>

እንኳን ‘ኢህአዴግ ሰው በላ’ ‘አበበ በሶ በላ’ ብለንም መጻፍ አልቻልንም፡፡”(ማህሌት ፋንታሁን)

ልክ የዛሬ አንድ አመት [ነሃሴ 28/2008] ነበር የቂሊንጦ እሳት ቃጠሎ አደጋ የሚባል ክስተት የተፈጠረው፡፡ ከዛች ቀን በኃላ በቂሊንጦ እስር ቤት ብዙ ታሪኮች ተለዋውጠዋል፡፡ በቃጠሎው ቀን እና እስረኞች የተዘዋወሩበት ቦታ እስከተለጠፈበት ቀን ድረስ ቂሊንጦ እና አካባቢው በእስረኛ ቤተሰቦች ጭንቀት፣ ሃዘን እና ለቅሶ ተሞልቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙ የቅርብ ጓደኞቼ እንዲሁም በስም የማቃቸው የፖለቲካ እስረኞች ቂሊንጦ ስለነበሩ ጭንቀት፣ ሃዘን እና ቁጭት ተሰምቶኛል፡፡ በቂሊንጦ ስማቸው የተለጠፈላቸው የእስረኛ ቤተሰቦች ጉዟቸውን ወደ ዝዋይ እና ሸዋሮቢት ሲያደርጉ፤ ስማቸው ያልተለጠፈ እስረኛ ቤተሰቦች ሃዘን እና ምሬት የከፋ ነበር፡፡ ጥቂቶች ሲቀሩ አብዛኛዎቹ ከሞት የተረፉ በቂሊንጦ የነበሩ እስረኞች ወደ ዝዋይ እና ሸዋሮቢት ተወስደው የሰው ልጅ ሊደርስበት የማይገባው ጭካኔ እና ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ምግብ ከቆሎ ውጪ አይሰጣቸውም ነበር፡፡ ልብሶቻቸው እና መጫሚያዎቻቸው እንዲሁም ሌሎች ንብረቶቻቸው የከፊሎቹ ስለተቃጠለ የከፊሎቹ ደግሞ ማረሚያ ቤቱ ስለዘረፋቸው የሚለብሱት እና የሚጫሙት አልነበራቸውም፡፡ ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ እጃችሁ አለበት ተብለው የተካሄደባቸው ምርመራ ዘግናኝ ነው፡፡ የመጨረሻው ምርመራ የተካሂደው ሸዋሮቢት ነው፡፡ ከዝዋይም፣ ከቃሊቲም፣ ከቂሊንጦም ተመርጠው ወደ ሸዋሮቢት ተጫኑ፡፡ ከነሃሴ 28/2007 እስከ ህዳር 10/2009 ግፍ ሲፈጸምባቸው ከቆዩት እስረኞች ውስጥ 38ቱ ህዳር 13/2009 ቀን በተፃፈ ክስ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ የተመሰረተባቸው ክስ ባጭሩ “አመፅ እና ሁከት በማስነሳት ከእስር በማምለጥ ከሽብር ቡድኑ ጋር እንቀላቀላለን በሚል ከህዳር ወር 2008 ጀምሮ በማቀድ፡ በማረሚያ ቤቱ በግንቦት 7፣ ኦነግ እና አልሻባብ ተጠርጥረው የተከሰሱትን የሽብር ቡድን አባላት የሆኑትን በማሰባሰብ እና በማደራጀት . . . . . . . . . . . . . . እቅድ በመያዝ ነሃሴ 28/2008 ቀን በየዞኑ የሚገኙ ታራሚ አባላትን ለአመፅ በመቀስቀስ . . . . . ባደራጇቸው የሽብር ቡድን አማካኝነት ንብረት እንዲወድም እና 23 የሚሆኑ ታራሚዎች በከባድ ሁኔታ ተደብድበው በእሳት እንዲቃጠሉ እና ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገዋል” የሚል ነው፡፡
የቀረበባቸው ክስ ህዳር 13/2009 ቀን የተፃፈ ይሁን እንጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸውን የሰሙት ህዳር 23/2009 ቀን ነው፡፡ በቀጣይ በነበራቸው ቀጠሮም [ታህሳስ 14/2009] ‘በቃጠሎው ወቅት ህይወታቸውን ላጡ ወንድሞቻችን የህሊና ፀሎት እናደርጋለን’ ካሉ በኋላ ለደረሰው ቃጠሎ እና ህይወት መጥፋት ተጠያቂው ያሰራቸው አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመናገር ዩኒፎርማቸውን አውልቀው ሰውነታቸውን በችሎት ያሳዩም አሉ፡፡ ከ38ቱ ውስጥ አብዛኛዎቹ በሽብር የተከሰሱ ወይም ተከሰው የተፈረደባቸው ናቸው፡፡ የመዝገቡ ስም የተሰየመውም የሽብር ክስ ቀርቦበት 10 ዓመት በተፈረደበት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ሲሆን፤ ሌሎች በሽብር የተከሰሱ፤ አበበ ኡርጌሳ፣ ፍቅረማሪያም አስማማው፣ ወልዴ ሞቱማ፣ አቤል ከበደ፣ ደሴ አንዳርገው፣ አግባው ሰጠኝ፣ አንጋው ተገኝ፣ ደረጀ መርጋ፣ ናአል ሻሚሮ፣ ቶሎሳ በዳዳ፣ ዲንሳ ፋፋ፣ ኡመር ሁሴን፣ ኢብራሂም ካሚል፣ ሸህቡዲን ነስረዲን፣ ፍፁም ቸርነት፣ አጥናፍ አበረ፣ እስማኤል በቀለ፣ ሰይፈ ግርማ፣ ከድር ታደለ፣ ከበደ ጨመዳ እንዲሁም አሸናፊ አካሉ ከተከሳሾቹ ውስጥ ይገኙባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና ሚፍታህ ከድር አመፁን በገንዘብ ሲረዱ እና ሲያበረታቱ ነበር በሚል በክሱ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ፣ አበበ ኡርጌሳ እና እስማኤል በቀለ ቃጠሎው በተነሳ ወቅት ለብቻቸው ጨለማ ክፍል ነበሩ፤ እንዲሁም ፍቅረማሪያም አስማማው ተፈርዶበት ዝዋይ የነበረ ሲሆን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በቃሊቲ ህክምና በመከታተል ላይ ነበሩ፡፡
ሌላው ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ 2ኛ ክስ የተመሰረተው ተጨማሪ 121 እስረኞች ላይ ነው፡፡ ክሳቸው በቀጥታ ንብረት በማጥፋት እና የእስረኞችን በእሳት እና በድብደባ በመግደል ተሳታፊ ናቸው በሚል ነው ክሱ የቀረበባቸው፡፡ በተጨማሪም 5ት የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ለብቻቸው ለእስረኞች ብር ሲያስገቡ ነበር፣ ሲላላኩላቸው ነበር በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ሸዋሮቢት በድብደባ እና በስቃይ የታጀበ “ምርመራ” አሳልፈውም ክስ ያልተመሰረተባቸው ብዙ አሉ፡፡

