>

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? በምን ይገለጻል? (በአለማየሁ አንበሴ)

“የኛን ስልጣኔ ሊያሳይ የሚችለውን
ኢትዮጵያን እንስራ”

ዲ/ን ዳንኤል ክብረት (ጸሃፊና ተመራማሪ)

ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት በተለያየ ጊዜ ድንበሯ ከፍም ዝቅም ሲል በኖረች ሀገር፣ ነገር ግን ብዙ አይነት ህዝቦች ዛሬ በስም የማናቃቸውና ወደ ሌላ ህዝብነት የተቀየሩትን ጨምሮ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍሉባት፤ ለታሪኳ፣ ለእድገቷ፣ ለህልውናዋ የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉባት የኖረች አንዲት ታላቅ ሀገር፣ የሂደቱ አካል መሆን ነው፡፡ ይሄ ነው ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት፡፡
የኢትዮጵያዊነት ስሜት መለኪያው ደግሞ አንድ ሰው ኢትዮጵያ ለሚባለው ከድሮው እስከ አሁን፣ ወደፊትም ለሚኖረው፣ እንደገና ደግሞ አሁን ባለው ድንበር ላይ በተለያየ አቅጣጫ ባሉት፣ ከኢትዮጵያም ወጥተው በተለያየ ሀገር ለሚኖሩት፤ ለእነዚህና ለሀገሪቱ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ነው። በቀድሞው ዘመን ኢትዮጵያዊነት ሲባል፣ ህብረትና አንድነትን ማዕከል አድርጎ፣ በዚያ ላይ ነው በርካታ ስራ የተሰራው፡፡ አሁን ደግሞ በብዛት የሰራነው ልዩነቶቻችን ላይ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ይኖራሉ፤ ወሳኙ የትኛው ላይ ነው በደንብ የሚሰራው የሚለው ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት በተለያየ አካሄድና ፍልስፍናም ቢሆን ሀገራዊ ህብረትና አንድነት ላይ ተሰርቷል፡፡ ዛሬ ደግሞ ልዩነቶቻችንን የበለጠ እንድናውቅ ነው የተሰራው፡፡
ለኔ የሰው ልጅ ስልጣኔ መለኪያው፣በተፈጥሮ ያገኛቸውን እሴቶች ጠብቆ፣ በዚያ ላይ እሴት እየጨመረ መሄዱ  ነው፡፡ የሰው ልጅ መታወቂያውም ይሄው ነው፡፡ በአካባቢው ወንዞች መፍሰሳቸው፣ ባህሮች፣ ተራሮች፣ ጫካዎች መኖራቸው ስልጣኔን አያሳይም፡፡ ተፈጥሮ ነው። የሰው ልጅ ስልጣኔ የሚታየው እነዚህን ለበለጠ ጠቀሜታ፣ ለበለጠ እሴት ሲያውላቸውና የበለጠ እሴት ሲጨምርባቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ አንድ ሰው፣ አንድ ቋንቋ ከሚናገር ቤተሰብ መወለዱና የአንድ ብሄረሰብ የስጋ ተወላጅ መሆኑ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይሄ ግን የአንድን ሰው ስልጣኔ ያሳያል ብዬ አልገምትም፡፡ የአንድን ሰው ስልጣኔ የሚያሳየው፣ እነዚህን በተፈጥሮ ያገኘናቸውን ደምሮ፣ አንድ ሌላ የእርሱን ስልጣኔ ወይም እውቀት የሚፈልግ ነገር በተጨማሪነት ሲሰራ ነው፡፡
እያንዳንዳችን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ — ወዘተ ልንሆን የቻልነው በተፈጥሮ ነው፡፡ እኛ ያበረከትነው ምንም አስተዋፅኦ የለም፡፡ ሁሉም ብሔር አይበላለጥም፡፡ ልዩነት የሚመጣው እነዚህ ብሔረሰቦች አንድ ሆነው፣ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውንና በታሪክ ያገኙትን እሴት በማቀናጀት፣ሀገር የሚባል ነገር ሲፈጥሩ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል ልዩነት የተፈጠረው በዚህ ነው። ሰው በሰውነቱ ልዩነት የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ልዩነት ላይ ብቻ ከመስራት፣ በጋራ ጉዳዮቻችንም ላይ እንስራ የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ተፈጥሮ የሰጠችንን እሴቶች ይዘን፣ የኛን ስልጣኔ ሊያሳይ የሚችለውን ኢትዮጵያን እንስራ፡፡
