>
4:39 pm - Sunday December 5, 2021

አዲሱን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እናንተው አምጣችሁ ውለዱ (ያሬድ ጥበቡ)

የእሬቻ በአል በሰላም ተፈፅሞ ታዳሚዎች ወደየቀዬአቸው በሰላም መመለሳቸውን የዜና ማእከላት ዘግበዋል ። ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፊታውራሪነት ራሱን የሾመውና የኦሮሞ ወጣትም ቢያንስ በዳያስፖራ እንደተቀበለው የማያከራክረው ጎልማሳው ጃዋር መሃመድ የኦሮሞ ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መጠየቁን ሰማሁ ። ማን ነበረች “ያልፈሳንበት ዳገት የለም” ያለችው? ለጉዳዩ አዲስ አይደለሁም ለማለት ነው ። “በየጎዳናው የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው!” በተፈከረበት ሃገር ላይ ለምን ይህ የመገንጠል ጥያቄ አስፈለገ?

ጃዋር ያነሳው የራስን እድል በራስ የመወሰን እንጂ የመገንጠል ጥያቄ አይደለም የሚል ክርክር ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ ። ለኔ ያው እሳት ካየው ምን ለየው ነው ። ጃዋር ከወጣትነት ወደ ጎልማሳነት የመመንደጉን ያህል እኔም ከጎልማሳነት ወደሸምግልናው አጎንብሻለሁና በጉዳዩ ላይ አንድ ሁለት ብልበት ተገቢ ሆኖ ተሰምቶኛል ። የራስን እድል በራስ መወሰን ከኤርትራ የተለየ ውጤት ያመጣል ብለን የምንዘናጋ ካለን የዋህነት ነው ። ኤርትራ ዳር ሃገር በመሆኑ 76ሺህ ወጣቶቻችንን ገብረን እናቶቻችን ማቅ ከለበሱ እነሆ የባድመ ጦርነት እንኳ 18 ዓመታት ሞላው ። ዛሬ ድረስ ቱቢታቸውን ያላወለቁ እናቶች እንዳሉ እሰማለሁ ። የጦርነቱ ምሬት አፋችን ላይ ዛሬም አለ ለማለት ብቻ ሳይሆን፣ ፈቅደን የሰጠነው የራስን እድል የመወሰን መብት እንኳ ምን ያህል እንደጎዳን ለማስመር ነው ያን ማለቴ ። ለዚህም የዳረገን የወያኔ/ኢህአዴግ ቋንቋን ማእከል ያደረገ የብሄረሰቦች መብት ርእዮተዓለም ነው ።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ቋንቋ ብቸኛው የማንነት መገለጫ ሆኗል ። የአማራ ክልል ወጣቶች ሳይቀሩ አማራ ነን ማለት ጀምረዋል ። እውን ቋንቋ እዚያ ሰገነት ላይ ፊጢጥ ሊል ይገባዋልን? ለመሆኑ ቋንቋ ምንድን ነው? በተፈጥሮ የተሰጠን፣ በዲኤንያችን የታተመ ጉዳይ ነው፣ ወይስ ለመግባቢያና ፣ አብሮነት አምጠን የወለድነው ማህበራዊ ቁስ? እኔ የኋለኛው ይመስለኛል ። እንስሳትም መግባበያ ቋንቋ አላቸው ። የሰው ልጅን ቋንቋ ከቀሩት እንስሳት የተለየ የሚያደርገው ፅንሰ ሃሳባትን ልንቀምርበትና አስተሳባችንን ተጠቅመን ህይወታችንን ልናሻሽልበት፣ ዓለሙን ልናስገብርበት፣ እንስሳትን ልንገራበት፣ እፅዋትን ልናዘምርበት፣ በዚህም ድላችን ልንዘምርበት በመቻላችን ነው ። የተለየ መለኮታዊ ተልእኮ ያለው አይመስለኝም ። ግዕዝ የፈጣሪ የመጀመሪያ ቃል ነበር የሚሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በተነሱበት ሃገር ላይ ይህ አነጋገሬ “ውግዝ ከም አርዮስ” ቢያደርገኝ ይገባኛል፣ ባልቀበለውም ።

ከላይ በቋንቋ ላይ የጀመርኩትን ሃተታ ልቀጥልና፣ የሰው ልጅ ቋንቋ ከአራዊቱ መግባቢያ የሚለየው፣ በፅንሰሃሳብ የተለወሰና፣ ሰውን የአስተሳሰብ ልእልና ስለሰጠው ከሆነ፣ የማይቀርልን ጥያቄ፣ ዛሬ ዓለሙ በድረገፅ በተሳሰረበትና፣ እያንዳንዱ የኢትዮጵያችን መንደር በቃና ፊልምና በሴልፎን ቴክኖሎጂ በተወረረበት ዘመን፣ ስለራሳችን ቋንቋና ስለጠራ ብሄር መናገር የምንችል ይመስላችኋል?