በአዲሱ ክሳቸውም ሆነ ቀድሞ ተከሰውበት በነበረው ክስ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ ንብረቶቻቸውን እንደተዘረፉ፣ በግዳጅ ቃላቸውን እንዲሰጡ እንደተደረጉ ሲገልፁ ነበር፡፡ ከሸዋሮቢት ከተመለሱ በኋላም ለብቻ እጃቸውን እና እግራቸውን በካቴና ታስረው በጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጡ መደረጋቸውን፣ ገንዘብ እንደማይገባላቸው፣ ከቤተሰብ እንዳይገናኙ መደረጋቸውን፣ እና ሌላም ማረሚያ ቤቱ ሚበድላቸውን ፍርድ ቤቱ በፈቀደላቸው ጊዜ ይናገራሉ፡፡ እስረኞቹ ሲናገሩ በምሬት እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ብሞትም ልሙት ብለው መሆኑ ያስታውቃል፡፡

“ሸዋሮቢት ከሞት ነው ተርፈን የመጣነው፡፡ ከዛ መልስም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አንችልም፡፡ ቤተሰብ አይጠይቀንም፡፡ እስክሪፕቶ ወረቀት እና መፅሃፍ አይገባልንም፡፡ እንኳን ‘ኢህአዴግ ሰው በላ’ ‘አበበ በሶ በላ’ ብለንም መጻፍ አልቻልንም፡፡” አባይ ዘውዴ፡፡ አባይ ዘውዱ በሰሜን ጎንደር የመኢአድ አመራር ነው፡፡ በተመሰረተበት የሽብር ክስ 4ዓመት ከ2ወር ተፈርዶበታል፡፡ ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ ክስ አልቀረበበትም፡፡

