>
7:24 pm - Wednesday February 8, 2023

የመለስ እርኩስ መንፈስ (ኃይሉ ማሞ)

አቶ መለስ ዜናዊ የሞተበት 5ኛ ዓመትን አስመልክቶ ደጋፊዎቹ ውርሱን እንዘክራለን በሚል ባገኙት መገናኛ መንገድ ሁሉ ቅዱስነቱን ሲሰብኩ እየታዘብን ከርመናል። ይህን ጊዜም በትዝብት አለፍ ስንል ሁሌም የመለስ ምናምን ከማለት ወጥተው በራሳቸው እንደሰው መቆም የማይችሉት ስንኩላን የስርዐቱ ስብስቦች ልክ መለስ ዜናዊ ባንዲራ ጨርቅ ነው ባለበት አፉ የባንዲራ ቀን የሚል ከበሮ እንደደለቀው ሁሉ፣ በህገመንግስቱ ሳይቀር የኢትዮጵያ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሳይሆን የብሄር ጥርቅም ነው እንዳላሉ የ2010 ዓ/ም ዘመን መለወጫን አስመልክቶ የከፍታ ቀን፣ የሀገር ፍቅር ቀን ወዘተ የሚሉ የካድሬ ጥሩንባዎችን እየሰማን አዲስ ዓመቱን ተቀበልን። ከካድሬው ጥሩንባ ባሻገር ያለው እውነት ግን የስርዓቱ የአፈና ተግባር ተባብሶ እንደሚቀጥል የተረጋገጠበት፣ የሀገር ፍቅሩ ቀርቶ ኢትዮጵያ ተብሎ ስሟ ሲጠራ ዘረኞቹ እስከስረኛው አንጀታቸው የሚታመሙ መሆኑን የቴዲ አፍሮ ኮንሰርትና አልበም ምረቃ ዝግጅቶች መታገድ ቀጣዩንም የጨለማ ጊዜ ነጭና ጥቀር በሆነ መልኩ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር። የኢትዮጵያ 2010 መባቻ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የመለስ እርኩስ መንፈስ ግዘፍ ነስቶ የታየበትም ነው። ህወሀት በሰሜን አማራና ቅማንት በማለት በህዝቦች መካከል የጥላቻና የመነጣጠል ዘር ለመዝራት ሲዳክር በደቡብ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል ደግሞ የዘር ካባን በለበሰ ሽፋን ልዩ ኃይል በተሰኘ የህወሀት ልዩ የግድያ ቡድን አማካይነት የኦሮሞን ህዝብ ሲጨፈጭፉ ከርመዋል። በደቡብም በአማሮ ኬሌ፣ በጉጂና በቡርጂ ህዝቦች መካከል የተለኮሰው እሳት አካባቢውን ሲያጋይና የህዝቡ ውሎ አዳር የፍርሀትና የስጋት ደመና ያንዣበበት እንደሆነ እስካሁንም ቀጥሏል። የመሀል ሀገሩ ህዝብም በገቢ ትመና ሰበብ ለዘረፋ ተዳርጎ ድኃው የእለት ጉርሱን ቃርሞ ማደር ያልቻለበት፣ አቤት የሚልበት ያጣበት የሰቆቃ ድምጾች ከየቦታው የሚሰሙበት ወቅት እንደሆነ 2010 ተንደረደረ። እናም የተቀበልነው አዲስ ዓመት ካድሬው የወደቀ ፕሮፓጋንዳውን ሲያንቋርር የህዝቡ ለቅሶ ደግሞ ህዋውን አልፎ ሰማየ ሰማያት የዘለቀበት ነው።

