>

"ማንበብ ያሳስራል!" (ወንድወሰን ውቤ)

“ምንድን ነው የያዝከው አንተ?” አለኝ በቁጣ ፊት ለፊቴ የተገተረው የደህንነት (በ “ህ” ፈንታ “ኅ” ፊደልን ያልተጠቀምኩት ሆን ብየ እንደሆነ ይያዝልኝማ) ሠራተኛ። አንድ የማታውቁት ሰው እጃችሁ ላይ በግልፅ የሚታይን ነገር ምንነት በቁጣ ከጠየቃችሁ መቼም ነገር ፍለጋ መሆኑ ይገባችኋል። ልክ ቁልቁል የሚወርደውን ውኃ “አደፈረስችብኝ!” ብሎ ከከፍታ ላይ ሁኖ አህያ ላይ እንደጮኸው አያ ጅቦ። የደህንነቱ አነጋገር ደግሞ በሥልጣን ነበር።

ስለመብት ፌስ ቡክ ላይ የማውራትን ያህል ነገር በሚፈልግህ አፍሪካዊ የፀጥታ ሠራተኛ ፊት ማውራት ቀላል እንዳልሆነ ደመ ነፍሴ ሹክ አለኝ።
በትክክል ከአፌ ሊያፈተልክ የነበረውን ቃል ዛሬ የአዋሽ ሰባት ኪሎ በርሐ እንግልት አስረስቶኝ ነው እንጂ አጀማመሬ ላይ “ምን አገባህ? ምን ፈለክ? … ” ለማለት አሞጥሙጬ የነበር ይመስለኛል።
ዞር ዞር ብየ ስመለከት ደህንነቴ( የአቤ ቶክቸውን ልዋስና) ብቻውን አይደለም። አካባቢው ተወጥሯል። ከኛ ሦስት ሜትር ርቀት ላይ ከጃዕፋር መጽሐፍ ቤት ፊት ለፊት ደግሞ ሌላ ደህንነት በቁጣ ጡፎ አፍጥጦብኛል።

” እ!? መ …መጽሐፍ … መጽሐፍ ነዋ! ነው የያዝኩት” ድምፄ ውስጥ ያቃጨለው ትህትና በንሥሐ አባቴ ፊት ነውሬን ሳራግፍ እንኳ እንዲህ አቃጭሎ የሚያውቅ አይመስለኝም።
“ለምን ያዝከው?” አላልኳችሁም— ነገር ፍለጋ ነው።
“ያ … ያው ላነበው ነው እንጂ …” አሁን ደግሞ ንብረቱን ሳያሸሽ ወታደር የተመራበት የዘመነ መሳፍንት ምስኪን አፈር ገፊ ነው የመሰልኩት።
“አንብበህዋል?”

“አወ!” በአጠቃላይ ስለኢትዮጵየ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ስለ አማራና ኦሮሞ ሕዝብ ትስስር የሚተርከው የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍን ነበር የያዝኩት። ከሳምንት በፊት የወጣ ቀን ገዝቸ አንብቤ ያን ቀን አገባድጀው ነበር። ከእጄ ቀምቶ ገለጥለጥ አድርጎ አየው። በጣም ያስገረሙኝን፣ ያስፈነደቁኝን፣ አዲስ የሆኑብኝን፣ ያልተመቹኝን ወዘተ እዛው መጽሐፉ ላይ አስምሬባቸዋለሁ። አያቸውና ሌላ ጥያቄ አከታተለ።

ሊለቀኝ ነው ብየ ሳስብ “መታወቂያ” አለኝ። የሥራ መታወቂያ ሰጠሁት። አልተመቸውም። የኪስ ቦርሳየን በኃይል ነጠቀኝና የቀበሌ መታወቂያየን አወጣ።
የትውልድ ቦታየን ጠራና እዛ መወለዴን ከአንደበቴ መስማት ጠየቀኝ።
“አወ!!” አልኩት ፈርጠም ብዬ። ከትከት ብሎ ሳቀ፤ ላንቃው እስኪሰነጠቅ። የነገር ሳቅ፤ “የታባህና አገኘሁህ!” የሚል ድምፀት ያለው ሳቅ መሰለኝ። ከንባብ ቀጥሎ የሚያሳስር ሌላ ምክንያት ተገኘ መሰል።

ከዛ በኋላ ጥያቄና መልሱ ቆመ። ራሴን መጀመሪያ በባዶ እግርና ውልቅ ውልቅ በሚል ቀበቶ አልባ ሱሪ ትንሿ ስታዲየም ውስጥ አገኘሁት።

ቀጥሎ ራሴን በተላጨ ፀጉር እሾህና ተዋጊ ጠጠር በተበተነበት የአፋር በርሐ፣ በአዋሽ ሰባት ኪሎ የአጥር ነቀላ( ከአጥር የተነቀለ እንጨት) በያዙ ፌደራል ፖሊሶች ቁም ስቅሉን ሲያይ አገአገኘሁት።
ከዛማ ራሴን ከ95 ወጣቶች ጋር ወረፋ ይዞ በአንዲት ኩባያ እየተቀባበለ የደረቀ ጉሮሮውን በውኃ ለማራስና ሕይወቱን ለማሰንበት ሲታትር አገኘሁታ።

ከዛም ራሴን “ጥፋተኛ ነኝ ብለህ ፈርም!” ከሚሉ በርካታ ኮማንደሮች እግር ሥር የሲሚንቶ ወለል ላይ ቁጭ ብሎ የበሰበሰ ዝናም አይፈራም በሚል ብሂል “አላጠፋሁም!አልፈርምም!” እያለ ሲሟገት አገኘሁታ።

ከዛማ ከ17 ቀናት መከራ(“ይችም እስር ከመከራ ተቆጠረች!” ትሉኝ ይሆናል። “ያላየ ሰው አለ አጎቴ” የሚል ነው መልሴ) በኋላ ከነሡኝ ቦታ አምጥተው ጣሉኝ።

ይህ የሆነው አምና ከሐምሌ 30—ነሐሴ 16 ነው

ቀኑ “የንባብ ቀን ነው! ጠ/ሚኒስተሩ ለሕፃናት ያነባሉ ” የሚል ስሰማ “እስኪ አስችለኝ” እያልኩ ፀጥ ብየ ዋልኩ። ግን ደጋግመው “መጭው ጊዜ የከፍታ ነው!!” ሲሉ ብሰማ ወደ ከፍታ የሚወጣ መንግሥታችን ቁልቁል ወደ እኔ ወርዶ ሌላ ሁለት ሰባት አያዝብኝም ብዬ በመተማመን ዓመት ሙሉ የደበኳችሁን በጥቂቱ አካፈልኳችሁ።

Filed in: Amharic