አንድ ሰው ድንገት አውሬ ይመጣበታል፡፡ የአውሬው ጩኸትና ድንፋታ እግሬ አውጭኝ ብሎ እንዲሸሽ ያደርገዋል፡፡ ከአውሬው ሸሸሁ ብሎ ሲሮጥ ጥልቅ ወደሆነ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ወደ ጉድጓዱ ጥልቅ እየተወረወረ እያለ በጉድጓዱ ግድግዳ ላይ የበቀለ ሁለት ቅርንጫፎች ያሉት ዛፍ ያገኝና ያንን በሁለት እጆቹ ይዞ ፋታ ያገኛል፡፡

እግሩም በዛፉ ሥሮች ላይ ያርፋል፡፡ ይህን ዕድል ሲያገኝ እስከ ጊዜው ድረስ ነፍሱ መትረፏን፡፡ ጥቂት በዚህ ሁኔታ ከቆየ ደግሞ ቀስ በቀስ ከዚህ ጉድጓድ ሊወጣ እንደሚችል ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ከሞት መትረፉንም  ርግጠኛ ሆነ፡፡የዛፉን ቅርንጫፎች እንደያዘ፣ እግሩንም በግንዱ ላይ እንዳስደገፈ አንገቱን ዝቅ አድርጎ ሊወድቅበት የነበረው ጉድጓድ ተመለከተው፡፡ በጉድጓዱ ሥር ዓይኑ አንደ እሳት የሚያበራ፣ ሰውነቱ አንደ ሰርዶ የተጠቀለለ፣ ራሱ እንደ ዱባ የሚንከባለል፣ አፉ እንደ ገደል የተከፈተ ዘንዶ ተመለከተ፡፡ በዚያ አጋጣሚ ነፍሱ ጥላው ልትሄድ ስትል ለጥቂት ነው የመለሳት፡፡
ከአንደኛው አውሬ አፍ አመለጥኩ ሲል ወደሌላው አውሬ አፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ሲያስበው ልቡ እንደ እማሪት ያለ ማቋረጥ ይመታ ጀመር፡፡ዓይኑን ከዘንዶው ነቅሎ ወደ ላይ ሲመልሰው እርሱ የተንጠለጠለበትን ቅርንጫፍ አንድ ነጭና አንድ ጥቁር አንበጣዎች ባለማቋረጥ እየበጠሱ ሲጥሉት ተመለከተ፡፡ ሁለቱም እጆቹ ስለያዙ ምን ያድርጋቸው፡፡
አንበጣዎቹ ለየትና ከበድ ያሉ ናቸው፡፡ ይበላሉ፣ ይበላሉ፣ ይበላሉ፣ አያቋርጡም፡፡

እርሱ ተማምኖ አጥብቆ የያዘውን ቅርንጫፍ እነርሱ በበሉት ቁጥር ግንዱ እየመነመነ  ይሄዳል፡፡ ይህንን ሲያስብም የተንጠለጠለበት ሰው ተስፋም እየመነመነ ሄደ፡፡ ያ ቅርንጫፍ ተቆርጦ አጆቹ የሚይዙት አጥተው ቢወድቅ የዚያ እሳታማ ዘንዶ ራት እንደሚሆን ሲያስበው ዘገነነው፡፡

የእጆቹ ነገር እንዲህ መሆኑን ሲያይ ያለ የሌለ ጉልበቱን ሰብስቦ እግሩ ያረፈበትን ግንድ
ተመለከተው፡፡ አራት እባቦች ከዛፉ ግንድ ስንጥቅ ውስጥ እየወጡ ነበር፡፡ የነዚያ እባቦች ቤት ያ የዛፉ ስንጥቅ ነው፡፡ እነዚያ አራት እባቦች ከዚያ ስንጥቅ ውስጥ ከወጡ እግሩ ወዳረፈበት ቦታ መምጣታቸው ነው፡፡ እንኳንስ አራቱንና አንዱንስ በምኑ ይከላከለዋል፡፡

