>

ጉልቻውን ትተን ድስቱን እንቀይር! (ዘውድአለም ታደሰ)

እኔ የሙስናም ሆነ ማንኛውም ኢ ፍትሃዊ የሆነ ተግባር ምንጩ ማህበረሰቡ ነው ባይ ነኝ። ዛሬ ዙፋን ላይ ያሉት ባለስልጣኖች ሌባ ሆነው ከሆነ ሌባ አድርጎ ያሳደጋቸው ማህበረሰብ አለ ማለት ነው። ስልጣን ላይ የወጣ ሁሉ (ብዙሃኑ) ሚሰርቅ ከሆነ ህዝቡ በሞራል የበለፀገና ጠንካራ ስብእና ያለው ሰው ማፍራት አልቻለም ማለት ነው።

ስለዚህ ህዝቡ ይታከም። መሪውን የሚፈጥረው ህዝብ ነው። አንድ ሰው በምርጫም መጣ በጠብመንጃ ያው ዞሮ ዞሮ ያሳደገው ቤተሰብና ማህበረሰብ ውጤት ነው። ፖለቲከኞቻችን ለውጥ ማምጣት ያልቻሉት ለዚህ ነው። ሃያ ስድስት አመት አንድን ስርአት ለመለወጥ ከሚፍጨረጨሩ ማህበረሰባዊ ንቃተ ህሊናን ለመፍጠርና የሐገር ፍቅር ስሜትን ለማጎልበት ህዝቡ ላይ ቢሰሩ ኖሮ ዛሬ ያለንበት የአስተሳሰብ ጥሻ ውስጥ ስንንደፋደፍ አንገኝም ነበር። እቺን ሐገር የገደላት የነቃ አእምሮ እጦት ነው። ቤተሰብ ስላልነቃ ሃላፊነት የማይሰማው ልጅ ያሳድጋል። አስተምሮ ለሀገር የሚጠቅም ሳይሆን ራሱን ብቻ የሚጠቅም ዜጋ እንዲሆን ይመክራል።

ሌብነትን የሚፀየፍ ሶሳይቲ ቢኖረን ሌብነትን የሚፀየፉ ባለስልጣናት በኖሩን ነበር። እውቀት የሌለው የሞራልና የስነምግባር ግድግዳውን በባህሉ ሲያንፅ ያልኖረ ማህበረሰብ ለራሱም ሆነ ለሐገሩ ሃላፊነት አይሰማውም። ከራሱ ደስታ ዝቅ ብሎ የሌላውን ጩኸት የሚሰማበት ፍትሃዊ ጆሮ የለውም። ምክኒያቱም አልነቃማ! የሰውነት ክብር አልገባውማ!

“ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” ይላል ሃበሻ። እውነቱን ነው። ደርግ የፊውዳሉን ስርአት ገርስሶ ወታደራዊ መንግስት አቋቋመ። ባለፈው ስርአት የነበሩትን ሁሉ አጠፋ። የርእዮተ አለምና የባለስልጣን ለውጥ በሃገሪቱ ታየ። ሁሉም ነገር እንደአዲስ ፈርሶ ተሰራ …. ነገር ግን ህዝቡ ከድህነት አመለጠ? ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት መጣ? በፍፁም! ለምን ለውጥ አልመጣም? ብለን መጠየቅ የለብንም ታዲያ?

ኢህአዴግ 17 አመት ታግሎ ደርግን ጣለ። አዲስ ርእዮተ አለም ፣ አዲስ ባለስልጣን ፣ አዲስ ስርአት በኢትዮጵያ ላይ ሰፈነ። ነገር ግን የህዝቡ ኑሮ ያው ነው። እንደውም ሙስናውና የኑሮ ውድነቱ ተባባሰ ፣ ጭቆናው በረታ ፣ መከራ መልኩን ቀይሮ በኢህአዴግ ዩኒፎርም መጣ። በቃ!

በግማሽ ክፍለ ዘመን ሁለት ግዜ ስርነቀል አብዮታዊ ለውጥ አድርገን ለምንድነው መለወጥ ያልቻልነው? ለምንድነው ኑሯችን ያልተሻሻለው? እንደኔ ምክኒያቱ አንድ ነው ፦ ስር ነቀል ማህበረሰባዊ ለውጥ መፍጠር ስላቃተን! ጉልቻውን እንጂ ድስቱን መቀየር ስላቃተን! የእውቀት አብዮት ማቀጣጠል ስለተሳነን! ይኸው ነው። ማህበረሰቡ ራሱ ባሳደጋቸው ልጆች ነው ራሱን ሚበድለው። ራሱ በሰራው ጠብመንጃ እንደሚሞት ቁጠሩት።

ስለዚህ ለሐገሩና ለወገኑ ከልቡ የሚቆረቆርና ዛሬ ላይ ሆኖ ነገውን መለወጥ የሚፈልግ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ፣ መሪ ፣ ምሁር ፣ የነፃነት ታጋይ ፣ ወይም ጋዜጠኛ ካለ …. ህዝቡን እንደገና በእውቀት ያንቃ። የሐገር ፍቅርንና አንድነትን ይስበክ! ባለጌውን ሳይሆን ባለጌ አድርጎ የሚያሳድገውን የተጣመመ ባህልና ስርአት ይታገል። ያኔ ብዙ ማህተመ ጋንዲዎች ፣ ብዙ ማርቲን ሉተር ኪንጎች ፣ ብዙ ማላላዎች ፣ ብዙ እስክንድሮች ፣ ይነሳሉ!

Filed in: Amharic