>
4:38 pm - Saturday December 2, 6834

ኢትዮጵያዊነት ከመታፈሪያነት እስከ ማስፈራሪያነት (መሃመድ እንድሪስ)

ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀሁ ሳለ አንድ ወዳጄ ከወደ አውስትራሊያ የመልካም በዓል ምኞቱን ሊገልፅልኝ ደወለ፡፡ የነገሮች መገጣጠም በጣም ገርሞኝ ይኸው ወዳጄ በአንድ ወቅት ያጫወተኝንና ከ9 አመት በፊት ለከፍተኛ ትምህርት ወደጀርመን ባቀናበት ወቅት ያጋጠመውን እስካሁንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተስፋ ያስቆጠረውን አጋጣሚ ለመግቢያነት ብጠቀመው ብዬ አሰብኩ፡፡

ጀርመን በገባ ሳምንት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ከሁሉም አገራት የትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች የትውውቅ ፕሮግራም ላይ ይህ ወዳጄ የገጠመውን ነገር እንዲህ ሲል ነበር ያጫወተኝ፡፡ “‘ስሜን አስተዋውቄ የመጣሁት እራሷን ከቅኝ ግዛት ያስጠበቀች ከነፃነት ተምሳሌቷ የአፍሪካ ኩራት ከሆነችው ከኢትዮጵያ ምድር ነው’ ከማለቴ አንድ እዛው አገር ብዙ የቆየና የሚያውቃቸው ልጆችን አጅቦ የገባ ሌላ ኢትዮጵያዊ ንግግሬን አቋርጦ ‘ኢትዮጵያ የምትባል ነፃ አገር የለችም፡፡ እራሷም አንድ ቀኝ ገዥ የሆነች አገር ነች’ ሲል ጮኸ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ካየኋቸው እዚህ ግባ የማይባሉ የካፌ ወጥ ቀጠነ እና ቋንቋዬን ሰደብክብኝ ሰበብ ከሚነሱ ግጭቶች ውጭ የገዘፈ ልዩነት እንዳለን ሳላጤን ኖሬ በዚያች ሰአት የሰማሁት ነገር ከዚያ በኋላ ንግግሬንም ለመቀጠል አላስቻለኝም ከዚያም በኋላ ከማንም ሰው ጋር ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንዳላወራ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል” ሲል ነበር ያወጋኝ፡፡

ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት (Ethiopian Nationalism) በመባል የሚታወቀው ብሄረተኝነት ብዙሀኑ በጋራ የሚግባባት መገለጫዎች እያጣ መምጣቱ በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ የማንነት ቀውስ ሲፈጥር በፖለቲከኞች ደረጃ ደግሞ ጉዳዩን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ አድርጎታል፡፡ በቀደሙ ግዚያት ኢትዮጵያ ሲባል በብዙሀኑ አዕምሮ የሚመጣው የተበታተኑ ህዝቦችን በአንድ አገር ጥላ ስር የማኖሪያ ቀመር፣ ከቅኝ ገዢዎች እራስን ለመከላከል ያስቻለ ዋነኛው ውስጠዊ ሀይል፣ በአፍሪካ የተደረጉ የነፃነት ትግሎችን ምሳሌ መሆን የቻለ አህጉራዊ ኩራትና የኛ መታፈሪያና መከበሪያ…ወዘተ የሚባሉ መገለጫዎች ዛሬ በጣሙን ትርጉማቸውን እያጡ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በኔ እይታ ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዘላቂ የሆነ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ስሜትን ልንፈጥረ የምንችልባቸውን የጋራ ገድሎቻችንን ማስጠበቅ አለመቻላችን ነው፡፡ በምኒልክ ግዛት የማስፋፋት እና የአገር ምስረታ ሂደት የነበሩ የታሪክ ጠባሳዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከመስፋፋቱ በኋላ የአገር ምስረታው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ተጠቃሚነት መዋል አለመቻሉ ቀድሞም በወረራ አንደተቀላቀለ የሚያምነው ክፍል በወራሪው ሀይል እየተገዛ እንደሆነ ከማሰብ ውጭ በተግባር ኢትዮጵያዊነቱን ሊያሳምኑት የሚችሉ የተግባር መገለጫዎች አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከጠላት ወረራ ለመከላከል ከመነሳቱ ውጭ ከጠላት ባስጣላት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቦታ ተረድቶ በውስጡ በባለቤትነት አምኖ እዲይዘው አልተደረገም፡፡

