>

የአፋቤት ጦርነት (ጸሓፊ፡አፈንዲ ሙተቂ)

መጋቢት 17/1988 (መጋቢት 9/ 1980)-እኩለ ሌሊት፡፡ በዚያች ደረቅ ሌሊት ሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ሳይጠበቅ የናደውን እዝ ወረረ፡፡ የህዝባዊት ኢትዮጵያ አብዮታዊ ሰራዊትም ይዞታውን ለማስጠበቅ ተከላከለ፡፡ ይሁንና በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ ሻዕቢያ ቀደም ብሎ ያገኘውን መረጃ በሚገባ ሊጠቀምበት ስለቻለ የአብዮታዊ ሰራዊትን ማዘዣና የግንኙት መስመሮችን በጣጠሰ፡፡ ተዋጊ ብርጌዶችን ከእዙ መሀል አስገብቶ በሰራዊቱ ላይ ወደ ውጪ ተኮሰ፡፡ ከውጪ በኩል ደግሞ ዙሪያውን ከቦ በመትረየስና በከባድ መሳሪያ አዋገደው፡፡ በዚህም የተነሳ ከእዙ ጠቅላይ መምሪያ ራቅ ብለው የሰፈሩ ክፍለ ጦሮች ወደ መሐል ተመልሰው እገዛ ማድረግ አቃታቸው፡፡ ሁሉም ክፍለ ጦር በያለበት በራሱ ውጊያ ተጠመደ፡፡ አብዮታዊ ሰራዊት በዚያ ትንፋሽ በሚያሳጥር ውጊያ ለሶስት ቀናት ከተዋከበ በኋላ ሁሉም ነገር ተበላሸበት፡፡ መጋቢት 20/1988 መንፈቀ ሌሊት ላይ የናደው እዝ ሙሉ በሙሉ ተናደ፡፡ የእዙ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ግርማ ጌታነህ ከሶስት የሶቪየት ህብረት የጦር አማካሪዎች ጋር ተማረኩ፡፡ ዋናው አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬና ዘጠኝ የሶቪየት የጦር አማካሪዎች ከውጊያው አምልጠው ሲሸሹ የወገን ሄሊኮፕተር ደርሶ አነሳቸው፡፡ ሌሎች ክፍለ ጦሮች ከዋናው ማዘዣ የሬድዮ ግንኙነት እንደተቋረጠባቸው ሲረዱ የውጊያ ቀጣናቸውን እየለቀቁ ወደ ከረን አፈገፈጉ፡፡ ሻዕቢያም የአፋቤትን ከተማ በእጁ አስገባ፡፡ የናደው እዝንም ከሙሉ ግምጃ ቤቱ ጋር ተቆጣጠረ፡፡
*****
ይህ የናደው ሽንፈት ብዙ ተብሎለታል፡፡ ብዙም ተጽፎበታል፡፡ በታወቁ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ግንባር ቀደም ወሬ ሆኖ ተዘግቧል፡፡ በርካታ የአውሮጳና የአሜሪካ ጋዜጠኞች ጦርነቱ የተካሄደባትን የአፋቤት ከተማ በመጎብኘት ዶክመንታሪ ፊልሞችን ሰርተውበታል፡፡ የታወቁ የጦር ኤክስፐርቶች ሻዕቢያ በአፋቤት ያገኘውን ድል የቪየት-ኮንግ ሽምቅ ተዋጊዎች በፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎች ላይ ከተጎናጸፉት የ“ዲየን ቢየን ፉ” ድል ጋር አወዳድረውታል፡፡ በአጠቃላይ የናደው ሽንፈት ስለሻዕቢያ የሚያውቁትንም ሆነ የማያውቁትን የውጪ ዜጎች “አደገኛ የጎሪላ ተዋጊ ሀይል ነው” እያሉ በአድናቆት እንዲመለከቱት የጋበዘ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