አራቱ ከአራቱም አቅጣጫ ከመጡበት ደግሞ እግሩን የሚያሳርፍበት ቦታ ፈጽሞ አይኖረውም፡፡ ከላይ አንበጦቹ አጁ ያረፈበትን ይገዘግዛሉ፣ ከታች እባቦቹ ራሳቸው እንደ ባትሪ እየወዘወዙ ከስንጥቁ ይወጣሉ፡፡ ከጉደጓዱ ሥር ደግሞ እሳታማው ዘንዶ አፉን ከፍቶ ይጠባበቃል፡፡

ሰውዬው ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ደርሶ የአንበጦቹን ፍጻሜ ለማየት ቀና ሲል አንዳች
ጣፋጭ ነገር አፉ ውስጥ ጠብ አለ፡፡ በዛፉ ቅርንጫፍ ጫፍ ላይ ንቦች ከበው ማር እየሠሩ ነው፡፡ ያ የንች ማር ጠብ፣ ጠብ ይላል፡፡ ከነዚያ ተብታዎች አንዷ ናት ምላሱ ላይ የነጠበችው፡፡

እፎይ አለ ሰውዬው፡፡ የማሩን ወለላ አጣጥሞ፡፡ የማሩን ወለላ ሲያጣጥም ጅቡ ከጉድቃዱ አፍ ቆሞ አንደሚጠብቀው፤ ቅርንጫፉን አንበጦቹ እንደሚገዘግዙት፤ አራቱ እባቦች እግሩ ከረገጠበት ግንድ ስንጥቃት ውስጥ እንደሚወጡ፣ ከጉድጓዱ ሥርም አፉን የከፈተ ዘንዶ እንደተኛ፤ ልጡ የተራሰ፣ ጉድጓዱ የተማሰ መሆኑን ዘነጋው፡፡ ልቡ በማሩ ጣዕም ከጉደጓዱ ወጣች፡፡

በዙሪያው ያለውን እውነታ ዘነጋና በጠብታዋ ማር ጊዜያዊ ርካታና ደስታ ተዋጠ፡፡ በዙሪያው ያለው ሊውጠው የደረሰውን ችግር ትቶ ድንገት ባገኛት ደስታ ሰመጠ፡፡ አንደኛዋን ጠብታ አጣጥም ሌላኛዋን ለመቀበል አፉን እየከፈተ፣ ከገዛ ድርጊቱ ጋር ፍቅር ይዞት ጅቡንም፣ አንበጣውንም፣ እባቦቹንም፣ዘንዶውንም ረሳቸው፡፡ እየመጣበት ካለው ጥፋት ይልቅ እየተንጠባጠበለት ወደለው ማር ዞረ፡፡በርለዓም እንዲህ ይተረጉማል፡፡

ጅብ የተባለ ሞትና ጥፋት ነው፡፡ ሰው መጥፊያው ሲያባርረው፣ ሞትም ሲከተለው የሚያመልጥ መስሎት ይሸሻል፡፡ ሲሸሽ ባላሰበው የችግር ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፡፡ መጋፈጥ እንጂ መሸሽ ማሸነፍን አያመጣም፡፡ ጉድጓዱ ሁሉም ዓይነት ችግር የተጠራቀመበት ነው፡፡ አንዱን ችግር በብልጠት አልፋለሁ ብለህ ከሸሸህ የባሰው ችግር ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ አንዱን መፍታት ካቃተህ ችግሮች በማኅበር ይመጡብሃል፡፡

አንዱን ቸላ ካልከው ከመከራ መንጋ ጋር ትጋፈጣለህ፡፡ ሰውዬው የተንጠለጠለበት ባለሁለት ቅርንጫፍ ዛፍ የተሰጠን የእድሜ ዘመናችን ነው፡፡ ዘመን ስትሠራበት አንጂ ስትንጠለጠልበት መከራ ይጎትታል፡፡ ሁለቱን ቅርንጫፎች ነጭና. ጥቁር አንበጦች ባለማቋረጥ ይገዘግዟቸው ነበር፡፡ እነዚህም ቀንና ሌሊት ናቸው፡፡አንተ የተንጠለጠልክበት ጊዜ የሚባለውን ዛፍ ቀንና
ሌሊት የተባሉ አንበጦች በየቀኑ እየገዘገዙ ያመናምኑታል፡፡ የያዝከው ይመስሃል እንጂ የያዝከው እስከጊዜው ብቻ ነው፡፡