ምንድን ነው አብሮ ያኖረን? ምንድን ነው ያስተሳሰረን? ይሄ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ ምክንያት አለው፡፡ በዚህ መንገድ ከተሳሰሩ አይቀር የበለጠ መልካም እሴቶችን ደምረን፣ ከሁላችንም በላይ የሆነ አንድ ነገር መፍጠር አለብን፡፡ እዚህ ላይ መሰራት አለበት፡፡ ሁልጊዜ ልዩነታችንን የምንናገር ከሆነ አንግባባም፡፡ የቤተሰብ ምስረታ ላይ አተኩረን እንስራ፡፡

“ኢትዮጵያዊነት የማይሻር ብሔራዊ ክብር ነው”
ዶ/ር ንጋት አሰፋ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት አንድ እምነት ነው። የተለያዩ ጎሳዎችን አሰባስቦ በመሃል አንድ ሀገራዊ ስሜትን የሚቀርጽ ሃይል ነው፤ ኢትዮጵያዊነት። ይሄ ብሔራዊ ኃይል መገለጫው ምንድን ነው? ካልን ደግሞ የአድዋ ድልን ማንሳት እንችላለን። አድዋ ላይ ድል ያደረግነው በዚህ አሰባሳቢ ኃይል ነው – ኢትዮጵያዊነት በሚለው፡፡ በጋራ በኢትዮጵያዊነታችን ድል ያደረግነው፣ የእገሌ ነው የማይባል፣ የሁላችንም ብሔራዊ ገድል ነው። የማይጨው ድል የኢትዮጵያዊ አንድነታችን መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የማይሻር ብሔራዊ ክብር ነው፡፡ የሁሉም ጎሳዎች ልዩ መገለጫ፣ ብሔራዊ ኩራት ነው – ኢትዮጵያዊነት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይሄ አረዳድ በሀገራችን የለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሔር ብሔረሰብ በሚል ተሸፍኗል፡፡ ብሔር ስንል ትርጉሙ በግልፅ መታወቅ አለበት፡፡ ዋነኛ ትርጉሙ አንድ ራሱን የቻለ ሀገር ማለት ነው፡፡ የራሱ መገለጫ የሆነ ቋንቋ፣ ሥነ – ልቦና፣ ባህል ያለው ማለት ነው፡፡ “ህብረተሰብ” ማለት ደግሞ በዚህ “ብሔር” ወይም “ሀገር” ውስጥ ያሉ ህዝቦች ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የሩሲያን ታሪክ ብናነሳ፤ አዘርባጃን፣ አርሜኒያ፣ ዩክሬን፣ ባልቲክ ሪፐብሊክ፣ ካዛኪስታን የመሳሰሉ ሀገራት እጅግ ጥንታዊ የሆነ ባህልና የራሳቸው ሥነ መንግስታዊ ታሪክ ያላቸው ሀገሮች ነበሩ፡፡ በኋላ ግን በእነ ሌኒንና በእነ ስታሊን አካሄድ እነዚህን “ብሄሮች” ወይም “ሀገሮች” ወደ ሩሲያ ለማጠቃለል ነው የተሞከረው። በሶሻሊዝም ስም ወደ ሶቪየት ህብረት እንዲካተቱ ተደረጉ፡፡ በኋላ እነዚህ “ብሔሮች” ወይም ሀገሮች ያነሱት ጥያቄ፣ የቅኝ ተገዥነት ጥያቄ በመሆኑ፣ ነፃነታቸውን አውጀው ነው ሶቭየት ህብረት የፈረሰችው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ይሄን የሶሻሊዝም መርህ ምንም ባልተፈጠረበት ሁኔታ ለማምጣት ነው የተሞከረው፡፡ ህውኃት ያነሳው ጥያቄ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የብሔር ጭቆና አለ የሚል ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ነው ድል የተገኘው፡፡ እነ መኢሶን፣ ኢህአፓ በአንፃሩ የሀገሪቱ ችግር፣የመደብ ችግር ነው ቢሉም ያን ያህል ውጤት አላመጡበትም። የብሔር ጥያቄ ዛሬ ላይ “የማንነት ጥያቄ” የሚል እየወለደ ነው፡፡