በርካታ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ወቅት የሀገሪቱ መጪ ጊዜ ከልብ የሚያስፈራቸው ሙሁራን የሚያነሱት ግን እንደዋዛ እየተሰማ የሚታለፍ ነጥብ አለ። ኢትዮጵያ በህወሀት እጅ ውስጥ በቆየች ቁጥር የሚገጥመን አደጋ የከፋ ከመሆን አልፎ እስከወዲያኛው ሀገር ሊያሳጣን እንደሚችል ተደጋግሞ ተወስቷል። የኢትዮጵያን ውሎ አዳር በቅርበት የተከታተለና የህወሀትን አመጣጥ ብሎም ስልጣን ላይ ለመቆየት የተመሰረተባቸውን ምሶሶዎች ለተገነዘበ ይህ ስርዓት የሀገራችን መጥፊያ መሆኑን ለመረዳት ደቂቃዎችን የሚፈጅ ጊዜም አይፈጅበትም። ህወሀትና የህወሀት ቅልቦች የመለስን እርኩስ መንፈስ ተሸክመው በዚሁ እርኩስ መንፈስ ሀገሪቱን እያመሷት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ኢትዮጵያም በዚህ እርኩስ መንፈስ የምትቃትት ሀገር፣ ህዝቧም በእርኩስ መንፈሱ የሚሸበር ሆኖ እየመሸ ይነጋል፥ እየነጋ ይመሻል።

ሁሉንም የመለስ የእርኩስ መንፈስ ውርሶች ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም አንኳር የሆኑት መጠቃቀሱ ግን ከላይ ለተንደረደርንበት ሀሳብ አጋዥ ይሆናልና ጥቂት እንጠቃቅስ።

 ጥላቻና ቂም

የመለስ የቀድሞ የትግል ባልደረባና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ነጻነትና ዳኝነት በኢትዮጵያ በሚለው መጽሀፋቸው ስለመለስ ዜናዊ ሲገልጹ፡ መለስ አባቱ ጣሊያንን መርተው ካስገቡ ባንዳዎች አንዱ በመሆናቸው የትምህርት ቤት እኩዮቹ የባንዳ ልጅ በሚል ያሸማቅቋቸው ስለነበር በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ የመረረ ጥላቻና ቂም አርግዞ ያደገ መሆኑን የዊንጌት ትምህርት ቤት የአብሮነት ቆይታቸውን ጠቅሰው አስነብበውናል። እንግዲህ ገና ከመነሻው በዚህ ዓይነት በጥላቻና በቂም ተለውሶ ያደገ ሰው የሚጠላውን ህዝብና ሀገር የመግዛት አጋጣሚን ሲያገኝ ለዚያች ሀገር አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ይሰራል ማለት በሬ ይወልዳል ብሎ የመጠበቅ ያህል ቂልነት ነው። በተግባር የታየውም ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ከምድረ ዓለም ካርታ ለማጥፋት የተሄደበት ርቀት የመለስ ዜናዊ የቂምና የበቀል ውጤት ነው። የመለስ ዜናዊ የቂመኝነት መጠንም ኢትዮጵያን የማጥፋት እልህ ብቻ ሳይሆን ለጥፋት ተልእኮው አብረው የታገሉትን ጓዶቹን ሳይቀር በየአጋጣሚው ቀረጣጥፎ የሚውጥ ጥቀር ዘንዶ መሆኑንም በተግባር ያሳየ ነው። የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አንባገነነናዊ ገዢ የነበረው ጆሴፍ ስታሊን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከምእራባዊያን ጋር አብሮ ናዚ ጀርመንን ማሸነፍ ቢችልም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ባላንጣቸው ለመሆን የቀድሞ የትግል አጋርነት አላገደውም። መለስ ዜናዊም እነስዬ አብርሀን፣ ቢተው በላይንና ሌሎችንም ሙስና በሚለው የመጠፍነጊያ ሰበብ ለቃቅሞ እስር ቤት ሲያጉር አዲስ አበባ ቤተመንግስት እስኪገቡ አብረው የወጡ የወረዱበትን ዳገትና ቁልቁለት፣ ጫካና እሾህ ለአፍታም ግምት ውስጥ አላስገባም።

