ተግባራት እንግዲህ የሚፈፀሙት በኢህአዴግ መንግስት ነው። ሌላው ቀርቶ አምና እና ዘንድሮ ብቻ በሰራው ስራ እጅግ ብዙ አዛውንቶች ረግመውታል፣ እናቶች አልቅሰውበታል፣ ሕፃናት እንደ ጭራቅ ይፈሩታል። “የሕግ ታራሚዎች’ማ…” የፈፀመባቸውን በደል ራሳቸው ያውቁታል።

“የህግ ታራሚዎች” ስትሉ አንድ ነገር ትዝ… አለኝ። በነገው ዕለት “የፍቅር ስጦታ” ከሚበረከትላቸው ውስጥ፤ እንደ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዮናታን ተስፋዬ፣…ወዘተ፣ ወይም ደግሞ በፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተንገላቱ ያሉትን እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገረባ፣ ንግስት ይርጋ፣…ወዘተ፣ በማዕከላዊ፥ ቃሊቲ፥ ቂሊንጦ፥ ዝዋይ፥ ሸዋ ሮቢት፥… በአጠቃላይ በታወቁና ባልታወቁ እስር ቤቶች መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ይገኙበታል? ኧረ ለመሆኑ፣ ከእነዚህ ሰዎች ፊት ቆሞ “ኑ እስኪ ዛሬ ‘የፍቅር ቀን’ እናክብር?” የሚል የኢህአዴግ ባለስልጣን አለ? ይህን ለማድረግ የሚያስችል ከፀፀት የፀዳ ሕሊና ያለው ባለስልጣን ይገኛል? በእርግጥ የለም! እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው የኢህአዴግ ባለስልጣን በባትሪ ቢፈለግ አይገኝም። የኢትዮጲያ ሕዝብን “‘የፍቅር ቀን’ እናክብር?” ለማለት ደፍረቱን ከየት አገኛችሁ? ነው ወይስ በሕዝቡና በፖለቲካ እስረኞቹ መካከል ያለው ግንኙነት በግልፅ አልታያችሁም?

በአሁኑ ግዜ በሀገራችን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ። እነዚህ እስረኞች ተራ ወንጀለኞች አይደሉም። ሁሉም በሞያቸው የተከበሩ፤ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ ፀሃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥…ወዘተ ናቸው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም በአሸባሪነት ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው፣ አሊያም በተንዛዛ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተንገላቱ ያሉ ሰዎች ናቸው። ዋና ጥፋታቸው ደግሞ “የሕዝብ መብትና ነፃነት ይከበር!” ማለታቸው ነው። ስለዚህ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች የሕዝብ ድምፅ እና አሌኝታ ናቸው። አዎ…በእነሱ መታሰር የሕዝብ ድምፅ ነው የታፈነው። እንግዲህ ነገ በዚህ መልኩ ካፈናችሁት ሕዝብ ጋር “የፍቅር ቀን” ልታከብሩ ነው።

ሕዝብ ያሰበውን የሚናገረው፣ ፍቅርና ጥላቻውን የሚገልፀው በግልፅ መናገር ሲችል ነው። የኢትዮጲያ ህዝብ ግን እንኳን መናገር መተንፈስ ተስኖታል። በፍርሃት ልጓም አንደበቱ ተለጉሟል። ድምፁን የሚያሰሙለት፣ ብሶትና አቤቱታውን የሚገልፁለት የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ፀሃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥…ወዘተ ለእስርና ስደት ተዳርገዋል። ሕዝቡ የኢህአዴግን የፍቅር ስጦታ ለመቀበል ወይም ለመተው የሚናገርበት አንደበት ያስፈልገዋል። የህዝቡ አንደበት ግን ከፖለቲካ እስረኞቹ ጋራ አብሮ ታስሯል። እነሱ ከእስር ካልተፈቱ ሕዝቡ የእናንተን “የፍቅር ስጦታ” በአክብሮት ይቀበለው፣ አሊያም አሽቀንጥሮ ይጣለው በፍፁም ማወቅ አትችሉም።

ሕዝባዊ ተቃውሞ

የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ ፀኃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ …ወዘተ በሌሉበት ሕዝብ አፍ አውጥቶ እውነቱን አይናገርም። ምክንያቱም፣ በኢህአዴግ ካድሬ ጋር መጣላት፥ መጠቆር አይሻም። “ለምን?” ቢባል፤ ነገ ልጆቹን በሰላም ማሳደግ ይፈልጋል! ነገ በስራው መቆየትና ማደግ ይፈልጋል! ነገ ስኳርና ዘይት ይፈልጋል!… በአጠቃላይ፣ እውነቱን ከተናገረ የኢህአዴግ ጋሻ-ጃግሬዎች ነገ መውጫ-መግቢያ ያሳጡታል። ስለዚህ፣ ሕዝቡ የይመስል ውሸቱን ለኢህአዴግ ይነግረዋል። እውነተኛ ብሶትና ምሬቱን ግን፤ ለተቃዋሚ መሪዎች፣ ለታማኝ ጋዜጠኞች፣ ለሃቀኛ ፀሃፊዎች፣ ለመብቱ ለሚሟገቱ ወይም ለነፍስ አባቱ ይነግራል። እነዚህ ሁሉ በአሸባሪነት ከተከስሰው ሲታሰሩ እውነት ነው የታሰረው፣ የብዙሃን ድምፅ ነው የታፈነው። ሕዝቡን መተንፈሻ ነው ያሳጣው። እንዲህ በፍርሃት ከታፈነ ሕዝብ የመከራ ሲቃ እንጂ የፍቅር ሳቅ መጠበቅ ፍፁም አላዋቂነት ነው።

በአጠቃላይ፣ ሕዝብ የእናንተን የፍቅር ስጦታ ለመቀበልና ላለመቀበል የሚናገርበት አንደበት ያስፈልገዋል። በማዕከላዊ፥ ቃሊቲ፥ ቂሊንጦ፥ ዝዋይ፥ ሸዋ ሮቢት፥…በመሳሰሉት እስር ቤቶች መከራና ፍዳ እያዩ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ የህዝቡ አንደበት ይፈታል። የእናንተን የፍቅር ስጦታ በአክብሮት መቀበሉን አሊያም በንቀት አሽቀንጥሮ መጣሉን በግልፅ ይነግራችኋል። ይህ ካልሆነ ግን በፍርሃት የተለጎመ ማህብረሰብ ቢያፈቅሩት አያፈቅርም፣ ሲጠላም አይታወቅም። ለምሳሌ፣ ነገ የምትሰጡትን “የፍቅር ስጦታ” የተቀበለ እናንተን ፈርቶ፣ ያልተቀበለም እናንተን ሸሽቶ ነው። ከነገ ወዲያም በየስብሰባው ስትጠሩት የሚመጣው፣ የእናንተን የተለመደ ወሬ የሚሰማ መስሏችሁ ነው? አይደለም! ብሶትና ምሬቱን ለፈጣሪ እየነገረ ነው። አሁን ነገ “የፍቅር ቀን” ስትሉ ሕዝቡ “’የቀብር ቀን’ አርግላቸው” እያለ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡

Filed in: Amharic