በሌላ በኩል የናደው ሽንፈት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ አስከትሏል፡፡ በናደው ሽንፈት ማግስት የኢህዲሪ መንግሥት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በስራ ላይ አውሏል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም መጋቢት 31/1988 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በኤርትራ ስለሚካሄደው ጦርነት ተናገሩ፡፡ ሰፊው ህዝብ ኤርትራን ከመገንጠል እንዲያድናት ጥሪ አቀረቡ፡፡ መንግሥት በሚመድበው በጀት ብቻ ጦርነቱን ማካሄድ ስላልተቻለ ህዝቡም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት በማለት ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ የ“አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች” በፊት ገጾቻቸው ጥግ ላይ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል መፈክር በቋሚነት ማስነበብ ጀመሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮም በምሽት ስርጭቱ ከሚያስተላልፈው ዜና ቀጥሎ “አንድነት ሀይል ነው”፣ “ሁሉም ለእናት ሀገሩ ዘብ ይቁም”፣ “የአባቶቻችንን አደራ አናስደፍርም” እና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚሉ አራት መፈክሮችን በመደበኛነት ማሰማት ጀመረ፡፡ ኤርትራ በአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ስር ወደቀች፡፡ በኤርትራ መሬት የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠብቅ ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ ክፍለ ሀገሩን ከሱዳንና ከቀይ ባህር ጋር የሚያገናኙ መሬቶች ለሲቪል እንቅስቃሴ ተከለከሉ፡፡
*****
በናደው እዝ ላይ የደረሰው ሽንፈት በአብዮታዊ ሰራዊት ውስጥ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩ እርግጥ ነው፡፡ በዘመኑ የነበሩ የታወቁ ወታደራዊ አዛዦችም “የፍጻሜው መጀመሪያ” በማለት ገልጸውታል፡፡ በጦርነቱ የተሰለፈው አብዮታዊ ሰራዊት ሃምሳ ሺህ ተዋጊዎችን ይዞ ከአስር ሺህ ያልበለጠ ሀይል በነበረው የሻዕቢያ ሰራዊት መሸነፉ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሻዕቢያ የጦርነቱን ውሎ አለም አቀፍ ዝና ለማግኘትና የአብዮታዊ ሰራዊት ሞራልን ለመስበር በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡ የሬድዮና የህትመት አውታሮቹ የሻዕቢያን ሀያልነት የሚያሳይ ፕሮፓጋንዳ እየደጋገሙ ሰርተውበታል፡፡ ለመሆኑ አስራ አምስት ሺህ ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮች ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ የሆኑበት የአፋቤት ሽንፈት እንዴት ተከሰተ?

በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከነዚህ ሁሉ ሚዛናዊ መስለው የታዩኝ አቶ ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) “ነበር” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሐፋቸው ያሰፈሯቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ በገስጥ ተጫኔ አመለካከት የአፋቤት ሽንፈት ምክንያቶች

1. የእዙ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደላቸውና በርሳቸው ምትክ የተመደቡት ጄኔራል ውበቱ ጸጋዬ የየክፍለጦሮቹን የውጊያ ቀጣና በደንብ ሳያጠኑና ተለዋጭ የውጊያ ስልት ሳይነድፉ ሻዕቢያ ፈጥኖ በማጥቃቱ
2. ሻዕቢያ በታሕሳስ ወር መጀመሪያ (በሐበሻ አቆጣጠር ህዳር ወር 1980 መጨረሻ ላይ) ባደረሰው ጥቃት ከማረካቸው መኮንኖችና የሬድዮ ሰራተኞች ስለናደው እዝ የጠራ መረጃ በማግኘቱ ወደ ውስጥ ዘልቆ በማጥቃት የማዘዣ ጣቢያውን መበተኑ
3. ውጊያው ጠላትና ወገን የተደባላለቀበት ስለነበር ለድጋፍ ሰጪ ከባድ መሳሪያዎች (ታንክ እና መድፍ) እና ለአውሮፕላኖች ድብደባ አለማመቸቱ
4. የእዙ ጠቅላይ መምሪያ ሻዕቢያ በታህሳስ ወር ያደረገውን ማጥቃት ተከትሎ ወደ አፋቤት እንደሚያመራ በመገመት ለጠንካራ መከላከል ዝግጅት አለማድረጉ
5. ሻዕቢያና ህወሐት የማዘዣ ጣቢያዎችን ቀድሞ መምታታቸው የተለመደ ስልት ሆኖ ሳለ የእዙ ዋና አዛዥ ምናልባት ማዘዣዬ ቢመታብኝ በማለት በሚስጢር የተሰናዳ ተለዋጭ የማዘዣ ጣቢያ አለማዘጋጀታቸው፤ ብሎም ሻዕቢያ ማዘዣቸውን እንዲለቁ ሲያስገድዳቸው “እዚህ ነኝ” ሳይሉ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ወደ ከረን መሸሻቸው የመሳሰሉት ናቸው፡፡