ዘረኝነት

የመለስ ዜናዊ እርኩስ መንፈስ ጎልቶ የሚገለጽበት አንዱ ነገር ይዞት ከመጣው ስርዓት ጋር የተከለው የዘረኝነት መርዝ ነው። ኢትዮጵያ በገዛ ህገ-መንግስቷ የሀገርነት እውቅና ያላገኘች የዓለማችን ሀገር ናት። እንደሀገር ጠንካራ መሰረት ያላት ሳትሆን የጥርቅሞሽ ምድር ተደርጋ የተገለጸችው በመለስ ዜናዊ ዘመን በተጻፈ ህገ መንግስት ተብዬ ነው። ዛሬ ይህ የዘር እርኩስ መንፈስ ኢትዮጵያችንን እያስቃተታት ነው። በሀዝቦቿ መካከል ጥርጣሬ፣ ስጋት፣ ፍርሀት፣ ጥላቻ፣ የዘወትር ኑሮ ሆነዋል። ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ከአንድ ገጠር ወደ ሌላ ገጠር የማይሄዱበት፣ ከከተማ ከተማ ተንቀሳቅሰው ሰርተው መኖር የማይችሉበት፣ መፈናቀል፣ ሞት፣ ቃጠሎ፣ እለት እለት እንደተራ ነገር የሚነገርባት ሀገር ሆና እያየናት ነው። ዛሬ ያለው ሁኔታም እያደገ ሄዶ የለየለት መተላለቅ ውስጥ እንዳይገባ የሁሉም ስጋት ሆኗል። አሁን የምናየው በህወሀት አዝማችነት የሚደረገው የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው እውነትም የአደጋውን ከፍተኛ ደረጃ ማሳያ ነው። ዛሬ ሰዎች መታወቂያቸው እየታየ በዘር ማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ ነው። ዛሬ እየሞቱ ላሉት እናዝናለን ምናልባትም እንደእሩቅ ወሬ ሰምተን ከንፈራችንን እንመጥጣለን። አደጋው ግን አንድ ቦታና ወቅት ላይ የሚቆም አይደለም። ህወሀት ላይ ያደረው ጋኔን የሚነዛው እርኩስ መንፈስ እስካልተወገደ የባሰ ይመጣል።

ዘረፋ

መለስ ዜናዊ ይዞት የመጣው አንዱ ምናልባትም ቶሎ የማይድነው በሽታ የዘረፋ ባህል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ትዕግስትና ልፋትን የሚጠይቅ ስራ ሰርቶ እራስን በኑሮ መለወጥ ከዘመኑ ጋር ያለመራመድ ወይም በዘመኑ ቋንቋ ገገማነት ነው። በአንጻሩ ከባለስልጣን ጋር ተሞዳሙዶ፣ ግቦ ሰጥቶና አቀባብሎ፣ አብልቶና ተመቻችቶ ማምለጥ የሚል የስግብግብነት ባህል ከባለስልጣናቱ አልፎ ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽና ባህል እንዲሆን የመለስ ስርዓት በአለማችን ወደር የማይገኝለት የሌብነት ተምሳሌት ነው። የመለስ የሌብነት እርኩስ መንፈስ ያስፋፋው የገንዘብና የሀብት ዘረፋ ብቻ አይደለም። በኢንቨስትመንት ስም በሚደርግ የመሬት ቅርምት አንድን ወረዳና ቀበሌ ብቻ ሳይሆን ድፍን ሀገርን የሚውጥ ጉድ ተፈጥሮብናል። አልፎ ተርፎም ባህልና ማንነት ሲዘረፍ ያየነውም በመለስ ዜናዊው ህወሀት አማካይነት ነው።

ውሸት

በኢትዮጵያዊያን ባህል ውሸት ጠቃሚ ነው ከተባለ ለእርቅ አገልግሎት ሲውል ብቻ ነው። ቀደምቶች በሚፈበረክ የሀሰት ምክንያት ጥላቻ እንዳይኖር ሲመክሩም “ሰው ዋሽቶ ያስታርቃል እንጂ ዋሽቶ አያጣላም” በማለት ክሽን አርገው ይገልጹታል። የህወሀት ስርዓት እግሩ ኢትዮጵያን ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ ግን ውሸት መለመዱ ብቻ ሳይሆን እውነት ሳይሰማ ከ26 ዓመታት በላይ ተደርሷል። የመንግስትነትን ትልቅ ስም የተሸከመ ተቋም፣ መንግስትን እመራለሁ የሚል ትልቅ ሰው ተብዬ፣ በህዝብ ሀብት የሚተዳደር ግዙፍ የመገናኛ ተቋም ሌት ተቀን ውሸትን እንደመተዳደሪያ ሲያወሩ ለለመደና ይህን እያዩ ለሚያድጉ ህጻናት የውሸታምነት ነውር እንዴት ሊገባቸው ይችላል? መንግስት ሲዋሽ ካላፈረ ግለሰብ ሲዋሽ እንዴት ሊያፍር ይችላል? የተራቡትን ጠግባችኋል የሚል፣ በውሸት ሪፖርት የሀገሪቱን እድገት የሚለካ፣ ውሸት ፈብርኮ ህዝብን ከሀዝብ የሚያናክስ፣ በውሸት ዲስኩር ታሪክን የሚበርዝ እንደመለስ ዜናዊ ያለ የርኩስ መንፈስ ተሸካሚ ከቶ ከየትስ ይገኛል?