ለመሆኑ የፅንሰሃሳቦቻችንና የአስተሳሰባችን መሰረቶች ምንድን ናቸው? በዘመናዊነት ስም የቃረምነውን የአውሮፓ አስተሳሰብና ቋንቋ አይደለምን የራሳችን አድርገን የምንኩራራበት? ለመሆኑ የጠራና ከልብ የምንኮራበት የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የኢትዮጵያ አስተሳሰብና ፅንሰሃሳብ አለን? ከአውሮፓ የቃረምነውን እምነትና አሳተሳሰብ በአማርኛ ተናገርነው ወይም በአፋን ኦሮሞ፣ ዞሮ ዞሮ ያው የፈረንጁ ግልባጭ እስከሆነ ድረስ ምን ለውጥ አለው? ጥራቱ ምኑ ላይ ነው? ብሄራዊ ልእልናው የቱ ጋ ነው? በእውን አስበንበታል?

በተለይ በየብሄረሰቡ የማንነትን ጉዳይ የሚያጦዘው “የተማረ” ልሂቅ የየራሱ የጠራ አስተሳሰብና እምነት ያለው ይመስላችኋል? ሁላችንም የፈረንጆቹ ዩኒቨርሲቲዎች ምራጭና፣ እነሱን ለመሆን የምንኳትን እንቅልፍ አልባ ተጓዦች አይደለንምን? አንድስ የምተራመሰው ባልገባን በነርሱ ቋንቋና ፅንሰሃሳብ ስለምንራኮት አይመሳላችሁም? ለምሳሌ እዚህ የምንኖርባት አሜሪካ ሰሜናዊ ክፍሉ በሁለት ውቅያኖሶች መሃል ያለውን አህጉር አንድ አገር አድርጎ ሲያዋድድ የከፈለውን መስዋእትነትና ያገኘውን ፍሬ አጣጥመን እናውቃለን? የዓለም ቋንቋዎች ሁሉ በተጠለሉባት አሜሪካ፣ ጀርመኑ፣ አይሪሹ፣ ፈረንሳዊው፣ ወዘተ ለምን የየራሱን በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ሃገር ሳይገነባ የቀረ ይመስላችኋል? በአንፃሩ የሰሜኑ ግማሽ የሆነው ደቡብ አሜሪካ ሁሉን የሚያቆራኝ የስፓኝ ቋንቋ እያለውና፣ እንደ ሲሞን ቦሊቫር አይነት አርቆ አሳቢ መሪዎች ተንበርክከው ለአህጉሩ አንድነት እያለቀሱ የለመኑም ቢሆን እንኳ ፣ ለምን ደቡብ አሜሪካ ወደ አስራ ሰድስት ያህል የተለያዩ ሃገራትና ፣ የሰሜኑ ዘለአለማዊ ገባር ለመሆን ቻለ?

ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ታሪካዊ ሂደት የምንማረው ነገር ቢኖር ቋንቋ የግድ ወደተለየ ክልል ብሎም ወደ ቋንቋ ላይ ወደመሠረተ ሃገራዊ መንግስት ምስረታ እንዲሄድ የሚያስገድድ ሎጂክ አለመኖሩን ነው ። ለእኔ ብሄርተኝነት ገበያቸውን ተቆጣጥረው መንግስታዊና አቀባባይ ከበርቴ በመሆን የራሳቸውን ህዝብ ከልለው ለመበዝበዝ የቋመጡ ስብስቦች፣ በታሪክ የቆየን ቁርሾ እያባባሱ መጠቀሚያቸው የሚያደርጉበት ሂደት ነው ። ከዚህ ውጪ የተለየ ታሪካዊ ተልእኮ የለውም ።