ከዚህ የከፋው ደግሞ በአፄ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት በተለይም ንጉሱ ከስደት ከተመለሱ በኋላ አገራቸውን ከፋሺስት ኢጣልያ ታግለው ያስቀሩትን አርበኞች ሳይቀር የመሸለም ሳይሆን የማጥፋት ስራ ሰርተዋል፡፡ ጣልያን ወረራውን ውጤታማ ለማድረግ የተገፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማባበል ወደመሀል እዲመጡ ያደረጋቸውን ጥረቶች ሀይለስላሴ ከስደት ሲመለሱ ባለበት መተዉ ቀርቶ ተጨማሪ የብቀላ እርምጃ ወስደው የንጉሱ ኢትዮጵያ ከጣልያን ኢትዮጵያ ሳይቀር የማትመች እንደሆነ ለህዝቡ በተግባር አረጋገጡ፡፡ በመግቢያዬ የጠቀስኩት የወዳጄ መጥፎ ተሞክሮ በዋናነት ያቆጠቆጠው በነዚህ ምክንያቶች ነው ማለት እችላለን፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ በታሪክ ትምህርትነት ስለኢትዮጵያ የሚሰጡ መገለጫዎቸ ቢያንስ በፊት በጦርነት እና ዘመቻ በጋራ ሊያሰባስብ የሚችለውን አገራዊነት የሚያጠፋ የአንድ ባህል ዘመም ኢትዮጵያዊነት የማጥመቁ ሂደት ለዚህ ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ Social Memory በሚባለው የጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱትም የታሪክ መፅሀፍት በሌላ በኩል የፖለቲካ መፅሀፍት ናቸው፡፡ መንግስታት ስለዛች አገር ታሪክ ትውልዱ ሊያውቀው ይገባል ብለው የሚያምኑትን የሚያስተምሩበት መወገዝ ያለበትን የሚያወግዙበት ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡ እነዚሁ ምሁራን አክለውም በመማሪያ መፅሀፍት የሚታወቀው ኦፊሴላዊ የአንድ አገር ታሪክ የዚያን አገር እውነተኛ ባህለዊ እና ማህበራዊ የጋራ ታሪክን እንደማይወክል ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ነፃ አገር ነበረችና ኢትዮጵያዊነት የነፃት ተምሳሌት ነው የሚለው ስብከትን በተግባር ማየት ያልቻሉ ሰዎች ከኢትዮጵያዊነት ማሳያ ሊያኮሩ የሚችሉትን እሴቶች ሳይቀር እንዲህ በቀላሉ እንዲገረሰሱ አድርጓቸዋል፡፡

ሁለተኛው እና ሶስተኛው ምክንያት ተያያዥነት ያላቸውና በዚህ ፅሁፍ በዋናነት የማተኩርባቸው ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንታገላለን የሚሉ ክፍሎች ስለኢትዮጵያዊነት የሰጡት ቦታ ኢትዮጵያዊነትን ትልቅ የፖለቲካ ካርድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ የመጫወቻ ካርድ ከመጫወቻነት የዘለለ ቦታ ሳይሰጠው በተለይም በስልጣን ላይ ያለው መንገስት በተደጋጋሚ ጥሩ በሆነ መልኩ እየመዘዘውና እየተጫወተበት ይገኛል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከአሰባሳቢ ሀይልነቱ ይልቅ ለፖለቲካ ፉክክር አጀንዳነት የመዋል እድሉ እያደገ መጥቷል፡፡ ዛሬ ላይ ስለ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት በጣም ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ መስሎ የሚታየኝም መንግስት እና ፖለቲከኞች ይህንን ብሄረተኝት ለምን ጉዳይ እና መቼ ነው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት የሚለው ሆኗል፡፡ ከህዝቡ ፍላጎት የተለየ ወይንም የተደበቀ ፍላጎት ያላቸው ፖለቲከኞች ብሄረተኝነትን ያንን አላማቸውን ለማሳካት እንደሚጠቀሙበት እሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዳበረ ዴሞክራሲ እንዳለባቸው በሚነገሩ አገራትም ጭምር የተለየ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ፍላጎት ያለቸው ተፎካካሪዎች በዋናነት ጥቅም ላይ የሚያውሉት ብሄረተኝነትን ሆኖ እያየን ነው፡፡ ይህ የራሱ የሆነ ምክንያት፣ ሂደት እና ውጤትም አለው፡፡ ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያ የሚሆኑ በኢህአዴግ መንግስት ዘመን ኢትዮጵያዊነትን የፖለቲካ መፎካከሪያ የሆነባቸውን አልፎ ተርፎም ማስፈራሪያ የሆነበትን የተመረጡ ማሳያዎችን በማየት እነዚህን ለፉክክር አመቻችቶ የመስጠቱ ኃላፊነትስ የማን ነው በሚለው ላይ ሀሳብ እንለዋወጣለን፡፡

ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሩ የፖለቲካ ካርድ

ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያዊነት በሁለት መልኩ ነዳጅ ሆና የፖለቲካውን እሳት እንድታቀጣጥል እድል እንደተሰጣት መረዳት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ህዝብን ለፖለቲካ ዓላማ ለማሰለፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከፊሉን ህዝብ በከፊሉ ላይ ለማስነሳት ወይንም አንድን አካል መሰዋዕት ለማድረግ በሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን እንይ

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያዊነት እስካሁን በድጋሜ ባልታየ መልኩ አጀንዳ ተደርጓል፡፡ የቴሌቪዥን መስኮቶች፣ ራዲዮኖች፣ በተለያዩ ደረጃ ባሉ ህዝባዊ መዋቅሮች ሁሉ ይሄ ሲሰበክ ነበር፡፡ ይሄንንም መንግስት ከገባበት የጦርነት አጣብቂኝ መሀል ከኢትዮጵያዊነት ውጪ የሚያተርፈው አዳኝ እንደሌላ አምኖበት እንዳደረገው የሚያምኑ አሉ፡፡ እዚህጋ የተዘነጉ ሁለት ቁምነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ የተባሉት በጫካ ስምምነት ታሪክ ያለው የባድመ የድንበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያኖች ስለኤርትራ ያላቸው ታሪካዊ የራስ አካል ቁራጭ አድርጎ የመውሰድ የባለቤትነት ስሜት በራሱ ትልቅ ሞተር ነበር፡፡ ሁለተኛው ጦርነት በራሱ ትልቅ ፖለቲካ መሆኑ ነው፡፡ በፖለቲካል ሳይንስ ጥናት ጦርነት የፖለቲካ አንድ ክፍል መሆኑ አለመሆኑ ላይ ምሁራኑ ክርክር እንዳለ ሆኖ ጦርነት የዓለማችን ፖለቲካ ዋነኛ መዘውር እንደሆነ ግን ቀጥሏል፡፡ ላነሳነው ርዕስ የሚያያዘው ሀሳብ ግን አንድ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታውቆ ከተገባበት ያ ጦርነት የዚያ አገር ትልቅ ፖለቲካ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ከቅስቀሳ እስከ ጦርነቱ ያሉት ስራዎች በሙሉ ውጤታማ እንዲሆኑ የተሰናሰለ የፖለቲካ አመራር እና ስልት ይፈልጋል፡፡ እንደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላሉ በቂ ሰበብ እና በቂ ውጤት ለሌላቸው ጦርነቶች ህዝብን ለማሰለፍ ብሄረተኝት ሲቀነቀን አላማው ያንን ብሄረተኝነት ማበልፀግ ሳይሆን በስሙ ህዝብ ለማሰባሰብ ብቻ ሲባል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ላይ ህዝቡን ለማሰለፍ ጥቅም ላይ የሚውለው ፖለቲካዊ ስልት የመንግስት መሰረታዊ የኢትዮጵያዊነት አቋም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ የትኛውም አይነት ጦርነት አገራዊ ስሜትን ማዕከል ሳያደርግ እንደማይካሄድ የሚያውቁ ምሁራን ሳይቀር ኢትዮጵያ ላይ ሲመጣ ጉዳዩን የኢትዮጵያዊነትን መድሀኒትነት ፍቱን የሆነበት አጋጣሚ አድርገው ማሳየታቸው አሁንም ኢትዮጵያዊነትን ወደመሬት ባይወርድ እንኳን ስልጣን ላይ ያለው አካል በስሙ ለመስራት ካሰበ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ያሳየ አንድ አጋጣሚ ነበር፡፡

