>
2:09 am - Tuesday December 7, 2021

ውሾቹን ተው በሏቸው! (ዳንኤል ክብረት)

 

በኦሮምኛ አንድ ድንቅ ተረት አለ፡፡ በአንድ የኦሮሞ መንደር ውስጥ ሮቤል መገራ የሚባሉ ጥበበኛ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን የሁለት ጎረቤታሞች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ ያያሉ፡፡

እኒህ ጥበበኛ ሽማግሌም «እነዚህን ውሾች እንገላግላቸው፤ ያለበለዚያ ችግራቸው ለሁላችንም ይተርፋል? በዓለም ላይ ችግር የሚነሣው ከአጥንት በላይ ማሰብ በማይችሉ ውሾች የተነሣ ነው» ይላሉ፡፡

በአካባቢው የነበሩ ሽማግሌዎች እና መንገደኞችም በሽማግሌው አባባል ተገርመው «ሁለት ውሾች ተጣልተው ምን ሊያመጡ ነው» እያሉ ሳቁባቸው፡፡

በዚህ መካከል ከሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል አንድ ልጅ ወጣና የውሾቹን ጠብ ተመለከተ፡፡ የእርሱ ውሻ የተበደለ ስለመሰለው ፍልጥ አምጥቶ ያኛውን ውሻ ደበደበው፡፡

ወዲያውም ከሌላኛው ቤት ሌላ ልጅ ወጣና ያኛውን ውሻ መደብደብ ጀመረ፡፡

ነገሩ ወደ ሁለቱ ልጆች ተዛመተና በውሾቹ ምትክ ልጆቹ ይደባደቡ ጀመር፡፡

ሽማግሌውም «እባካችሁ እነዚህን ልጆች አስታርቁ» አሉ፡፡ በሥፍራው የነበሩትም «ተዋቸው ይዋጣላቸው» ብለው እንደ ቀልድ አለፉት፡፡

ልጆቹ እየተደባደቡ እያሉ የአንዱ እናት ብቅ አለች፡፡ ወዲያውም ያኛውን ልጅ በፍልጥ ታንቆራጥጠው ጀመር፡፡

የልጇን ጩኸት የሰማቺው ሌላዋ እናትም መጣች፡፡

የልጆቹ ጠብ ቀረና ድበድቡ በሁለቱ እናቶች መካከል ሆነ፡፡

ሮቤል መገራም «እባካችሁ ይህ ጠብ ተዛምቶ ሁላችንንም ከማካተቱ በፊት ገላግለን እናስማማቸው» አሉ፡፡

ተመልካቾቹ ግን የሁለቱን ጠብ እንደ ነጻ ትግል እያዩ ይዝናኑ ነበር፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎችም «ሁለት ሴቶች ተጣልተው የት ይደርሳሉ» እያሉ ንቀው ተውት፡፡

በግርግሩ የከበቡትን ሰዎች እየጣሰ አንድ ሰው ወደ መካከል ገባ፡፡ ያንደኛዋ ባል ነበር፡፡ እንዴት ሚስቴን ትመቻታለሽ ብሎ ያቺኛይቱን ሴት መደብደብ ያዘ፡፡

ይኼኔ ነገሩን የሰማው ሌላኛው ባልም ሲሮጥ መጥቶ ድብድቡን ተቀላቀለ፡፡ ሮቤል መገራ አሁንም «እባካችሁ ገላግሏቸው፤ ይህ ጠብ ለሀገር ይተርፋል» ሲሉ ተናገሩ፡፡ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡

ሁሉም የራሱን ልጅ፣ ሚስት እና ቤት ብቻ ይጠበቅ ነበር፡፡ ወንዶቹም ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እንዳይገቡ ይቆጡ ነበር፡፡

የሁለቱ ባሎች ጠብ ተባባሰ፡፡ ሕዝቡም ከብቦ ያይ ጀመር፡፡
በዚህ መካከል የሰውዬው ወገኖች ነን ያሉ ያንደኛዋን ባል መደብደብ ያዙ፡፡ ተመልካች ሆነው ከቆሙት መካከል የዛኛው ወገን ነን የሚሉ ደግሞ ያኛውን ይዘው ይደበድቡ ጀመር፡፡

