>
5:43 pm - Thursday February 2, 2023

የመስቀል ስር ዳንሰኞች (በአዲ የንጉስ ክርስቶስ)

ምስጋና ለማሕበር ጮምዓ መቐለ ይድረስና ከአለማችን በርዝማኔ ስምንተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ የሆነ መስቀል በመቐለ ከተማ በጮምዓ ተራራ ተተክሎልናል።ይህ 52 ሜትር የሆነ መስቀል የፊታችን እሁድ መስከረም 14 ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት በብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ይመረቃል። አንድ በአል ሲከበር ስለ በዓሉ የሚያወሱ ዝግጅቶች ሊኖሩ ግድ ነው።ከፊታችን የሚጠብቀን ትልቅ በዓል ደግሞ መስቀል ነው።አከባበሩ ምን እንደሚመስል ደግሞ አዘጋጆቹን በይፋ ለህዝቡ አሳዉቀዉታል።

እኔ ይህን ፅሁፍ እንድፅፍ ያደረገኝ ምክንያትም ከአከባበሩ ዝርዝር ዉስጥ የመጨረሻዉን ነው። ጽሁፉ እንዲህ ይነበባል “ካብ መስከረም 13-17/2010 ዓ.ም ኣብ ዘለዉ መዓልትታት ኣብ ጎቦ ጮምዓ ፍሉጣት ከየንቲ ዝርከብሉ ምርኢት ሙዚቃ ይካየድ።” ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ከ መስከረም 13 እስከ 17 ባሉት ቀናት በጮምዓ ተራራ ታዋቂ ሙዚቀኞች በሚገኙበት የሙዚቃ ድግስ ይደረጋል”ይላል። አስቡት እንግዲያዉስ ይህ ኮንሰርት የሚደረገው ከመስቀሉ ግርጌ ነው፤ይህ እንደ አማኝ በጣም ዉስጤ አሳዝኖታል መሆን የሌለበት ጉዳይ ነው። መስቀል ህብረቱ ከሰማያዊ ምስጋና ከዝማሬ እንጂ ጠላ ቤት ቁጭ ተብሎ ከተስቆነቆነ ዘፈንና ዳንኬራ አይደለም።

መጽሃፍ ቅዱስም እንደሆነ”ፅድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? “ነው የሚለው። ከመስቀል ግርጌ የሚገኙት የጌታ ወዳጆች አመስጋኞች እንጂ ፂማቸው ያስረዘሙ አዝማሪዎች አይደሉም።መዝለል ማጓራት ከፈለጉ የለመዱት ሮማናት አደባባይ ነዉና ከመስቀሉ ተራራ ይውረዱልን። ሰዉስ እንዴት በጌታዉ መስቀል ስር የጭፈራ ጥሙ ሊያረካ ይደፍራል? እንዴት ይሆንለታል?እንዴትስ ይዋጥለታል?መቼም ክርስትያኑ ነው እዛ የሚገኘው፤አይደለም መስቀሉ ስር ተሁኖ ሮማናትም ተወርዶ መጨፈር የክርስትያን ወጉም እምነቱም አይደለም። በተለይ ጮምዓ ወጥቶ የሚዘል ጥጃ ካለ ግን ከአይሁዶች አያንስብኝም። ወዴት ወዴት እየሄድን ነው!? የክርስቶስ መስቀል ወዳጅ የሆነ ሁሉ ይህ መቃወም አለበት።

ነገሮች በየአቅጣጫቸው እየተለዋወጡ ነው ያሉት። ክርስትያናዊ በዓሎች ሲከበሩ የሚመጥናቸው ኣከባበር መኖር አለበት።ቀስ በቀስ ሃይማኖታዊው በዓል ወደ ምናምን በዓል እንዳይቀይሩት ነው የምፈራው።በአል አሸንዳ መጣ ሲባል ሴቶቹን ሰብሰብ አድርጎ ማስጨፈር ነው፤እንዲሁም መስቀል ሲገባ ከተማይቱ ዘፈን ሲያደነቁራት ይሰነብታል…..ምኑ ተሻለ ወገኔ!?ሰዉ ቆይቶ “መንግስተ ሰማያት የሚገባው በነ እንትና ዘፈን ታጅቦ ነው” እንዳይል ነው ስጋቴ።

እናንተ ሰዎች ሳናስበው አይሁድን እየመሰልን እንዳይሆን እንጠንቀቅ
1- አይሁድ በጌታ መስቀል ሥር ቁማር
ተጫውተዋል በእኛ ዘመንም ደግሞ በዳንኪራና ዘፈን የመስቀል በዓል ይከበር እየተባለ ነው፡፡
2-አይሁድ የጌታ መስቀል እንዳይገኝ
ቀብረውታል በእኛ ጊዜ ታሪኩና ኃይሉ በዝማሬ እንዳይታወቅ የሰውን ቀልብ በዘፈን እየተወሰደ ነው፡፡
3-አይሁድ በማያገባቸው ጣልቃ እየገቡ የክርስቶስን ድንቅ ተአምራቶች ሲቃወሙ ነበር፣ በእኛም ዘመን የማይመለከታቸው ፖለቲከኞች የሚመስሉ ሃይማኖት ሽፋን ያደረጉ አካላት መስቀላችን ያውም ደሙ የፈሰሰበት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለማስተውና ለማስረሳት እየሞከሩና ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ ነው፡፡
ዝም በማለታችን ብዙ ነገሮች ጎድለውብናል
ለምሳሌ፡-
1- አብያተ ክርስቲያኖቻችን ልክ እንደ አይሁድ ዋና የገበያ ማእከላት ሁነዋል፡፡ ሃይማኖት
የለሹ ሳይቀር እየዘነጠባቸው ነው፡፡
2- የምንመካባቸው ታላላቅ ገዳማቶቻችን በዓመት ንግስ በዓላቸው ላይ የዳንኪራና የዘፈን
የጭፈራም አደባባዮች ሁነዋል፡፡ ለምሳሌ አብርሀ ወአፅበሀ ገዳም የንግስ በዓሉ ሲከበር በቁርጥ፣ በጥብስና በተለያዩ ቢራዎች ነው..
ስለዚህ አይሁድ ቤተ መቅደስ የገበያ አዳራሽ ሲያደርጉት ጊዜ ያገኛቸው የጌታ ጅራፍ
እንዳያገኘን ብንቃወመው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

መቐሌዎች እባካቹ የመስቀል ስር ዳንሰኞች አታስብሉን። የክርስቶስ መስቀል የሚወድ ካለ ይህን መልእክት ይጋራው።
ዮው 19:25 “በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።” አሁን ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አጠገብ ዳንሰኞች፣ ዘፋኞች አዝማሪዎች ሊቆሙበት ነው!!!

Filed in: Amharic