>
8:45 pm - Tuesday January 31, 2023

ኬንያ ምርጫ (ዮናስ ሐጎስ - ናይሮቢ)

በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ምድር ለመጀመርያ ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ በስልጣን ላይ የነበረውና በድጋሚ ምርጫ አሸንፌያለሁ ብሎ ያወጀ መንግስት በፍርድ ቤት ውሳኔ ውጤቱ ሲሰረዝና ለድጋሚ ምርጫ ሲዘጋጅ ለማየት የበቃነው እዚህ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ ነው።
***
ለመሆኑ ወደዚህ ነጥብ ላይ እንዴት ደረስን የሚለውን ጠቅለል አድርገን በወፍ በረር ስናቃኘው…
***
የኬንያ ይዚህ ዓመት ምርጫ በችግሮች መታመስ የጀመረው ከምርጫው አንድና ሁለት ወራት አስቀድሞ ነው። በምርጫው ዘመቻ ጊዜ በመንግስትና ተቃዋሚ ደጋፊዎች መሐል የነበረው የሶሻል ሚድያ ጦርነት፣ የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ድንገተኛ ሞት በ2007ም በምርጫ ሰሞን ሕይወቱ ካለፈው የደህንነት ሐላፊ ጋር መገጣጠሙ የ2007ቱን ሁከትና ብጥብጥ ለመደገሙ እንደ አመላካች ምልክት መወሰዱ፣ መንግስት በከፍተኛ ወጪ የአድማ መበተኛ መሳርያዎችን ከውጭ ማስመጣቱና ወታደሮቹንና ፖሊሶቹን እንዲሁም የደህንነት ተቋም ሰራተኞችን ከምርጫው አንድ ወር አስቀድሞ ወደ 24 ሰዓት ስልጠና ውስጥ ማስገባቱ፣ ኤሌክትሮኒካሊ የምርጫውን ውጤት በቀጥታ ለሚድያዎችና ለሕዝብ ለማስተላለፍ የተቋቋመው የምርጫ ቦርዱ የኦንላይን ሰርቨር ዋና ሐላፊ ተገድሎ መገኘት እና የመሳሰሉት ነገሮች ምርጫው በሰላም እንደማያልፍ አመላካች ነበሩ።
***
የተፈራው አልቀረም ተቃዋሚዎች ምርጫው እንደተጭበረበረ ለመናገር የፀሐይ ብርሐንን አልጠበቁም። የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት እያስተላለፈ በነበረበት ምሽት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ የተቃዋሚዎቹ መሪ ራይላ ኦሞሎ ኦዲንጋ ምርጫው መጭበርበሩንና ወጤቱን እንደማይቀበሉ አሳወቁ። ወድያውኑ የተኮሰው የሁከት እሳት ውጤቱ ተጠቃልሎ እስኪወጣ እንዲቀዘቅዝ ተፅዕኖ ቢደረግበትም ምርጫ ቦርዱ ኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊ መሆኑን ካወጀበት ዕለት ጀምሮ ተቃዋሚዎች ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ እስከወሰኑበት ዕለት ድረስ ከ30 የማያንሱ ንፁሃንን ሕይወት ቀጥፏል።
***
ራይላ ኦሞሎ ኦዲንጋ ዛሬ ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወዲህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሳወቁት ለተቃዋሚዎች ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ወሳኙን ሚና የተጫወተው እንደ ታዛቢነት በምርጫው ላይ በነበረው ተሳትፎ ምርጫው መጭበርበሩን በማሳወቁ ከቀናት በኋላ በታክስ ማጭበርበር ፈቃዱን እንዲቀማ የተደረገው የኬንያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (KNHRC) ነው። ይህ ተቋም ምርጫውን በታዛቢነት ከተሳተፉ ሌሎች ዓለም ዓቀድና አህጉር ዓቀፍ ተቋማት በብቸኘነት ምርጫው መጭበርበሩን ደፍሮ ለመናገር የበቃ ተቋም ነው። ምርጫውን ሐገራችን የተወከልችበት የአፍሪካ ሕብረት፣ የካርተር ማዕከል፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ድርጅቶች በታዛቢነት ተሳትፈውበታል። የካርተር ማዕከልና የአፍሪካ ሕበረት ታዛቢዎች ምርጫው «ከአንዳንድ ቴክኒካል ስህተቶች» ውጭ ትክክለኛና ፍትሃዊ እንደነበር ነው ታዝበው የሄዱት።