እንዳጋጣሚ የሁለቱ ሰዎች ጎሳች የተለያዩ ስለነበሩ ጠቡ ወደ ጎሳ አደገ፡፡ ዱላ እና እጅ ብቻም ሳይሆን የጦር መሣርያም ተጨመረበት፡፡ ቤት ንብረት መዝረፍ፣ ማቃጠል እና መግደል እየተባባሰ መጣ፡፡ መንደሩም የጦርነት አውድማ ሆነ፡፡

ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት ሰዎች ሞቱ፡፡

በስንት መከራ ጠቡ ቆመ፡፡ ሮቤል መገራም አዘኑ፡፡ «ውሾቹ ሲጣሉ ብናስቆማቸው ኖሮ ጎሳዎቹ አይጣሉም ነበር» አሉ፡፡

ሽማግሌዎቹ ጉማ ተቀመጡ፡፡

በባህሉ መሠረት ለእያንዳንዱ ለሞተው ነፍስ ከሌላው ወገን ሰው ይገደላል ወይንም መቶ መቶ ከብት ይሰጣል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሁለቱም ወገን ስምንት ስምንት መቶ ከብት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በሞቱት ምትክ ከሌላው ወገን ሰው ይገደልም ከተባለ በተጨማሪ አስራ ስድስት ሰዎች ሊገደሉ ነው፡፡ የሟቾቹም ቁጥር ወደ ሠላሳ ሁለት ከፍ ሊል ነው፡፡ ይህ ነገር ሽማግሌዎቹን አስጨነቀ፡፡

ይኼኔ ሮቤል መገራ ተነሡ፡፡ «ቅድሞ እኔን ሰምታችሁኝ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፡፡ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን እንጂ ስለ ሌሎች ግድ ስለሌለን ዕዳው በመጨረሻ እኛው ላይ መጣ፡፡ ውሾቹን ተው ማለት አቅቶን እዚህ ደረጃ ደረስን፡፡ ምን ጊዜም ጦርነቶች የሚነሡት ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡

ጎረቤት እና ጎረቤት፣ ጎሳ እና ጎሳ፣ ንጉሥ እና ንጉሥ፣ ሀገር እና ሀገር፣ እስላም እና ክርስቲያን፣ መንደር እና መንደር፣ የሚጣላው ውሾቹን ተው የሚል እየጠፋ ነው፡፡ የጦርነት መነሻ ውሾች ናቸው፡፡

ውሾቹ በአጥንት የጀመሩት ጠብ ሕይወት አስከፈለን፡፡ እነዚህ ውሾችኮ ከአጥንት በላይ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ውሾች ናቸው፡፡ ዓላማቸው አጥንት መጋጥ ብቻ ነው፡፡ አገር ቢጠፋ፣ ሕይወት ቢጠፋ፣ ንብረት ቢጠፋ እነርሱ ምን ጨነቃቸው፡፡
እንዴት ከአጥንት በላይ ማሰብ የማይችሉ ውሾች ይህንን ሁሉ ዋጋ ያስከፍሉናል?

«እነዚያን ውሾች ለያዩዋቸው ስላችሁ ሁላችሁም የእናንተ ውሾች አለመሆናቸውን ብቻ ነበር የምታዩት፡፡ ሌሎች ተበጥብጠው እኛ እንዴት ሰላም እንሆናለን? ሌሎች እየተዋጉ እንዴት እኛ በደኅና እናድራለን? ሌሎች ተርበው እንዴት እኛ እንጠግባለን? የማይሆን ነገር ነው፡፡

በሉ አሁንም ሌላ ሕይወት ማጣት የለብንም፣ ከብቶቻችንንም ማጣት የለብንም፤ ከሁለቱም ወገን የየአንገ ታችሁን የብር ማተብ አምጡ፤ ያንንም ሰብስባችሁ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፣ ሁሉም ጦሱን ይውሰድ፤ እናንተ ግን ይቅር ተባባሉ» ብለው አስታረቋቸው ይባላል፡፡