ለምሳሌ ቅማንት፣ ወልቃይት ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሄ የሀገር አንድነትን መንፈስ እየሸረሸረ ያለ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። በኔ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ “ብሔር” የለም። አንድ ኢትዮጵያዊነት ነው ያለው፡፡ በአንድ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው፣ ክፍለ ህዝብ ወይም ጎሳ ሊሆን ይችላል እንጂ ብሔር አይደለም፡፡ ይህን እረጋ ብለን መመርመር አለብን፡፡ “ብሔር” ካልን የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ማሳደግ አንችልም፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት የተረጨውን የብሔር መርዝ አስወግዶ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲያቆጠቁጥ ሌላ የአንድ ትውልድ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ 25 ዓመት ውስጥ የተወለደና ከ25 ዓመት በፊት አፍላ ታዳጊ የነበረ ልጅ ሁሉ፣ጎሰኝቱን እንዲያጠናክር ነው የተደረገው። በተደናበረ የኢትዮጵያዊነት ስሜትና በተደናበረ የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ዛሬም መደናበሩ ቀጥሏል፡፡
የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲጠናከር የትምህርት ካሪኩለም እንደገና መከለስ አለበት። የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ወይም “ኢትዮጵያኒዝም” ላይ መመራመርና ማስተማር አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ ውይይት መደረግ አለበት፡፡ ይህ ጊዜ የሚወስድ ሥራ ቢሆንም በቁርጠኝነት ከተሰራ ኢትዮጵያዊነት ወደ ብሔራዊ ክብርነት ተመልሶ ሊመጣና ሊለመልም ይችላል፡፡ እኔ ከፌደራሊዝም ጋር ጠብ የለኝም፡፡ ግን ቅኝቱ መፈተሽ አለበት፡፡ ጎሳዎች አስፈላጊውን ክብር ማግኘት አለባቸው፤ግን ደግሞ ብሔራዊ ክብርም የበለጠ ማቆጥቆጥ አለበት፡፡

“ኢትዮጵያዊነት የጋራ አብሮነት ውጤት ነው”

ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው፡፡ ዜግነት ደግሞ በአንድ የተወሰነ ሀገር ውስጥ የጋራ አብሮነትን የሚያሳይ ነው፡፡ አንድ ጆሴ ኦርቴጋ የሚባል ፖርቹጋላዊ ፀሐፊ አለ፡፡ ይህ ጸሐፊ፤ ሀገር የሚመሰረተው በምን ላይ ነው? ሲል ይጠይቃል፡፡ ሀገር የሚመሰረተው በእሱ አተያይ፣ በጋራ አብሮነት (common feature) ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም የጋራ አብሮነት ውጤት ነው፡፡ የጋራ መሰረት ያለን፣ የጋራ ጉዳይ ያለን፣ ለወደፊትም የጋራ እድል ያለን ሰዎች ነን፤ በኢትዮጵያዊነት ስር  የተሰባሰብነው፡፡፡ ይሄ ማለት ዛሬ እና ትናንት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ነገና ለወደፊትም አብሮ ለመኖር የጋራ ስምምነት ያለን ህዝቦች ነን፡፡
የአሁኗ ኢትዮጵያ እንዴት ተመሰረተች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ የአሁኗ የቆመችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው፡፡ አሁን ላይ ላለው የአንድነት ክፍፍልና የእርስ በእርስ መጠላለፍ መሰረት የሆነውም ያንን የኢትዮጵያ አመሰራረት የምንረዳበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ነው፡፡ ግማሹ በቅኝ ግዛት (ወረራ) አይነት የተፈጠረች ነች ይላል፤ ግማሹ ደግሞ ቀድሞ የነበረችውና ኋላ ላይ በታሪክ አጋጣሚ የተበታተነች ኢትዮጵያን መልሶ አንድነቷን ማስጠበቅ ነው ይላል። በዚህ መሃል ግን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች፣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ መስፋፋት ሲጀምሩ፣ በወቅቱ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግሬ በተባሉት አምስት ግዛቶች ላይ ብቻ ተወስና የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ሀገራዊ ኃይልና አንድነት ለማጠናከር፣ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ መስፋፋት ጀመረች፡፡
አፄ ምኒልክ፤ በሉአላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት፣ ሁሉም በጋራ መቆም አለባቸው ከሚል መነሻ ነው መስፋፋትን ያደረጉት፡፡ በዚህ መሃል ግጭት ተፈጥሮ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ይሄ ክስተት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ሆኖ የሚታየው አብዛኛው ሀገር፣ አሁን ላይ የያዘው ቅርፅ በእንዲህ አይነት ክስተቶች አልፎ የመጣ ነው፡፡ የዚህ አይነት የማሰባሰብ ውጤት የታየው በአድዋ ጦርነት ላይ ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በግልፅ ለአንዲት የጋራ ሉአላዊ ሀገር ተዋድቀዋል፡፡ ስለዚህ አድዋ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ነው፡፡ አድዋ ላይ የምናየው ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጋራ የሉአላዊነት አደጋን የቀለበሱበትና አብሮነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ወደፊትም በነፃነት ለመኖር የተስማሙበትና መስዋዕትነት የከፈሉበት፣ ሁሉም ለወደፊት አብሮነታቸው አሻራቸውን ያሳረፉበት ነው አድዋ ማለት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ለኔ አድዋ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ማለት በአብሮነት፣የወደፊት ነፃነትን አስከብሮ፣ በጋራ ለማደግ የመስማማት ውጤት ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ነው ነፃነታችንን አስከብረን ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ቅኝ ግዛት ውስጥ የወደቁበት ሚስጥሩ፣ ይሄን አብሮነት ማጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆንነውና ራሳችንን አስከብረን የኖርነው፡፡
የኢትዮጵያ አንድነትን ለማምጣት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ብዙ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡ ይሄ ግን እኛ ብቻ ሳንሆን  ሰልጥነዋል የተባሉ ሀገሮችም የዛሬ አንድነታቸውን ያገኙት፣ በእንዲህ ያለውና ከዚህም በከፋ ሂደት ነው፡፡ አኖሌ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ፣ የኢትዮጵያ አንድነት በሚመሰረትበት ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ነው፡፡ አኖሌ ላይ ወገኖቻቸው የተጨፈጨፉባቸው ሰዎች ናቸው፣ አድዋ ላይ ለጋራ ነፃነት የተዋጉት፡፡ አድዋን ያለ ኦሮሞ ብሔር ተሳትፎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የአፄ ምኒልክ ወታደር ኦሮሞ ነው፡፡
