>
4:32 am - Tuesday January 31, 2023

የቀበሮው ምክር (ታምሩ ተመስገን)

…ቅድመ አለም ምድር ውብና መልካም ሳለች በርካታ አይነት ዶሮዎች የሚኖሩበት የሰጡትን ሁሉ የሚያበቅል ከደስታ ዜማ በቀር ዋይታ የማይሰማበት አንድ ለምለም ሀገር ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ዶሮዎች በህብረት የሚያርሱትም ሰፊ የበቆሎ እርሻም ነበራቸው፡፡ የበቆሎ መትከያ ጊዜም በደረሰ ጊዜ ወጣት ወንድና ሴት ዶሮዎች ሰፊ ማሳቸውን እያረሱ ለዘር ያዘጋጁት ነበር፡፡ የተቀሩት ሸመጋግሌና እናት ዶሮዎች ህፃናት ዶሮዎችን እየተንከባከቡና ቀያቸውን ሲጠብቁ ይውላሉ፡፡ ማምሻውን ደግሞ ሌሎቹ ዶሮዎች ከእርሻ ሲመለሱ እሳትዳር ከበው ይቀመጡና የተከካ በቆሏቸውን እየበሉ ከሽመጋግሌዎች ዘንድ የዶሮነታቸውን ጥንተ ታሪክና የአንድነታቸውን ምክር ይስሙም ይማሩም ነበር፡፡

…አንድ ጧት ዶሮዎቹ በክረምት የዘሩትን እህል በበጋ እያጨዱ በጎተራም እያከማቹ ሳለ አንድ ቀበሮ በአካባቢያቸው ያልፍ ነበርና የደሮዎቹን መወፋፈርና ማማር ተመልክቶ ሊበላቸው ጎመዠ፡፡ ግና ዶሮዎቹ እንቅስቃሴአቸው በአንድነት ስለነበር ነጥሎ ለመብላት አልተቻለውም፡፡ ዘዴም መዘየድ እንዳለበት አስቦ እስኪመሽ ድረስ ከዶሮዎች ሰፈር ካገኘው አንድ ጉድባ ውስጥ ተደበቀ፡፡ በመሸም ጊዜ አንድ ዶሮ ፋኖሱን እንዳንጠለጠለ ሽንቱን ሊሸና ወደ ዱር እንደገባ ቀበሮው ባስተዋለ ጊዜ ዳናውን አጥፍቶ ተከተለው፡፡ ዶሮው አጠገብም በደረሰ ጊዜ “እንዴት አመሹ ጌታ ዶሮ?” ሲል እጅ ነሳ፡፡ ዶሮውም ሰምቶትና አይቶት የማያውቅ አፉ የሾለ አራት እግርም ያለው እንስሳ ካጠገቡ ቆሞ ሲያነጋግረው በተመለከተ ጊዜ ግራ ተጋብቶ “እዝጌሩ ይመስገን፡፡ ማነህ አንተ?” ሲል እንዲጠይቀው ሆነ፡፡ “ስለኔ ብዙም ሰምተው እንደማያቁ ታነጋግሮ ተረድታቸለሁ፡፡ እኔ ባለ ብዙ ሙያ ቀበሮ እባላለሁ፡፡ ወዲህም የመጣሁት አርሶን በአንዳንድ ነገር እንድረዳዎ ከአምላክ ተልኬ ነው፡፡” አለ ቀበሮው ውሸቱን፡፡ ዶሮው ግን ሀይማኖተኛ ስለነበረ ቀበሮው ያለውን አመነው፡፡ “እንግዲህ ውለታዎን ፈጣሪ ይክፈሎት፡፡ ታዲያ በምን ጉዳይ ሊረዱኝ ወዲህ መጡ፡፡” ዶሮ ጠየቀ፡፡ ቀበሮው በቀጣፊ ምላሱ አፍንጫውን ልሶ ሲያበቃ መለሰ “ጌታ ዶሮ እንግዲህ እንደነገርኩዎ የተላኩት ከፈጣሪ ዘንድ ነው፡፡ እርሱ በፈቀደ ዘመናዊነትን ላስተምሮ የፈጣሪንም ቋንቋ ላስገነዝብዎ በሁሉም ዶሮ ላይ ልሾምዎ ነው አመጣጤ፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ አበረክትሎ ዘንድ ይሄ ጉዳይ በሚስጢር መያዝ አለበት፡፡ በእርሶና በእኔ መካከል ቃል ኪዳንም ይሁን፡፡ ከዚያ ባሻገር ወዲህ የእርሶን ስኬት የማይሹ ዶሮዎች ከመሀከልዎ ይገኛሉና አነርሱን እቀጣ ዘንድም ተቀብቻለሁ፡፡ እነርሱንም ማንም ዶሮ ሳያዮት በድብቅ ወደኔ ያመጡልኛል፡፡” ከቀበሮው ንግግር ውስጥ በሌሎች ዶሮዎች ላይ እንደሚነግስ የተረዳው ዶሮ ደስ አለው፡፡

