>

ቀፋፊው የሁቱና ቱትሲ የዘር ፍጅት በኢትዮጵያችን ምልክቱ እየታየ ነው (ዘመድኩን በቀለ)

አብዝተን እንጸልይ፤ ንስሐም እንግባ

” አንደበተ ርትዑ ኢትዮጵያዊው ምሁር ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊን የመከሯቸውን አሳዛኝ ምክር  ይመልከቱ ዘንድ እጋብዝዎታለሁ “

https://www.youtube.com/watch?v=sz3M9jiwx0w&feature=youtu.be

[ እንደ #ሩዋንዳው_ኢንተርሃምዌ መታወቂያ እየታየ እርምጃ መውሰድ በምስራቅ ኢትዮጵያ ተጀመረ ። ህወሓት ሆይ ደስ ይበልሽ ] ። የኢትዮጵያ ህዝብ በፍቅር አሁንም ይሄንን ሴራ ማክሸፍ አለበት ። ኦህዴድ ፣ ደኢህዴን ፣ ህወሓት ፣ ብአዴን የሚባሉ ጉደኞች የሚቀሰቀሱትን የዘር ቅስቀሳ ባለመቀበል ልናሳፍራቸውም ይገባል ።

ኢትዮጵያ  ጅጅጋ_ሐረር_ጎንደር_ደቡብ_ቤኒሻንጉል ¶ ህወሓት ሆይ ደስ ይበልሽ.! በእውነት ደስ ይበልሽ በኢትዮጵያ ምድር የዘራሽው የጥፋት ዘር አሁን ለፍሬ ደርሶ እሸቱን ቀጥፈን መብላት እየጀመርን ስለሆነ በድጋሚ ደስ ይበልሽ.! እሰይ የኔ አንበሳ.! ጎበዝ ልጅ.! ።

በቪድዮው ላይ የምትመለከቷቸው ኢትዮጵያዊ ምሑር [ አቶ መለስ እባክዎ የብሔር ፖለቲካን ከሚገባው በላይ አራግባችሁታል ። አሁን ኳሷ በእርስዎ ቁጥጥር ስር ናት ። ከእጅዎ የመለጠች እንደሁ አደጋ ላይ ይጥሉናል ፣ እናም አሁን እርስዎ እንዲራሩልን ከመለመን በቀር ሌላ አማራጭ የለንም ] በማለት ነበር በቪድዮው ላይ የምትመለከቷቸው ምሁር የዘር ፖለቲካ አርክቴክቱን አቶ መለስ ዜናዊን በግልጽ የተማጽኖ ጥያቄ ያቀረቡላቸው ። አቶ መለስም ይቅር ሳይሉን እንዲያውም ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ ቀብረውብን ሞቱ ። ይኸው አሁን ኳሷ ከህወሓት እጅ አፈትልካ እየወጣች ያለ ይመስላል ።

ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በአንድ የፕሮቴስታንት ፓስተር አማካኝነት በተደረሰ መጽሐፍ ትንቢት መሠረት አሁን የፕሮቴስታንት እምነትን በራሽን ካርድ የታደሉት ገዢዎቻችን #ከፍታው_ዘመን በማለት እስከ መስከረም አንድ ዋዜማ ድርስ ሀገሪቷን ድግስ በድግስ አድርገዋት መክረማቸው የሚታወስ ነው ። ” የቁም ተዝካራቸው ነው የሚሉም አሉ ” ብቻ የፕሮፓጋንዳውን አያያዝ ለተመለከተ ሰው በ2010 ዓም ኢትዮጵያ ሀገራችን የሚፈናቀል ፣ የሚገደል ፣ የሚራብ ፣ የሚጠማ ፣ የሚታሰር ፣ የሚሰደድ ሰው የማይገኝባት ይመስል ነበር ። ነገር ግን እንደ ፕሮፓጋንዳውና እንደ ኢቲቪ ምኞት አልሆነም ።

ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው ። ቀደም ሲል በህወሓት የተቀረጸውና ተግባር ላይ የዋለው ቋንቋን እና ዘርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ይኽ ከፍታ ፣ አንድነት ይሉት ነገር ስለማይስማማውና ወደላይ ቋቅ እያለ ስለሚያስመልሰው ነው ። አሁን የመታመስ ፣ የመገደል ፣ የመፈናቀል ፣ የማልቀስ ፣ የመታሰር ፣ የመሸበር ፣ ያለመረጋጋት ተራው በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ግዛትና በክልሉ የሚኖሩት የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሊያ ዜጎች ክፍለ ጊዜ ነው ።