የህወሀት ለሁለት መሰንጠቅ

በ 1993 የህወሀት ለሁለት መሰንጠቅ ሲያጋጥም ኢትዮጵያዊነት በመውጫ ቀዳዳነት ጥቅም ላይ እንደዋለች ቢያንስ በአንጃነት እረሳቸውን የገነጠሉት ክፍሎች የነአቶ መለስን ቡድን በኢትዮጵያዊነትና ትግራይን በመክዳት ይከሱበት ከነበረው አካሄድ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት እነ አቶ መለስ አንጃውን ሊረቱ የቻሉት የኢትዮጵያዊነት ካርድ በመምዘዝ ነበር ማለት ነው፡፡ ብዙዎች እንዲህ አይነቱን ክስተት ኢትዮጵያ ለሚያጋጥማት ችግር ሁሉ እነርሱ ኢትዮጵያዊነት ብለው የሚያምኑት አጀንዳ መራገብ መፍትሄ እንደሆነ እና የነፍስ አባት ተደርጎ እንደተወሰደ ፅፈዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ሳይቀር የቁርጡ ቀን ሲመጣ እነ አቶ መለስ ሳይቀሩ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያዊነት እያዞሩ እንደነበር ያመኑ ይመስላል፡፡

የኢትዮጵያ ሚሊኒየም

በኢትዮጵያ ሚሊኒየም የታየው መነቃቃት መልካም ሆኖ ሳለ ‘ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን’ መፈክር አሻሚ ትርጉም አዝሎ ግራ አጋቢ ስሜቶችን የፈጠረ ነበር፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በተመሳሳይ አጀንዳዎች እና በተደጋጋሚ በሚቀረቡ የኢትዮጵያን አንድ ወገን የገናናት ትርክት ሰባኪዎች ማጨናነቁ ነገርየውን internal coup አስመስሎት ነበር፡፡ ይህ ወቅት የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልልሎች የሚባሉት ነገርየውን በጥርጣሬ የሚያዩበትም ወቅት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሄር ተኮር ፌዴራሊዝሙ አገሪቱ ላይ ደቅኖታል ከተባለው አደጋ የመውጫ የኢትዮጵያዊነት ተሀድሶ በሚል ያወደሱትም ነበሩ፡፡ የሚሊኒየሙ ‘ህዳሴ’ በተለያዩ የልማት ስራዎች ስያሜነት እየዋለ ስሙን እስካሁን ማስጠበቅ ቢችልም ኢትዮጵያዊነት ግን ዛሬም መሬት መንካት ያቃታት የአየር ላይ አጀንዳ እንደሆነች ቀጥላለች፡፡