ከዚያች ቀን ጀምሮ ቀበሮው ፈፅም ያለውን ያለ ማንገራገር ይፈፅም ጀመር፡፡ ማንም ሳያስተውለው ቀበሮው ጠላትህ ናቸው ያላቸውን ዶሮዎች እያፈነ አምጥቶ ለቀበሮው ይቀልበው ጀመር፡፡ ቀበሮውም ለስልቱ ይረዳው ዘንድ ለበፊቱ ዶሮ የነገረውን በሙሉ ለሌላ ዶሮ ነገረው፡፡ ይሄኛውም ዶሮ ከበፊቱ ዶሮ የተሻለ ሰርቶ እንደሚያስደስተውና እንደሚነግስ ለቀበሮው አስረድቶ ወገኖቹን እያመጣ ይገብር ጀመር፡፡ “ሌሊት እየጮኸ ድመት የሚጠራባችሁን ዶሮ ወዲህ በል” ይለዋል አንደኛውን ዶሮ፡፡ ተዕዛዙን ይፈፅማል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላኛውን ዶሮ “በምሽት በግልፅ እየታየ አነር የሚጠራባችሁ ያን ወደል ዶሮ እያዳፋህ አምጣልኝ፡፡” ይለዋል፡፡ ለዙፋን የተጠማው ዶሮ ደግሞ ከሰፈር ዘልቆ የተባለውን አይነት ዶሮ ደም እያስደፈቀ ቀበሮው ድረስ ያመጣዋል፡፡
.
… የዶሮዎቹን መመናመንና የቀበሮውን ድርጊት ትመለከት የነበረች የዶሮዎች ጎረቤት የነበረች አንዲት ጅግራ ለባሏ አማከረችው፡፡ “አንቱ ጅግራ ግን በዶሮዎቹ መንደር እየሆነ ያለውን ነገር አስተውለዋል?” ወንዱ ጅግራም ጋቢያቸውን አጣፍተው ሲያበቁ፡፡ “ምን ሆኑ ደግሞ?” እንደተኮፈሱ ጠየቁ፡፡ “ይሄው የዛን የቀበሮ ምክር ከሰሙ በኋላ እርስ በርስ ተከፋፍለውና ጎራ ለይተው እየተባሉ ነው፡፡ ደካሞችን ደግሞ መስዋት እያደረጉለት ነው፡፡” “ታድያ አንቺ ምን አስጨነቀሽ?” አሁንም ከተኮፈሰበት ወንበር ሳይነቃነቅ ጠየቀ፡፡ ሴቷ ጅግራ አሻግራ ከምታየው የዶሮዎቹ መንደር ፊቷን መለስ አድርጋ ባሏን እየተመለከተች “አይ አንቱ ጎረቤቴ ሲጮህ ለኔ ብለህ ስማ ‘ኮ ነው ‘ሚባለው፡፡ ሄደን አንዳች እርዳታ እናድርግላቸው እንጅ፡፡” “አንቺ ጅግራ በማይመለከትሽ ነገር ዘው ብለሽ አትግቢ እነርሱ ዶሮ እኛ ደግሞ ጅግራ ምናችንም አይገናኝም፡፡ ይልቁንስ እራት የሚሆን ጥራጥሬ አቅርቢ እስኪ፡፡” ሴቷ ጅግራ ቱግ አለች፡፡ “እርሶ ጅግራ ግን እንዴት እንዴት ነው ‘ሚናገሩት፡፡ እኒህ ምስኪን ዶሮዎች እኛ በተበደልን ጊዜ አልደረሱልንምን? ደርሰውልናል፡፡ ደግሞስ እኛ ጅግራ እነርሱ ዶሮ ምን ያገናኘናል ‘ሚሉት… ቀለማችንና አዋዋላችን እንዲሁም ቋንቋችን ይለያይ እንጅ እነርሱም የዶሮ ዘር እኛም የዶሮ ዘር፡፡ እስቲ ይበሉ ይንገሩኝ የቱ ጋር ነው ልዩነታችን?” “አንቺ ጦሰኛ ጅግራ አድቢ ብያለሁ፡፡ ቀድሞውንም ቀበሮው ዶሮዎቹን አፋጃቸው እንጅ ከኛ ዘንድ መች ደረሰ! የራስሽን ድንበር ታከብሪ እንደሆን ተግተሸ ጠብቂ፡፡ ጎረቤታችን ከገቡበት ማጥ ራሳቸው ዋኝተው ይውጡ፡፡ እኛ እንደሆን እንኳን ይሄ ኮስማና ቀበሮ አንበሳ እንኳን የማይዳፈረው አጥር አበጅተናል፡፡ የሚያሰጋሽ ነገር የለም፡፡ አሁን ወሬውን ተይና እስኪ እራት ጥራጥሬውን በርከት አድርገሽ አቅርቢልኝ፡፡” “አንቱ ጅግራ ግን ጎረቤቶቻችን ሲበደሉ ያልረዳናቸው እኛ ኋላ እጣችን እንደነሱ ነው የሚሆነው፡፡” “ወይ ጉድ አንቺ ጅግራ ግን ለምን አትተይኝም…”
.
… ዶሮዎቹም በቀበሮ እየተከፋፈሉ እየተበሉም አንዳቸው አንዳቸውን ደም እያስገበሩ ዘመናት አለፉ፡፡ ያም ኮስማና ቀበሮ ዶሮዎቹን ሲበላ ኖሮ አለቅጥ ወፍሮ ግርማውም ያንበሳ ሆነ፡፡ በማሳው በርከተው የነበሩት ዶሮዎች እርስ በእርስ ተጫርሰው ኖሮ ቀበሮው የሚበላው አጣ፡፡ ዙሪያ ገባውን ሲያደባም የዶሮዎቹን ጎረቤት የጅግራዎቹን ቤት ተመለከተ፡፡ ወደ አጥራቸውም ተጠግቶ ሲያስተውል በርካታ ጅግራዎች በማህበር ተሰብስበው የጥራጥሬው አይነት የመጠጡ አይነት በሴማ በሴማ ሆኖ ፍስሃ ሲያደርጉ ተመለከተ፡፡ ርሃቡን ያስታግስም ዘንድ አጥራቸውን ጥሶ ገባ….
.
… በሀገራችን እና በህዝባችን እየሆነ ያለውን ነገር ነግ በኔ ነው፡፡ ጎረቤቱ ሲጮህ ከቋንቋየ አላበረም ከባህሌ አልወገነም ከታሪኬ አልተወዳጀም ብሎ ቤቱ ያደፈጠ ጎረቤት ብቻውን በቀበሮ ፊት የሚቆምበት ጊዜም ሩቅ አይደለም፡፡ ቅድሚያ ሀበሻ!

Filed in: Amharic