 ብሄራዊ ውርደት

ኢትዮጵያ እንደሀገር የተዋረደችበት እንደህወሀት ዘመን ያለ ቀድሞ እንዳልነበረው ሁሉ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ለኢትዮጵያ ጥላቻና ቂምን ሰንቆ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የዜናዊ ልጅ መቼም ለኢትዮጵያ ክብር ይጨነቃል ተብሎ ባይታሰብም ባለፉት 26 ዓመታት የታዩ ብሄራዊ ውርደቶች ግን ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ አልነበሩም። መለስ የፈጠራት ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ በማንኛውም ሀይልና ጊዜ የሚደፈር፣ ዜጎቿ እንደሸቀጥ የሚሸጡባት፣ የነዋሪዎቿ ደህንነት የማይጠበቅባት ባለቤት አልባ የዘረፋ ቤት ሆና ቀርታለች። ኢትዮጵያዊነት ክብር እንዳልነበር ሁሉ ገንዘብ ካወጡ ታዳጊ ሴት ልጆች ሳይቀር ለአረብ በመንግስት ፊርማ የሚሸጥባት፣ ሀገርና ህዝብን ሊጠብቅ የተሰለፈ ወታደር ለሀብታም ሀገሮች ቅጥር ሆኖ የትም ሞቶ አስክሬኑ የሚጎተትባት፣ እዚህ ግቡ የማይባሉ ቡድኖች በተደጋጋሚ ድንበር እየተሻገሩ የአንድን አውራጃ ህጻናትና ከብት ነድተው የሚሄዱባት፣ ድኅነትና የካድሬ ዛቻ ኑሮ የነሳቸው ዜጎች በስደት የበረሀና የሽፍታ ብሎም የአራዊት ሲሳይ የሆኑባት ሀገር ሆና ያየናት በመለስ ዜናዊ ዘመን ነው።

አምባገነንነት

መለስ ዜናዊ እንደሞተ ዘ ኢኮኖሚስት የተሰኘው ታዋቂ መጽሄት ባወጣው ዘገባ መለስን ሲገልጸው የአፍሪካ አምባገነነናዊ አገዛዝ ተቀባይነት እንዲያገኝ የተጋ በማለት የመለስ የአምባገነንነት ምሳሌነት አፍሪካን የወከለ እንደሆነ አስነብቧል። መለስ ስለሀገር የሚያስቡና እንደሰው በራሳቸው መቆም፣ ማሰብ፣ ማቀድና መጠየቅ የሚችሉ ዜጎችን ሁሉ ከዙሪያው አባርሮ ሁሉን የተቆጣጠረና ሀሳበ ድኩማንን አጠገቡ የኮለኮለ ስጉና ፈሪ አምባገነነን ነበር። ዛሬ የምናያቸው እነሀይለማሪያም ደሳለኝ የዚያ ውጤት ናቸው። ፈሪ ያልኩበት ምክንያትም የአምባገነን ጀግና ስለሌለው ነው። ሰዎችን አምባገነን የሚያደርጋቸው ፈሪነታቸው ነው። ተሟግተው፣ ተፎካክረው፣ ተፋጭተው መውጣትና ማሸነፍ በራሳቸውም መተማመን የማይችሉ ፈሪዎች ስልጣናቸውንና ኃይልን ተጠቅመው ሁሉን ካባረሩ በኋላ ለብቻቸው ተወዳድረው አሸናፊ የሚሆኑበትን ሜዳ ይጠርጋሉ። ስለሆነም ሀሳብ ያስፈራቸዋል። ከእነሱ ውጪ ማንም እንዲሰማም ሆነ እንዲታይ አይሹም። ይህ የአምባገነኖች ባህርይ ነው። ይህን ሁሉ የሚያደርጉበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ፍርሀታቸው ነው። መለስ ዜናዊም በአፍሪካ የፈሪ አምባገነን ምሳሌ ሆኖ ያለፈ ነው። የመለስ የፈሪ አምባገነንነትም ኢትዮጵያን ውድ ልጆቿን ከተዘጋ ብረት ጀርባ አስቀርቶባታል። እነ እስክንድር ነጋ፣ እነአንዷለም አራጌ፣ እነውብሸት ታዬ፣ እነ ተመስገን ደሳለኝ፣ ስንቱን እንዘርዝረው ለእስርና መከራ የተዳረጉት ብእራቸውን ታጥቀው እንደሰው ስለቆሙ እንጂ ነፍጥ አንስተው እንዳልሆነ ሁሉም ያውቀዋል። የአምባገነንነት ፈሪነት ግን ትእግስትና አስተውሎት አያውቅምና የፈሪ ዱላውን አሳረፈባቸው። የመለስን ውርስ እናስቀጥላለን የሚሉትም የእርሱኑ እርኩስ መንፈስ ተሸክመው ሰይጣናዊ ተግባራቱን በስራ እያዋሉ ቀጥለውበታል። እነዶ/ር መረራ ጉዲና፣ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ሌሎቹም የእርኩስ መንፈስ ወራሾቹ ሰለባ ሆነው የእስር ቤትን ፍዳ እያዩ ነው። ዛሬ የፈሪ አምባገነንነት ጣሪያ ደርሶ ለትችት ብዕር ማንሳት ይቅርና ኢትዮጵያ ብሎ መዝፈን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

