>

"ኢህአዴግ እንዴት ይወድቃል?"… ገባልኝ፥ አስገቡልኝ!! (ስዩም ተሾመ)

ከተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን “እንዴት ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሳዊ ስርዓት የተሳካ ሽግግር ማድረግ ይቻላል?” በሚለው ላይ ስልጠና እየሰጡ ነው፡፡ ከአሰልጣኞቹ አንዱ የሆነው የአሜሪካዊ ፕሮፌሰር የተለያዩ የጥናቶችን ዋቢ በማድረግ “ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ 3%ቱን ያሳተፈ ህዝባዊ ንቅናቄ ዓላማውን ያሳካል!” እያለ በእርግጠኝነት ሲናገር በሆዴ “ቲሽ… ጥራዝ ነጠቅ!” አልኩና እጄን አወጣሁ፡፡

እንድናገር እድል እንደተሰጠኝ “የሄውላችሁ… የአምባገነን መንግስት ስልት የገባችሁ አይመስለኝም! የአምባገነን መንግስት፤ በመጀመሪያ፦ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን ለእስርና ስደት በመዳረግ አማራጭ የፖለቲካ ሃይልን እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በመቀጠል፦ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያን በማጥፋት የራሱን በውሸትና ግነት የተሞላ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በብዙሃኑ አመለካከትን ላይ ፍርሃትና አለመተማመን እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ በመጨረሻም፦ የሲቭል ማህብራትን በማጥፋት የተቀናጀ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት ሶስቱን የዴሞክራሲ መዋቅር ምሶሶዎች (Pillars) ያፈርሳል፡፡ ከዚያ በኋላ በህዝባዊ ንቅናቄው 3% ቀርቶ 33%ቱ ህዝብ ቢሳተፍ አምባገነናዊ ስርዓቱን በሰላማዊ መንገድ ከስልጣን ማስወገድ እጅግ ከባድ ይሆናል! አሁን በኢትዮጲያ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት አመታት በግምት ከ3% በላይ ህዝብ የተሳተፈበት ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ ቢቻልም አምባገነኑን የኢህአዴግ መንግስት ከስልጣን ማስወገድ ግን አልተቻለም፡፡ ቅድም ካነሳችሁት ሃሳብ አንፃር ይሄን እውነታ እንዴት ታዩታላችሁ?” በማለት ጠየቅኳቸው፡፡

የአሜሪካዊው ፕሮፌሰር ግን አንድና አንድ ነው፣ እሱም፦ አንድነት ነው፡፡ “የኢትዮጲያን ፖለቲካ በቅርበት እከታተላለሁ፡፡ አሁን ላነሳህው ችግር ዋና መንስዔው ህዝባዊ ንቅናቄው አንድነት የለውም፡፡ በተለይ ከሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸው የኦሮሞና አማራ ህዝብ ንቅናቄ አንድነት የለውም!” ሲለኝ በተቀመጥኩበት ወንበር ላይ ወደፊት እየተንፏቀቅኩ እግሮቼን ወደፊት፥ እጆቼን ወደጎን ዘርግቼ ተለጥጬ ተቀመጥኩና 7ቁና ተነፈስኩ!!! ፕሮፌሰሩ ቀጠለና “ገብቶሃል?” ሲለኝ ! በእርግጥ “ገብቶኛል” ከማለት ይልቅ “ገብቶልኛል!” ብለው ይቀላል ብዬ “Oh.. I don’t got you… rather you got me!” አልኩት፡፡ አዳራሹ በሳቅ ተናጋ!… ምድረ ጎጠኞች ፈጣሪ የእጃችሁን ይስጣችሁ!!

Filed in: Amharic