አሁን የሚንጸባረቀው  የመበደል ስሜትና የብሔርተኝነት ስሜትም ሂደት የፈጠረው ነው። በየትኛውም ተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ባለፈ ሀገር ይሄ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይን ማንሳት እንችላለን፡፡ ይሄ የመበደል (ብሔርተኝት) ስሜትና የአንድነት ስሜትን የማራመድ ጉዳይ አዲስ ክስተት ሳይሆን ሊፈጠር የሚችል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ልሂቃን እንደሚሉት፤የሀገር አብሮነትን ለማስጠበቅ፣ ይሄን አይነቱን የበደለኝነት ስሜት መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ አሰቃቂ ክስተቶችን መዘንጋትና አስተማሪ ወይም በጎ የሆኑትን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ሀገር ያለው የብሔርተኝነት ስሜት መሰረቱ የበደለኝነት ስሜት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት ጎራ ደግሞ የግድ ኢትዮጵያዊ አንድነትን መቀበል አለብን ብሎ መጫን አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከእንግዲህ ወዲህ፣ ፈቅደን መርጠን የምንወስደው እንጂ በግድ የሚጫንብን መሆን እንደሌለበት ማስተዋል አለብን፡፡ የብሔርተኝነቱና የአንድነቱ ጎራ ግጭት በዚህ መንገድ መታረቅና የጋራ የወደፊት አብሮነት መታሰብ ይኖርበታል። የበደለኝነት ስሜትን ትቶ አንድነትን ለማሰብ የአኖሌን ጭፍጨፋ ዘወትር ማንሳቱን ትተን፣ አንድ ያደረገንን አድዋን መዘከር አለብን፡፡ በጎ የታሪክ ገፅታችንን ማጉላት ይገባናል። የቀድሞ ታሪካችን ላይ ቆዝመን አንድነታችንን መሸርሸር ትተን፣ በወደፊት አብሮነታችንና የጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተ የጋራ አንድነትን ለመፍጠር መጣር አለብን፡፡ የፖለቲካ ሃይሎችም አቅጣጫቸው፣በወደፊት የጋራ አብሮነት ላይ የሚያጠነጥን መሆን አለበት፡፡ አሁን ልዩነቶችን ማጉላት ላይ ነው ያተኮርነው፡፡
ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ትግሬ እያልን እርስ በእርስ የምንከራከረው፣ የጋራ ጉዳይ፣ የጋራ አገር ስላለን ነው፡፡ ክርክሩ ራሱ የተመሰረተው በጋራ ጉዳያችን ላይ ነው፡፡ አሁን ማተኮር ያለብን “ለወደፊት በጋራ እንዴት እንኑር” በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እየከረረ የመጣውን ልዩነታችንን ማስታረቅ እንችላለን፡፡

“ኢትዮጵያዊነት እያበበና
እየለመለመ የሚሄድ ሃሳብ ነው”

ያሬድ ሹመቴ (የፊልም ዳይሬክተር)
ኢትዮጵያዊነት ተገልፆ የማያልቅ፣ መግለፅም የማይቻል ነገር ነው፡፡ ስሜቱን ማስረዳት ይቸግራል። በጥቅሉ ግን ከእኔ ህይወት በፊት የነበረን ትዝታ፣ የእኔን ህይወትና የእኔን ተስፋ – ሦስቱን አጣምሮ የያዘ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት፡፡ የአያት ቅድመ አያቶቻችን ታሪክ፣ ዛሬ እኔ የምኖረውና ያሳለፍኩት፣ በምኞቴ፣ በፍላጎቴ የሀገሬን መጨረሻ የምገምትበት ወዘተ– የያዘ እሳቤ ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡ “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚለው ሃሳብ መሰረት፣ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው፣ የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር ሊያስከፍል የሚችል፣ ሀይል ወይም ስሜት ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መስራቾች ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያን የሰራት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ዘንድሮ “እኛ ነን የፈጠርናት” የሚሉ ጎበዞች፣ በታሪክ ምን አይነት ቦታ እንዳላቸው በሂደት የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከምትባል ሀገር በፊት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ አሁን በፖለቲካ ጫና ምክንያት ነው ኢትዮጵያ የሚለው ቅርፅ የተለያየ መልክ ያመጣው፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስት ለፖለቲካ አገዛዙ ሲል ያደረገው ነው፡፡