***
አሁን ከመሸ ባሰባሰብኩት መረጃዎች በመንተራስ ወደዚህ ነጥብ ለመደረስ የተቻለበትን ሁኔታ ብዙ ኬንያውያን የኬንያታን ባለፈው ምርጫ በተነሳ ሁከት ላይ ለጠፉ ነፍሳት በአይሲሲ ቀርቦበት «ነፃ» የተባለበት ክስ ጉዳይ ጥሩ ሚና መጫወቱን ይናገራሉ። እነዚህ ኬንያውያን ኬንያታ ነፃ ይባል እንጂ ብዙ የወቅቱ ምስክሮች ሕይወታቸው እንዲጠፋ መደረጉን፣ ብዙ በርሱ ላይ ሊመሰክሩ በዓቃቤ ሕጓ ተመዝግበው የነበሩ ምስክሮች የደረሱበት ሳይታወቅ እንዲቀር በመደረጋቸው ምክንያት ነፃ መውጣቱን ነው የሚናገሩት። «አሁን ያንን መድገም አይችልም…» አለኝ አንዱ ኬንያዊ። «አሁን ያንን ለማድረግ በፍፁም ሊያስበው አይችልም።»
ከመሸ የተሰማው የኬንያታ መግለጫም ይህን በትክክል የሚያሳይ ሆኑዋል። ኡሁሩ ኬንያታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ «እንደማይስማሙበት» ነገር ግን ሁሉም ሰው ለህግ ተገዢ መሆን ስላለበት ውሳኔውን በመቀበል ለድጋሚ የምርጫ ቅስቀሳ እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል። «ስምንት ሚልዮን ሕዝብ የሰጠኝን ድምፅ ስድስት ሰዎች አይገባህም ብለውኛል። (የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ስድስት መሆናቸውን ልብ ይሏል) እኔ ደጋፊዎቼ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገቡ አልፈልግም። በድጋሚ በሚካሄደው የምርጫ ቀን እንደገና ወጥታችሁ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምፃችሁን ስጡኝ» በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።
***
ኬንያ ነፃነቷን ካገኘችበት ዕለት ጀምሮ ሁሉም ኬንያዊ በሐገሪቱ አንድነት ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት ዓቋም ነው ያለው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። አዎ ኬንያውያን ምንም ቢከፋቸው እንኩዋን ሆ! ብለው ትግል ይጀምራሉ እንጂ የመለያየት፣ የመገንጠል ነገር አውርተው አያውቁም። በ2007 ከ1000 ሰው በላይ በሞተበት ዓመፅ እንኳ ይህ ጉዳይ በአማራጭነት ሲቀርብ አልታየም። በዘንድሮው ምርጫ ክውጤቱና የምርጫ ቦርድ ውጤት መግለፅ በኋላ ግን የኬንያውያን የመነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ የነበረው ይህ የመገንጠል ጉዳይ ነው። የገዢው ፓርቲ አመራር የወጡበት የኪኩዩና ካለንሂን ብሔር የሰፈረበት የማዕከላዊው ኬንያና የተቀረው ኬንያ በመስሉ ላይ እንደምታዩት ለሁለት መከፈል አለበት የሚለው አጀንዳ ጭምጭምታው በተሰማበት አጭር ቀናት ውስጥ ከ40% በላይ የተቃዋሚዎችን ድጋፍ ማግኘቱ ለመንግስትም ሆነ ለተቀረው ኬንያዊ ከፍተኛን ድንጋጤ የፈጠረ ክስተት ሆኗል። ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤት ካልተሳካላቸው ሶስተኛና አራተኛ አማራጮች እንዳሏቸው በግልፅ ሲናገሩ መሰንበታቸውም ሶስተኛ አማራጭ ከመቶ በላይ የሆኑ የነርሱ አባላት የሆኑ የፓርላማ አባላትን በተመሳሳይ ቀን የስራ መልቀቂያ እንዲያስገቡ በማድረግ አሁን የተቋቋመውን መንግስት ማፍረስና በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ይህን የመገንጠል ጥያቄ አንስተው ሕዝቡ በሪፈንደም ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ነው። አሁን 40% ያህል ድጋፍ ያገኘው ይህ የመገንጠል ጥያቄ በትክክል ወደ ጠርጴዛው ሲቀርብ ከዚያ በላይ የሆነ ድምፅ ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን ብዙ ኬንያውያን ይስማሙበታል።
***
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሳኔ ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ያደረገው የምርጫ ቦርዱን ሲሆን ሕገ መንግስታዊ አሰራርን በመጣስ ከሕገ መንግስቱ ውጪ በሆነ መንገድ አሸናፊ አሳውቀዋል በማለት ጥፋተኛ አድርጓቸዋል። በምርጫው ውጤት ማሳወቅ ጊዜ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ወረቀቶች የምርጫ ቦርድ ትክክለኛ ማሕተም ያላረፈበትና የተቃዋሚዎችና ታዛቢ ተወካዮች ፊርማ ያላረፈበት መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ባለፉት 14 ቀናት ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን በውሳኔው ላይ አንብቧል። ፍርድ ቤቱ ለምርመራ የራሱን ባለሙያዎች ይዞ በመሄድ የምርጫ ቦርዱን ሰርቨር ያስመረመረ ሲሆን በሰርቨሩ ላይ ለሚድያ ይተላለፍ የነበረው ኡሁሩን አሸናፊ ያደረገው ድምፅ በዋና ፎርሞች (34A እና 34B) ላይ ከነበረው ውጤት የተለየ መሆኑን አረጋግጫለሁ በማለት የምርጫ ቦርድ ነሐሴ 8፣ 2007 ያደረገው ምርጫ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በውሳኔው አፅድቋል።
***
ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው።
***
በውሳኔው የዳኛው መዶሻ ጠረጲዛው ላይ ገጭ ባለበት ቅፅበት ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ፕሬዝደንትነት ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ወደ እጁ አስገብቷል። ምርጫው ከተካሄደበት ዕለት ነሐሴ 8 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቃለ መሐላ ያልፈፀመው ኡሁሩ ኬንያታ ሐገሪቷን ይመራ የነበረው በባለ አደራ ፕሬዝዳንትነት ስልጣን ሲሆን በዚህ ስልጣኑ ማድረግ የማይችላቸው ብዙ ክስተቶች ነበሩ። በሕጉ መሰረት ቃለ መሐላ ያልፈፀመ ፕሬዝዳንት ሐገሪቱን ወክሎ ምንም ዓይነት ስምምነት መፈረም አይችልም፣ የዳኞችን ስልጣን መቀየር አይችልም፣ ፓርላማውን መምራት አይችልምና አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በቀር የሐገሪቱ የደህንነት፣ ፖሊስና ወታደራዊ ተቋማትም መመርያ የሚቀበሉት ከሱ አይሆንም። አሁን ግን የዳኛው ውሳኔ ያለፈውን ምርጫ ዲስኩዋሊፋይ ካደረገው ዘንዳ በቀጣይ 60 ቀናቶች ውስጥ ሌላ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ኡሁሩ ኬንያታ ሐገሪቷን በሙሉ ፐሬዝዳንትነት ያስተዳድራሉ ማለት ነው።