“እጅና እግራችን በካቴና ታስረን ነው የምናድረው፡፡ እሳቱን ማቃጠላችሁን እመኑ እየተባለን ነው ይሄ ሁላ ስቃይ የሚደርስብን፡፡ ወይ አቃጥለናል በሉ፤ ወይ ያቃጠሉት ላይ መስክሩ፡፡ አለበለዚያ በሙሉ አካልም ሆነ በህይወት አትወጡም ብለውናል፡፡” ደረጄ መርጋ፡፡ ደረጄ መርጋ ከኦሮሚያ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከነ በቀለ ገርባ ጋር በተመሳሳይ መዝገብ የሽብር ክስ የቀረበበት ሲሆን በቂሊንጦ ቃጠሎ ምክንያት ከተከሰሱ 38 ተከሳሾች ውስጥ ነው፡፡ ደረጄ መርጋ ይህን ፍርድ ቤት በተናገረ እለት የማረሚያ ቤት ሃላፊ የተባለው ድርጊት እንደማይፈፀም ለዳኘቹ ተናግረው ሳይጨርሱ ደረጄ እጁን ከፍ አድርጎ በማሳየት ከእጁ ጋር በመዋል በማደሩ ምክንያት ከእጁ አልፈታ ያለውን ካቴና አሳይቷል፡፡ ዳኞችም በአስቸኳይ እንዲፈታለት ቢያዙም የማረሚያ ቤት ሰዎች ካልተሰበረ በቀር መክፈት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ተናግረው ከነካቴናው ችሎቱን ፍርድ ቤት ውስጥ ሊከታተል ተገዷል፡፡

“ምግብ ከቆሻሻ ገንዳ ላይ እየለቀምን መብላት ጀምረናል፡፡ ንብረታችን ተዘርፈናል፡፡ ተደብድበናል፡፡ እኔ ፍርድ ቤት ስመላለስ 2ዓመት ከ10 ወሬ ነው፡፡ ድምፄ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ሁሉ ነገር ከአቅሜ በላይ ሆኗል፡፡ ያለንበት ሁኔታ ከምገልፅላችሁ በላይ ነው፡፡ ይህን በመናገራችንም የሚደርስብን ነገር አለ፡፡ ማረሚያ ቤቱ ሽፍታ ነው፡፡ በራሱ ችግር የመጣውን አደጋ እኛ ነን በሉ እያሉን ነው፡፡ እኛ የሰጠናችሁን የወንጀል ካባ መልበስ አለባችሁ እያሉን ነው፡፡ ችሎት በመረበሻቸው ነው ጨለማ ክፍል ያደረግናቸው እያሉ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ችሎት እረብሸን እንኳን ቢሆን ችሎት የረበሸ እስረኛ የሚቀጣው ፍርድ ቤት ነው እንጂ ማረሚያ ቤት አይደለም፡፡” እስማኤል በቀለ፡፡ እስማኤል ከአልሻባብ እና አልቃየዳ ጋር ግንኙነት አላህ ተብሎ ከሌሎች 22 ሰዎች ጋር ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን በቅርቡ የ15ት አመት ፍርድ ተወስኖበታል፡፡ ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የሽብር ክስ ከተመሰረተባቸው 38 ውስጥ አንዱ ነው፡፡
“ሸዋሮቢት እንደ በግ ተሰቅለናል፡፡ ወይ እናንተ አዛችሁ ከሆነ ንገሩን፡፡ ፍረዱልን አላልንም፡፡ ፍረዱብን ነው የምንለው፡፡ . . . . ያላበድነው ራሱ በእ/ር ሃይል ነው፡፡” አቤል ከበደ፡፡ በሽብር ክስ ተመስርቶበት በቅርቡ 4ዓመት ከ5ት ወር ተፈርዶበታል፡፡ ከ38ቱ ውስጥ ነው፡፡

“ለቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠያቂ ነህ ተብዬ በደረሰብኝ ድብደባ ብዙ ስቃይ አሳልፌአለው፡፡ ክስም ተመስርቶብኛል፡፡ አብሮኝ የተከሰሰው ሰጠኝ ሙሉ በቃጠሎው ሰአት ሞቷል፡፡ በጥይት ይሁን በእሳት እሱን እ/ር ነው የሚያውቀው፡፡ ሰጠኝ ለእናቱ አንድ ልጅ ነው፡፡ ሰጠኝን ገድያለው ብለህ እመን እየተባለ አንድ አይምሮ በሸተኛ የሆነ እስረኛ ሲደበድቡት አይቻለው፡፡ እኔም የሰጠኝ ሙሉን መሞት ከተናገርኩ የእሱ እጣ እንደሚደርሰኝ ነግረውኛል፡፡ ያለበት አልታወቀም የሚሉት ውሸታቸውን ነው፡፡” መሳይ ትኩ አባሪው [በአንድ መዝገብ የተከሰሰ] የነበረው ሰጠኝ ሙሉ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እየቀረ ማረሚያቤቱ ያለበትን ስላላወቅን ነው የሚል ምላሽ በሰጠ ወቅት የተናገረው፡፡ መሳይ ትኩ የቀድሞ የአንድነት አባል የነበረ ሲሆን ቀድሞ በቀረበበት የሽብር ክስ በቅርቡ 4ዓመት ተፈርዶበታል፡፡ ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘም የወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው 121 እስረኞች መሃከል ይገኝበታል፡፡

“እናንተን ላለማሰልቸት እና ላለማስጨነቅ ብዬ ነው ዝም የምለው፡፡ ጥቅምት/2007 ታስረን መጋቢት/2007 ነው የተከሰስነው፡፡ ሸዋሮቢት ያሳለፍኩትን ስቃይ በቃላት መግለፅ አልችልም፡፡ ጤናዬን አጥቻለው፡፡ በጠላትነት ተፈርጄ 7ወር የአይምሮ በሽተኛ፣ ግብረሰዶማውያን እና ዱርዬዎች ለብቻ ከሚቀመጡበት ክፍል ነበርኩ፡፡ በማረሚያ ቤት ውስጥ የአንድ ጎሳ የበላይነት ነው የሰፈነው፡፡ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ለህግ፣ ለህሊናችሁ እና ለእ/ር ብላችሁ ትሰራላችሁ፤ አንድ ሁለት ዳኛ አይጠፋም ብለን ነው የምንመጣው፡፡ እዚህ ፍርድ ቤት የሚያደርሱብንን በተናገርን ቁጥር ስንመለስ ሁኔታዎች ይብሱብናል።” ተስፋዬ ታሪኩ፡፡ ተስፋዬ በጎጃም የመኢአድ አመራር ነው፡፡ በጥር ወር 2007 በሽብር ተጠርጥረሃል ተብሎ ታሰረ፡፡ ሰኔ ወር 2009 ላይ ከቀረበበት ክስ “ነፃ” ተብሎ ከእስር የወጣ ነው፡፡ ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ ክስ አልቀረበበትም፡፡

ከላይ ያነበባችኋቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሽብር ክሶችን የሚያዩት የከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ እና 19ኛ ችሎት ዳኞች በዚህ አመት ስራ ከጀመሩ በኋላ ከክሱ ጎን ለጎን የተከሳሾችን በምሬት የተሞላ አቤቱታ ፈቃዳቸው በሆነ ሰዓት ሲሰሙ ነው የከረሙት፡፡ ዳኞቹ መፍትሄ ያሉትን ነገር ሲያዙ ማረሚያቤትም የዳኞች ትእዛዝ ሳያከብር አልፎ አልፎም እውነታውን የካደ ምላሽ እያቀረበ ተከሳሾቹም መሬት ጠብ የሚል ምላሸ ሳይሰጣቸው የስቃይ ህይወት ከጀመሩ ይኸው አንድ አመት ሞላቸው፡፡ ክሱ ከተመሰረተባቸው አስር ወራት ቢቆጠሩም የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰምተውም አላለቁም፡፡ እስካሁን ከተሰሙት ውስጥ የረባ ምስክርነት የሰጠ ምስክር አለያሁም፡፡ <“ግ7 እና ኦነግ ደርሰዋል” “መንግስት አብቅቶለታል” “ኦሮሞ እና አማራን የሚያጣላው ኢህአዴግ ነው” እያሉ “አማራ” “ኦሮሞ” ሆነው ተሰብስበው ያወራሉ፡፡ ለግ7 እና ኦነግ እስረኞችን መልምለዋል፡፡ ስኳር፣ በሶ እና ገንዘብ ሲሰጣጡ አይቻለው፡፡ አማራዎችን የሚሰበስበው መቶ አለቃ ማስረሻ ነው፡፡ ኦሮሞዎቹን የሚሰበስበው ወልዴ ሞቱማ ነው፡፡ ስኳር በሶ እና ገንዘብ የሚሰጡት ዶ/ር ፍቅሩ እና ሚስባህ ናቸው፡፡> አይነት ምስክርነት ነው የሚሰጡት ምስክሮቹ፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጣርቼ አቀረብኩ ባለው ሪፖርት ላይ የእስረኞቹ ህይወት ያለፈው በቃጠሎ እና በድብደባ ብቻ መሆኑን ቢገልፅም፤ በጥይት ተመተው ሲወድቁ ያዩአቸው እስረኞች እንደነበሩ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃላቸውን ሲሰጡ ሰምቻለው፡፡ አቃቤ ህግ አሰማለው ካለው 85 ምስክሮች ግማሹንም አላሰማም፡፡ ቀሪ ምስክሮችን እንዲያሰማ ከታህሳስ 23/2010 እስከ ጥር 3/2010 ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