የሙስሊሙ ሰላማዊ ጥያቄ እና አሁን ያሉ ተቃውሞዎችን ማስተንፈሻ

ህዝብ ጥያቄ ሲያነሳ እና ያንን ጥያቄ ማስተናገድ ሲያቅት ጥያቄውን እና አቅራቢውን ክፍል የኢትዮጵያዊነት አደጋ አድርጎ በመሳልም ኢትዮጵያዊነት ጥቅም ላይ ትውላለች፡፡ ሙስሊሞች ባነሱት የመብት ጥያቄ እና ተከትሎ በመጣው ውጥረት መንግስት ከፍተኛ ጫና ደርሶበት ነበር፡፡ የመብት ጥያቄውን እና አቅራቢውን ህዝብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በአደጋነት እንዲታይ ከተካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ሁሉ በአንፃራዊ መልኩ ጆሮ ለማግኘት የቻለው የኢትዮጵያዊነት አደጋ የምትለዋ ካርድ ስትሳብ ነበር፡፡ በአንዋር መስጂድ በተደረገው ተቃውሞ ሆን ተብሎ ለዜና ግብዓት እንደተቀናበረ በሚገመተው የተቀደደ እና በተገቢው ክብር ያልተያዘ ሰንደቅዓላማ ሙስሊሞች ተጠቅመዋል የሚለው ረዘም ላለ ግዜ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በዚያው አመት በተከበረው የሰንደቅዓላማ በዓልም ላይ እስከቀበሌ ድረስ የኢትዮጵያዊነት ካርድ እየተመዘዘች ሙስሊሞቸን ባንዲራ በማዋረድ ውንጀላ ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ ውላለች፡፡ እስካሁን በወጉ እልባት ባላገኘው የኦሮምያ እና የአማራ ክልል የተነሱ ከፍተኛ ተቃውሞዎች መንግስት ላይ ያሳደሩት ጫና ኢትዮጵያዊነት ውስጥ በመመሸግ ለማምለጥ እየተሞከረ እንደሆነ የዘንድሮ አዲስ አመት አከባበር መርሀግብር ላይ ፍንጮች ይታያሉ፡፡ አገሪቱ በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ እየታመሰች ባለችበት ወቅት የከፍታ ዘመን መፈክር መቅረቡ መንግስት ስለኢትዮጵያ የሚያሳስበቻው ወገኖች ግብሩ ሳይን ስሙ እንደሚያስደስታቸው ልብ ብሎ የተገነዘበ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚሀም አልፎ የኢትዮጵያ ከፍታ ስያሜ ሀይማኖታዊ ይዘት እንዳለው መታወቁ ኢትዮጵያዊነት ከመታፈሪያነት ይልቅ ለተወሰነው ወገን ማስፈራሪያነት መዋሉ እንደቀጠለ ማሳያ ነው፡፡

የኢትዮጵያዊነት ካርድን ለጨዋታ ማን አመቻቸው?

ኢትዮጵያዊነትን ጥሩ የፖለቲካ ካርድ እዲሆን ያደረጉት ስለኢትዮጵያዊነት በልሂቃኑ የሚቀነቀኑት ሀሳቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ሁለት ማሳያዎችን ብቻ ልጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያውያንን የሚገልፅ ተጨባጭ ማሳያ የሌለው ባዶ መንፈስ ተመስሎ እንዲቀርብ መደረጉ ነው፡፡ የተቃዋሚው ጎራ በተለይም ቀኝ ዘመም ፖለቲካን የሚያቀነቅነው ክፍል የህዝቦች ባህል፣ እምነት፣ ታሪክ እና መብት መጣስ ሳይገደው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚለው ንፋስ እንደገበባት ሲሰማው የሚያሳየው ቁጣ ለመንግስት ጥሩ የመጫወቻ ሜዳ ፈጥሮለታል፡፡ እንደውም ይህንን ካርድ መንግስት በሚገባ እንዳልተጫወተበት ሁሉ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ለኢትዮጵያዊነት ከመንፈስነት ባለፈ ተግባራዊ ማሳያ እስካልተጠየቀ ድረስ ባሻው ሰአት ከፍ እያደረገ ሊጠቀመው በቻለ ነበር፡፡ መንግስት አልተጠቀመበትም ካልኩበት አንዱ አጋጣሚ የቴዲ አፍሮ አደሱ አልበም በወጣ ሰሞን አርቲስቱን በኢቢሲ ቀረፃ አካሄዶ አለማቅረቡ ነው፡፡ የአርቲስቱ በኢቢሲ እንደሚቀርብ ማስታወቂያ መነገር ከላይ እንዳየነው ኢህአዴግ ማጣፊያ ሲያጥረው ወደኢትዮጵያዊነት ተመለሰ በሚል ድሮም የኛን ምክር ቢሰማ ይበጀው ነበር ፉከራ ማህበራዊ ሚድያውን አጣቦት ነበር፡፡ ኢቢሲን ዞር ብለው አይተውት የማያውቁ ተቃዋሚዎች ሰአት ቆጠራ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ምንያቱም ኢትዮጵያዊነት ለነሱ ከዚያ የዘለለ ማሳያ ስለለሌለው በዚያ ፕሮግራም ብቻ የኢትዮጵያዊትን አሸናፊነት አይተው ሊረኩ በማሰብ፡፡

