>
9:00 pm - Thursday May 19, 2022

እንኳን ደስ አለህ ኢህአዴግ!

ቶማስ ሰብስቤ

እንኳን ደስ አለ መባል የሚጣላ የለም።መቼም ሀሳቡ የሰመረለት፣የወጠነው የተሳካለት ፣ያቀደው የሆነለት ፣ ህልሞ እውን የሆነለት ሰው ሁሉ “እንኳን ደስ አለህ/ሽ” ማለት ልማዳችን እና አስፈላጊም ነው።ኢህአዴግን እንኳን ደስ አለህ! ስለው ለ11 በመቶ ልማት ፣ለአባይ ግድብ ፣ ከመቀሌ እስከ ሽሬ ላለው መንገድ ፣ በእየሰፈሩ ለተሰሩት ዮኒቨርስቲዎች ፣ለጥልቅ ተሃድሶ ፣ ከኮሚኒስት ወደ ካፒታሊስት ስላጠመጣንና መሰል ጨዋታዎች ሳይሆን ላለፍት 26 አመታት በስልጣን ፤ ለ17 አመታት በትግል ሲመኘው ለነበረው የጎሳ ፌደራሊዝም ፍሬ በማየት እንኳን ደስ አለህ! ጥልዝ !ዝቃጭ ዘረኛ!ለ26 አመታት አመታት የደከምክበት ዘረኝነት፣ ክልላዊ ፍቅር ፣የጎሳ አምልኮ ይህው ዛሬ ፍሬውን አፍርቶ ዓይንህን በዓይንህ ሰላየህ በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ! የኦሮሞና የሱማሌ ኢትዮጵያ ግጭት ፣ሞትና ስደት ባለፉት አመታት ኢህአዴግ በፍቅር ሲሰራው የነበሬ ሀቅ ነው።

በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንድነት በጎሳ ላይ የተመሰረተ እንጂ ሰው በመሆን ለይ እንዳልሆነ ሰርዓት የዘረጋ እለት ነው ኢህአዴግ ዘረኝነት ውሃ እያጣጣ ያሳደገው።አለም በጎሳና በዘር ላይ መሰረት ያደረግ ዲሞክራሲ ፣አምባገነንነት ሆነ የትኛውም አሰተዳደር በቃኝ በተባለበት አመት ከጫካ የመጣው መንግስት ግን በዘር ፍቅር ወድቆ ይህን ሰርዓት አመጣ።ሰርዓቱም ከመምጣጡ በፊት ብዙ ፍትህ የሚጠብቀው ኢትዮጵያዊ  ሳያሰበው ወደ ለየለት የጥላቻ ፖለቲካ ተወረወረ።ዛሬ ጊዜው የዘረኛ ነው።አማራ ከትግሬ ፣ኦሮሞ ከአማራ ፣ ሱማሌ ከኦሮሞ ፣አፋር ከትግራይ …ብቻ የማይጋጭ የለም።የሁሉም ግጭት አንድና አንድ ነው።አብዛኛው “የእኔ” ወይም “እኔ” ብቻ ነው የሚሉት።መሬቱ የእኔ፣ ስልጣን የእኔ፣ የበላይነት እኔ ፣ መሪ እኔ ፣ ቀዳሚ እኔ… … በእኔ ውስጥ ሆኖ በዘር ፍቅር ሌላውን መጥላት ፣ሌላውን ማባረት ፣መግደል ቀላል ሆነ።ይህ ደሞ በኢህአዴግ ፖለቲካ ዋና አቀንቃኝነት ይመራል።መከፋፈል የኢህአዴግ ድብቅ አጀንዳ አይደለም ፣ የጎሳ ግጭት መፍጠር ግልፅ አጀንዳ ነው ፣ አንድነት ማጥፋት የውስጥ ገፅ ሳይሆን በግልፅ ያለ ጫወታ ነው።በኢህአዴግ ፌደራሊዝም ለዘር ፣ጎሳ ፣ብሄር የሰጠው ቦታ ሰዎችን በአጉል ጥላቻ ከጊዜያት በሃላ እንዱጫረሱ ፣ከላይ ሲታይ ጤነኛ የመሰለ የእርስ በእርስ መከባባር ነገር ግን ውስጥ ውስጡን የለየለት ጥላቻን መተግበር ፣ ሲያዮት አንድነት የሚመስል ህብረት ነገር ግን ልዮንት ያሸነፈበት አንድነት የተንሰራፋባት ሰርዓት ውስጥ ነው የዘፈቀን።ህውሀት ኢህአዴግ ቀዳሚ ይሁን እንዲ የትኛውም የኢህአዴግ ድርጅት ለሰው ልጅ የሚገባውን ክብር አልሰጡም።