አጅሬ ህወሓት ጉዳዩ መጠነ ሰፊ ሆኖ በሰው ኃይል እጥረት እንዳትቸገር አስቀድማ በሰሜን በኩል ከጎንደር ዐማራዎች ጋር የጀመረችውን ግልጽ ጦርነት መቀሌ ድረስ የዐማራ ተወካዮችን ጠርታ ፣ ቄጤማ ፣ ጎዝጉዛ ፣ ፍሪዳ ጥላ ፣ ጠጁን ጥላ ፣ ጠላውን ጠምቃ ፣ መስቀልና ድንጋይ ተሸክማ እንታረቅ እንጂ ብላ ካደነዘዘች በኋላ በዚያ በኩል ትንሽ ጋብ ሲልላት ፊቷን ወደ ምስራቅ አዙራ የሱማሌ ልዩ ኃይልን እስከአፍንጫው አስታጥቃ የኦሮሞ ብሔርን አናት አናቱን እየፈጠፈጠ እንዲጨርሰው የማርያም መንገድ ሰጥታ ከዳር ቆማ ታጨበጭባለች ። ኦሮሞው በኦነግ ሰበብ መሳሪያ ተቀምቶ በእጁ ዱላ እንኳን እንዳይዝ ካደረገችው ሰነበተች ። የክልሉ ፖሊስ እንኳ ከዱላ በቀር መሳሪያ እፉ ነው ተብሎ በእጁ አይነካም ። ሱማሌዎቹ ግን ስናይፐር ነው እንዲታጠቁ የተደረገው ።

ከጎንደር ተፈናቀሉ ተብለው ፕሮፓጋንዳ የተሠራባቸው የትግራይ ተወላጆች መቀሌ ገቡ በተባለ ጊዜ ከክልሉ ባጀት ላይ 10 ሚልየን ቀንሰው መቀሌ ድረስ ሮጠው ሄድው ቼክ ያሰረከቡት እኚሁ የሶማሊያ ክልል ፕሬዘዳንት ናቸው ። እናም እኚህ ሰው ለህወሓት ታማኝ አገልጋይ እንደሆኑ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ በቪድዮ ሲናገሩ ተደምጠዋል ። የፈለጉትን ቢያደርጉ ህወሓት የሆነ ቀን እንደሸንኮራ መጥጣ መጥጣ ሲበቃት የጦስ ዶሮ ካላደረገችው በቀር አሁን ከጀርባ ሆና አይዞህ በለው ፣ እኔ አለሁልህ ማለቷ እንደሁ እየታየ ነው ።

በጅጅጋ ፖሊሶች እና የክልሉ ባለስልጣናት ያደራጁዋቸዉ ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የኦሮሞ ተወላጆችን መታወቂያ በማየት ወደ ማጎሪያ ቦታ መውሰዳቸውን የዐይን እማኞች ከሥፍራው ለዜና አውታሮች ሲናገሩም እያደመጥን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው ። የሚገርመው የሱማሌ ልዩ ኃይል እና ህወሓት ያደራጀቻቸው የቀበሌ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የኦሮሞ ተወላጆችን በመታወቂያቸው አማካኝነት ሲለቅሟቸው
የሱማሌ ተወላጆች የኦሮሞ ወንድሞቻቸውን በመደበቅ አጋርነታቸዉን እየገለጹ ነውም ተብሏል ። በካራሚሌ ቢያንስ 5 ሰዎች በወታደሮች ተገድለዋል ፡፡

ይኽን ይኽን ስናይ ከፊታችን አደጋ እንደተደቀነብን ይሰማኛል ። አሁን የህወሓት የዘር ፖለቲካ ሴራ ተጀመረ እንጂ ገና አላለቀም ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች እተፈናቀሉ ከክልሉ በሚዘገንን መልኩ እንዲወጡ እየተደረገ ነው ። ተፈናቃዮቹ የኦሮሞ ተወላጆች አሁን ሐረር ደርሰው በመጠለያ ውስጥ መሆናቸውን መንግሥት ራሱ አምኗል ። በሐረር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሱቆቻቸውን ዘግተው ሥራቸውን በማቆም ምግብ ፣ ልብስ ፣ ወኃ በማቅረብ አጋርነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ ።

ልብ በሉ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ከሱማሌ ኦሮሞ ትርምስ ውጪ በሦስት የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ ግልጽ ትርምስ እንዲፈጠር መንግሥታችን ያለ እረፍት እየሠራ ይገኛል ። ለጊዜው የመተንፈሻ ዘዴ መሆኑ ነው ። እዚያም እዚያም ችግር በመፍጠር በተፈጠሩት ችግሮች ዙሪያ ህዝቡ ሲጠዛጠዝ እሷ ከዳር ቆማ አየር ስባ በመምጣት መጨረሻ ላይ የሌለ አንደኛ አስታራቂ ሽማግሌ ሆና ልትከሰት ነው ።

