>
1:14 am - Thursday July 7, 2022

በገለምሶ ተቃውሞ ተነሳ?...ይህ ነገር ድራማ ነው የሚመስለኝ (አፈንዲ ሙተቂ)

ይሄ የማይመስል ነገር ነው። በ2008/2009 ኦሮሚያ በሙሉ በተቃውሞ ስትናወጥ ገለምሶ ለብቻዋ ፀጥ ብላ ታዳምጥ ነበር። የፀጥታዋ ምክንያት ወኔ ማጣት አይደለም። በቃ ከተማዋ ከልክ በላይ እርጅና ተጫጭኖአታል። የቅፅል ስሟም “ግሪክ” ነው (ግሪክ በስልጣኔዋ ከሁሉም ቀድማ አሁን ወደ ኋላ እንደቀረችው ማለት ነው)። ከተማዋን ለዚህ ያበቃት ለዘመናት ሲደርስባት የነበረው ጭቆናና እርሱን ተከትሎ የመጣባት የኢኮኖሚ ድቀት ነው። “ከኦነግ ጋር ኒካህ አስራችኋል” እየተባለ በከተማዋ ህዝብ ላይ የደረሰውን ፍዳ ለመናገር ይከብዳል።

ያቺ “የተቃውሞ እምብርት” ስትባል የነበረችው ገለምሶ ናት በዚህ ዘመን ረጭ ያለችው። እና ዛሬ ምን ሰምታ ብቻዋን ለተቃውሞ ተነሳች? ዘይገርም ነገር!! ደግሞ እኮ “ኦሮሞች የሶማሊዎችን ንብረት አወደሙ” እያሉ ነው የሚጽፉት። 
——-
በመጀመሪያ ደረጃ በአሁኑ ዘመን በገለምሶ የሚኖሩት ሶማሊዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ስማቸውን ጥራ ብባል መጥራት እችላለሁ። በርካታ የሶማሊ ተወላጆች የከተማዋ ኢኮኖሚ ከመዳከሙ የተነሳ ወደ ጅጅጋና ድሬ ዳዋ ገብተዋል። ስለዚህ አሁን ኢንተርኔት ላይ እየተጋነነ ከሚጻፈው ቁጥር ጋር የሚስተካከል ብዙ የሶማሊ ማህበረሰብ በከተማዋ የለም።

በከተማ የቀሩት ሌሎች ሶማሊዎች ከሰላሳ እስከ አርባ ዓመት ከመኖራቸው የተነሳ ከኦሮሞ ተወላጆች እነርሱን ነጥሎ ማየቱ ያስቸግራል። በጋብቻም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተዋህደዋል። ሶማሊ መሆናቸውን የምናውቀው እኛ ወደ አርባ አመት የተጠጋነው የከተማዋ ተወላጆች እንጂ ታዳጊዎቹ አይደሉም። የገለምሶ ህዝብ እነዚህን የሶማሊ ወገኖቻቸን ያጠቃል ቢባል አላምንም። የከተማችን ሰው በብሄርም ሆነ በሀይማኖት ግጭት የሚታማ አይደለም።

ይህ ነገር ድራማ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ደራሲዎቹ የድራማውን ሴራ ሊቀርፁ የሚችሉበት አንድ ዘመኑ ያመጣው ችግርም አለ።

ከአርባ ረከቴ-ገለምሶ-መቻራ የሚወስደው መንገድ ወደ አስፋልት እየተቀየረ ነው። የዚህን አስፋልት ስራ የሚሰራው ኩባኒያ ባለቤት ተቀማጭነቱ በዱባይ የሆነ ቱርካዊ ነው። የዚህ ሰው ባለቤት ኢትዮጵያዊት ሶማሊ ናት። በዚህም የተነሳ ከላይ ለጠቀስኩት መንገድ ግንባታ አንድ መቶ የሚሆኑ የሶማሊ ተወላጆች በኮንትራት ተቀጥረው ወደ በዴሳ፣ ገለምሶ፣ በልበሌቲና መቻራ ከተሞች መጥተዋል።ኩባኒያው በመንገድ ስራው እርሻቸው ለሚነካባቸው ገበሬዎችና የከተማ ነጋዴዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠር ካሳ ይከፍላል። ነገር ግን አብዛኛው ገንዘብ ባለቤቶቹ ዘንድ ሳይደርስ በመሀል ይበላል። የሚበሉት ደግሞ የኩባኒያው ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዳይመስሏችሁ። ገንዘቡን “ዋጥ!ስልቅጥ” የሚያደርጉት የካሳ ክፍያ ኮሚቴ ተባብለው የተሰባሰቡት የቀን ጅቦች ናቸው። እነዚህ ጅቦች የገበሬውን ገንዘብ ከበሉት በኋላ “ኩባኒያው ገንዘብህን አስቀርቶብሀል” ይሉታል። በዚህም የተነሳ ከሶስት ዓመታት በፊት የመንገዱን መሰራት ይደግፍ የነበረው ገበሬ አሁን በጣም እየተማረረ ይገኛል። ዛሬ ደግሞ ጅቦቹ የገበሬውን ምሬት ሁለቱን ህዝቦች የሚያጋድሉበት ድራማ መተወኛ አድርገውታል። ለዚህም ማስረጃው “በልበሌቲ” የምትባለው ከተማ ሰሞኑን በኢንተርኔት ስሟ ተደጋግሞ መነሳቱ ነው።በበልበሌቲ የሚኖር የሶማሊ ተወላጅ አለ እንዴ? እኔ እስከማውቀው ድረስ የሀጂ መሀመድ አብዱላሂ ኦክሰዴ ተወካይ ሆኖ ሲኖር ከነበረው አንድ ቤተሰብ በስተቀር ሌሎች ሶማሊዎች በከተማዋ የሉም። የመንገድ ግንባታው ከተጀመረ ወዲህ ግን ኩባኒያው በከተማዋ አቅራቢያ በሰራው ካምፕ ሀያ ያህል የሶማሊ ተወላጆች መኖር ጀምረዋል። እነዚህን እንደመነሻ ወስደው ነው እነ እንቶኔ “በበልበሌቲ የሚኖሩ ሶማሊዎች ጥቃት ደረሰባቸው” እያሉ ሲያሸብሩ የነበሩት።እነዚህም ቢሆኑ ወገኖቻችን ናቸውና መነካት የለባቸውም። ታዲያ እነርሱም የድራማው አካል እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለባቸው።በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ አስተዳደር ለህዝብ ቆሜአለሁ የሚል ከሆነ እነዚህን ጅቦች ለፍርድ ማቅረብ አለበት።
ደጋግመን እንደጻፍነው የሶማሊ ህዝብ ወንድማችን ነው። እኛ እየተቃወምን ያለነው የሶማሊ ክልል ልዩ ፖሊስ የሚባለውን ተስፋፊ ሃይልና መሪዎቹን ነው። ከዚያ ውጪ በሰላማዊው የሶማሊ ወገናችን ላይ ጥቃት መፈጸም በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ በገለምሶም ሆነ በሌሎች ከተሞች ከሚኖሩት ሶማሊዎች ጋር የነበረንን ግንኙነት ሳናቀዘቅዝ እንደ ድሮው አብሮ መኖራችንን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን

Filed in: Amharic