እንደ‘ኔ ብሔርተኝነት ማለት ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከር ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ማጠናከር ነው ብሄርኝነት፡፡ አንድ ብሔርን ብቻ ነጥሎ ሳይሆን አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝት ነው የኔ አመለካከት፡፡ አንድ “ብሔር ተኮር ፍቅር” እና “ሀገር ተኮር ፍቅር” እንዴት ይታረቃሉ”? የሚለው ሰብአዊነትን በማክበር የሚመለስ ጥያቄ ነው፡፡ ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የሚከበር ከሆነ ዘሩን መጠየቅ አያስፈልገንም፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሲሰቀል፣ የሚዘመረው መዝሙር፣ የመጀመሪያዋ ቃል፣ “የዜግነት ክብር” የምትል ነች፡፡ “የዜግነት ክብር”፣ አንድ ሰው በቅድሚያ ዜግነቱ እንዲታየው የሚያደርግ ነው፡፡ ከሁሉም መቅደም ያለበት ሰብአዊነት ነው፡፡ አሁን መታወቂያ እየታየ መከራ ውስጥ የሚገባው‘ኮ ከብሔር ጋር ባለ ንፅፅሮሽ ብቻ አይደለም፤ ከሰብአዊነትም መውረድ ጭምር ነው፡፡ ሰውነትን የማስቀደም ነገር ተዘንግቷል፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡
እስካሁን ባየነው፣ የሚጠቅመን በአንድነት በፍቅር ያደረግነው ነገር ነው፡፡፡ እነ አክሱም፣ እነ ላሊበላ ሌሎችም የስልጣኔ ምልክቶች ሆነው የተቀመጡ የታሪክ አሻራዎች፣ በተረጋጋና ፍቅር በሰፈነበት ዘመን የተሰሩ ናቸው፡፡
ባልተረጋጋው ዘመነ መሳፍንት፣ ከአፄ ኢዮአስ መውደቅ እስከ አፄ ቴዎድሮስ ባለው ዘመን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የተሰራ ቋሚ ነገር አይገኝም፡፡ ምክንያቱም እርስ በእርስ ተከፋፍለን የነበረበት ዘመን  ነው፡፡ ስለዚህ የሚጠቅመንን  ማወቅ አለብን፡፡
ኢትዮጵያ “የዛሬ” ብቻ ሀገር አይደለችም። ኢትዮጵያ “የዛሬይቱ” በሚል ቅኝት ውስጥ የምትወድቅ ሀገር አይደለችም፡፡ “የዛሬይቱ” በሚል ቅኝት ውስጥ ወድቃ፣ ዛሬ በተሰጣት መስፈርትና ልክ ብቻ እንድትኖር ብትገደድ የማይተኛ፣ የማይሞት፣ የማያንቀላፋ፣ ወድቆ የማይቀር፣ አያቶቻችን የሰሩት፣ በየጊዜው ጎናችንን እየቆሰቆሰ የሚያስነሳ በርካታ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያዊነት፤ ለጊዜው ያዘቀዘቀ ቢመስልም ሁሌም ከፍ እያለ፣ ይበልጥ እያበበና እየለመለመ የሚሄድ ሃሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሁንም ይለምልም!

“ብሔርተኝነትና ኢትዮጵያዊነት ተጣጥመው መሄድ አለባቸው”
ዳንኤል ብርሃነ (ጋዜጠኛና ጦማሪ)

ኢትዮጵያዊነትም ይሁን ብሔር እንደ ማንነት ገፅታዎች አድርጌ ነው የምወስዳቸው፡፡ ሃይማኖትም የማንነት መገለጫ ነው፡፡ በተለያየ መጠን ይገልፀናል። አንዳንዴ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ያልናቸው በደንብ ስንረዳቸው ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በዘመነ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያን የሚወክለው፡- ቋንቋ፣ ፊደላት፣ ጥበብ ልብስ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሌሎችም መገለጫዎችን አውቀናል፡፡