¶ በሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች እንዲፈናቀሉ ካደረጉ በኋላ በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆኑ የሲዳማ ተወላጆች ከኣዛውንት እስከ ሕፃናት ሴቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የሲዳማ ተወላጆች ኦሮሚያን ለቀው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ እነዚሁ ተፈናቃዮች ከአድካሚ የእግር ጉዞ በኋላ ወደ ደቡብ ክልል ለመግባት ሲደርሱ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ደግሞ አላስገባ ብሎአቸው ሜዳ ላይ የመፍሰሳቸው አሳዛኝና አስገራሚ ዜናም እየተሰማ ነው ።

¶ በሰሜን በጎንደር አይከል ከትግራይ በሄዱ የህወሓት ሚሊሻዎች የሚታገዙና ራሳቸውን ቅማንት ብለው የሚጠሩ ጥቂት የታጠቁ ሰዎች ያልታጠቁ ንጹሐን የዐማራ ተወላጆችን በመሳሪያ በማስፈራራት ዐማራ ሐገራችንን ለቆ ይውጣ በማለት ብዙሃኑን ምስኪን የዐማራ ነገድ በማፈናቀል ላይ ይገኛሉ ።

¶ በቤንሻንጉል ጉምዝ በመተከል ዞን የሚኖሩ የዐማራ ብሔር ተወላጆች በአስቸኳይ አከባቢውን ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ ሲሆን እነዚህ ዐማሮች የመደብደብ እና ንብረታቸውን የማቃጠል ርምጃም እንደተወሰደባቸው ጉዳቱ የደረሰባቸው ዜጎች እያለቀሱ ሜዳ ላይ መበተናቸውን የአይን እማኞች በመናገር ላይ ይገኛሉ ።

¶ ሐረር ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን በግልጽ ማረድ መጀመሩን ከወደ ሐረር የሚመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ወደ ጠበል ይሄዱ የነበሩ እናትና ልጅን አስቁመው ሴት ልጃቸውን በእናትየው ፊት በኮብል እስቶን ድንጋይ መቀጥቀጣቸው ፤ የባለፈው ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ወደ ቤተ ክርስትያን ይሄዱ የነበሩን አንዲት እናት ከባጃጅ የወረዱ ግለሰቦች በጩቤ ሆዳቸው ላይ ወግተው ጥለዋቸው መሄዳቸው ፤ በአሁኑ ሰዓት በሐረር ከተማ በሚገኘው ጥምቀተ ባህር ውስጥ ወደ ታነጸው የቅዱስ ፊልጶስ ቤተ ክርስትያን የሚሄዱ ምእመናንን ማለፍ መከልከላቸው እየተነገረ ነው ። ይኽን ድርጊት እየፈጸሙ የሚገኙት ደግሞ ከቤተ ክርስትያኑ ከፍ ብሎ ቱርኮች በከፈቱት የሙስሊሞች አዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ አክራሪ ሙስሊሞች አማካኝነት መሆኑ እየተነገረ ነው ። ጉዳዩ እዚህ ደረጃ ደርሶም የመንግሥት አካላት ባላየ ባልሰማ ጮጋ ብለዋል ።

¶ ማክሰኞ እና ዕሮብ ዕለት በአወዳይ ከተማ በተነሳ የብሔር ግጭት ቁጥራቸው ከ10 በላይ የሚሆኑ ዜጎች እርስ በራሳቸው ሱማሌ ኦሮሞ ተባብለው ሲገዳደሉ ፣ ንጹሐን ዜጎችን ከመኪና አያወረዱ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲያርዷቸው ፣ ግማሹን ደግሞ ከፎቅ ላይ እየወረወሩ ፈጥፍጠው ሲገድሏቸው ። የከተማው ፓሊስ እና ልዩ ኃይል ተብዬዎቹ የሚገዳደለውን ህዝብ መኪና ብቻ እንዳትነኩ እንጂ እናንተ የራሳችሁ ጉዳይ በማለት ቆመው ያዩ እንደነበርም ተነግሯል።

አሁን በዚህ ወቅት ለጊዜው ሰላማዊ አየር የሚተነፈስባት ፣ ህዝቧ ያለስጋት በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባት የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ብቻ ናት ። ሸአቢያ እንኳን አሁን እንደማያሰጋቸው እየታየ ነው ። ከሻአቢያ ጋር ጦርነት የሚገባው ሌላውን አካባቢ ትርምስምሱን ካወጡ በኋላ ” ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ ” በመጫወት የህዝብ ቅነሳ ለማድረግ ሲፈልጉ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እየተነገረም ነው ። ከዚያ ኦሮሞው ፣ ዐማራው ፣ ደቡቡ ሀገሬ እያለ ግርር ብሎ መጥቶ እንደቅጠል ይረግፍላቸዋል ። አከተመ ።