የእያንዳንዱ ብሄረሰብ ልሂቅ ራሱን ‘በዘመናዊ” የአውሮፓ አስተሳሰብ ለመቅረፅ ጥድፊያ በያዘበት ወቅት ፣ ቋንቋ የሃሳባችን መግለጫ ቁስ መሆኑን ከተስማማን፣ በቋንቋችን ዙሪያ የራሳችን ብሄራዊ መንግስት ያሻናል የሚለው ቡፋ፣ ለየብሄረሰቡ ልሂቅ የሥልጣን መወጣጫ መሰላል ከመሆን ውጪ የተለየ ፋይዳ እንደሌለው ግልፅ ነው ። የተለያዩት ብሄርተኛ ንቅናቄዎች አላማ ሁሉን አይነት ጭቆናዎች መደምሰስ ሆኖ አያውቅም ። ሩቅ መሄድ የለብንም ። በብሄርተኞች ትግልና አበሳ “ነፃ የወጡትን” ኤርትራን ፣ ደቡብ ሱዳንንና የወያኔዋን ኢትዮጵያ ማየት ነው ። እንኳንስ ነፃነት ታገልነት ለሚሉት ብሄረሰብ ሰላምና ሰብአዊ መብት እንኳ ሊያስገኙለት አልቻሉም ። ህዝቡ ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ነው የተወረወረው ። በሁሉም ወሰኖች ጦርነትና መቆራቆስ በእለቱ አጀንዳ ላይ ሰፈሯል ። ከሁሉም ሃገራት የሚሰደደውን ወጣት ብዛት ማየት ነው ። ይህን ትርኢት በአስር ሺህ እጅ በላቀ ደረጃ ለመድገም መሽቀዳደም የለብንም ። ዛሬ የጃዋር የራስን አድል በራስ የመወሰን ጥሪ ሌላ ውጤት ሊኖረው አይችልም ።

ከአመታት በፊት ብዬዋለሁ፣ ግን ዛሬም ልድገመው ። የራስን እድል በራስ መወሰን የመገንጠል ዝቅተኛው አርከን ስለሆነ፣ ከኤርትራ የተለየ ውጤት አያመጣም ። በታሪክ ታፍሮ የቆየ የብሄረሰቦች ወሰን በሌለባት ኢትዮጵያችን የመገንጠል መብት ዘለአለማዊ ፍጅትንና መቆራቆስን የሚያስከትል የድህነትና የብካይ ተስፋ ነው ። ከቶም ልንመርጠው አይገባም ። ዛሬ ኢትዮጵያን ይዘን፣ ዛሬ አንድ ሃገር እያለን በሃሳብ ሙግት እንግጠምበት ። በኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ ብሄርተኝነት ጎራ የተሰለፉትም ወንድሞች ክርክሩን ይቀላቀሉ ። ተዳቆ የቆየው ተስፋ መቁረጥና ግዴለሽነት ይቁም ። የኦሮሞ ብሄርተኞች ከቁመናቸው ጋር የሚመጣጠን ሚና በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊጫወቱበት የሚችሉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህ ሃላፊነት ሸሽተው፣ ኦሮሚያን ከልለው የበላይ የሚሆኑበትን ጠባብ ፍላጎት ላይ ብቻ የሚብሰከሰኩ ከሆነ፣ እምነታቸውና ድርጊታቸው አሳፋሪ ይሆናል ። ከእንዲህ አይነት አስተሳሰብ መራቅ ይኖርባቸዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወላይታነቱም ሆነ አክራሪ ጴንጠነቱ አነጋጋሪና አወዛጋቢ ባልሆነባት ሆደሰፊዋ ኢትዮጵያ፣ ከታላቁ የኦሮሞ ብሄር የሚመጡትን ልጆቿን ኢትዮጵያ እጇን ዘርግታ እንደምትቀበላቸው እምነቴ ነው ። ኦሮሞነታቸውንም ሆነ ሙስሊምነታቸውን ማግለያ ምክንያት የማታደርግ አዲስ ኢትዮጵያን ታላቁ የየካቲት አብዮት መውለዱን ለደቂቃ እንኳ ሊስቱት አይገባም ። ይህ በአሜሪካም ሆነ በብዙ አውሮፓ ሃገሮች ሊደረግ የማይታሰብ፣ ሆኖም በኢትዮጵያችን የተደረገና ወደፊትም የሚደገም ኩነት ወይም ፍፃሜ ነው። ኢትዮጵያ ለማናችንም የእንጀራ እናት አይደለችም ። እኩል ልጆቿ ነን ። በሙሉ ልባችን ለማቀፍ መድፈር ደግሞ የያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው።