የኢትዮጵያዊነት ትርጉም እየሰፋና እየዳበረ እንደሚሄድ፣አሁን ያለው ሁኔታ ያሳየናል፡፡ በመርህ ደረጃ ሁሉም ሰው፤ ኢትዮጵያዊነት ጠብቦ መተርጎም እንደሌለበት ይረዳል፡፡ ግን አስተሳሰቦች በአጭር ጊዜ ስለማይቀየሩ፣ አሁንም ኢትዮጵያዊነትን ከአማራ ወይም ትግራይ ባህል ጋር አያይዘን  የመግለፅ ነገር አለ፡፡ አማራና ትግራይ የኢትዮጵያ ባህል መገለጫ ባለቤቶች መሆናቸው ጥሩ ነው፤ የበለጠ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያጠናክረዋል፡፡ ግን በዚያው ልክ የሌሎች ማንነትም የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሌሎችን ባህል ማስተዋወቅ ላይ መሰራት አለበት፡፡
የአንድ ብሔር አባልነትና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይም ተጣጥመው መሄድ አለባቸው፡፡ የሚጋጩበት ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ሀገራዊ ማንነት እንደሚቀድም የግድ ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ከአስተዳደር አወቃቀሩም ሆነ ከፖለቲካው አንፃር፣ ብሔርተኛነት ልኬት የተቀመጠለት አይደለም። በመሆኑም አንዳንዶች ለጥጠውት፣ የብሔሮች ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የምንኖር ያስመስሉታል። እያንዳንዱ ብሔር የየራሱ መሬት፣ ለሌላ የማያካፍለው መንግስትና ግዛት ያለው፤ ሌላው የማያገባው፣ የራሱ መፃኢ እድል ያለው በሚመስል መልኩ ነው አጠቃላይ ሁኔታው የተቃኘው፡፡ ይሄ በጣም መታረምና መስተካከል ያለበት ነው፡፡
መጀመሪያ ላይ በብሔር የመደራጀት ጉዳይ ሲፈቀድ፣ ለዚህ ማለስለሻ ወይም ማቀዝቀዣ አልተሰራለትም፡፡ በብሔርተኝነቱና በፅንፈኝነቱ መሃል ሚዛናዊ የሚያደርግ ነገር መቀመጥ ነበረበት። የብሔርተኝነት አደረጃጀቶች ሲፈጠሩ፣ ሚዛናዊ ማድረጊያ መንገዶች ጎን ለጎን አለመቀመጣቸው፣ አሁን የሚታየውን በጣም የተለጠጠ ብሔርተኝነት ፈጥሯል፡፡
የድንበር ግጭቶችን ስንመለከት፣ አንዳንዱ አንቀፅ 39ን በአዕምሮው ይዞ የሚጨቃጨቅ ነው የሚመስለው፡፡ “መሬቴን አጣሁ” እየተባለ በታሪክ ጭምር ግዛት እየተጠቀሰ የሚፈጠር ጭቅጭቅ፣ ብሔርተኝነት ቅኝቱን የመሳቱ ውጤት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ብሔርተኝነትን ከፍ ያደረገው ማህበራዊ ሚዲያው የሰጠው ቦታ ነው ወይስ በፊትም የነበረ ነው? የሚለው መመርመር አለበት። እንደኔ ጠርዝ የወጣ ብሔርተኝነት የመፈጠሩ ምክንያቶች፤ ማህበራዊ ሚዲያውና የማዕከላዊ መንግስቱ መዳከም ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች የብሄርተኝነት መንፈሱ እንዲጎላ አድርገውት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄን ማስተካከል የሚቻለው አንደኛ፣ መንግስት በጉዳዩ ላይ ህዝባዊ ነፃ ውይይቶች እንዲካሄዱ መፍቀድ አለበት፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ነገሮች ሊቻቻሉና ማንነት ላይ ነጥሮ የሚመጣ ገዥ ሃሳብ ሊፈጠር ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ለብሔር ማንነት ብዙም ቦታ የማይሰጡና ሃገራዊ አንድነት ላይ የሚያተኩሩ ሃይሎች፣ ሃሳባቸውን አውጥተው የሚገልፁበት እድል ሊመቻች ይገባል፡፡ አስተሳሰባቸው ጥሩም ሆነ አልሆነ፣ ለሌላኛው አስተሳሰብ ማመዛዘኛ ይሆናል። አሁን በስፋት የምንሰማው … የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ሃገራዊ ማንነት የሚሰማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሃሳባቸው ለውይይትና ክርክር በስፋት መቅረብ አለበት፡፡

Filed in: Amharic