የሚገርመው አንድም የትግራይ ተወላጅ የሆነ ዜጋ አሁን በሀገሪቱ ውስጥ እየተፈጠረ ባለው ነገር ህወሓትን ለመውቀስ አይሞክርም ። አንድም ሰው ስላችሁ ። አንድም ሰው ።

በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ሀገር ፤ ትምህርት ጠል ሆነው ጫካ በገቡ ወጣት የትግራይ ልጆች መዳፍ ስር ገብታ ያለፉትን ሩብ ምዕተ ዓመታት በእነዚሁ ወጣት ጎረምሶች አገዛዝ ስትደቆስ መክረሟ ይታወቃል ። ኢትዮጵያችን በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀውን ፈተናም አጋጥሟት ፍዳዋን መብላት ከጀመረችም ይኸው 26 ዓመታት አለፉ

እነዚህ ሰዎች ገና ስልጣን ላይ እንደወጡ በወሰዱት እርምጃ የተደናገጡ የሀገር አድባር የሆኑ አረጋውያን የሀገር ሽማግሌዎችና ጥቂት ሆድ አደር ያልሆኑ ምሁራን ጎሮምሶቹን እነ አቶ መለስ ዜናዊን ” ተዉ ግድየለም ይኽ ነገር ይቅር ፤ አደጋም አለው ። እናም ግድየለም ይቅር እባካችሁ በማለት በብርቱ ተማጽነው ወትውተዋቸውም ነበር ። እነ አቶ መለስ ዜናዊ ግን በእምቢተኝነታቸው ገፉበት ። እናም ያ ገና ከመነሻው በአረጋውያን የሀገር ሽማግሌዎችና ሆዳቸው ከማንነታቸው ባልበለጠባቸው ምሁራን የፈራው ነገር አሁን ያ ስጋት አይኑን አፍጥጦ ጥርሱንም አግጥጦ በኢትዮጵያ ምድር በገሃድ በመታየት ላይ ነው ።

ህወሓት ኢትዮጵያን በብሔር ሸንሽና ከመቆራረጧም ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ እንዳይኮራና እንዳይመካ በየቀበሌው የሚኖር ዜጋ በመታወቂያው ላይ ሳይወድ በግዱ የፈለገውን ብሔር ፤ ወይ የእናቱን ፣ ወይደግሞ የአባቱን የብሔር ስም ጠቅሶ በመታወቂያው ላይ እንዲሰፍር አስገድዳ ተግባራዊ አደረገች ። ብሔሩን በመታወቂያው ላይ ለመጥቀስ የማይፈልግ ዜጋ ሲያጋጥምም የአባቱ ስም እስከ አያቱ ተጠይቆ በቀበሌ ሠራተኞች በግምት አማራ ፣ ትግሬ ፣ ኦሮሞ ፣ ወላይታ እያሉ መስጠት ግዴታም ነው ።

እኔ እስከ አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ምክንያቱን ባላውቅም አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች መታወቂያ ብሔር በሚለው ሥፍራ ” ኢትዮጵያዊ ” የሚል ከመኖሩ በቀርና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በግላቸው ባደረጉት ትግል በኢትዮጵያ ምድር በመታወቂያቸው ላይ ብሔር በሚለው ሥፍራ [ ኢትዮጵያዊ ] የሚለው ከከበሩ ማእድናት በላይ ውድ የሆነው ቃል የሰፈረላቸው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ነው የሚሰማው ።

ህወሓት በመታወቂያችን ላይ ብሔር የሚለውን ቃል እንዲሰፍር ያደረገችው ስለ ሁለት ምክንያት እንደሆነ በዘረፉ በጉዳዩ ላይ ምርምር ያደረጉ ሰዎች ይናገራሉ ። አንደኛው ምክንያቷ በተለየ ሁኔታ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎችን በሚደርሱበት ሥፍራ ሁሉ ቢሮክራሲ እንዳይገጥማቸውና በሟቹ መለስ ዜናዊ አጠራር ” የወርቅ ዘር የተባሉትን ” የጨርቅ ዘር ከተባልነው ከእኛ ከቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን በመለየት ልዩ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ነው ይሉና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እንዲህ እንደ አሁኑ [ ወሳኝ የዘር ማጽዳት ] ለማድረግ በታሰበ ጊዜ ተፈላጊውን [ ወርቅ የሆነውን ዘር ] ለማዳንና የሚወገደውን [ ጨርቅ ዘር ] ደግሞ በፍጥነት ለመለየት እንዲቻል አስበው ነው ይህን ያደረጉት ።