***
ፍርድ ቤቱ በድጋሚው ምርጫ ላይ ምርጫ ቦርድ ሊያስተካክላቸው የሚገባ «የውስጥ ጉዳዮች» እንዳሉ በውሳኔው ላይ ያሳወቀ ቢሆንም ተቃዋሚዎች ግን ያላቸው ሐሳብ ከዚህ ለየት ያለ ነው። የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የምርጫ ቦርዱ ሐላፊዎች የሰሩት ስህተት በሐገሪቱ ሕግ ወንጀል በመሆኑ እንደሚጠየቁበትና የተቃዋሚው ጠበቆችም ከዛሬ ጀምሮ የምርጫ ቦርዱን ሐላፊዎች ለፍርድ ለማቆም ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። «ያለፈውን ምርጫ ያበላሸው ይህ የምርጫ ቦርድ የሚል ውሳኔ ሰምተን እየወጣን ይኸው ምርጫ ቦርድ በድጋሚ የሚደረገውን ምርጫ እንዲመራ መፍቀድ ጅልነት ነው» ያሉት ራይላ ኦዲንጋ የድጋሚው ምርጫ በነዚህ የምርጫ ቦርድ ሐላፊዎች እንዲካሄድ እንደማይፈልጉ በግልፅ አስቀምጠዋል።
***
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ባለፈው በተነሳው ሁከት ሰዎች የሞቱባቸው የኬንያ ክፍሎች ዘንድ ልክ እንደ ዓመት በዓል ሆኖ ነው የዋለው። እኔ ያለሁበት ኪቢራ የበዓል ስሜቱም አሁንም ድረስ ያልበረደ ሲሆን የስዉ ሁሉ ሰላምታ «ቲቢም» (እናሸንፋለን) ሆኗል። የራይላ የትውልድ ቦታ የሆነችውና በወታደራዊው ሐይል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ኪሱሙ ዛሬ የሟቾቻቸውን ፎቶ በያዙና በደስታ አስፓልት ላይ በሚንከባለሉ የራይላ ደጋፊዎች ስትታመስ የዋለች ሲሆን ማምሻውን ኪሱሙን ለቀናት ተቆጣጥሮ የነበረው ወታደራዊ ኃይል ኪሱሙን ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ መውጣቱን ማወቅ ተችሏል። በሶሻል ሚድያው የ«በድጋሚ እናሸንፋለን»ና «አሁንማ አታሸንፉንም!» ክርክሩ እንደ አዲስ ያገረሸበት ሲሆን ሐገሪቱ ሊትራሊ ከምርጫው በፊት ወደነበርችበት ሁኔታ እየተመለሰች ነው።
***
ማጠቃለያ
ምርጫው ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ባሉት 60 ቀናቶች ውስጥ መፈፀም ያለበት ሲሆን ትክክለኛውን ቀን የምርጫ ቦርድ በቀጣይ ቀናት ያሳውቃል። የድጋሚ ውድድሩ የሚደረገው በፕሬዝዳንታዊ ዕጭጩዎች ብቻ በመሆኑ ሌሎች የፓርላማ ተወካዮች ሰሞኑን ሲያደርጉ እንደሰነበቱት ቃለ መሐላ መፈፀማቸውንና ቢሮዎቻቸውን መረከብ ይቀጥላሉ። ከቀጣይ ሳምንት በሁዋላ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች እንደ አዲስ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመጫ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
***
ያም ተባለ ይህ ኬንያ በዴሞክራሲያዊ ሂደት በአፍሪካ ደረጃ ማንም ሐገር ያልደረሰበት ከፍታ ላይ መድረሷን ዛሬ ለዓለም አስመስክራለች! በምርጫው ሁከት የሞቱ ወጣቶችና ሕፃናት የሞቱለት ዓላማ እንደዚህ ሬሳቸው ሳይፈርስ እውን ሲሆን ለማየት መቻልና የኛን የ97 ሰማዕታት ዛሬም ድረስ የሞቱለት የተሰዉለት ዴሞክራሲ ውሃ በልቶት በአፍ ብቻ «ከፍታ» እየተባለ ቁልቁል እየተንሸራተትን መሆኑን በማስብ ጊዜ እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃዘን ይሰማኛል።

Filed in: Amharic