ከላይ ለመዘርዘር የተሞከረው የመለስ እርኩስ መንፈስ መገለጫዎችን ለማሳየት ያህል እንጂ ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አይደለም። ዛሬ የመለስን እርኩስ መንፈስ የተሸከሙ ነገን ማየት የማይችሉ ድኩማን ከላይ ታች ዋይ ዋይ ይላሉ። የመለስ እርኩስ መንፈስን እነሱ የመለስ ራዕይ ይሉታል። የመለስ እርኩስ መንፈስ በህወሀትና ቀለብተኞቹ ላይ አድሮ ዛሬም ኢትዮጵያን እያንዘፈዘፈ ይገኛል። እግዚአብሄር ኢትዮጵያ ላይ የማይጨክን መሆኑን ምልክት ሲያሳየን ዋናውን የእርኩስ መንፈስ ጌታ አንስቶልናል። ኢትዮጵያ ግን ዛሬም በጥላቻ፣ በዘረኝነት፣ በዘረፋ፣ በውሸት፣ በውርደት፣ በአምገነንነት እርኩስ መንፈሶች ታማ ፈውስ ትለምናለች። የመጀመሪያው የፈውስ እርምጃ ኢትዮጵያን የምንል ሁሉ ተራ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሳናባክን አብረን ሆነን የታመመች ሀገራችንን ለማዳን የጋራ ቃል ኪዳን መግባት፣ ሁለተኛው እርምጃችን ደግሞ በህብረት የምናገኘውን አቅም ተጠቅመን ኢትዮጵያን ለህመም የዳረጓትን የእርኩስ መንፈስ ተሸካሚዎች ከነ እርኩስ መንፈሳቸው ከሀገራችን ላይ መግፈፍ፣ ሶስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ፣ መለያየትን በአብሮነት፣ ዘረኝነትን በዜግነት እኩልነት፣ አምባገነንነትን በህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ተክተን በመለስ እርኩስ መንፈስ የታመመችውን ሀገር እስከወዲያኛው ማዳን። ይህን ያህል ግዙፍ ተግባር እያለብንና የታመመች እናት ወደእኛ አይኖቿን እያንከራተተች በተራ ጉዳይ ስንነታረክ መዋልና ማደር ግን አያምርብንም ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍረንም ነው። በጋራ የመለስን እርኩስ መንፈስ እናክሽፍ። የእርኩስ መንፈሱ ክሽፈት መቋጫው ደግሞ የህወሀት ግብዓተመሬትነው። ህወሀት ነፍስ ዘርቶ እየተንቀሳቀሰ ግን የኢትዮጵያ ህመም ሊድን አይችልም።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!!

ኃይሉ ማሞ

Filed in: Amharic