እነ አቶ መለስ ይኽንን ቆሻሻ የሆነ ክፉ ተግባር የተማሩትና የቀጸሉት ደግሞ ሩዋንዳንና ቡሩንዲን በቅኝ ግዛት ገዝታ ታስተዳድር ከነበረው ከአውሮፓዊቷ ቅኝ ገዢ ከሀገረ ቤልጅየም ነው ። በአውሮፓ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ውስጥ እንግሊዝ ሰፊውን የዓለማችንን ክፍል በመግዛት ትታወቃለች ። ዋና መለያዋም በደረሰችበት ሀገሩን ከፋፍለህ ግዛው የሚል ፖሊሲን በመቅረጽ ነው ። ዛሬ በዓለማችን ላይ በተለይ በአፍሪካ ጎልቶ የሚነሳውና እስከአሁን ድረስ ደም የሚያፋስስ ጦርነቶች በሁለት ወንድማማቾች መካከል የሚካሄደው በእንግሊዞች አማካኝነት ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ በተደረጉ ፈንጂዎች አማካኝነት ነው ። ፈረንሳዮች ደግሞ በአዋህደህ ወይም አመሳስለህ ግዛ ዘይቤያቸው የሚታወቁ ሲሆን ይኽን የአገዛዝ ዘይቤያቸውን ግን በሩዋንዳ ላይ የካቶሊክ ቄሶቿና የጦር መኮንኖቿ ቆንጨራ በማቀበልና ህዝቡ እርስ በእርሱ እንዲፋጅ ቤንዚኑ ላይ እሳት በመለኮስ በታሪክ ከባድ ጥፋት በማጥፋት ሲታወሱ ይኖራሉ ።

ከእንግሊዝም ሆነ ከሌሎቹ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ለየት የሚል የቅዥ አገዛዝ ዘይቤ ይከተሉ የነበሩት የቤልጅየም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ሊዎፖልዷ ናቸው ። የቤልጅየም የቅኝ አገዛዝ ዘይቤ ከእንግሊዝም ሆነ ከፈረንሳይ የአገዛዝ ዘይቤ በእጅጉ የተለየ ነው ፡፡ የቤልጅየምን ቅኝ አገዛዝ ዘይቤን አስከፊ የወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አገዛዝ በማለት አጠር አድርጎ የአገዛዙን አስከፊነት ከመግለጽ በቀር ሌላ ቃል ተፈልጐ አይገኝለትም ፡፡

የሩዋንዳና ቡሩንዲ ቀዳሚ ቅኝ ገዢ ጀርመን ነበረች ።በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጠናቀቂያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የአፍሪካን አህጉር ለመቃረት በጀርመኗ በርሊን ከተማ ጉባኤ ጠርተው የአፍሪካን ምድር ካርታ ከጠረጴዛ ላይ ዘርግተው ይኼ ለእኔ ያ ላንተ ተባብለው አፍሪካን እና በመላው ዓለም የሚገኙ ጭቁን ህዝቦችን ተቀራመቱ ።

እናም ከበርሊኑ ሸንጎ በኋላ አፍሪካውያኑ #ሩዋንዳና_ብሩንዲ ለጀርመኖች ተሰጡ ። የጀርመን ቅኝ ገዢዎችም እንደ ዘመኑ አቻ ቅኝ ገዢ ጎረቤቶቻቸው የሀገሬው ህዝብ በላያቸው ላይ በአንድነት እንዳይነሳባቸው የከፋፍለህ ግዛው ዘይቤያቸውን ሥራ ላይ አዋሉ ፡፡ የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ቱትሲዎቹን አቀረቡ፡፡
ሁቱዎችን ደግሞ ገፏቸው ፡፡ ጀርመን በ1ኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ፤ በዓለም ላይ የነበራት ጥቆሞቿን ሁሉ ስትነጠቅ ቅኝ ግዛቷ የነበሩት ሩዋንዳና ብሩንዲም ከእርሷ ተነጥቀው በሌላዋ ቅኝ ገዢ በቤልጂየም እጅ እንዲገቡ ተደረገ ።

አዲሶቹ የቤልጄየሞቹ ቅኝ ገዢዎችም በጀርመኖቹ የተጀመረውን የሁቱዎችንና ቱትሲዎችን ልዩነት እንዳለ ከማስቀጠላቸውም በተጨማሪ አዲስ ሁለቱን ብሔሮች የሚያፋጅ ዘዴም ተግባራዊ አደረጉ ። እርሱም ሁለቱን ብሔሮች የከፋ ቀን ሲመጣ የሚተርፍ ዘር እንዳይኖር የሚያደርግና ማንነትን አጉልቶ የሚያሳይ የመታወቂያ ካርድ በማዘጋጀት ልክ ዛሬ በእኛ ሀገር የእነ አቶ መለስ ዜናዊ ህወሓት እንዳደረገው [ ብሔር ሁቱ ፣ ብሔር ቱትሲ ] የሚል መታወቂያ አዘጋጅተው በሥራ ላይ አዋሉ ፡፡ ይኽ የከፋፍለህ ግዛው የቅኝ አገዛዝ ዘይቤያቸውም ስር እሰደደ ሄደ ፡፡

