>

ላሊበላ:- የቀድሞዎቹ ዘመን አይሽሬ የጥበብ ውጤት

ላሊበላን ለማታውቁ እየሩሳሌም በእስልምና እምነት ተከታዮች በተከበበችበት ጊዜ የኢትዮጵያው ንጉስ ላሊበላ ላሊበላን አዲሷ እየሩሳሌምን ከውቅር ድንጋይ ገነባ።
በዛጉዬ ዘመነ መንግስት ከ920 እስከ 1237 ዓ.ም 11 ነገሥታት ነግሰዋል። መቀመጫቸውም ላስታ ነበር። ከ 11ዱ ውስጥ ቅዱስ የሚባል ስም የተሰጣቸው ፅላት ተቀርጾ ከክህነት ጋር ንግስን አጣምረው የያዙ 4ት ሲሆኑ እነሱም፦
1. ቅ/ይምረሀክርስቶስ
2. ቅ/ገ/ማርያም
3. ቅ/ላሊበላ
4. ቅ/ነአኩቶለብ ናቸው።
ስለ ላሊበላ ሲነሳ በአብዛኛው የሚነገረው ስለ ንጉስና ቅ/ላሊበላ ነው። /ላሊበላ የተወለደው በ1101 ዓ.ም ታህሣሥ 29 ከእናቱ ከኬርዮርና ከአባቱ ጃን ስዩም ላስታ ቡግና ወረዳ ሮሃ ከተባለች ቦታ ነው። ቅ/ላሊበላ ሲወለድ በንቦች ተከቦ እንደነበረና እናቱም በክስተቱ በጣም እንደተገረመች ይነገራል። «ከእናቱ ወተት በፊት ማር አቀመሱት ምን አይነት ተአምር ነው» በማለት ስሙን ላልይበላ እንዳለችው ታሪክ ይነግረናል። ላል በአገውኛ ማር/ንብ ማለት ነው። ላልይበላ ማለትም ማር ይበላ ማለት ነው። ከዛን ወዲህ አባቶች መጽሐፍ ሲጽፉ ላሊበላ አሉት።
ቅ/ላሊበላ ከስድስት አመት እድሜው ጀምሮ የተለያዩ የቤተክርስትያን ትምህርቶችን በአገር ውስጥ በኋላም በእየሩሳሌም በነበረው አስራ ሶስት አመት ቆይታው ተምሯል። ላነፃቸው አብያተ ቤተክርስትያን መሰረት የሆኑት የመፅሐፍ ቅዱስ እውቀቱ እና እየሩሳሌም ለአስራ ሶስት አመታት በኖረበት ጊዜ የተማራቸውና የቀሰማቸው የቤተ ክህነት እውቀቶቹ እንደሆነ ይነገራል።
ንጉስ ላሊበላ ከመሬት ውስጥ ፈልፍሎ ከሰራቸው 10 ቤተክርስትያኖች በፊት ማነጽ የጀመረው አሸተ ማርያምን ነበር።
የላሊበላ ቤተክርትያናት በሁለት የተከፈሉ ናቸው።

1ኛ በምድራዊ እየሩሳሌም የተሰየሙት
ቤተ መድኃኔአለም
ቤተ ማርያም
ቤተ መስቀል
ቤተ ደናግል
ቤተ ሚካኤል
ቤተ ጊዮርጊስ
2ኛ በሰማያዊ እየሩሳሌም የተሰየሙት
ቤተ ገብርኤል
ቤተ መርቆሬዎስ
ቤተ አማኑኤል
ቤተ ሊባኖስ
ቤተ ጊዮርጊስ
አለም የሚደነቅበት ሲመለከቱት ስራዊ አስገራሚና ማራኪ የሆነው የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የቅ/ላሊበላ የመጨረሻ ስራው ነው። ይህ ቤተመቅደስ በመስቀል ቅርፅ ከላይ አስከታች የተሰራ ነው። መግብያው በሸለቆ መልክ የተሰራ ሲሆን አስገራሚነቱ የውሃ ፍሳሽ መውረጃው አሰራርና ቴክኒኩ ነው። ይህ የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የተሰራው በኖህ መርከብ አምሳያ መሆኑ ያንን የሚያመላቱ ስራዎች ተሰርተውበታል።

የውጭው ክፍል
በእግዚአብሔር ትእዛዝ ኖህ መርከብ ሰርቶ ከያንዳንዱ ፍጡር ይዞ ከመጥለቅለቅ የቆየበትን ታሪክ የሚያሳይ ህንፃ ነው። የታችኛው የቤተክርስትያኑ ክፍል 9 ዝግ መስኮቶች ያሉት ሲሆን የላይኛው የቤተክርስትያኑ ክፍል ደግሞ ለብርሃን ማስገብያ የሚሆኑ 12 ክፍት መስኮቶች አሉት።
ከቤተክርስትያኑ መግቢያ ፊትለፊት በስተግራ በኩል የሚታየው የቄጤማ ሳር ተክል የኖህ መልክተኛ እርግብ የውሃውን መጉደል ለማብሰር ቀንጥባ ያመጣችውን ሳር የሚያመላክት ነው። በመቀጠል ከቤተክርስትያኑ ጀርባ በስተቀኝ የሚታየው ጉብታ ቦታ የኖህ መርከብ መሬትን የነካችበትን የአራራ ተራራ የሚያመላክት ነው።
ግን አንዳንድ የሀገራችን ሰወች ስለ ላሊበላ ያላቸው ግንዛቤ እና የሚሰጡት ትርጓሜ እጂግ ያሳዝናል አለማወቅ ሀጢያት አይደለም ግን እማያውቁትን ማውራት እጂግ ነውር ነው። ብዙወቻችን ባህር ማዶ ያለውን እና እማናቀውን ነገር ማድነቅ መከተል እንፈልጋለን። የራሳችን የሆነውን ነገር እንድንከተል እና እንድናውቅ እግዚአብሔር ይርዳን!

ምንጭ(chifrgochi.com)
Filed in: Amharic