>
4:38 pm - Tuesday December 2, 8921

የኢትዮጵያዊነት ከፍታ በመቶ ሚሊየን ዜጎች ከፍታ የሚገኝ እሴት ነው፡፡(ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

መቼስ ከአዙሪት መውጣት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ምጽአት ነው፡፡ የየዘመኑን ታሪክ ብንመረምር ነገስታትና መንግስታት የሚኮንኑትና የሚጸየፉት ያለፈውን ንጉስና መንግስት እንጂ፣ የግፍና የጭቆና ተግባራቸውን አይደለም፡፡ በመሆኑም ውለው ሲያድሩ የረገሙት መንግስት ተግባር የእነሱም መለያ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆነው የየመንግስታቱ ዋናው ማጠንጠኛ ስልጣናቸው በመሆኑ ነው፡፡ ለሀገር የሚበጃትን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፤ የህዝቡን ፍላጎት የሚያውቁት እነሱ ናቸው፤ የእውቀትና የፍትህ ሚዛን ስልጣናቸው ነው፡፡ በመሆኑም እንዴትም ከተለያየ ምንጭ ይፍለቁ የሚፈሱበት ቦይ አንድ አይነት ለመሆን ጊዜ አይፈጅበትም፡፡
,

እንደሚታወቀው ኢህአዴግ አብዝቶ የሰራው በብሄር ብሄረሰቦች ላይ ነው፡፡ ‹‹ይህን ያደረገው ለዚህ ወይም ለዚያ ብሎ ነው›› ብሎ የሚከራከር ይኖራል፡፡ ‹‹በብሄር ብሄረሰቦች ላይ አልሰራም›› የሚል ግን ያለ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነው›› ብሎ ነው፣ ህዳር 29ን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አድርጎ ያወጀው፡፡ ዛሬ ከሩብ ምእተ አመት በኋላ፣ ሰንደቅ አላማን ጨርቅ ሳያደርጉና ኢትዮጵያዊነትን ትቢያ ጥለው ሳይረግጡ፣ ብሄር ብሄረሰቦችን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ተረድቶ፣ የኢትዮጵያዊነትን ከፍታ መሻት ቢዘገይም የሚደገፍ አላማ ነው፡፡ ችግሩ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማምጣት ኢህአዴግ የተከተለው መንገድ ነው፡፡ በተለያዩ መፈክሮች ጥላ ስር፣ ለአስር ቀናት የአደባባይ ዝግጅቶች ተደርጓል፡፡
,