የአፋቤት ውድቀት ከደረሰ በኋላ የሻዕቢያ አስመራ መግባት የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ ሁለቱም ወገኖች ተረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ተነጣጥለው ሁለት ሀገር እንደሚሆኑ መተንበይ የተጀመረውም ከዚያ በኋላ ነበር፡፡

የደርግ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በአፋቤት የደረሰው ውድቀት የወገን ጦር በመዘናጋቱና የሻዕቢያን አቅም አሳንሶ በማየቱ የተከሰተ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሽንፈቱ ማግስት የሻዕቢያ ሲሳይ የሆነው ግዙፍ የጦር መሳሪያና የቁሳቁስ ክምችት ለአፋቤት ወታደራዊ ጠቀሜታ በተሰጠው የተጋነነ ግምት ሳቢያ የተከሰተ እንደሆነ ያወሳሉ (ሻዕቢያ 50 ታንክና 60 ከባድ መድፎች ለመማረክ ችሎ ነበር)፡፡ ከተማዋና ዙሪያዋ በተራሮች የተከበቡ ሆነው ሳሉ አካባቢው ከሚችለው በላይ አምስት ክፍለ ጦር የሚሆን ሰራዊት ተፋፍጎ እንዲቀመጥበት ስለተደረገ ለሻዕቢያ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መጋለጡንም ጨምረው ይናገራሉ፡፡ የጄኔራል ታሪኩ አይኔ መገደልም የወታደሮቹን ሞራል እንደሰበረ ያክላሉ፡፡

ሻዕቢያዎች ግን ይህንን አይቀበሉም፡፡ የአፋቤት ድል በነርሱ ጀግንነትና የጦር መላ አዋቂነት የተገኘ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ጄኔራል ታሪኩ ባይረሸን እንኳ አፋቤትን ከመያዝ የሚገድባቸው ሀይል እንዳልነበረ ይከራከራሉ፡፡ ወጣም ወረደ ግን ሁሉም በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ የአፋቤት ሽንፈት የጦርነቱን አቅጣጫ ከመሰረቱ የቀየረ መሆኑን ያለ ምንም ማመንታት ይቀበሉታል፡፡ ከዚያ በኋላ የነበረው የአብዮታዊ ሰራዊት ጉዞ በኋላ ማርሽ የመጓዝ ዓይነት ነበር ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተለየ አስተያየት የሰጡት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ብቻ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የአፋቤትን ሸንፈት ያጋነኑት የዓለም ሚዲያዎች ናቸው እንጂ በወቅቱ የሰራዊቱ አቅም አልተነካም (ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ለብሄራዊ ሸንጎ ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው በናደው እዝ ላይ የደረሰውን ውድቀት ትተው ስለአፋቤት ከተማ ከንቱነት ነበር የተናገሩት፤ “በኢትዮጵያ ስታንዳርድ ቀበሌ አይደለም፤ አልማዝ አይቆፈርበት፣ ቤንዚን አይወጣበት፣ ሀገር አይደለ፣ nothing” እያሉ ተሳልቀውባታል)፡፡ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ አባባል በኤርትራ ምድር እጅግ ወሳኝ የሆነ ውድቀት የሚባለው በምጽዋ የደረሰው ነው እንጂ በአፋቤት የታየው አይደለም፡፡
—–
ምንጮች
1. David Lamb, “Evil Days: Thirty Years of War and Famine in Ethiopia (1961-1991), Africa Watch Group, New York, 1991
2. Paul B. Henze, “Eritrea’s War”, Shama Books, Addis Ababa, 2002
3. ገነት አየለ፣ “የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች”፣ አዲስ አበባ፣ 1994
4. ገነት አየለ፣ “የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች-ቁጥር ሁለት”፣ አዲስ አበባ፣ 2003
5. ጌታቸው ሀይሉ፡ “ቀያይ ተራሮች”፣ አዲስ አበባ፣ 1993
6. ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ፣ “አይ ምጽዋ”፣ አዲስ አበባ፤ 1997
7. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ አዲስ አበባ፣ 1996
8. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር-2”፣ አዲስ አበባ፣ 2001
9. ጌታቸው የሮም፣ “ፍረጂ ኢትዮጵያ”፣ አዲስ አበባ፣ 1993

Filed in: Amharic