ልክ ህወሓት ኢህአዴግ የደርግን መንግሥት ጥሎ ከመግባቱና በብሔርና በጎጥ ከፋፍሎን እንዲህ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ከማጣታችን በፊት በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላና መፈክር ስር እንደነበርነው ሁሉ ከቅኝ በሩዋንዳ የሚገኙት የሁቱና የቱትሲ ብሔረሰብ አባላትም ከቅኝ ግዛት በፊት ለረጅም ዓመታት በአንድነትና በፍቅርና በሰላም አብረው የኖሩ ህዝቦች ነበሩ ። ሁቱዎች የሀገሪቱን 85 በመቶ የህዝብ ቁጥር በመወከል ብዙሀን ሲሆኑ 14 በመቶ የሚሆኑት ግን አናሳዎቹ የቱትሲ ብሔረሰብ አባላት የነበሩ ጎሳዎች ናቸው፡፡ ሌላም በቁጥር ከቱትሲዎች ያነሱ የትዋ የሚባል ጐሳ አባላት በሩዋንዳ ይኖሩ ነበር ።

ከጀርመኖቹ አቻዎቻቸው የቅኝግዛቱን የተረከቡት ቤልጂየሞች ከመጀመሪያው የቅኝ ግዛታቸው ዕለት አንስቶ እስከ ቅኝ ግዛት ዘመናቸው መገባደጃ አካባቢ ድረስ ብዙሁኑ ሁቱዎች ወደ እነሱ በማቅረብ በተቀሩት አናሳዎቹ እህት ወንድሞቻቸው ላይ በሁሉም ዘርፍ የበላይ እንዲሆኑ በማድረግ ቱትሲዎቹ በሁቱዎቹ ላይ ቂም እንዲቋጥሩ አደረጉ ። ኋላ ላይ የነፃነት ጥያቄው በርትቶ መነሳት ሲጀምር ደግሞ የቆየውን አሠራራቸውን በመቀየር አባላጫ ቁጥር ያላቸውን ሁቱዎቹን በመግፋት ገፍተዋቸው የነበሩትን አናሳዎቹን ቱትሲዎች በማቅረብ በሁሉም የሀገሪቱ ማኅበራዊም ሆነ ኢኮነሚያዊ ዘርፎች ላይ በብዙኀኑ ሁቱዎች ላይ ጭምር የበላይ እንዲሆኑ አደረጉ ፡፡

ቤተክርስቲያን ብትሄዱ አዛዡ ቄስ ዲያቆኑ ዘበኛው ተላላኪ ፀሓፊው ቱትሲ ሆነ ። ነጋዴው ፣ ፖሊሱ ፣ ዐቃቤ ህጉ ፣ ዳኛው ቱትሲ ሆነ ፣ የመንግሥት ሹመኛው ፣ ባለሥልጣኑ ሁሉ ከአናሳው የቱትሲ ብሔር የተውጣጣ እንዲሆን በማድረግ አብዛኛውን ቁጥር የያዙት የሁቱ ጎሳ አባላት ቱትሲዎች ሲበሉ ሆዳቸው እየጮኸ በስቃይ በመከራ እንዲያሳልፉ ተገደዱ ። የጦር መሳሪያውና መንግሥታዊው ስልጣን ሙሉ በሙሉ በአናሳዎቹ እጅ ስለነበረ ብዙኅኑ የሁቱ ብሔር አባላት ጥርስ በመንከስ ቀን እስኪመጣ ከመጠበቅ በቀር አማራጭ አልነበራቸውም ።

በመጨረሻም እጅግ አስከፊ የነበረው የቤልጅየም ቅኝ አገዛዝ አብቅቶ ሩዋንዳ ነፃነቷን ተቀዳጀች ። ሀገሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ትውጣ እንጂ ሩዋንዳውያን ግን በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘራው የዘር ጥላቻ ሆድ ሆዳቸውን እየቆረጣቸው አላስተኛ ብሏቸው ተቸገሩ ። በብዙዎች ዘንድ ሩዋንዳውያን በመካከላቸው የተፈጠረውን ጭፍን የዘር ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ትተው፣ በአዲስ የነፃነት ስሜት እንደ በፊቱ በአንድነትና በመቻቻል በጋራ መኖር ይጀምራሉ ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የከፋው ዘመን አልፏል የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም ከግምትነት የሚያልፍ ሆኖ አልተገኘም ።