ሁለተኛው ማሳያ ኢትዮጵውያዊነት ወይንም የኢትዮጵያ ባህል ተነካ የሚባለው የተወሰነ ህዝብ እና ባህል ሲነካ ብቻ በመሆኑ ለመንግስት ጥሩ የመጫወቻ ካርድ ሆኖታል፡፡ ይህ ካርድ አደገኛነቱም ከሌሎቹ የባሰ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የአጋር ፓርቲዎችን እና ታዳጊ ክልሎችን የሚያስፈራራበት ሁነኛ ዘዴ ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአንድ ባህል ተቆርቋሪነት ጋር ተስተካክሎ መቅረቡ እነዛን ክልሎች ከኢትዮጵያዊነት አደጋ የሚታደጋቸው እርሱ ብቻ እንደሆነ የሚያሳምንበትን እድል ሰጥቶታል፡፡ ሌለው ቢቀር በአመታዊ በበጀት ድጎማ ወቅት ታዳጊ ክልሎች ለሚሰጣቸው ድጋፍ በተለይ ከአማራ ክልል የሚገጥመው ተቃውሞ በአማራው እንደሚቀነቀን ለሚታሰበው የመንፈስ ኢትዮጵያዊነት ለሌሎች አደጋ አድርጎ ማሳየት በጣም ቀላል እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊነትን በካርድነት ብቻ መጠቀሙ ከበቂ በላይ ውጤት ካመጣለት ታዳጊ ክልሎችን ወደሚያሰጋው ኢትዮጵያዊነት የሚመሽግበት ክንያትም የለም፡፡

ከላይ በመጠኑ እንዳየነው ኢትዮጵያዊነት ተግባራዊ ቀርቶ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ መገለጫ እንኳን እንዲኖረው አለመሰራቱ ስለኢትዮጵያዊነት የሚታገለውም ስለምን አይነት ኢትዮጵያዊነት እንደሚታገል በውል እንዳያውቀው አድርጓል፡፡ መንግስትም ኢትዮጵያዊነትን በካርድነት ብቻ መጠቀሙ ከችግር መውጫና በስልጣን መቆያ አንድ ስልት እንደሆነ እንዲያምን አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለመንግስት በአንድ ቢላዋ በሁለቱም ስለቱ በኩል መቁረጫነት አገልግሎታል፡፡ በአንዱ ስለት ያለምንም ተጨማሪ ጥረት ኢትዮጵያዊነትን ወግኖ በመቅረብ ኢትዮጵያኒስት ነኝ ከሚለው ወገን ጋር የተበተበውን የፀብ ድር ይቆርጥበታል፡፡ በሁለተኛው ስለት በዚያው ኢትዮጵያዊነት የሌሎችን ህልውና እንደሚቆርጥበት ያስፈራራበታል፡፡

መንግስት እና ፖለቲከኞች ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ለራሳቸው ፍላጎት እንዳያውሉት መከላከያው ዋናው መንገድ የአንድ አገር ብሄረተኝነት ሊወከልበት የሚችል የጋረ መገለጫዎች እና ተግባራዊ ማሳያዎች ላይ ህዝቡ የፀና አቋም እንዲኖረው በማድረግ ነው፡፡ በዚህ የፀና አቋም ላይ የሚደራጁ የፖለቲካ ሀይሎች ማፍራትም ሲቻል ነው፡፡ ፖለቲከኞች መቼ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የሚገጥም ብሄረተኝነትን እያቀነቀኑ እንደሆነ እና መቼ ደግሞ ብሄረተኝነትን ለሽፋን እየተጠቀሙ እንደሆነ በራሱ የሚያውቅበት ስነልቦናን ማዳበር ሳይቻል ማንም ማንንም ሊከስ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን በመበታተን ፕሮፓጋንዳ በተደጋጋሚ ለሀሜት የተጋለጠው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አንቅስቃሴ እንኳን ጥሩ ፖለቲካ እና ጥሩ ተዋናዮች ቢያገኝ ትልቅ የጋራ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚውል ሀይል መሆኑን በቅርቡ ኦቦ ጀዋር በኢትዮጵያዊነት የማስፈራራት ይዘት ላለው በኢሳት ለነበረው ውይይት መልስ እንዲሆን ብለው እንደሰጡት በሚያስታውቀው ቃለ ምልልሰ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህን ፅሁፍ ካገባደድኩ በኋላ BefeQadu Z. Hailu በተመሳሳይ ርዕስ ነገር ግን በተለየ አቀራረብ ዘለግ ያለ ጥሩ ፅሁፍ ለጥፎ አይቻለሁና እሱንም እንድታነቡት ጋብዣለሁ

Filed in: Amharic