ዛሬ መቀሌ ላይ በስብሰባ ላይ ለሚገኙትም የወያኔ የቀድሞና የአሁን መሪዎችም ያለኝ መልእክት ከላይ በስፋት ለሌሎች ብሄርተኞች የተላከ መልእክት ለናንተም የተላከ መልእክት ነው ። የኢትዮጵያንና የኦሮሞ ብሄርተኝነቶችን በማላተምና በማጋጨት እናንተ የመስመር ዳኛ ሆናችሁ በሥልጣን ለመቀጠል ያወጠነጠናችሁት ስልት አድማሱ ላይ ደርሶ ማሽቆልቆል ጀምሯል ። ከዚህ ባሻገር የክልል ማንነቶችን ማጦዝ የማታቆሙትን ሱናሚ መጋበዝ ነው ። አሁን ያካበታችሁትን ሃብት ሃገራችሁን ለመልቀቅ ሳትገደዱ በሰላም የምትበሉበትና፣ ልጆቻችሁም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስልት መቀየስ ላይ ብትመክሩ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል ። የኢህአዴግ ድርጅቶችን ነፃነት በማክበር መጀመር ትችላላችሁ ። ድርጅቶቹ በየክልላቸው ተቀባይነት እያገኙ ከሄዱና የየክልሉን ተሰሚ ዜጋ አባል ካደረጉ በሁዋላ፣ ኢህአዴግን ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት ማሸጋገርና፣ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን እየለመዳችሁ መሄድ ትችላላችሁ ። ቀስ ብሎም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተአማኒነትና ተቀባይነት ወዳለው መንግስት መሸጋገር ትችላላችሁ ። በምርጫ ብትሸነፉ እንኳ፣ ተመልሳችሁ የመምጣት እድል ይኖራችኋል ። ለዚህ አማራጭ ሃሳብ እምቢተኛ ሆናችሁ በለመዳችሁት የአፈናና የብካይ መንገድ እንቀጥል ካላችሁ ግን ለስሙ ኢህአዴግ ቢጎለትም፣ አምባገነን ግለሰቦች የሰራዊትና ደህንነት ተቋማትን እየዘወሩ የሚሄዱበት ጨለማ ይቀጥላል ። እነዚያ 65ሺህ የትግራይ ወጣቶች የተሰውት ወታደራዊ ደርግን በወያኔያዊ ደርግ ለመተካት እንዳልነበር ለናንተ ማስታወስ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል ። ዛሬ እንኳንስ ተቃዋሚውና ህዝቡ፣ ራሳችሁም የወያኔ መሪዎች ሳሞራንና ጌታቸውን አቤት ወዴት ብላችሁ በሰቀቀን የምትኖሩ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ከቀድሞ ምክትል አቦ ወንበራችሁ ግደይ ዘርአፅዮን ጋር ባደረግነው ውይይት ላይ በሰፊው ተረድቻለሁ ። ይህን አስከፊ ሁኔታ መለወጥ ይኖርባችኋል ። እንዴት በፍርሃት ትኖራላችሁ? ደህንነቱንና ሰራዊቱን ለፓርቲው ተገዢ ወይም ተጠሪ ማድረግ ይገባችኋል ። ከዚሁ ጎን ግን ያንን በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም ያሰገኘውን ጥቅምና ያስከተለውን ጦስ እስኪ ገምግሙት! እየፈራችሁት የመጣችሁት የኦህዴድ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጥርሳችሁን እያወለቀው በድዳችሁ ልትቀሩ እኮ ነው! ቁርጥ ማኘክ ካልቻላችሁ ዶላሩን ብታጠራቅሙት ምን ፋይዳ አለው! ለሁሉም እናንተ እንደምታስቧት የአሉላ ኢትዮጵያ የእንጀራ እናታችሁ አይደለችም ። እዘኑላት ። ያላትን ሁሉ ለሩብ ክፍለዘመናት ሰጥታችኋለች። ለሚቀጥለው ሩብ ደግሞ እስቲ እናንተ ስጧት ። ሁሉን ያካተተ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አዋላጆችና ጂኦሜትራ መሆን ትችላላችሁ። ስላለፈው ከማልቀስ፣ እስቲ አዲሱን ሃገር አቀፍ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እናንተው አምጣችሁ ውለዱ ። ብሄርተኝነት እኮ መለኮታዊ መንፈስ ሳይሆን የየዘመኑ ገዢ ልሂቅ ጥቅም ማሰሪያ ጦማር ነው ። ወደኋላ እያያችሁ ሙሾ ደርዳሪ አስለቃሽ ከመሆን፣ የወደፊቱን የሚማትር ነብይ መሆን ይቻላችኋል ፣ አይዞን!
ሰኳሬ እየወረደ ነው፣ አቦ ምሳዬን ልብላበት!

Filed in: Amharic