[ሚስባህ ከድር፣ አግባው ሰጠኝ እና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ቀድሞ ከቀረበባቸው ክስ “ነፃ” የተባሉ ሲሆን ይህ አዲስ ክስ ባይኖርባቸው ከእስር ውጪ መሆን የነበረባቸው ናቸው፡፡ ፍቅረማርያምም ከሁለት ወር በኃላ ፍርዱን ጨርሶ ተፈቺ ነበር፡፡ አቤል ከበደ፣ ከድር ታደለ፣ ኢብራሂም ካሚል፣ ሸህቡዲን ነስረዲን፣ ፍፁም ቸርነት፣ አጥናፍ አበረ እና ሰይፈ ግርማ ፍርዳቸውን ጨርሰው በቀጣይ አመት ውስጥ ከእስር ውጪ ይሆኑ ነበር፡፡]

*******

***********

በቃጠሎወረ ወቅት በተተኮሰ ጥይት በርካቶች ቆስለዋል። ሞተዋል። ሆኖም በምርመራ ወቅት እስረኞች በእሳትና በጥይት የተገደሉትን ” እኔ ነኝ የገደልኩት” ብለው እንዲያምኑ ተደርገዋል። አንድ ሰው እስከ 5 ሰው ገድለሃል ተብሏል። ምርመራው አሰቃቂ ስለነበር ያልሞተ ሰው ሁሉ ገድያለሁ ያለ እስረኛ አለ። እስረኞች የሚድሩበት ቆርቆሮ ቤት ነው። ከጎኑ ደግሞ ሶስት መግረፊያዎች አሉ። አንድ እስረኛ ሲገረፍ ሌላው የሚሆነውን ይሰማል። ከ170 በላይ እስረኛ ተሰቅሎ ሲገረፍ ሌላው ይሰማል። በዚህ ሁሉ መከራ የስነ ልቦና ችግር ያጋጥማል። ይህን ሁሉ ሰቆቃ ሲሰማ የሰነበተ አንድ እስረኛ ሳይገረፍ ገና ወደ ምርመራ ክፍሉ ሲገባ ያልገደለውን ገደልኩ ብሏል። እስረኛው ማንን እንደገደለ ሲጠየቅ ” ጠሃን እኔ ነኝ የገደልኩት “ይላል። መርማሪዎቹ አልተስማሙም። ጠሃን በተመሳሳይ ሁኔታ ለሌላ ሰው አድለውታል። በዚህ መከራ ወቅት እንትናን ገድየዋለሁ ብሎ ከመርማሪው ይሁንታ ማግኘት ቀላል አይደለም። ከሰቆቃ ያድናል። እስረኛው አሁንም ሞቷል የተባለ ሰው ስም ጠርቶ እኔ ነኝ የገደልኩት ይላል። ሲሰማ የሰነበተው መከራ እንዳይደርስበት ነው። አሁን የጠራው ሟችንም ቀድሞ የተመረመረ “እድለኛ” ወስዶታል። እስረኛው በዚህ ሁኔታ እስከ አምስት ሰው እየጠራ ” እድሉን ይሞክራል”። አልቀናውም። በሙሉ ተይዘዋል። መርማሪውም ” ተይዘዋል” እያለ ሌላ እድል ይሰጠዋል። አምስተኛ ላይ የሰጠኝ ሙሉን ስም ጠራ። “እስኪ ቆይ” ብሎ መርማሪው መዝገቡን አገላበጠና ” ያዘው አልተያዘም! አለው። ሰጠኝ ሙሉን ገድለኸዋል ተብሎ ተከሰሰበት። የቂሊንጦ ድራማ እንዲህ ነው። ሰው ባልሰራው የሚከሰስበት ድራማ!

Mahlet Fantahun 
Filed in: Amharic