ከዚያስ? . . . ከዚያማ በቃ! የየአደባባዩ ባንዲራና መፈክር ይወርዳል፤ . . . ህዝቡም በግብር የተነሳ ኢትዮጵያዊነቱን እንደረገመ፣ . . . ቴዲም ሲዲውን ለማስመረቅ አዳራሽ እንደተከለከለ፣ . . . አንዳንድ ልማታዊ የየከተማው ነዋሪዎች ስለሰፈነው ሰላምና ስለልማቱ በቲቪና ራዲዮ አስተያየት እንደሰጡ . . . ልማታዊ ‹‹የጥበብ ሰዎች›› ከአስሩ ቀን የኢትዮጵያ ከፍታ ፕሮጀክት ያገኙትን የባንክ አካውንታቸው ጨምረው፣ በ2011 የዘመን መለወጫ የኢትዮጵያን ከፍታ ለ20 ቀናት እንዲከበር ፕሮጀክት እየነደፉ . . . . ህይወት ይቀጥላል፡፡
,
ኢህአዴግ ከልክ ያለፈ ጎጠኝነትና ጠባብነት ያመላከተውን አደጋ ለመግፈፍ የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ከፍታ ፈልጎታል፡፡ ለዚህም በተለያዩ የብዙሀን መገናኛዎች እንደተገለጸው፣ ለአስር ቀን የአደባባይ እግጅት፣ በሁለት ልማታዊ አርቲስቶች ተወጥኖ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
,
በእርግጥ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከወደቀበት መነሳት . . . ከፍ ማለት አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እያነወርንና እየዘረጠጥን፣ በብሄር ብሄረሰቦች ልዩነት የደመቀች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ አይቻልም፡፡ በየዘመኑ የነበሩት መንግስታት በሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ያደረሱትን በደል፣ በኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሀሳብ የተፈጸመ አድርጎ በመቁጠር፣ ኢትዮጵያዊነትን ለክስ ማቅረብ ተገቢነት አልነበረም፡፡ በየዘመኑ ህዝቦች በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የነበራቸው መብትና የተጣለባቸው ግዴታ ፍትሀዊ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ፍትሀዊ ያልነበረ የዜግነት አስተዳደርን ብሄራዊ ስሜት ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ኢትዮጵያዊነትን በመኮነንና በህዝቦች ላይ ለደረሰው መድሎ ተጠያቂ በማድረግ አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢፍትሀዊ የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት ግንኙነት እሴቶች ፍትሀዊ አድርጎ በማደስና በዚህ አዲስ ፍትሀዊ የዜግነት ግንኙነት ዜጎች በእኩልነት እንዲጠቀሙ በማድረግ ነው፡፡ በቀደሙት ዘመናት የሀገሪቱ ህዝቦች በብሄራቸው የተነሳ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ፍትሀዊ መብት አልነበራቸውም፡፡ በተለይ በደርግና በኢህአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ዜጎች በጎሳዊ ማንነታቸው የተነሳ የሚደርስባቸው መድልኦ እየቀለለ መጥቷል፡፡ በነዚህ ሁለት መንግስታት ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች የሚደርስባቸው መድልኦ በጎሳዊ ማንነታቸው የተነሳ መሆኑ ቀርቶ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ምክንያት ነው፡፡
,
ሁለቱም መንግስታት የእነሱን ፖለቲካዊ አመለካከት የማይቀበል ዜጋን በጸጋ አይቀበሉም፡፡ ደርግ ገና በነገሰ ማግስት፣ ‹‹አድሀሪ፣ አቆርቋዥ፣ ጸረ ህዝብ፣ ጸረ አብዮት፣ ጸረ አንድነት . . ወዘተ.›› የሚሉ አሉታዊ ቅጥያዎችን ፖለቲካዊ አስተዳደሩን በሚቃወሙ ዜጎች ላይ በመለጠፍ ሲያሳድዳቸው ኗሯል፡፡ ኢህአዴግም ገና በጠዋቱ ነው የሽግግር ቻርተሩን ባጸደቀበት ጉባኤ፣ ‹‹ጸረ ቻርተር›› ብሎ ታቴላ መለጠፍ የጀመረው፡፡ እነሆ ይህ አድጎ ‹‹ጸረ ሰላምና ጸረ ልማት›› ላይ ደርሷል፡፡ በአንጻሩ የኢህአዴግን ፖለቲካዊ አመለካከት መደገፍ ‹‹ልማታዊ›› የሚል ማእረግ ያስገኛል፡፡ ኢህአዴግ ከዜጎች መካከል ልማታዊያኑን ሰብስቧል፡፡ በልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ልማታዊ አርቲስት፣ ልማታዊ አርሶ አደር፣ ልማታዊ ነጋዴ፣ ልማታዊ መምህር . . . ወዘተ. ታጅቦ ለልማት ደፋ ቀናውን ተያይዞታል፡፡
,