ይልቁኑ በአሳዛኝ ሁኔታ ሁሉም ሩዋንዳውያን ሁቱና ትቱሲዎች፤ ቅኝ ገዥዎች በአዕምሯቸው ውስጥ የዘሩባቸውን ጭፍን የዘር ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ይበልጡኑ እያረሙና እየኮተኮቱ በሚገባ እንዲያድግና እጅግ ጠንቀኛ የሆነውን የጥፋትና የእልቂት ፍሬ እንዲያፈራ በማድረግ የዓለምን ህዝብ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ቆሻሻ የዘር እልቂት ፈጸሙ ። ለበርካታ ዓመታትም ለዚህ የጥፋትና የእልቂት ፍሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐቻቸዉን ህይወትና አካል ያለ አንዳች ስስት ገበሩለት፡፡ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዘር ላይ ተመስርተው ከተፈፀሙ ጭፍጨፋዎች ሁሉ ምን አልባት አሁን በበርማ ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝ ድርጊት ካልሆነ በቀር ይኽን የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት የሚስተካከለው እስከ አሁን አልተገኘም።

ሩዋንዳ ከ50 ዓመት በፊት ነፃነቷን ስትቀዳጅና የቅኝ አገዛዝን ከሀገሯ ስታወስግደው የቅኝ አገዛዙ ቅሪት የነበረውን የዘር ጥላቻ ሰንኮፍንም ሳትነቅለውና ሳታራግፈው ቀርታለች ፡፡ ይኽ የከፋ የእርስ በርስ ጥላቻ ከነፃነት በኋላም መፍትሄ ሳይበጅለት ባለበት እንዲዘልቅ ሆነ ። በዚህ ድርጊት የተከፉ
ቱትሲዎች ነፃነታችን ማስመለስ የምንችለው በጦርነት ብቻ ነው በሚል ቱትሲዎች የሚልቁበት [ የሩዋንዳ አርበኞች ግምባር ] የሚል ፓርቲ መሥርተው በቀጥታ ወደ ትጥቅ ትግል አመሩ ፡፡

ይኽን ችግር ለመፍታትና ፖለቲካዊ ዕልባት ለማስገኘት ሲባል ብዙ ሀገራት መፍትሄ ፍለጋ ላይ ታች በማለት በብዙ መባከኑ ጀመሩ ። በሁለቱ ብሔሮች መካከል የነበረው ድርድር እልባት ሳያገኝ የቀድሞው ከሁቱ ብሔር ወገን የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንትና የብሩንዲ አቻቸውን ያሳፈረ አውሮፕላን እስከ አሁን አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ በመዲናዋ ኪጋሊ አቅራቢያ ተመትቶ እንዲወድቅ ተደረገ ።

በዚህን ጊዜ የሁቱ የፖለቲካ መሪዎች ይኽማ የቱትሲዎች ክፉ ሥራ ነው ሲሉ በእጅጉ ተቆጡ ፡፡ወታደሮቻቸውን አሰለፉ ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም #ኢንተርሐምዌ ተብሎ የሚጠራ ገዳይ የሚሊሺያ ቡድን አደራጁ፡፡ ጠመንጃ ያለው ጠመንጃውን እንዲያነሳ ጠመንጃ የለለውም በእጅ ላይ ባገኘው መሳሪያ በቢለዋ ፣ በድንጋይና በዱላም ቢሆን ቱትሲዎች ላይ እንዲዘምት አዋጅ አወጁ ። የኤፍ ኤም ራዲዮዎችም በዚህ በኩል ታላቅ የማራገብና የቅስቀሳ ሥራ እንዲሠሩ አደረጉ ። የሚገርመው ነገር ከውጭ ሀገራት ሳይቀር ገጀራ በእውቅ እየተሠራ በአውሮፕላን እየተጫነ ብዛት ሀገር ውስጥ እንዲገባ ተደረገ ።

በኢንተርሃምዌ ቡድን የተደራጁ ወጣቶችም ገጀራ ታጣቂዎች ሆኑ ፡፡ በመቀጠልም በየመንደሩ የመቆጣጠሪያ ኬላ እንዲቆም አደረጉ ። ከዚህ በኋላ የሆነው ነገር ምንድነው ያልን እንደሆነ ቅኝ ገዢዎቹ ባስተማሩዋቸው ክፉና በዘር ላይ የተመሰረተ #የመታወቂያ ስርዓት መሰረት በመታወቂያ ካርዳቸው ላይ #ቱትሲ የሚል መለያ የሰፈረባቸው ሩዋንዳውያን ሁሉ አንገታቸው በዚያ ገጀራ ይቀነጠስ ያዘ፡፡