በዘር ፣በጎሳና በብሄር በግድ የሰው ልጅን ማጎር ኢ-ሰበዓዊ ብቻ ሳይሆን አንባገነንትና እንስሳነት ነው።ከየትኛው ብሄርና ጎሳ በላይ ሰው ክብር ሊሰጠው ይገባል። ሰው ክብር እንዲያገኝ ደሞ የግድ ጎሳና ብሄሩን ማወቅ ፣መደልደልና ይሄ ያንተ ይሄ የሱ ማለት አይፈለግም።ነገር ግን በኢህአዴግ ሰርዓት ከሰው በላይ ለብሄርና ጎሳ ቅድሚያ ሲሰጠው ሆን ተብሎ የታቀደበት ሰለሆነ ነው ።ስልጣን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣው ፓርቲው ጥላቻም ለኢትዮጵያ ሰላለው ነው።የትኛውም የብሄር ግጭት ለኢህአዴግ የሰራው ውጤት ሰለሆነ አይገርመውም ይበልጥ ደስታው ነው።

በሚነሱ የብሄር ግጭቶች እኔ ከሌለው አለቀልሽ ብሎ ያሰተምርሃል! እኔ ከሌለው ኢትዮጵያ አበቃላት ይልሃል! እኔ ከሌለው አንድነት የለም ብሎም ሳያፍር ይነግርሃል! እኛ የምናውቀው ግን ኢህአዴግ ከሌለ ዘረኝነት የለም ፣ጥላቻ የለም ፣መከፋፈል የለም ፣ ኢ_ፍትሃዊነት የለም ፣ግድያ የለም ፣መሰደድ የለም ነው።ለዚህ ለዘቀጠ ሰርዓት እንኳን ደስ አለህ! ስል በድጋም ለፈጠርከው ዘረኝነት ፣ጥላቻ ፣ ግድያ ፣ እስር ፣መከፋፈል ፣ፀረ_ሀገር እንቅስቃሴ ሲሆን የሰራህን ውጤት ደሞ ታገኘዋለህ።በብሄር ግጭት የማንም ዘር አይቀርም ከሞት ፣ከሰደት።የትኛውም ብሄር እስከ አፍንጫው ቢታጠቅ በለየለት የብሄር ግጭት መጎዳቱ አይቀርም።የዘረኘነት ሆነ የብሄር ግጭት ያለማወቅ ፣የዝቅጠትና የአንድ ሀገር ክፉ የሚመኝ የሚሰራው ሰራ ነው።ይህ እንዲ በሆነበት ውስጥ ከላይ ከላይ መዋደድ (ኢህአዴግ ስታየል) ይቅርብን እና ሰውን እንደ ሰው አክብረን ፣ እንደ ሰው ተከባብረን ከምድር የሰውን የመከባበር የአእምሮ ስልጣኔ ፤ ከሰማይ የአምላክን በረከት እንካፈል።እኔ ሰው ነኝ።ወደ ምድር ሰመጣም ሰው ፤ ስመለስም ሰው ሆኜ ነው።ሁሉንም በሰው አይን የማከብር ነኝ።ብሄር ፣ዘር ፣ጎሳ የለኝም ፤ አላውቅም።ዘሬ ሰው ነው፤ ጎሳዮ ሰው ነው።ስለዚህም ከማንም በላይ ለሰውና ለሀገሬ እኖራለው።እናተስ? ለጎሳህ ነው ወይስ ለሰው ነው የቆምከው?

Filed in: Amharic