ይህ ዜጎችን የሚከፋፍልና በደረጃ የሚመድብ አስተሳሰብ ነው፤ ሀገራዊ አንድነትን፣ ልማትንና የታሰበውን ከፍታ አያመጣም፡፡ ሀገራዊ እድገትና ከፍታ ሊገኝ የሚችለው ዜጎች በሙሉ በሀገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ ሲደረጉ ነው፡፡ የአንድ ሀገርን ዜጎች በሙሉ የአንድ መዝሙር ተቀባይ ለማድረግ መሞከር የሰውን ተፈጥሮ አለመረዳት ነው፡፡ ሀሳብን የሚሞግቱ – ሞግተው የሚቀበሉ ወይም አንቀበልም ብለው የራሳቸውን ሀሳብ የሚያቀርቡ ዜጎች አሉ፡፡ የራሳቸው ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ የቀረበላቸውን የሚቀበሉ – ሀሳብን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ብቻ የሚመዝኑ እራስ ወዳዶች አሉ፡፡ ጥቅም አስገኘላቸውም አላስገኘላቸውም የተባሉትን አሜን ብለው የሚቀበሉ – በፍርሀት የተሸበቡ ዜጎችም አሉ፡፡ አንድ መንግስት ዜጎቹን ሲያስተዳደር የሀሳብና የፖሊሲ ግብአት ማድረግ ያለበት የመጀመሪያዎቹን ነው – ሀሳብን መርምረው የሚቀበሉ ወይም የሚቃወሙትን፡፡ ኢህአዴግ በአብዛኛው በነዚህ ላይ ሲያተኩር አይታይም፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያ በኢህአዴግ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የአስተዳደር ስልጣን ውስጥ የአዲስ ሰዎች እምብዛም አለመታየት ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነትን የሚሞግቱ ሰዎችን እንደተቃዋሚ ስለሚመለከታቸው ሀሳቡን የተቀበሉትን ልሂቃን፣ በየአምስት አመቱ ከስልጣን ወደ ስልጣን እያቀያየረ ቀጥሏል፡፡ የዜጎችን የ‹‹ሀገሬ›› ስሜት ሸርሽሮ፣ የኢትዮጵያዊነትን ዝቅታ ያስከተለው አንዱ ምክንያት ይህ ይመስለኛል፡፡
,
‹‹የኢትዮጵያዊነት ከፍታ›› የሚለው መፈክር የዘመን መለወጫ እንዲሆን ሲመረጥ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተፈለገው ከፍታ ላይ አለመገኘቱን፣ መኮሰሱን ነው፡፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ኮስሷል፡፡ ይህን መንፈስ ከፋ ለማድረግ በመጀመሪያ መንፈሱን ያኮሰሱትን ሁኔታዎች መለየት ያሻል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ መኮሰስ የምናውቀው፣ ከፍታውንም የምናመጣው እኛ ነኝ›› ከሚል ያሰለች ተግባር ተላቆ፣ ህዝብን በማነጋገር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማማከርና በምሁራን ምክንያታዊ የሁኔታዎች ትንታኔ ላይ ተመርኩዞ መሰራት አለበት፡፡ ይህ ሳይደረግ መንግስት ላለፉት አመታት ኢትዮጵያዊነትን ባኮሰሰበት አካሄድ ኢትዮጵያዊነትን ሊያነግስ አይችልም፡፡
,
ኢህአዴግ አዲስ አይን ማውጣት . . . ወደ ውስጡ መመልከት አለበት፡፡ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ የፕሮፓጋንዳ ስራ በህዝብና በመንግስት መካከል ግንብ ያቆም እንደሁ እንጂ፣ ፍቅርና መተባበርን አያመጣም፡፡ ለሀያ አምስት አመታት የኢትዮጵያዊነት መንፈስን ባኮሰሰው ስትራቴጂ፣ መፈክር በመደርደር ብቻ የኢትዮጵያዊነትን ልእልና ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ አመለካከቱን መፈተሽ አለበት፡፡ ቡድናዊነት ከተቆራኘው አመለካከት እስካልጸዳን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ማድረግ ዘበት ነው፡፡ ሰራተኛውንና ዜጋውን ‹‹ልማታዊ›› እና ‹‹ጸረ- ልማት›› ብለን ከፋፍለን የኢትዮጵያ ከፍታ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ መንፈስ ኮስሷል ካልን፣ ይመነደግ ዘንድ ይህን ‹‹የልማት – ጸረ ልማት›› ግንብ ማፍረስ አለብን፡፡ ኢህአዴግ ይህን ግንብ አፍርሶ ስለሀገራቸው ጉዳይ ዜጎቹን ሁሉ ማሳተፍ አለበት፡፡ የኢትዮጵያዊነት ከፍታ በመቶ ሚሊየን ዜጎች ከፍታ የሚገኝ እሴት ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ የማያገባው ዜጋ የለም፡፡ ሁሉም ሊደመጥ ይገባል፡፡ ሀገሪቱ የአምስት አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ሀገር ብቻ እንደሆነች ሁሉ፣ እነዚያን ‹‹ልማታዊ›› ብሎ በማቆላመጥ፣ እነዚያን ብቻ የአንድ ሀገር ህዝቦች ሙሾ ደርዳሪና ዘፈን አውራጅ ማድረግ ጠብ የሚል ለውጥ አያመጣም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ከፍታ በተወሰኑ ልማታዊ አርቲስቶች የአስር ቀን ፕሮጀክት የሚደረስበት አይደለም፡፡ ዜጎችን ሁሉ በማሳተፍ ከአመት አመት አይደለም፣ ከዘመን ዘመን ያለማቋረጥ ልንሰራበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡

Filed in: Amharic