የቱትሲዎች እጅና እግራቸው ተቆራረጠ ፡፡ ሁቱዎች ጉረቤቶቻቸው የነበሩ ቱትሲዎችን እያሳደዱ የገቡበት እየገቡም እንደ ሽንኮራ አገዳ ከተከቷቸው ፡፡ እንደ ቲማቲምም ከታተፏቸው ። ለዚህ ለፍጅቱ ትብብር የነፈጉ ለዘብተኛ ሁቱዎችም የዚህ ጭፍጨፋ ሰለባዎች ሆኑ፡፡ ለ100 ቀናት በዘለቀው በዚህ የዘር ፍጅት አብዛኞቹ ቱትሲዎች የሆኑ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚልየን የሚጠጉ ዜጎች ማለቃቸውን የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

ይኸውልህ ወገኔ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለማችን ኃያላን አገሮች እልቂቱን ለማስቆምና ለመቀነስ ፈጥነው መድረስ ብቻ ሳይሆን የረባ ነገር እንኳን እንዳላደረጉ እስከአሁን የሚነገር ሃቅ ነው ።

አሁን ሩዋንዳ በየዓመቱ የዘር ፍጅቱን ለ100 ቀናት በብሔራዊ ደረጃ እያሰበች አስከፊውን የታሪክ ቁስሏን ለማከም በሚረዱ የብሔራዊ እርቅ ክንዋኔዎች እያከናወነች ትገኛለች ። አሁን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃም የሩዋንዳው ዓይነት የዘር ፍጅት መነሻ የሆነው የዘር ጥላቻና የዘረኝነት ነቀርሳ እንዲወገድ የሚያሳስቡ መልዕክቶች ጎላ ብለው ይሰማሉ ፡፡ አስቂኙ ነገር ደግሞ ይኽንን መፈክር በማሰማት በኩል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንደኛዋና ዋነኛዋ መሆኗ ነው ።

እኛም በኢትዮጵያችን በህወሓት አማካኝነት የተደገሰልን ድግስ ልክ እንደዚሁ እንደ ሀገረ ሩዋንዳ አይነት እልቂት መሆኑን ከወዲሁ ልብ ልንለው ይገባል ። ኢትዮጵያ የቅዱሳኑ አባቶች ጸሎት ይጠብቃት እንጂ መጪው ጊዜ በእጅጉ አስፈሪ ነው ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል ፣የእርስ በርስ ጦርነት እንዲበረታ እያደረገ የሚገኘው ኮከብ ተሸላሚ የሚሆነው ደግሞ በህወሓት አምበልነት ወደ ሜዳው የገባው የፌዴራል መንግሥት ነኝ የሚለው መንግሥታችን ነው ።

ማሳሰቢያም .! ማስጠንቀቂያም .! ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ። አሁን በእጃችሁ ላይ የሚገኘውን መታወቂያ ይዛችሁ ችግሮች ወደ ተፈጠሩበት አካባቢ ባትሄዱ ይመረጣል ። የህወሓት የዘር ፖሊሲ እንደሆነ ልክ እንደ ሩዋንዳ ቱትሲ መታወቂያ አይቶ ወደህ እና መርጠህ ፈቅደህም ባልሆንከው ዘር ምክንያት ጭዳ ነው የምትሆኑት ።

የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ምነው ዝም አሉ ብላችሁም አትጨነቁ ። አትሸበሩም ። አብዛኛዎቹ የሃይማኖት አባቶቻችን ያው ማን እንደሆኑ ታውቁ የለ ። እንደዚያ ነው ። እነሱ ታቦት ይዘው እርቅ ይፈጠር የሚሉትና ጆሮአችንን የሚያደነቁሩት ህወሓት የምትነካ ፣ ነቅነቅም የምትል ሲመስላቸው እና መመሪያውም ከፓርቲያቸው ሲወርድላቸው ነው ። እስከዚያው ይኼ የጨርቅ ዘር የፈለገውን ያህል ቢጨፈጨፍ ጉዳያቸው አይደለም ። በባለፈው ግርግር ወቅት ያ ሁሉ የዐማራና የኦሮሞ ህዝብ በአግአዚ ጦር ተጨፍጭፎ ሲረግፍ ቅዱስ ፓትሪያርካችን አባ ማትያስ ያሉትን አስታውሰን የጀመርነውን ጉዳይ እንቋጨው ።

” ወላጆች ሆይ.! ልጆቻችሁን ተቆጡ ፣ ምከሩዋቸውም ” አራት ነጥብ ። ፓትሪያርክ አባ ማትያስ ።

 

Filed in: Amharic