***

ውሾቹን «ተው» ካላልናቸው የመጨረሻውን ውጤት ማንም ሊገምተው አይችልም፡፡ ሂትለር እና ሞሶሎኒ የሚባሉ ውሾች ሲነሡ ማንም «ተው» ማለት አቅቶት ዓለምን በእሳት ለበለቧት፡፡ በወቅቱ አይሁድ እየተሰቃዩ መሆኑን የተለያዩ ምንጮች እየተናገሩ ምዕራባውያን ግን ዓይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው በበርሊን ኦሎምፒክ ሂትለርን ሲያመሰግኑ ሰነበቱ፡፡ እንዲህ በመጨረሻ ጦሱ ለእነርሱም ሊተርፍ፡፡

ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በዓለም ማኅበር ተገኝተው ውሾቹን «ተው» በሏቸው ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ብዙዎች ራሳቸው እንደ ውሻ በመጮኽ የንጉሠ ነገሥቱን ንግግር ለመበጥበጥ ሞከሩ እንጂ አልሰ ሟቸውም ነበር፡፡

በመጨረሻ ግን የውሾቹ ጠብ ወደ ዓለም ጦርነት ተቀየረ፡፡

***
ዛሬ ዓለም በኢራን የኑክሌር መሣርያ እንዲጨነቅ ያደረገቺው ራሷ አሜሪካ ናት፡፡ ኢራኖች ኒኩልየር የሚባል መኖሩን ባላወቁበት ዘመን የግድ ኒኩልየር ካልኖራችሁ ብላ በራቸውን አንኳኩታ ስትሄድ ዓለም በዝምታ ነበር ያያት፡፡

ያኔ ውሾቹን «ተው» የሚላቸው ቢኖር እንዲህ እሥራኤል እና አሜሪካ በጭንቀት ውለው አያድሩም ነበር፡፡

***
አሜሪካ ሶቪየት ኅብረትን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ቢን ላድንን ስታሠማራ ተይ የሚላት ባለመኖሩ ራስዋ ያመጣችው መከራ ለእርሷም ለዓለምም ተረፈ፡፡ ያሳደግኩት ውሻ ነከሰኝ፣ የቀለብኩት ፈረስ ጣለኝ እንደሚባለው ሆነ፡፡

***
ሩዋንዳ ላይ ሬዲዮ ከፍተው ጎሳ ከጎሳ የሚያጣላ ፕሮግራም የሚያራምዱትን፣ ግደሉ ጨፍጭፉ እያሉ የሚያቅራሩትን ውሾች በወቅቱ ፈረንሳዮች በዝምታ ነበር ያዩዋቸው፡፡ የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ሲጀመር የተባ በሩት መንግሥታት ድርጀትን ጨምሮ ብዙዎች አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆኑ፡፡ ውሾቹን ተው የሚል ጠፍቶ ውሾቹ ያመጡት ጣጣ ምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካን የሚያቃጥል እሳት ወለደ፡፡

ለዚህ ነው ከአጥንት በላይ ማሰብ የማይችሉትን ውሾች በጊዜ «ተው» ማለት የሚያስፈልገው፡፡

***
ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህ ቦታ እንዲህ ያለ ቤተ እምነት ተቃጠለ ሲባል በዝምታ እየታየ ነው፡፡ ይህ እኩይ ተግባር ማንኛውንም የእምነት ማኅበረሰብ የሚወክል ነው ተብሎ ፈጽሞ አይታመንም፡፡ ነገር ግን ሙስሊ ሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች ይህንን እሳት የሚለኩሱትን ውሾች «ተው» ልንላቸው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ፍጻሜው ለሁላችንም ይደርስና ከባድ ዋጋ ይጠይቀን ይሆናል፡፡ እነዚህ ውሾች ከዕለት አጥንት አርቀው ማሰብ አይችሉም፡፡ ለጊዜውከሌላው ጋር ተሻምተው አንድ አጥንት ማግኘታቸውን ብቻ ነው የሚያውቁት፡፡

***
እዚህ ዓይን ማጥፋት፣ እዚያ አሲድ መድፋት፣ እዚያ ሕፃን መድፈር፣ እዚህ ግብረ ሰዶም፣ እዚያ አካል ማጉደል፣ እዚህ በፈላ ውኃ መንከር ሚዲያዎቹ ይጮኻሉ፣ በሹክሹክታ ይነገራል፣ አንድ ሰሞን ጉድ ይባላል፡፡ ውሾቹን ተው የሚላቸው ግን እየጠፋ ነው፡፡