አራቱ ከዛፉ ስንጥቃት ውስጥ በየተራ የሚወጡት እባቦች አራቱ የሰዎች ጠባዮች ናቸው፡፡ ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና አፈር፡፡ እነዚህ በየተራ ከጊዜ ውስጥ እየወጡ ልጅነትህን፣ ወጣትነትህን፣ ጉልምስናህንና እርጅናህን እየበሉ ይጨርሱታል፡፡

አራቱም በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አራቱም የእድሜ ምዕራፎች በዘመንህ ውስጥ አሉ፡፡ እሳቱ ከውኃው ጋር፣ ነፋሱም ከአፈሩ ጋር ተሰጥቶሃል፡፡ በየዘመናቱ ካልሠራህባቸው ግን ከጉደጓዳቸው እየወጡ መምጣታቸው እንደሆነ አይቀርም፡፡

በጉደጓዱ መጨረሻ የነበረው ዘንዶ ሞት ወይም ጥፋት ነው፡፡ በስተመጨረሻ የሚጠብቀው ይህ ነው፡፡ የምንዘነጋውም ይህን ነው፡፡ ከታች ያንን የመሰለ ዘንዶ እየጠበቀው ሰውየው ድንገት ባገኛት የማር ጠብታ ነገር ዓለሙን ሁሉ ዘነጋው፡፡ችግሮችህ ከበውህ፣ ዙሪያህንም እየገዘገዙህ፣ ወደ መጨረሻው ጥፋትም እየወሰዱህ፣ ጉድጓድ ውስጥ መውደቅህን አያወቅህ፤ ከእውነታው ጋር ስትጋፈጥ ድንገት እንደ ማር ጠብታዋ ያለች ጊዜያዊ ድል፣ ርካታና ፋታ ታገኛለህ፡፡ ያን ጊዜ ጅቡንም፣ አንበጣውንም፣ እባቡንም ዘንዶውን ትረሳዋለህ፡፡

ከእውነታው ጋር ከመጋፋጥ ይልቅ እውነታውን መርሳትን ትመርጣለህ፡፡ ጅቡም፣  አንበጣውም፣ እባቦቹም፣ ዘንዶው ባሉበት አሉ፡፡ ጅቡ እየጮኸ ነው፤ አንበጦቹም እየገዘገዙ ነው፣ እባቦቹ ከስንጥቃቱ እየወጡ ነው፤ ዘንዶው አፉን ከፍቶ ሊያጣጥምህ እየቋመጠ ነው፡፡ ሁሉም ነገር አልተቀየረም፡፡ የተቀየረው የአንተ ልቡና ብቻ ነው፡፡ እውነታውን ረሳኸው፡፡ የማሩን ጠብታ ስትልስ ከጉድጓድ የወጣህ መሰለህ፡፡ ሁሉም ነገር የተቀየረ፣ ሰላም የሆነና
የተረጋጋ መሰለህ፤ ጉድጓዱን ሜዳ፣ ዘንዶው በግ፣ አንበጣውን ቢራቢሮ፣ እባቦቹን ርግቦች፣ ጅቡንም ፈረስ አድርገህ ቆጠርከው፡፡

እውነታውን መርሳት እውነታውን አይቀይረውም፡፡ አንተ የማሩን ጠብታ ስላጣጣምክ ጅቡም፣ አንበጦቹም፣ እባቦቹም ዘንዶው ሥራቸውን አያቆሙም፡፡ ምናልባት እየተራቡና እየተማረሩ ከመሞት የማር ወለላ እያጣጣሙ መሞት ይሻላል ካላልክ በስተቀር፡፡