እነዚህን ሕፃናትን የሚደፍሩትን፣ የእኅቶቻችንን አካል የሚያጎድሉትን፣ በአውሬነት መንፈስ አረመኔ ተግባር የሚፈጽሙትን ውሾች ተው የሚል አልተገ ኘም፡፡ ምናልባት ሁላችንም የምንነቃው የሁላችን በር ሲንኳኳ፣ የሁላችንም ልጆች ሲነኩ፣ የሁላችንም አካል ሲጎድል፣ የሁላችንም አኅቶች ሲደፈሩ ነው ማለት ነው፡፡ ኧረ ውሾቹን ተው እንበላቸው፡፡

***
ገንዘብ ከማግኘት ባለፈ ማሰብ የማይችሉ፣ የሀገር ክብር፣ የዜጎች መበት፣ የሰው ልጅ ሰብአዊነት የማይገዳቸው ላኪዎች አቀባዮች እና ተቀባዮች ከየገጠሩ ምንም የማያውቁ ኢትዮጵያውያንን እየመለመሉ፣ ሕጋዊ በሚመስል ሕገ ወጥነት ወደ ዓረቡ ዓለም ሲያሻግሩ ዝም እየተባሉ ነው፡፡ ውሾቹ አጥንታቸውን ብቻ እንደሚያዩት እነርሱም ገንዘባቸውን ብቻ ነው የሚያዩት፡፡ የሚላከው ሰው የት ይውደቅ የት፣ ምን ይግጠመው ምን፣ እንዴት ይሁን እንዴትም አያገባቸውም፡፡ ወገን ግን እየተሰቃየ ነው፡፡

***
የሰው ኃይል ወደ ዓረብ ሀገር መላክ በኛ አልተጀመረም፡፡ ሕንዶች፣ ፊሊፒኖች፣ ፓኪስታኖች፣ ባንግላዴሾች፣ ሱዳኖች፣ ግብጾች ይጎርፋሉ፡፡ የኛ ሰውን ያህል ግን መከራ የበዛበት የለም፡፡ ለምን? ውሾቹን ተው የሚል በመጥፋቱ፡፡ የናንተ ጦስ ለሀገር እና ለወገን ይተርፋል ብሎ የሚቆጣ በመጥፋቱ፣ መሥመር የሚያስይዘ በመጥፋቱ፡፡ ዛሬ ዛሬ አንዳንድ ሀገሮች አበሻ አታምጡበን፣ ቪዛ አንሰጥም፣ አንቀበልም እስከማለት የደረሱት ኃላፊነት የማይሰማቸው እንደ ውሾች አጥንታቸውን ብቻ የሚያስቡ ሰዎች በሚፈጽሙት ሕገ ወጥነት ምክንያት ነው፡፡

አንዱ እምነት በሌላው ላይ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ፣ አንዱ ፓርቲ በሌላው ላይ ቂም እንዲቋጥር፣ እንዲያዝን፣ የጥላቻ ስሜት እንዲያዳብር፣ የሚያደርጉ ትምህርቶች፣ ጽሑፎች፣ ንግግሮች፣ ዘፈኖች፣ አሠራ ሮች፣ በዝምታ እየታዩ ነው፡፡ እነዚህን ከጊዜያዊ ሥልጣን፣ ሹመት፣ ገንዘብ፣ ግብዣ፣ ጭብጨባ ባለፈ ማሰብ የማይችሉ ውሾችን ተው ማለት ይገባል፡፡ አንዳንዶቻችን የኛ በመሆናቸው፣ ሌሎቻችን የተነኩት ከኛ ውጭ ያሉት በመሆናቸው ዝም እያልናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ቤታችን የተሠራው በመስተዋት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ውሾቹን ተው ካላልናቸው እነርሱ እንደ ዋዛ መወራወር የጀመሩት ድንጋይ በመጨረሻ የሁላችንንም ቤት ሊፈረካክሰው ይችላል፡፡

እናም ውሾቹን «ተው» በሏቸው”

Filed in: Amharic